በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማልፈልግ መሆኔን እንዴት ብዬ ልንገረው?

የማልፈልግ መሆኔን እንዴት ብዬ ልንገረው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...

የማልፈልግ መሆኔን እንዴት ብዬ ልንገረው?

“በቅርቡ በጉባኤያችን የሚገኝ አንድ ወንድም እንዳፈቀረኝ ነገረኝ። እኔ ደግሞ ለእርሱ የተለየ ስሜት የለኝም። ችግሩ ግን ስሜቱን ሳልጎዳ እንዴት ልነግረው እንደምችል አላውቅም።”​—ኤሊዛቤት *

“ብንጠናና ምን ይመስልሻል?” አንድ ወጣት እንዲህ ያለ ጥያቄ አቅርቦልሽ ያውቃል? ወጣት ሴት * እንደመሆንሽ መጠን እንዲህ ተብሎ መጠየቁ ሊያስደስትሽ ብሎም ሊያስፈነድቅሽ ይችላል! በሌላው በኩል ግን ምን ተብሎ መልስ እንደሚሰጥ አለማወቅሽ ግራ ሊያጋባሽ ይችላል።

አንድ ሰው ለአንቺ ያለውን ፍቅር ሲገልጽልሽ ሁኔታው የተዘበራረቀ ስሜት ሊፈጥርብሽ ይችላል። በተለይ ማግባት በምትችይበት እድሜ ላይ ከደረስሽና እንዲህ ላለው ጥያቄ መልስ መስጠት በምትችይበት ሁኔታ ላይ ከሆንሽ እንዲህ ያለው ስሜት እንደሚፈጠርብሽ የታወቀ ነው! * ያም ሆኖ ግን የምትሰጪው መልስ በአብዛኛው በሚጠይቅሽ ሰው ማንነት ላይ የተመካ ነው። በስሜት የበሰለና አንቺም የምትወጂው ከሆነ መልስ መስጠቱ አይከብድሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ የጠየቀሽ ሰው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለመሆን የሚያስችሉ ብቃቶች ባይኖሩትስ? ወይም ደግሞ ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ቢኖሩትና አንቺ ግን ለእርሱ የተለየ ስሜት ባይኖርሽስ?

ከአንድ ወጣት ጋር ለተወሰነ ጊዜ እየተቀጣጠረች ብትጫወትም የኋላ ኋላ ቀሪ ሕይወቷን እንዲህ ካለው ሰው ጋር ለማሳለፍ እንደማትፈልግ የተገነዘበችውን ወጣት ሁኔታም ተመልከቺ። ግንኙነቱን በማቋረጥ ፋንታ ከሰውዬው ጋር እየተቀጣጠረች መጫወቷን ቀጠለች። “የማልፈልግ መሆኔን እንዴት ብዬ ልንገረው?” በማለት ትጠይቃለች።

ለእርሱ የተለየ ስሜት ባይኖርሽስ?

በዕብራውያን አባቶች ዘመን ልጆች ወላጆቻቸው የመረጡላቸውን ሰዎች ያገቡ የነበረ ይመስላል። (ዘፍጥረት 24:​2-4, 8) በምዕራባውያን አገሮች የሚኖሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ደግሞ የመረጡትን የማግባት ነጻነት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ግዴታ ክርስቲያኖች “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ የሚል ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 7:​39

ታዲያ ይህ ማለት እንደሚወድሽ የገለጸልሽን ወይም እየተቀጣጠርሽ በመጫወት አብረሽው የተወሰነ ጊዜ ያሳለፍሽውን ማንኛውንም ክርስቲያን ማግባት አለብሽ ማለት ነውን? እስቲ ሱነም ከሚባለው በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኝ መንደር የመጣችውን የአንዲት የገጠር ልጃገረድ ምሳሌ ተመልከቺ። ንጉሥዋ የሆነው ሰሎሞን አያትና በፍቅሯ ተነደፈ። ሆኖም ሊያግባባት በሞከረ ጊዜ የማትፈልግ መሆኗን መንገር ብቻ ሳይሆን “ፍቅር ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት” በማለት የንጉሡን ሴት አገልጋዮች ተማጽናቸዋለች። (መኃልየ መኃልይ 2:​7 የ1980 ትርጉም ) ይህች ብልህ ልጃገረድ ሌሎች ስሜታዊ ውሳኔ እንድታደርግ እንዲገፋፏት አልፈቀደችም። አንድ ተራ እረኛ አፍቅራ ስለነበር ለሰሎሞን የተለየ ስሜት አልነበራትም።

