አያቶቼን በቅርብ ላውቃቸው የሚገባኝ ለምንድን ነው?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
አያቶቼን በቅርብ ላውቃቸው የሚገባኝ ለምንድን ነው?
“እናቴና እኔ ሳንግባባ በምንቀርበት ጊዜ አያቴ መጥታ ታስማማናለች።”—ዳመሪስ
“በታሪክ ዘመናት ሁሉ አያቶች ለቤተሰብ ሕይወት ስምምነትና ዘላቂነት ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል።” ግራንድፓረንትስ ፓወር! በተባለው መጽሐፋቸው ይህን ያሉት ዶክተር አርተር ኮርንሃበር ናቸው። እንዲህ በማለት አክለው ጽፈዋል:- “እንደ አስተማሪ፣ የወላጆች ረዳት፣ ታሪክ አስተላላፊ፣ ሞግዚት፣ አማካሪ፣ አልፎ ተርፎም አጫዋች በመሆን በስነ ልቦና፣ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ መስኮች የሚያበረክቱት ድርሻ ከፍተኛ ነው። አያቶች የሚጫወቱትን ጉልህና በርካታ ገጽታ ያለው ሚና ኅብረተሰባችን እንዴት ችላ ሊለው እንደቻለ ሳስብ ይገርመኛል።”
ቀደም ባሉት ዘመናት አያቶች ለቤተሰብ ሕይወት በተለይ ደግሞ ይሖዋ አምላክን ለሚያመልክ ቤተሰብ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያን አረጋውያንን እንዲያከብሩና ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጧቸው ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:32) በተለይ ደግሞ አያቶች አክብሮት ሊሰጣቸው የሚገቡ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:4
የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ሁኔታው ተለውጧል። ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦች ተራርቀው መኖራቸው እንቅፋት በመሆኑ በርካታ ወጣቶች ከአያቶቻቸው ጋር የሚገናኙበት አጋጣሚ የላቸውም። የሰዎች አስተሳሰብም ተለውጧል። በብዙ የዓለም ክፍል አረጋውያን ዝምድና ያላቸውም ጭምር ተገቢውን አክብሮት አያገኙም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) በትውልዶች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ሰፍቶ አሁን የሰማይና የምድርን ያህል ሆኗል። በርካታ ወጣቶች አያቶቻቸውን እንደ አረጁና ኋላ ቀር እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። እነዚህ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ተጽዕኖዎችና ችግሮች ይገነዘባሉ ብለው አያስቡም።
አንተም የሚሰማህ እንደዚህ ከሆነ ጉዳዩን እንደገና ለማጤን ተዘጋጅ! አያቶችህን በተለይ ደግሞ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን በቅርብ ለማወቅ መጣርህ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልሃል። ካልሆነ ግን ብዙ ነገር ሊያመልጥህ ይችላል። እንዴት?
የጥበብና የምክር ምንጭ
በርካታ ወጣቶች አስቸጋሪ በሆነው አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ወቅት አያቶች እንደ መጠለያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። ሰቨንቲን የተባለው መጽሔት የሚከተለውን ብሏል:- “የበርካታ አሥርተ ዓመታት ተሞክሮ ያካበቱ በመሆናቸው ተመሳሳይ ችግር ካለባቸው የዕድሜ እኩዮቻችሁ ይልቅ ችግሮችን በመፍታት ረገድ እነርሱ የተሻለ እርዳታ ይሰጧችኋል። እናንተም ሆናችሁ የዕድሜ እኩዮቻችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ በሚከሰተው የመጀመሪያ የለውጥ ሂደት ላይ ስትሆኑ አያቶቻችሁ ግን ምሳሌ 16:31
