በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው በኢኳዶር ነው?

እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው በኢኳዶር ነው?

እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው በኢኳዶር ነው?

ኢኳዶር በሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ የተጻፈ

ገዢውን አጭበርብረውት ይሆን? ለተመልካች እንደዚያ ሊመስል ይችላል። ደግሞም እኮ ሰውዬው እውነተኛውን ፓናማ ባርኔጣ ለመግዛት 300 የአሜሪካ ዶላር ነው የከፈለው። ሆኖም ሻጩ ባርኔጣውን ያወጣው “በኢኳዶር የተሠራ” የሚል ጽሑፍ በግልጽ ከሠፈረበት ካርቶን ውስጥ ነው! ታዲያ ይህ ማጭበርበር አይደለም? በጭራሽ። እንዲያውም እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው በኢኳዶር ነው። ታዲያ እንዲህ ዓይነት የተሳሳተ ስም ሊሰጠው የቻለው እንዴት ነው? ደግሞስ እንዲህ ዓይነት ባርኔጣ ዋጋው በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

በ1800ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ወርቅ አሳሾች ወደ ካሊፎርኒያ ያቀኑት በፓናማ ልሳነ ምድር በኩል ነበር። ፓናማ ውስጥ ከኢኳዶር የመጡ ባርኔጣዎችን ገዙ። ከጊዜ በኋላ ባርኔጣው በተሠራበት አገር ሳይሆን በተገዛበት አገር ስም ይጠራ ጀመር። ያም ሆነ ይህ ፓናማ ባርኔጣ ከፍተኛ ተወዳጅነት አገኘ። ለምሳሌ ያህል በ1849 ኢኳዶር 220, 000 ፓናማ ባርኔጣዎችን ለውጭ ገበያ አቅርባለች! ከዚያም በ1855 በፓናማ የሚኖር አንድ ፈረንሳዊ በፓሪስ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ባርኔጣዎቹን አስተዋወቀ። ፋሽን ተከታይ የሆኑ ፈረንሳውያን በባርኔጣው ልስላሴ ተማረኩ። አንዳንዶቹም “ከሣር የተሠራ ልብስ” ብለው ጠርተውታል። ወዲያው ሌላ ዓይነት ባርኔጣዎች ፈላጊ አጡ!

በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ቄንጠኛ ፊኖ አድርገው የተነሱት ፎቶግራፍ በዓለማችን ጋዜጦች ላይ ከወጣ በኋላ የፓናማ ባርኔጣ ተወዳጅነት በጣም ጨመረ። የዚህ ድንቅ ባርኔጣ ተፈላጊነትም እያደገ ሄደ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አንጋፋ ኩባንያዎች ባርኔጣውን ማከፋፈል ጀመሩ። በ1925 ቱርክ ውስጥ ዘመናዊ ሥልጣኔ ለማስፋፋት የወጡ ሕጎች ባሕላዊውን ቆብ አግደው ፓናማ ባርኔጣዎችን መጠቀም ግዴታ አደረጉ። በ1944 ፓናማ ባርኔጣ ኢኳዶር በአንደኛ ደረጃ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ምርት ሆኖ ነበር።

በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የባርኔጣዎች ተፈላጊነት እያሽቆለቆለ መጣ። ይሁን እንጂ በጥንቃቄ ተጠልፎ የሚሠራው የኢኳዶሩ ፓናማ ባርኔጣ ተፈላጊነቱን እንደያዘ ቀጠለ። እርግጥ ነው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልምድ ያላቸው ባርኔጣ ነጋዴዎች ጥራት ያለውን ፓናማ ባርኔጣ ማግኘት ይፈልጋሉ። ከበርካታ ዘመናት በፊት የኖሩትም ሆኑ የዘመናችን ታዋቂ ሰዎች የፓናማ ባርኔጣ ባለው ውበት ተማርከዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ዊንስተን ቸርችል፣ ኒኪታ ክሩሽቼቭ፣ ሐምፍሬይ ቦጋርትና ማይክል ጆርዳን በባርኔጣው ተውበዋል።

