በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከፍተኛ ችግር ፈጥረዋል

የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከፍተኛ ችግር ፈጥረዋል

የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከፍተኛ ችግር ፈጥረዋል

ባለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት የጦር መሣሪያ ቅነሳ ውይይት ያተኮረው በኑክሊየር መሣሪያዎች ላይ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ነጠላ የኑክሊየር ቦምብ አንድ ሙሉ ከተማ እንዳለ ሊያወድም ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ከፍተኛ የማውደም ኃይል ያላቸው መሣሪያዎች ከ50 ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ ወዲህ አንድም ጊዜ ሥራ ላይ ውለው ባለማወቃቸው ከነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ይለያሉ።

ከፍተኛ ተደማጭነት ያተረፉትና የውትድርና ታሪክ ሊቅ የሆኑት ጆን ኪገን እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የኑክሊየር መሣሪያዎች ከነሐሴ 9, 1945 ወዲህ አንድም ሰው ገድለው አያውቁም። ከዚያች ዕለት ወዲህ በጦር ሜዳ የወደቁት 50, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች የተገደሉት በአብዛኛው ርካሽ በሆኑና በገፍ በሚመረቱ እንዲሁም በዚሁ ወቅት የዓለምን ገበያ ካጥለቀለቁት ትራንዚስተር ራዲዮዎችና የባትሪ ድንጋዮች የበለጠ ወጪ በማይጠይቁ የጦር መሣሪያዎችና አነስተኛ ካሊበር ባላቸው መትረየሶች ነው። ርካሽ የጦር መሣሪያዎች በበለጸጉት አገሮች ላይ ያደረሱት የኑሮ መናጋት የአደገኛ ዕፆች ንግድ በተስፋፋባቸውና ፖለቲካዊ አሸባሪነት ሥር በሰደደባቸው አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ በመሆኑ የበለጸጉ አገሮች ሕዝቦች የነዚህ መሣሪያዎች በብዛት መበተን የሚያስከትለውን አሰቃቂ ውጤት ሳይገነዘቡ ኖረዋል።”

በሥርጭት ላይ የሚገኙት የነፍስ ወከፍና ቀላል መሣሪያዎች ብዛት ምን ያህል እንደሚሆን በትክክል የሚያውቅ ሰው ባይኖርም ሊቃውንት 500 ሚልዮን የሚያክሉ በውትድርናው መስክ ጥቅም ላይ የዋሉ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች እንደሚኖሩ ይገምታሉ። በተጨማሪም ወታደራዊ ላልሆኑ ግልጋሎቶች የሚውሉ በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ጠመንጃዎችና ሽጉጦች በተራ ሰዎች እጅ እንደሚገኙ ይገመታል። ከዚህ በላይ ደግሞ በየዓመቱ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች እየተመረቱ ገበያ ላይ ይውላሉ።

ተመራጭነት ያላቸው መሣሪያዎች

የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚደረጉ ጦርነቶች ይበልጥ ተመራጭ የሆኑት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት በግጭትና በድህነት መካከል ባለው ዝምድና ላይ የተመሠረተ ነው። በ1990ዎቹ ዓመታት ከተደረጉት ጦርነቶች አብዛኞቹ የተካሄዱት የተራቀቁ መሣሪያዎች የመግዛት አቅም በሌላቸው ድሃ አገሮች ነው። የነፍስ ወከፍና ቀላል መሣሪያዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ርካሽ ናቸው። ለምሳሌ አንድ ዘመናዊ ተዋጊ ጄት አውሮፕላን ለመግዛት 50 ሚልዮን ዶላር ያህል ሲጠይቅ በዚሁ ገንዘብ 200, 000 ሠራዊት ለማስታጠቅ የሚበቃ ጠመንጃ መግዛት ይቻላል።

ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከዚህም ባነሰ ዋጋ የሚገኙበት ጊዜ አለ። የሠራዊት ቁጥር በሚቀነስበት ጊዜ በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ መሣሪያዎች በነፃ ይሰጣሉ። አለበለዚያም ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላው ግጭት እንዲሻገሩ ይደረጋል። በአንዳንድ አገሮች ያለው የጠመንጃዎች ብዛት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ከሃምሳ ብር ባነሰ ገንዘብ ይሸጣሉ ወይም በአንድ ፍየል፣ በአንድ ዶሮ ወይም በአሮጌ ልብሶች ይለወጣሉ።

