በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ምን ተስፋ አለ?

የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ምን ተስፋ አለ?

የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ምን ተስፋ አለ?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥታት የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን ሕገ ወጥ ንግድ መግታት ስለሚቻልበት መንገድ መወያየት ጀምረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤም በጉዳዩ ላይ መክሯል። ሪፖርቶች ተዘጋጅተዋል፣ የመፍትሔ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፣ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል። ይሁን እንጂ በጥቁሩ ገበያ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ማተኮር ዋነኞቹን የመሣሪያ ነጋዴዎች፣ ማለትም መንግሥታትን አለ ታዛቢ ያስቀራል የሚሉ ተቺዎች አሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጋዊና ሕገወጥ በሆነው የመሣሪያ ሽያጭ መካከል ያለው ልዩነት ብዙም ግልጽ አይደለም። ብዙዎቹ ሕገወጥ መሣሪያዎች በአንድ ወቅት በሕጋዊ መንገድ የተሸጡ ናቸው። በአንድ ወቅት ለጦር ወይም ለፖሊስ ሠራዊት ተሸጦ የነበረ መሣሪያ ተሠርቆ ጥቁር ገበያ ውስጥ ይገባል። በተጨማሪም ከመጀመሪያው ሻጭ ፈቃድና እውቅና ውጭ መሣሪያዎች ለሌላ ሁለተኛ ተቀባይ መተላለፋቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። አርምስ ኮንትሮል ቱደይ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ብሔራዊ መንግሥታት በተለይ በቀላል መሣሪያዎች ንግድ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ከመደገፍ አልፈው በዚህ ንግድ ውስጥ ያላቸውን ሚና መመርመር ይኖርባቸዋል።” ብሔራት ይዋል ይደር እንጂ በነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ንግድ ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰዳቸው አይቀርም የሚል ተስፋ ያላቸው ብዙዎች ቢሆኑም አንድ ጋዜጠኛ “[የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ] ምክር ቤት ቋሚ አባላት የሆኑት አምስቱ አገሮች ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆነው የጦር መሣሪያ ንግድ ባለድርሻ በሆኑበት ሁኔታ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ብለን መጓጓት አይኖርብን ይሆናል” ብለዋል።

የቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን ስርጭት የመቆጣጠርን ችግር ይበልጥ የሚያባብሰው እነዚህን መሣሪያዎች ማምረት አስቸጋሪ አለመሆኑ ነው። እንደ ታንክ፣ አውሮፕላንና የጦር መርከብ የመሰሉትን የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎች የሚያመርቱ አገሮች ከአንድ ደርዘን የማይበልጡ ሲሆን ቀላል መሣሪያዎችን ግን 50 በሚያክሉ አገሮች የሚገኙ ከ300 የሚበልጡ ድርጅቶች ያመርታሉ። የጦር መሣሪያ አምራች ቁጥር መብዛቱና እየጨመረም መሄዱ የብሔራትን የመሣሪያ ክምችት ከማዳበር አልፎ የጦር መሣሪያዎች በሚሊሺያዎች፣ በሸማቂዎችና በወንጀለኛ ድርጅቶች እጅ የሚገቡበትን አጋጣሚ ያሰፋል።