እንዲህ ዓይነት ብዙ የሕይወት ምዕራፎችን አልፈዋል። ጥበበኛ ከመሆናቸውም በላይ ብልሆች ናቸው።” ይህ ምክር መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት “የሸበተ ጠጉር የክብር ዘውድ ነው፣ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል” በማለት የተናገረውን ሐሳብ የሚያስተጋባ ነው።—እርግጥ ነው፣ አያቶችህ ያደጉት አንተ አሁን ከምትኖርበት ፈጽሞ በተለየ ዓለም ውስጥ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት አሁን አንተ የገጠመህ ዓይነት ስሜቶች እነርሱም ይሰሟቸው እንደነበር እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። አንተ እነዚህን ስሜቶች ለመቋቋም በአንጻራዊ ሁኔታ ተሞክሮ የሚጎድልህ ብትሆንም አያቶችህ ግን እነዚህን ስሜቶች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል በሕይወታቸው አይተዋል። (ምሳሌ 1:4) “በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፣ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል” በማለት ጻድቁ ኢዮብ ተናግሯል። (ኢዮብ 12:12) አዎን፣ በዚህ የተነሳ አንድ ወጣት ሚዛናዊ የሆነ ምክር፣ ማበረታቻ ወይም ድጋፍ ማግኘት በሚያስፈልገው ጊዜ አያቶች እሴት ሆነው ሊገኙ ይችላሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ የዳመሪስ ሴት አያት በአንድ ከተማ ሕንጻ ውስጥ ከዳመሪስና ከእናቷ ጋር ይኖራሉ። “እኔና እናቴ ሳንግባባ በምንቀርበት ጊዜ” ትላለች ዳመሪስ “አያቴ መጥታ ታስማማናለች። ነገሮችን ከሌላ አቅጣጫ እንዴት መመልከት እንደሚቻል ታሳየኛለች።”
አሌግዛንድሪያ ቤተሰቧ የሚኖሩበትን አካባቢ ለቅቀው ወደ ሌላ አካባቢ በሄዱበትና የምትማርበትን ትምህርት ቤት መቀየር ግድ በሆነባት ጊዜ ተመሳሳይ ተሞክሮ አጋጥሟታል። “አዲሷ አስተማሪዬ ኃይለኛ ስትሆን አልፎ አልፎም በቁጣ ትገነፍል ነበር” በማለት አሌግዛንድሪያ ትናገራለች። በዚህ የተነሳ አሌግዛንድሪያ አዲሱን ትምህርት ቤቷን ለመልመድ ተቸገረች። ይሁን እንጂ ሴት አያቷ ጥሩ ድጋፍ ሰጥተዋታል። ሁኔታውን ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንድትመለከት በማበረታታት አሌግዛንድሪያ ማስተካከያ እንድታደርግ ረዷት። “አሁን ትምህርት ቤቱንም ሆነ አስተማሪዬን እወዳቸዋለሁ” በማለት አሌግዛንድሪያ ትናገራለች።
ራፋኤል የተባለ በብራዚል የሚኖር አንድ ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል በጀመረ ጊዜ አያቶቹ የሰጡትን እርዳታ በማስመልከት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ስለ ባልንጀርነት እንዲሁም ከአደገኛ ዕፅ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን መቋቋም ስለምችልበት መንገድ ብዙ ምክር ሰጡኝ።” ራፋኤል አሁን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ ያገለግላል።
ግራንድፓረንቲንግ ኢን ኤ ቼንቺግ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ኤዳ ለሼን በአያትነታቸው የገጠማቸውን የራሳቸውን ተሞክሮ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል:- “አንድ ቀን የልጅ ልጄ ጠራችኝና ‘አያቴ፣ የዕኩዮች ተፅዕኖን በተመለከተ እርዳታ እንድትሰጪኝ እፈልጋለሁ’ አለችኝ። አንዳንድ የክፍሏ ተማሪዎች ከወንዶች ጋር ተቀጣጥራ እንድትጫወት ይገፋፏት የነበረ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ወንዶች ስልክ ይደውሉላት ነበር።” እንዲረዷት አያቷን መጠየቋ የሚያስፈልጋትን ድጋፍ እንድታገኝ አስችሏታል። አንተም በተመሳሳይ አፍቃሪ ከሆነ አያትህ ጋር አጠር ያለ ውይይት ማድረግህ እውነተኛ የሥነ ምግባር ድጋፍ የምታገኝበት ምንጭ ሊሆንልህ ይችላል።
እንደ ሕመምና ሞት ያሉ ችግሮች በቤተሰብ ውስጥ በሚነሱበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ አያቶች ከፍተኛ የእርዳታ ምንጭ ሆነው ይገኛሉ። ወጣቷ ሌሲ ባደረበት ከባድ ሕመም ምክንያት አባቷን በሞት ባጣች ጊዜ አያቷ ሐዘኗን እንድትቋቋም ረድተዋታል። “ዝምድናችን ከበፊቱ ይበልጥ ጠነከረ” በማለት ሌሲ ትናገራለች።
ልዩ የፍቅር ማሠሪያ
ከአያትህ ጋር የሚኖርህ ቅርርብ አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በወላጆቻቸው ፊት ከሚሰማቸው ዓይነት ጭንቀት ነፃ ምሳሌ 17:6