ይህ በዛሬው ጊዜ ለማግባት ለሚያስቡ ጠቃሚ ትምህርት ያስተላልፋል:- እንዲሁ ማንኛውንም ሰው ልታፈቅሩ አትችሉም። አንዲት ወጣት ሴት ከአንድ ወጣት ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተቀጣጥራ ብትጫወትም ልታፈቅረው እንደማትችል ይሰማት ይሆናል። ምናልባት እንዲህ ሊሰማት የቻለው ሌላኛው ወገን የጎላ የባሕርይ ድክመት ስላለበት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በፍቅሩ ስላልተማረከች ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ስሜት ችላ ማለት ሞኝነት ከመሆኑም በላይ እንዲሁ ችላ ማለት ስሜቱን ያጠፋዋል ማለት አይደለም። * ታማራ እየተቀጣጠረች በመጫወት አብራው ጊዜ ታሳልፍ ስለነበረ አንድ ወጣት ስትናገር “በጭንቅላቴ ውስጥ የሚመላለሱ ብዙ ጥርጣሬዎች ነበሩኝ። እነዚህ ጥርጣሬዎች ደግሞ እንዲሁ ጥቃቅን ሳይሆኑ ከእርሱ ጋር መሆን እስኪያስጨንቀኝ ድረስ በጣም የጎሉ ነበሩ” ብላለች። በኋላም ታማራ በእነዚህ ጥርጣሬዎች ሳቢያ ግንኙነቱን ማቋረጡ የተሻለ እንደሚሆን ተገነዘበች።

የማትፈልጊ መሆኑን መግለጽ ከባድ የሆነበት ምክንያት

ያም ሆኖ የማትፈልጊ መሆኑን መግለጽ የሚባለውን ያህል ቀላል አይደለም። ልክ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰችው ኤሊዛቤት ስሜቱን እጎዳው ይሆናል ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ስለ ሌሎች ስሜት ማሰብ እንደሚኖርብን እሙን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ርህራሄን እንዲለብሱና’ ሌሎችን እነርሱ መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ እንዲይዙ ያበረታታል። (ቆላስይስ 3:​12፤ ማቴዎስ 7:​12) ታዲያ ይህ ማለት ይህንን ወጣት ላለማሳዘን ወይም ላለመጉዳት ስትይ ግንኙነቱን መቀጠል ይኖርብሻል ማለት ነው? ይዋል ይደር እንጂ ስለ እርሱ ምን እንደሚሰማሽ ማወቁ አይቀርም። ከዛሬ ነገ እያልሽ የሚሰማሽን በሐቀኝነት ከመግለጽ ማመንታትሽ ደግሞ ችግሩን ከማባባስ ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ስሜቱን ላለመጉዳት ስትይ ይህንን ሰው ማግባትሽ ነው። የሌላውን ስሜት ላለመጉዳት ብቻ ተብሎ የሚመሠረት ትዳር ጥሩ መሠረት አይኖረውም።

ምናልባትም “እርሱን ካላገባሁ ሌላ ሰው አላገኝ ይሆናል” ከሚለው ሐሳብ ጋር እየታገልሽ ይሆናል። በቲን መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዳስቀመጠው አንዲት ወጣት እንዲህ ብላ ልታስብ ትችላለች:- “ ‘ለትዳር የምመኘው ዓይነት ሰው’ አይደለም። ግን ቢያንስ ላገባው እችላለሁ። ብቻዬን መሆን ደግሞ አልፈልግም።” ተጓዳኝ ለማግኘት ያለሽ ጉጉት ጠንካራ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ይህንን ፍላጎት በተገቢው መንገድ ማርካት ማለት አንድን ሰው ማግባት ማለት ብቻ አይደለም። ከልብ የምታፈቅሪውንና ትዳር የሚያስከትላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት የሚችል ሰው ማግኘትንም ይጨምራል። (ኤፌሶን 5:​33) ስለዚህ የትዳር ጓደኛ በመምረጥ ረገድ አትቸኩይ! ብዙዎች በችኮላ በማግባታቸው የኋላ ኋላ ተጸጽተዋል።

በመጨረሻም፣ አንዳንዶች እየተቀጣጠሩ በመጫወት አብረው ጊዜ የሚያሳልፉት ሰው ከባድ ድክመቶች እንዳሉበት ካወቁም በኋላ ግንኙነታቸውን አያቋርጡ ይሆናል። ‘ትንሽ ጊዜ ከሰጠሁት ይለወጥ ይሆናል’ ብለው ያስባሉ። ይህ በእርግጥ አስተዋይነት ነውን? እንዲያውም መጥፎ ልማዶችና ጠባዮች አብዛኛውን ጊዜ ሥር የሰደዱ ስለሚሆኑ እነርሱን መለወጡ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ ሰው ያልታሰቡ አስገራሚ ለውጦች ቢያደርግ እንኳ እነዚህ ለውጦች ዘላቂ ስለመሆናቸው እርግጠኛ ነሽ? ይህንን የመሰለ ሁኔታ ገጥሟት የነበረችው ካረን ተመሳሳይ ግብ እንደሌላቸው ስትገነዘብ የነበራትን ግንኙነት ለማቋረጥ በጥበብ ወሰነች። ካረን “ከባድ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “ምክንያቱም በመልኩና በቁመናው ተማርኬ ነበር። ሆኖም ግንኙነታችንን ማቋረጥ ላደርገው የሚገባኝ ትክክለኛ ነገር መሆኑን ተገንዝቤ ነበር።”