የተፋፋመ ክርክር የሚደረግባቸው ጉዳዮች

እስካሁን በአብዛኛው ያተኮርነው የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በጦርነት በታመሱ አገሮች እንዴት ባለ አገልግሎት ላይ እየዋሉ እንዳለ ነው። ይሁን እንጂ ጦርነት በማይደረግባቸውና የተረጋጉ በሚባሉ አገሮችም የጠመንጃ ቁጥጥር ጉዳይ የተፋፋመ ክርክር እየተደረገበት ነው። የጠመንጃ ዝውውርን የሚገታ ጠንካራ ሕግ መውጣት አለበት የሚሉት ወገኖች ጠመንጃ በበዛ መጠን ግድያ ይበራከታል ብለው ይከራከራሉ። ቁጥጥሩ በላላበትና ጠመንጃ እንደልብ ማግኘት በሚቻልበት በዩናይትድ ስቴትስ የነፍስ ግድያ ወንጀል ከጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ ሲሆን ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት በእንግሊዝ አገር ግን ዝቅተኛ ነው ይላሉ። ቁጥጥር መደረግ የለበትም የሚሉት ወገኖች ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች ጠመንጃ በቀላሉ ለማግኘት በሚችሉበት በስዊዘርላንድ የነፍስ ግድያ ወንጀል ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ ይቃወማሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ አለጠመንጃ የተፈጸሙ የነፍስ ግድያ ወንጀሎች ከብዙዎቹ የአውሮፓ አገሮች አጠቃላይ የነፍስ ግድያ ወንጀል እንደሚበልጥ በጥናቶች መረጋገጡ ሁኔታውን ይበልጥ አወሳስቦታል። ሆኖም ከዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ የነፍስ ግድያ ወንጀል የበለጠ አለጠመንጃ ነፍስ ግድያ የሚፈጸምባቸው አገሮች አሉ።

ለአንድ ዓይነት አመለካከት ድጋፍ ለማግኘት ስታትስቲካዊ መረጃዎችን በአግባቡም ሆነ አጣምሞ መጠቀም የተለመደ ነገር ነው። ስለ ጠመንጃ ቁጥጥር በሚደረገው ክርክር ረገድም ለእያንዳንዱ መከራከሪያ ነጥብ ሌላ አሳማኝ የሚመስል መቃወሚያ ይቀርባል። ጉዳዩ በጣም የተወሳሰበ ነው። ይሁን እንጂ ሊቃውንቱ በአጠቃላይ የሚስማሙበት ነጥብ አለ። የነፍስ ግድያና የወንጀል መጠን መብዛትና ማነስ ባለጠመንጃ በመሆንና ባለመሆን ጉዳይ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም።

ከፍተኛ ተሰሚነት ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጠመንጃ ማኅበር “ሰዎችን የሚገድሉት ሰዎች እንጂ ጠመንጃዎች አይደሉም” የሚል አስተያየት አዘውትሮ ሲሰጥ ይደመጣል። በዚህ አባባል መሠረት ጠመንጃ የተሠራው ለመግደያ ቢሆንም ጠመንጃው በራሱ አይገድልም። ሆነ ብሎም ይሁን ሳያውቅ ቃታ የሚስብ ሰው መኖር አለበት። እርግጥ ጠመንጃ ሰዎችን በቀላሉ መግደል ያስችላል ብለው የሚከራከሩ ይኖራሉ።

ሰይፍን ማረሻ ለማድረግ መቀጥቀጥ

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የነፍስ ግድያ ወንጀል የመግደል ዓላማ ካላቸው ሰዎች እጅ ጠመንጃ በመንጠቅ መፍትሔ አያገኝም። ወንጀል ማኅበራዊ ችግር እንጂ የመሣሪያ ችግር አይደለም። ትክክለኛው መፍትሔ የሰዎችን ዝንባሌና አስተሳሰብ በመለወጥ ላይ የተመካ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “[አምላክ] በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”​—⁠ኢሳይያስ 2:​4

ይህ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ሊሆን የማይችል ነገር አይደለም። የኢሳይያስ ትንቢት ዛሬ በመላው ዓለም በሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ነው። በምሳሌያዊ ሁኔታ የጦር መሣሪያቸውን ወደ ሰላማዊ መሣሪያ መለወጣቸው አምላካቸውን ለማስደሰትና ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል። ጊዜው ሲደርስ ደግሞ በምድር የሚኖር ሰው ሁሉ በአምላክ መንግሥት ሥር በተሟላ ሰላምና ፀጥታ ይኖራል። (ሚክያስ 4:​3, 4) በዚያ ዘመን ጠመንጃዎች ሰዎችን አይገድሉም። ሰዎችም ሰዎችን አይገድሉም። የመግደያ መሣሪያዎች ጊዜ ያለፈባቸው አሮጌ ዕቃዎች ይሆናሉ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

‘ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ ’