በሞዛምቢክ የደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ—ክርስቲያኖች ለጉዳቱ ሰለባዎች የለገሱት እርዳታ
በሞዛምቢክ የደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ—ክርስቲያኖች ለጉዳቱ ሰለባዎች የለገሱት እርዳታ
ሞዛምቢክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ከደረሰባቸው የውኃ መጥለቅለቅ ለመዳን በየዛፉ ቅርንጫፍ ላይ የተንጠለጠሉትን የሞዛምቢክ ሰዎች ምስል በቴሌቪዥን የተመለከቱ ሁሉ ልባቸው በእጅጉ አዝኗል። አንዲት ሴት በዛፉ ላይ እንዳለች በመውለዷ ልጅዋንና እርሷን እርዳታ ማግኘት ወደሚችሉበት ቦታ ለመውሰድ በሄሊኮፕተር ሲያነሷቸው ታይቷል። ይሁን እንጂ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ውኃው እስኪጎድል ወይም ሄሊኮፕተሮች መጥተው እስኪያነሷቸው ድረስ አንዳንዶቹም ከእባቦች ጋር ዛፍ ላይ እንደተንጠለጠሉ ለቀናት ቆይተዋል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት የጀመረው የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በሆነችው በማፑቶ ከባድ ዝናብ በጣለበት ወቅት ነበር። በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከከተማው ወጣ ብለው የሚገኙ ቦታዎች በውኃ ተጥለቀለቁ። በአንዳንድ ቦታዎች ውኃው የቤት ጣሪያዎችን ሸፍኖ ነበር። መንገዶች ወደ ትላልቅ ወንዞች ተለወጡ። ሰፋፊ ቦዮች የተፈጠሩ ሲሆን ቤቶችንና መኪኖችን ጨምሮ ሁሉም ነገር ለማለት ይቻላል በውኃ እየታጠበ ሄዶ ነበር። ይሁንና ገና የከፋ ነገር ይጠብቃቸው ነበር።
ዝናቡ መላውን የአገሪቱን ደቡባዊ ክፍል ማጥለቅለቁን ቀጠለ። በሞዛምቢክ አጎራባች አገሮች ማለትም በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባብዌና በቦትስዋናም ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበር። የኢንኮማቲ፣ የሊምፖፖና የዛምቤዚ ወንዞች ወደ ውቅያኖስ የሚገቡት ሞዛምቢክን አቋርጠው
ስለሆነ በእነዚህ ወንዞች ሙላት ምክንያት ሰፊ የሞዛምቢክ ክልል ውድመት ደርሶበታል። በዚህ ድንገተኛ አደጋ ወቅት ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው ስለተረዳዱበት መንገድ ማወቅ እምነትን የሚያጠነክር ነው።መጀመሪያ ላይ የደረሰውን ጉዳት መገምገም
ባለፈው ዓመት የካቲት 9 ቀን ማፑቶ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የወከላቸው ሁለት ወንድሞች ሰሜናዊውን ክፍል ለመጎብኘት ሄዱ። ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ የሺናቫኒን ከተማ ያለፉ ሲሆን እዚህ ከተማ የሚገኘው የኢንኮሉዋኔ ወንዝ ከፍታው ጨምሮ ነበር። ከዚያም የጌዛ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ሻይሻይ ለመቀጠል ወሰኑ። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ኃይለኛ ዝናብ ሲጥል ከፍተኛ ውድመት በሚደርስባት በሼክዌ ከተማ ችግር እንደነበረ የሚያሳይ አንድም ፍንጭ ስላልነበረ ወደ ማፑቶ ለመመለስ ወሰኑ።
ይሁን እንጂ ወደ ሺናቫኒ ሲቃረቡ ፖሊስ አስቆማቸውና “ከደቡብ አፍሪካ የመጣው ጎርፍ ዋናውን መንገድ ቆርጦታል። ስለዚህ አውቶቡሶችም ሆኑ የጭነት መኪኖች ማለፍ አይችሉም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ጠዋት ያለፉበት መንገድ አሁን ሙሉ በሙሉ በውኃ ተውጧል! ትንሽ ከፍ ብሎ በስተ ሰሜን በኩል የሚገኙት ወንዞችም እየሞሉ ስለነበር አካባቢው ከቀረው የአገሪቱ ክፍል ተቆራርጦ ነበር።
ስለዚህ ሁለቱ ወንድሞች ሌሊቱን አቅራቢያቸው በምትገኘው በሞሲያ ለማሳለፍ ወሰኑ። ሆኖም ሌሊት ላይ ሁኔታው በጣም ተባብሶ የሺናቫኒ ከተማ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ በመጥለቅለቋ እዚያ የሚኖሩ ሰዎች ንብረታቸውን በሙሉ አጡ። ሞሲያ ውስጥ የተቋቋመ ተለዋጭ የስደተኞች መጠለያ በመኖሩ ምሥክሮቹ እዚያ ወዳለው የመንግሥት አዳራሽ እንዲሄዱ ዝግጅት ተደረገ። ምሥክሮቹ ፈጥነው ወደ ገበያ በመሄድ ሩዝ፣ ባቄላ፣ ዱቄትና ዘይት የመሳሰሉትን መሠረታዊ ነገሮች ገዙ።
አሁን ትኩረት የተደረገው በሼክዌ እና አካባቢዋ ባሉ ከተሞች ውስጥ በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ ነበር። ሼክዌ የሚገኙት የጉባኤ ሽማግሌዎች ስብሰባ ካደረጉ በኋላ አንድ ላይ ሆነው አካባቢውን ለቅቆ ለመውጣት ዝግጅት አደረጉ። “ይህንን ቦታ በፍጥነት ለቅቃችሁ ወደ ሞሲያ ሂዱ!” የሚለው መልእክት ተሰራጨ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በሺናቫኒ የሚገኙ ብዙ ምሥክሮች ሞሲያ እንዳልደረሱ በመስተዋሉ ሌሎች ምሥክሮች ሄደው ያሉበትን ሁኔታ እንዲያጣሩ ተደረገ። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ቤቱ ውስጥ እንዳለ ሰጥሞ በመሞቱ የቀብሩ ሥነ ሥርዓት የተካሄደ ሲሆን በየጣሪያዎቹ ላይ የነበሩትን አንዳንድ ምሥክሮች ጨምሮ ሁሉም ወደ ሞሲያ እንዲሄዱ ተደረገ።
እነዚህ ዝግጅቶች ከተደረጉ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው የወከላቸው ወንድሞች ወደ ትንሿ የጠረፍ ከተማ ወደ ቢሌኒ ተጉዘው አውሮፕላን በመኮናተር ወደ ማፑቶ ተመለሱ። በዕይታቸው ሥር የነበረው ክልል በጠቅላላ በጎርፍ ተጥለቅልቆ ነበር። በጌዛ ክፍለ ሃገር ብቻ 600, 000 ሰዎች የጉዳቱ ሰለባዎች እንደሆኑ ሪፖርት ተደርጓል።
ችግሩ ተባባሰ
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የዝናቡ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የመካከለኛው ሞዛምቢክ ግዛቶች ሳይቀሩ ወደሙ። ከዚያም የካቲት 20 የተነሳው ኤሊን የተባለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በኢንዮምቦኔ፣ በሶፋላ እንዲሁም በሞኒካ ግዛቶች ከባድ ዝናብ በማስከተሉ ተጨማሪ የውኃ መጥለቅለቅ፣ ሞትና ውድመት ደርሷል።
የካቲት መገባደጃ ላይ የሼክዌ ከተማና አጎራባቾቿ ክልሎች በጠቅላላ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በጎርፍ ተጥለቀለቁ። ቅዳሜ የካቲት 26 እኩለ ሌሊት ሊሆን ሲል ጎርፉ በመንገድ ላይ ያገኘውን ሁሉ የሚጠራርግ ፈረሰኛ ውኃ ሆኖ መጣ። “ከመኝታችን የነቃነው አንድ ጎረቤታችን በመስኮት በኩል ስትጮኽ ነበር” በማለት ሉዊሽ ሺትላንጎ የተባለ የ32 ዓመት ምሥክር ተናግሯል።
ሺትላንጎ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ከአልጋው ውስጥ ዘልለን ስንወጣ ውኃው እያስገመገመ ሲመጣ ይሰማን ነበር። በምንሸሽበት ወቅት በመንገዳችን ላይ ብዙ እባቦች አጋጥመውን ነበር። አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ከፍ ያለ ቦታ ብናገኝም ረፋዱ ላይ ግን ጎርፉ ሁሉንም ቦታ ሸፍኖት ስለነበር ዛፍ ላይ መውጣት ነበረብን። አንድ ላይ የነበርነው 20 የምናክል ሰዎች ነን።