ዋጋቸው አነስተኛ ከመሆኑና እንደ ልብ የሚገኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ ቀላል መሣሪያዎች ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑበት ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ከፍተኛ የመግደል አቅም አላቸው። አንድ መትረየስ በደቂቃ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥይቶች ሊተፋ ይችላል። በተጨማሪም ለመጠቀምም ሆነ ለመጠገን ቀላል ናቸው። አንድ የአሥር ዓመት ልጅ ጠመንጃ ፈትቶ መግጠም ሊማር ይችላል። በተጨማሪም ሕፃን ልጅ ሳይቀር እጅብ ብለው በቆሙ ሰዎች ላይ አነጣጥሮ እንዲተኩስ ማሰልጠን ይቻላል።

ጠመንጃዎች ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑበት ሌላው ምክንያት ጠንካራ መሆናቸውና ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ለመስጠት መቻላቸው ነው። በቬትናም ጦርነት ዘምተው የነበሩ ወታደሮች አንግተዋቸው የነበሩት እንደ ኤ ኬ-47 እና ኤም 16 የመሰሉት ጠመንጃዎች ዛሬም በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ እያገለገሉ ነው። በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጠመንጃዎች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጊዜ የተሠሩ ናቸው። ከዚህም በላይ ጠመንጃዎችን በቀላሉ ማጓጓዝና መሸሸግ ይቻላል። በአንድ ፈረስ ላይ አንድ ደርዘን የሚያክል ጠመንጃ ጭኖ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ወይም ራቅ ብሎ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ለሚገኙ ሸማቂዎች ማድረስ ይቻላል። አንድ አነስተኛ ሠራዊት የሚያስታጥቅ ጠመንጃ ለመጫን የሚያስፈልጉት ጥቂት ፈረሶች ብቻ ናቸው።

ጠመንጃዎች፣ አደገኛ ዕፆችና አልማዝ

ዓለም አቀፋዊው የጠመንጃዎች ሥርጭት ባሕርይ በጣም የተወሳሰበ ነው። ከፍተኛ ብዛት ያላቸው ጠመንጃዎች በሕጋዊ መንገድ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ይተላለፋሉ። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም የሠራዊት ቅነሳ በመደረጉ መንግሥታት ትርፍ የሆኑ መሣሪያዎችን ለወዳጆቻቸውና ለአጋሮቻቸው በነፃ ሰጥተዋል ወይም ሸጠዋል። በኦስሎ ኖርዌይ የሚገኘው የሰላም ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑ አንዲት ጸሐፊ እንዳሉት ከሆነ ከ1995 ወዲህ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ300, 000 በላይ የሚሆኑ ጠመንጃዎች፣ ሽጉጦች፣ መትረየሶችና ላውንቸሮች ሰጥታለች። የጦር መሣሪያዎችን ፈታትቶ ከማስቀመጥና ከማስጠበቅ ለሌሎች አገሮች መስጠት እንደሚቀልና የሚጠይቀውም ወጪ እንደሚያንስ ይታሰባል። አንዳንድ ተመራማሪዎች በየዓመቱ ከአንዱ ድንበር ወደ ሌላው ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚሸጋገሩ የነፍስ ወከፍና ቀላል መሣሪያዎች ዋጋ ሦስት ቢልዮን ዶላር ሳይደርስ እንደማይቀር ይገምታሉ።

ይሁን እንጂ ሕገ ወጡ ንግድ ከዚህ በጣም ሊበልጥ ይችላል። በጥቁር ገበያ የሚሸጡ መሣሪያዎችን መግዛት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በአንዳንድ የአፍሪካ ጦርነቶች መደበኛ ያልሆኑ ወታደራዊ ቡድኖች በመቶ ሚልዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡ ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በገንዘብ ሳይሆን አልማዝ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች በተዘረፈ አልማዝ ይገዛሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ በማለት ተችቷል:- “በሙስና የተዘፈቁ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች አማፂያን ምህረት የለሾች ይሆናሉ፤ ድንበሮችን መቆጣጠርም በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። . . . የሚያብለጨልጩት ድንጋዮች ለባርነት ሥራ፣ ለነፍስ ግድያ፣ ለአካል ጉዳተኛነት፣ ከቤት ለመፈናቀልና አጠቃላይ ለሆነ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ምክንያት ሆነዋል።” በጠመንጃ የተለወጠ ዕንቁ በጣም በተዋበ የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ የዘላለማዊ ፍቅር ተምሳሌት ሆኖ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ መሸጡ ምንኛ የሚያስገርም ነገር ነው!