ጥንቃቄ ይጠይቃል

ቅርርባችሁ እንዲቀጥል የማትፈልጊ መሆኑን መግለጹ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። በውስጡ የሚሰበር እቃ እንደያዘ ጥቅል ይህም ሁኔታ ጥንቃቄን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ጉዳዩን ከወላጆችሽ ወይም ጉባኤ ውስጥ ከሚገኝ ከአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጋር ተወያዪበት። ምናልባት ከእርሱ በምትጠብቂው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን አለመሆንሽን እንድትገነዘቢ ሊረዱሽ ይችሉ ይሆናል።

ግልጽና ቀጥተኛ ሁኚ። ምን እንደሚሰማሽ ስትነግሪው አእምሮው ውስጥ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ እንዲኖር አታድርጊ። “አይ፣ እኔ አልፈልግም” ማለቱ ብቻውን ለብዙዎቹ ጋብቻ ጠያቂዎች በቂ መልስ ሊሆን ይችላል። አስፈላጊ ከሆነም እምቢታሽን ጠንከር ባለ አነጋገር ግለጪ። ለምሳሌ “አዝናለሁ፣ እኔ ምንም ፍላጎት የለኝም” ልትይ ትችያለሽ። ምናልባት ትንሽ ጥረት ባደርግ ሐሳቧን ትቀይራለች ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ ፍንጭ ከመስጠት ተቆጠቢ። ለእርሱ ምንም ዓይነት የፍቅር ስሜት እንደሌለሽ ግልጽ ማድረግሽ ማንኛውንም ግራ መጋባት ሊያስወግድና የሚሰማውን ቅሬታ እንዲቋቋም ሁኔታውን ቀላል ሊያደርግለት ይገባል።

ሐቁን በምትናገሪበት ጊዜ ብልሃት ይኑርሽ። ምሳሌ 12:​18 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ” በማለት ይናገራል። ግልጽነት አስፈላጊ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ንግግራችን “በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ” መሆን እንዳለበትም ይናገራል።​—⁠ቆላስይስ 4:​6

በውሳኔሽ ጽኚ። ጓደኞችሽ ከውሳኔሽ ጀርባ ያሉትን ምክንያቶች ሳይረዱ ለግንኙነቱ ሌላ እድል እንድትሰጪው በቅንነት ግፊት ሊያደርጉብሽ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ውሳኔሽ የሚያስከትለውን ውጤት የምትቀበዪው አንቺ እንጂ ጓደኞችሽ አይደሉም።

ድርጊትሽ ከቃልሽ ጋር የሚስማማ ይሁን። ቀደም ሲል ሁለታችሁ ጥሩ ጓደኛሞች የነበራችሁ ልትሆኑ ስለምትችሉ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲለወጡ ብትመኚ የሚያስገርም አይሆንም። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ምኞት እውን ሊሆን አይችልም፤ ደግሞም አይሆንም። አሁን ለአንቺ ያለው ስሜት ተለውጧል። ስሜቱን ችላ ማለትና ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ማስመሰል ይችላል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነውን? አንዳችሁ ለሌላው ወዳጃዊ መንፈስ ማሳየታችሁ ጥሩ ቢሆንም ዘወትር በስልክ መነጋገሩም ሆነ በማሕበራዊ ዝግጅቶች ረዥም ጊዜ አብሮ ማሳለፉ ስሜቱ ይበልጥ እንዲረበሽ ከማድረግ ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እንዲህ ማድረጉ በስሜቱ እንደመጫወት ይቆጠራል። ይህ ደግሞ ደግነት አይሆንም።

ሐዋርያው ጳውሎስ እርስ በእርሳቸው “እውነትን” እንዲነጋገሩ ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 4:​25) እንዲህ ማድረጉ ሊከብድ ቢችልም ለሁለታችሁም የሚበጅ ነገር ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.4 ይህ ርዕስ በወጣት ሴቶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለወጣት ወንዶችም ይሠራሉ።

^ አን.5 ማግባት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሳይደርሱ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት የሚያስከትለው አደጋ በመጋቢት 2001 እትም ላይ ተብራርቷል።

^ አን.10 በሐምሌ 22, 1988 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . መለያየት ይኖርብን ይሆን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቺ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንዲሁ ማንኛውንም ሰው ልታፈቅሩ አትችሉም

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሜትሽን ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ግለጪ