“በመጀመሪያ ዛፎቹ ላይ የወጡት ወንዶቹ ነበሩ። ከዚያም ሴቶቹ ተለቅ ተለቅ ያሉትን ልጆች ለወንዶቹ አቀበሉአቸው። ወንዶቹም ልጆቹን ከዛፉ ቅርንጫፎች ጋር ካሠሩዋቸው በኋላ ሴቶቹ ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ተከተሉ። አሁንም
አሁንም ከዛፎቹ እየወረድን በአካባቢው እንደሚበቅል የምናውቀውን ኦቾሎኒ በውኃ ከተሸፈነው መሬት ላይ ለማግኘት እናስስ ነበር።“ከሦስት ቀናት በኋላ ግን ሁላችንም በእግራችን ወደ ሼክዌ እንድንጓዝ ተወሰነ። ውኃው ደረታችን ላይ የደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ ከኃይለኛው ሞገድ ጋር መታገል ነበረብን። በጉዞአችንም ላይ እንዳለን ዛፎችና ጣሪያዎች ላይ የወጡ ብዙ ሰዎች ተመለከትን። በሚቀጥለው ቀን ግን ውኃው በመጉደሉ የጭነት መኪኖች ወደ ከተማው መግባትና ሰዎችን ወደ ሞሲያ መውሰድ ችለው ነበር።”
የምሥክሮቹ መጠለያ
መጋቢት 4 የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አውሮፕላን በመከራየት የወከላቸውን ወንድሞች ጉዳት ወደደረሰበት ቦታ ላካቸው። አብዛኛው ሕዝብ ወደ ትልቅ የስደተኞች መጠለያነት ወደተለወጠችው ሞሲያ ሸሽቶ ነበር። ብዙዎቹ የጎርፉ ሰለባዎች ለኢንፍሎዌንዛ፣ ለምግብ እጦት፣ ለወባና ለሌሎች በሽታዎች ተዳርገው ነበር።
ቦታው የጦር ቀጠና ይመስል ነበር። የተለያዩ አገሮች የላኩዋቸው ሄሊኮፕተሮች የከተማውን ሰማይ የሞሉት ሲሆን የያዙትን እቃ የሚያራግፉባቸው ጊዜያዊ ማኮብኮቢያዎች ተሠርተው ነበር። ምሥክሮቹ ያቋቋሙት የእርዳታ ቡድን ሞሲያ ሲደርስ ለጎርፉ ሰለባዎች የሚሆን ምግብ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የሕክምና ማዕከልም አቋቁሟል። ይሁንና ቡድኑ እንዲህ ከማድረጉ በፊት የአካባቢውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ፈቃድ የጠየቀ ሲሆን ባለሥልጣናቱም ቡድኑ በራሱ ተነሳስቶ እንዲህ ያለ እርምጃ በመውሰዱ አመስግነውታል።
ሌሎችን ጨምሮ ወደ 700 የሚጠጉ ምሥክሮችን ባቀፈው መጠለያ ጣቢያ ሁልጊዜ ከጠዋቱ 12:30 ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይመረመራል። ክርስቲያን እህቶች ያዘጋጁት ቁርስ ሲደርስ እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ በስሙ ይጠራል። ከዚያም የቤተሰቡ ራስ ምን ያህል ሳህኖች እንደሚያስፈልጉት በጣቱ ምልክት ይሰጥና ምግቡ ይታደላል።
በመጠለያው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በደንብ የተደራጀ ነው። አንዳንዶች ምግብ እንዲገዙ ይመደባሉ። ሌሎች ደግሞ የመጠጡን ውኃ፣ የመጸዳጃ ቤቶቹን እንዲሁም የሌሎች ነገሮችን ንጽሕና እንዲጠብቁ ይመደባሉ። እንዲህ
ያለው ጥሩ አደረጃጀት በመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሳይስተዋል አላለፈም። እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- ‘እዚህ መሆን ያስደስታል። ምግብ ሳይደርሰው የሚቀር የለም፤ በመካከላቸውም ጥል የለም።’ አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ‘እያንዳንዱ ሰው ወደ ምሥክሮቹ መጠለያ ሄዶ ነገሮች እንዴት መከናወን እንደሚገባቸው ማየት አለበት’ ሲሉ ተናግረዋል።አንድ ቀን እርዳታ ሰጪ ኮሚቴው ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አንድ ላይ አሰባስቦ ቅርንጫፍ ቢሮው ለጎርፉ ተጠቂዎች የሚሆኑ የመኖሪያ ቤቶችንና የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባትና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ እንዳሰበ ገለጸላቸው። በሚቀጥለው ቀን የዕለት ጥቅሱ በመካሄድ ላይ እንዳለ ይህንን እቅድ አስመልክቶ ማስታወቂያ ተነገረ። ጭብጨባው ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ ነበር።