በተጨማሪም የጦር መሣሪያዎች ዝውውር ሕገ ወጥ ከሆነው የአደገኛ ዕፅ ንግድ ጋር ዝምድና አለው። ወንጀለኛ ድርጅቶች አደገኛ ዕፆችን ካደረሱ በኋላ በዚያው መንገድ ሲመለሱ ጠመንጃዎችን ይዘው መመለሳቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። በዚህ መንገድ የጦር መሣሪያ በአደገኛ ዕፅ እንደሚመነዘር ገንዘብ ሆኗል።

ጠመንጃዎች ፀጥ እንዲሉ ከተደረገ በኋላስ?

ጦርነቶች ካበቁ በኋላ ተዋጊዎቹ ይገለገሉባቸው የነበሩት ጠመንጃዎች በወንጀለኞች እጅ ይገባሉ። ከፖለቲካዊ ዓመፅ ወደ ተራ የወንጀለኝነት ዓመፅ በተሸጋገረች አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት አገር የሆነውን እንመልከት። በዚያች አገር የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ዓመፅ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ10, 000 ሰዎችን ሕይወት ቀጭቷል። ይህ ግጭት ካበቃ በኋላ የተራ ወንጀል ዓመፅ በከፍተኛ መጠን አደገ። በታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ውድድር ምክንያት ነፍሰ ገዳዮች ተቀጥረው በተቀናቃኝ ኩባንያዎች አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ላይ እንዲተኩሱ ተደርጓል። በዘረፋና በሌሎች ወንጀሎች እንደ ጠመንጃ ያሉትን ወታደራዊ መሣሪያዎች የመጠቀም ልማድ እየተስፋፋ መጥቷል። በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ በጠመንጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 11, 000 የደረሰ ሲሆን ይህ አኃዝ ጦርነት በማይካሄድባቸው አገሮች ከሚፈጸም ግድያ አንጻር ሲታይ በዓለም የሁለተኛነት ደረጃ ይይዛል።

ወንጀለኞች የታጠቁና አደገኞች መሆናቸውን ማወቅ ብቻውን ፍርሃትና ሥጋት ያሳድራል። በብዙ ታዳጊ አገሮች ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩት በግንብና በኤሌክትሪክ አጥር ተከብበው ቀንና ሌሊት እየተጠበቁ በመሆኑ በምሽግ ውስጥ እንደሚኖሩ ያህል ሆኗል። ያደጉ አገሮች ነዋሪዎችም ቢሆኑ ጥንቃቄ ለማድረግ ተገድደዋል። የእርስ በርስ ብጥብጥ በሌለባቸው አገሮች እንኳን ሁኔታው የተለየ አልሆነም።

ስለዚህ ጦርነት በሚካሄድባቸው አገሮችም ሆነ “ሰላም” ባለባቸው አገሮች ላለው አለመረጋጋት ጠመንጃዎች አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በጠመንጃዎች የደረሰውን ጉዳት በትክክል ሊመዝን የሚችል ሰው የለም። እኛም ብንሆን በጠመንጃ የተገደሉትን፣ የቆሰሉትን፣ የሚወዱትን ሰው ያጡትንና ኑሯቸው የተናጋባቸውን ቆጥረን መጨረስ አንችልም። ሆኖም መላው ዓለም በጦር መሣሪያዎች የተጥለቀለቀ መሆኑንና ቁጥራቸው ያለማቋረጥ ከፍ እያለ መሄዱን እናውቃለን። አንድ ነገር መደረግ አለበት የሚሉ ሰዎች ቁጥርም እየበዛ ሄዷል። ታዲያ ምን ሊደረግ ይችላል? ምንስ ይደረጋል? በሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ የቀድሞ ተዋጊ ‘ክፉኛ ተሞኝቶ እንደነበረ’ ተገነዘበ

በመጀመሪያው ርዕስ የተገለጹትን ሰዎች ለስደተኝነት በዳረገው ውጊያ በውትድርና የተካፈለ አንድ ልጅ ተዋግቶ በቁጥጥር ሥር እንድትውል ባስቻላት ከተማ ባልጠበቀው ሁኔታ ሥራ ፈትና ቤሳ ቤስቲን የሌለው ድሃ ሆነ። የመሪያቸው ልጅ በተዋበ ሞተር ብስክሌት ከተማዋን ሲያስስና የቀድሞዎቹ የጦር አበጋዞች ሥልጣንና ክብር ለማግኘት ሲሯሯጡ ማየቱ በጣም እንዳሳዘነው ተናገረ። “ሰዎችን እየገደልኩና እየተተኮሰብኝ በጫካ ያሳለፍኩትን አምስት ዓመት ሳስብ ክፉኛ ተሞኝቼ እንደነበረ ይሰማኛል። ሕይወታችንን እንሠዋ የነበረው ላሉበት ቦታ እንዴት እንደበቁ እንኳን ለማያስታውሱ ሰዎች ነው” ይላል ይህ የቀድሞ ተዋጊ።