ሊሆን ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት አያቶች ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ለየት ያለ ቅርርብ ስለሚኖራቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው” በማለት ይናገራል።—አንተን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” የማሳደግ ከባድ ኃላፊነት የወደቀው በአያቶችህ ላይ ሳይሆን በወላጆችህ ላይ መሆኑንም አስታውስ። (ኤፌሶን 6:4) በዚህ ረገድ ከአያቶችህ ብዙም የሚጠበቅባቸው ነገር ስለ ሌለ የምታደርገውን እያንዳንዱን ነገር የወላጆችህን ያህል ላይከታተሉህ ይችላሉ። እንዲሁም አያቶች ቤተሰብን መንከባከብ ከሚያስከትለው ኃላፊነትና ተጽዕኖ ብዙውን ጊዜ ነፃ ናቸው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እነዚህ ኃላፊነቶች ከሚያስከትሉት ውጥረት ነፃ በመሆናቸው ለሚያስፈልጉህ ነገሮች ምላሽ ለመስጠት ወይም ለአንተ በቂ ትኩረት ለመስጠት ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል። የአሥራ ሰባት ዓመቱ ቶም አያቶቹ እንዴት ይንከባከቡት እንደነበር ያስታውሳል። “የትምህርት ቤት ውጤቱ ጥሩ ከሆነ መጠነኛ ስጦታዎችን ይልኩለት ነበር።” ከዚያም በላይ ፒያኖ ሲማር ወጪውን የቻሉለት እነርሱ ናቸው።
እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለውን ስጦታ መስጠት የሚችሉት ሁሉም አያቶች አይደሉም። ይሁን አንጂ ምናልባት ምስጋናና ማበረታቻ በመስጠት ወይም በየጊዜው የምትናገረውን በጥሞና በማዳመጥ ለአንተ ያላቸውን አሳቢነት ሊገልጹ ይችላሉ። ይህም በመካከላችሁ ጠንካራ ትስስር ሊፈጥር ይችላል። ዳመሪስ ሴት አያቷን በማስመልከት እንዲህ ብላለች:- “ዘና እንድል ትረዳኛለች። የምናገራቸው ነገሮች ያን ያህል ቁም ነገር ያላቸው ባይሆኑም እንኳን እኔን ለማዳመጥ ሁልጊዜ ፈቃደኛ ስለሆነች በፈለኩት ጊዜ ወደ እርሷ ሄጄ ላነጋግራት እችላለሁ።” ጆኔተስ የተባለውም ወጣት ከአያቶቹ ጋር በነፃነት መነጋገር እንደሚችልና ከበድ ያሉ ጉዳዮችን አንስቶ ለማነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ እንዳለው ገልጿል።
መደጋገፍ
አያቶችህ ጥበባቸውንና ፍቅራቸውን ሊለግሱህ ቢችሉም እነርሱም ከአንተ የወጣትነት ጉልበትና ወዳጅነት ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። እንዴት? አያቶችህን ልትረዳቸውና ልትደግፋቸው የምትችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ብዙውን ጊዜ አያቶች አቅማቸው እየተዳከመ ይሄዳል። ወይም ካለባቸው ህመም ጋር ይታገሉ ይሆናል። የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ በመገዛዛትና የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ብታግዛቸው እንደሚበረታቱ ምንም አያጠራጥርም።
በርካታ አያቶች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ በመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ለእነርሱ ያለህን አሳቢነት ሁልጊዜ በማሳየት የሚሰማቸውን የብቸኝነት ስሜት እንዲዋጉና ከሕይወት የሚገኘውን ደስታ ማጣጣማቸውን እንዲቀጥሉ በመርዳት ትልቅ ድርሻ ልታበረክት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የምትተገብርበት አንደኛው መንገድ ነው። “ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው ብድር የመመለስን . . . ግዴታ ይማሩ፤ ምክንያቱም ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 5:4 የ1980 ትርጉም
ከአያቶችህ ጋር መቀራረብህ የአንተንም ሆነ የእነርሱን ሕይወት አስደሳች እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም! እስከ አሁን ድረስ አያቶችህን ብዙም የማትቀርባቸው ልትሆንና ይህንን ሁኔታ ግን መለወጥ ትፈልግ ይሆናል። ሆኖም ከየት መጀመር እንዳለብህ አታውቅ ይሆናል። አያቶችህ የሚኖሩት በጣም ርቆ በሚገኝ አካባቢ ሊሆን ይችላል ወይም ወላጆችህ አንድ ላይ አይኖሩ ይሆናል። ይህም ከአያቶችህ ጋር እንዳትቀራረብ ጋሬጣ ፈጥሮብህ ሊሆን ይችላል። ወደፊት የሚወጣው ርዕስ እንደነዚህ ያሉትን ሁኔታዎች እንዴት መቋቋም እንደምትችል አንዳንድ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦችን ያቀርባል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አያቶች ጥሩ አድማጮች እንዲሁም የምክርና የድጋፍ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አያቶችህን እርዳቸው