እርግጥ ነው፣ እውነተኛውን ፓናማ ባርኔጣ አስመስለው የሚሠሩ በገፍ የሚመረቱ ርካሽ ባርኔጣዎች አሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የሚሰባበሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አየር አያስገቡም። ከዚህ በተቃራኒ እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ ቀላልና አየር የሚያስገባ ከመሆኑም በላይ የዕድሜ ልክ ዕቃ ነው። እያንዳንዱ ባርኔጣ በእጅ የሚጠለፍ ስለሆነ በዓይነቱ ለየት ያለ ነው። ጥቂት መቶ ዶላሮች ከሚያወጡት ዘርዘር ብለው የተሠሩ ባርኔጣዎች አንስቶ በሞንቴክሪስቲ እስከሚመረቱት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ከ1, 000 የአሜሪካ ዶላር በላይ እስከሚያወጡት ድረስ ዋጋቸው የተለያየ ነው። ጥራቱ የሚለካው በአጠላለፉ ጥራትና ወጥ መሆን እንዲሁም በቀለሙ ተመሳሳይነት ነው። ሆኖም አንድ ነገር አትዘንጉ:- እውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው ኢኳዶር ውስጥ ብቻ ነው።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የፓናማ ባርኔጣ አሠራር

ፓናማ ባርኔጣ የሚሠራው እንዴት ነው? የሚሠራው እንደ ዘንባባ ተክል ካለ ቶኪያ ከሚባል ጠንካራ ቃጫ ነው። የኢኳዶር ቆላማ የባሕር ዳርቻዎች ለዚህ ተክል እድገትም ሆነ መስፋፋት ምቹ ናቸው። ባርኔጣ የመሥራት ሙያ ያላቸው ኢኳዶራውያን በዓለማችን ላይ ካሉ ድንቅ ጠላፊዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ደግሞም የሚያከናውኑት ሥራ እጅግ አድካሚ ነው! ከፍተኛ ጥራት ያለውን ሞንቴክሪስቲ ሱፐርፊኖ ሠርቶ ለመጨረስ ስድስት ወራት ወይም ከዚያ በላይ ሊፈጅባቸው ይችላል። ባርኔጣውን ለመሥራት የሚጠቀሙበት የእያንዳንዱ ቃጫ ርዝመት በጣም አጭር ነው። ሆኖም በእውነተኛው ፓናማ ባርኔጣ ላይ አንድ የቃጫ ቁራጭ ያለቀበትንና ሌላው የጀመረበትን ቦታ መለየት አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም ቁርጥራጮቹ እርስ በርሳቸው ጥብቅ ተደርገው የተጠለፉ ከመሆናቸው የተነሳ ውኃ እንኳ አያስገቡም!

ሞንቴክሪስቲ በጣም ምርጥ በሆኑ በእጅ የተጠለፉ ባርኔጣዎቿ የምትታወቅ ከተማ ናት። በሞንቴክሪስቲ አካባቢ የሚኖሩ በሙያው የተካኑ ሰዎች የአካባቢያቸው ሙቀት የቃጫውን ጥራት እንዳያበላሸው ሥራቸውን የሚያከናውኑት ጠዋት በማለዳ አሊያም ከሰዓት በኋላ አመሻሹ ላይ ነው። ተፈላጊው የስፋት መጠን ላይ እስኪደርሱ ድረስ ውስብስብ በሆነ መንገድ እርስ በርስ የታሠሩትን ቃጫዎች አንዱን ዙር በሌላው ላይ በክብ በጥንቃቄ እየገመዱ አናቱን መሥራት ይጀምራሉ። ከዚያም ባለሙያው የባርኔጣውን ጎን ሲጠልፍ እጆቹን በቅልጥፍና እያሠራ ዙሪያውን ወደታች መውረድ እንዲችል የባርኔጣውን አናት ሞላላ እንጨት ላይ ያስቀምጠዋል። ከብዙ ሳምንታት በኋላ የባርኔጣውን ክፈፍ ለመሥራት ወደ ጎን መጥለፉን ይቀጥላል። በደንብ ከተጌጠ፣ ከታጠበና ከጸዳ እንዲሁም ልዩ ልዩ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ከተካሄዱ በኋላ ባለ ዝናው የፓናማ ባርኔጣ ሥራ ያበቃል።

[ሥዕሎች]

የጠለፋ ሥራው ከመጀመሩ በፊት ከተላጠው የተክሉ ቅርንጫፍ የተወሰዱት ቃጫዎች በውኃ ይቀቀሉና እንዲደርቁ ይደረጋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊንስተን ቸርችል ፓናማ ባርኔጣን ካደረጉ በርካታ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው

[ምንጭ]

U.S. National Archives photo