[ምንጭ]

ሽፋኑና ገጽ 7:- በውትድርና አገልግሎት የተሰማራ ልጅ:- Nanzer/Sipa Press

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ተሸሽጎ መዳን አይቻልም”

ዘመናዊው ጠመንጃ የመግደል ኃይል ይኑረው እንጂ የአቅም ውሱንነት አለው። ሥራው ጥይት መተኮስ ብቻ ነው። በጠንካራ ግንብ ወይም ምሽግ ውስጥ የተሸሸጉ ሰዎችን መግደል አይችልም። አንድ ወታደር የውጊያ ፍርሃትና ድንጋጤ ሲያንቀጠቅጠው ዒላማው ላይ አስተካክሎ መተኮስ አይችልም። በትክክል ቢተኩስ እንኳን ዒላማውን መምታት የሚችለው እስከ 460 ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ ብቻ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል ለዚህ “ችግር” መፍትሔ አግኝቷል። ኦብጀክቲቭ ኢንዲቪጅዋል ኮምባት ዌፐን (ዒላማ ፈላጊ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ (ኦ አይ ሲ ደብሊው)) የተባለ የተራቀቀ ሁለገብ ጠመንጃ ፈልስፏል። ኦ አይ ሲ ደብሊው ቀላልና በአንድ ወታደር ሊነገብ የሚችል ሲሆን ጥይት ብቻ ሳይሆን ባለ 20 ሚሊ ሜትር ፈንጂዎችን የመተኮስ ችሎታ አለው። ይህን ጠመንጃ ልዩ የሚያደርገው ሌላ ነገር ደግሞ ምሽግ ውስጥ የተደበቀ ጠላት መግደል መቻሉ ነው። ወታደሩ ከዒላማው በላይ ወይም አካባቢ መተኮስ ይበቃዋል። ጠመንጃው በራሱ የተመረጠው ዒላማ በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝ ካሰላ በኋላ ኤሌክትሮኒክ ቦምብ ማፈንጃ ይለቅና ቦምቡ ትክክለኛው ርቀት ላይ እንዲፈነዳ ያደርጋል። የተተኮሰበት ጠላት በፍንዳታው ኃይል ድምጥማጡ ይጠፋል። መሣሪያውን የሚሠራው ኩባንያ ተወካይ “ይህ መሣሪያ ያለው ልዩ ችሎታ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በዘወርዋራ ቦታ ያለ ዒላማ ሳይቀር መምታት ያስችላቸዋል” ብሏል። ማነጣጠሪያው በኢንፍራሬድ ጨረር ስለሚሠራ በጨለማ ጊዜ ሳይቀር ዒላማ ማየት ይቻላል።

ከዚህ ጠመንጃ “ተሸሽጎ መዳን አይቻልም” በማለት የሚኩራሩት ሠሪዎች መሣሪያው ኤም 16 እና ኤም 203 ከሚባሉት ላውንቸር ወንጫፊ መሣሪያዎች አምስት እጥፍ የበለጠ የመግደል ኃይል እንዳለው ይናገራሉ። በርቀት የመምታት አቅሙም በእጥፍ ይበልጣል። በዚህ ጠመንጃ የሚጠቀሙ ወታደሮች በትክክል ለማነጣጠር መጨነቅ አያስፈልጋቸውም። በማነጣጠሪያው ቀዳዳ አይተው ቃታውን መሳብ ብቻ ነው። ወዲያው የጥይትና የፈንጂ እሩምታ አካባቢውን ያናጋዋል። ሥራው በታሰበበት ፕሮግራም ከቀጠለ በ2007 የመጀመሪያው ወታደራዊ ጓድ ኦ አይ ሲ ደብሊው ይታጠቃል።

ይሁን እንጂ ተቺዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ:- ወታደሮች የጠላት ተዋጊዎች ከሰላማዊ ሰዎች ጋር ተጎራብተው የሚኖሩባቸውን የተጨናነቁ አካባቢዎች በሚቃኙበት ጊዜ እንዴት በዚህ መሣሪያ መጠቀም ይችላሉ? ኦ አይ ሲ ደብሊው ለሌሎች የዓለም አገሮች ተሸጦ መሣሪያውን የገዙት ሠራዊቶች አፈሙዙን ወደ ገዛ ሕዝቦቻቸው በሚያዞሩበት ጊዜ ምን ይደረጋል? መሣሪያው በአሸባሪዎችና በወንጀለኞች እጅ ቢገባስ?

[ምንጭ]

Alliant Techsystems

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ብዙ ጊዜ ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በአልማዝና በአደገኛ ዕፆች ይለወጣሉ