ባለሥልጣናቱ ሁለት ትልልቅ ድንኳኖች ለግሰው የነበረ ቢሆንም ብዙዎች የሚያድሩት ውጭ ነበር። በዚያ አካባቢ የጉባኤው ንብረት በሆነ ቦታ ላይ አንድ ትልቅ የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት ከጎርፉ ሰለባዎች የተውጣጣ አንድ ቡድን ተቋቋመ። ሁለት መቶ ሰዎችን የሚይዘው ከመቃና ከቆርቆሮ የተሠራ አዳራሽ ግንባታ በሁለት ቀናት ውስጥ ተጠናቀቀ! ይህ አዳራሽ የሞዛምቢካውያንን የአሠራር ዘይቤ የተከተለ ነው።
በገለልተኛ አካባቢዎች የሚኖሩትን መፈለግ
በዚህ መሃል መጋቢት 5 ውኃው ጋብ ካለ በኋላ አንድ እርዳታ ሰጪ ቡድን ጎርፉ በአንደኛ ደረጃ ካጠቃቸው ክልሎች መካከል ወደ አንዱ ማለትም ወደ አልዳ ዳ ቤራዚ ከተማ እንዲሄድ ተደረገ። ዘጠና የሚያክሉ ምሥክሮችን የያዘው ይህ ጉባኤ ምን እንደደረሰበት ምንም የታወቀ ነገር አልነበረም።
ቡድኑ እግረ መንገዱን 100, 000 የሚያክሉ ሰዎችን በሚይዘው በሼክላኔ ትልቅ የስደተኞች መጠለያ በኩል አልፎ ነበር። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መንገዱ ራሱ ተጠርጎ የተወሰደ ሲሆን ዓይን ማየት እስከሚችለው ድረስ ክልሉ በጎርፍ ተጥለቅልቆ ነበር። አንድ የቡድኑ አባል እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ሼክዌ ስንደርስ አንድ አሳዛኝ ነገር ተመለከትን። በከተማው መግቢያ ላይ የሚገኙት ብዙ ቤቶች ውኃው እስከ ጣሪያቸው ደርሷል። አብዛኞቹም በጎርፉ ተውጠው ነበር። ቀኑ እየመሸ የነበረ ሲሆን አልዳ ዳ ቤራዚ ለመድረስ ገና 25 ኪሎ ሜትር ይቀረን ነበር።”
በመጨረሻ ቡድኑ ሌሊት ላይ ቦታው ደረሰ። አንድ የቡድኑ አባል እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “ቆም አልንና ቀጥሎ ምን እንደምናደርግ አሰብን።” ግን ወዲያው ሰዎች ብቅ አሉና “ወንድሞች!” ብለው ጮኹ። በኋላም ከፍተኛ የደስታ ሳቅ ተከተለ። ለካስ የአካባቢው ምሥክሮች የሁለቱን መኪኖች መብራት ሲመለከቱ ወንድሞቻቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምተው ነበር። ይህንንም ለሌሎች ነግረው ነበር። ሁኔታውን የተመለከቱ ሰዎች በጣም ከመደነቃቸው የተነሣ ‘እነዚህ ሰዎች በእርግጥ ፍቅር አላቸው። ምግብ በመላክ ብቻ ሳይወሰኑ ሊጠይቋቸውም ጭምር ይመጣሉ!’ ሲሉ ተናግረዋል።
ቀጣይ የሆነ እንክብካቤ
ከአልዳ ዳ ቤራዚ የመጡት ወንድሞች ምግብ፣ መጠለያና ሕክምና ማግኘት ወደሚችሉበት ሞሲያ ወደሚገኘው መጠለያ ጣቢያ እንዲሄዱ እርዳታ ተደረገላቸው። በዚህ መሃል ግን በሞሲያ የነበረው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ምግብ፣ መድኃኒትና ነዳጅ የሚላከው በአየር ስለነበረ እጥረት ተከስቶ ነበር። ከተማዋን ከማፑቶ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል የመሬት መገናኛ መስመር በአስቸኳይ መክፈት አስፈልጎ ነበር። ይህንንም መጋቢት 8 ቀን ማከናወን ተችሎ ነበር።
ትልቁ የሻይሻይ ከተማ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ከመጥለቅለቁም በላይ መኻል ከተማ የሚገኙት አንዳንድ ቦታዎች 3 ሜትር ያህል ጥልቀት ባለው ውኃ ተሸፍነው ነበር! ምሥክሮቹ እዚያ የሚገኙትን ወንድሞች ለመርዳት አንድ ኮሚቴ አቋቋሙ። በተጨማሪም በሶፋላና በሞኒካ ግዛቶች የሚገኙ ወንድሞችን በሚያስፈልጋቸው ለመርዳት ሌሎች ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር።
በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ምሥክሮች የእርዳታ ቁሳቁሶች ልከው ነበር። ለምሳሌ፣ የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በብዙ ቶን የሚቆጠሩ ልብሶች፣ ብርድ ልብሶችና፣ ሌሎች ቁሳቁሶች ልኳል። እንዲሁም ብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለጎርፉ ተጠቂዎች የሚሆን ገንዘብ መድቦ ነበር።
ጎርፉ በበቂ ሁኔታ ከጎደለና ቤታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከታወቀ በኋላ የመኖሪያ ቤቶችንና የመንግሥት አዳራሾችን የመገንባቱ ሥራ ተጀመረ። የመልሶ ግንባታ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ሲሆን ወዲያው ብዙ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሥራው ላይ መረባረብ ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከ270 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶችና ቢያንስ አምስት የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል።
ፈቃደኛ በሆኑ ምሥክሮች የተገነቡት የመጀመሪያ ቤቶች ሲያልቁ ሌሎች ሰዎች ሁኔታውን ያስተዋሉ ሲሆን አንድ ጎረቤት እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- ‘እናንተ የምታመልኩት አምላክ ሕያው ነው። ቄሶቻችን መከራ ውስጥ የሚገኙ በጎቻቸውን ረስተዋቸዋል። እናንተ ግን ይኸው እንደዚህ የሚያምር ቤት ታገኛላችሁ።’ በእነዚህ አካባቢዎች ብዙዎች የይሖዋ ምሥክሮች ለሚሰብኩት የመንግሥት መልእክት ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተጀምረዋል።—ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 21:3, 4
ብዙዎቹ ምሥክሮች ቁሳዊ ንብረቶቻቸውን ቢያጡም አንዳቸውም ቢሆኑ እምነታቸውን አላጡም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ አምላክና በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ላይ ያላቸው እምነት ተጠናክሯል። ለዚህ አሰቃቂ ክስተት ፈጣን ምላሽ ለሰጠው ለዓለም አቀፉ አፍቃሪ የወንድማማች ማኅበር አመስጋኞች ናቸው። የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤና ጥበቃ በግለሰብ ደረጃ በማግኘታቸው “ይሖዋ ታላቅ ነው” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ዘወትር ያስታውሳሉ።—መዝሙር 48:1
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሻይሻይ ከተማ በጨቀየ ውኃ ተጥለቅልቃ ነበር
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእርዳታ ቁሳቁሶች ተልከው ነበር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምሥክሮቹ የእርዳታ ቡድን የሕክምና ማዕከል አቋቁሟል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳዲስ ቤቶች መሠራታቸውን ቀጥለዋል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትልቁ የስደተኞች መጠለያ 100,000 ሰዎች ይዞ ነበር