በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በደቡብ አፍሪካ ያለ ደም የሚካሄድ ቀዶ ሕክምና

“ኤድስን በተመለከተ በሚወጡት እጅግ አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃዎች ሳቢያ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ የተለያዩ የግል ሆስፒታሎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ‘ያለ ደም ማከምና ቀዶ ሕክምና ማድረግ’ መርጧል” ሲል ዘ ሜርኩሪ የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል። “ዓላማችን” አሉ የፕሮግራሙ ሜዲካል ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ኤፍሬም ክሬመር፣ “እንደ እኛው ያሉ ሌሎች የሕክምና ቡድኖችም ታካሚዎቻቸውን ያለ ደም እንዲያክሙና ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉላቸው ማበረታታት ነው።” በደቡብ አፍሪካ በግለሰብ ደረጃ ያለ ደም ለማከምና ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ቢያንስ 800 የሚሆኑ ዶክተሮች ቢኖሩም የተለያዩ ሆስፒታሎችን ያቀፈ አንድ ቡድን በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ እንዲህ ያለ ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ሲወስን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ዶክተር ክሬመር ሐኪሞች የሰጡት ምላሽ “እጅግ አበረታች” እንደሆነ ገልጸዋል። “ፈጽሞ ደም የማይወስዱትን የይሖዋ ምሥክሮችን የመሰሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚያቀርቡት ጥያቄ ውጤታማ የሆኑ ያለ ደም የሚሠራባቸው የሕክምና ዘዴዎች እንዲዳብሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል” ይላል ዘ ሜርኩሪ የተሰኘው ጋዜጣ።

የሕፃን ምግብ የሚመገቡ ዐዋቂዎች

የዐዋቂዎች የሕፃን ምግብ ፍጆታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ሲል ድፓ- ባዚስዲንስት የተሰኘው የጀርመን የዜና አገልግሎት ዘግቧል። አንድ ትልቅ የጀርመን የሕፃን ምግብ አምራች ድርጅት ካመረተው የሕፃን ምግብ ውስጥ አሥር በመቶው የተሸጠው ልጆች ለሌሉባቸው ቤተሰቦች ነው። በየትኛውም የዕድሜ ክልልና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የወተት ፑዲንግና ለሕፃናት የሚዘጋጁ የተቀቀሉ ፍራፍሬዎችን መመገብ ይወዳሉ። ብዙውን ጊዜ አንድ የሕፃን መብል የሚኖረው የካሎሪ መጠን ከ100 የማይበልጥ በመሆኑ የሰውነት ክብደታቸውን መቆጣጠር የሚፈልጉ ብዙ ዐዋቂዎች መክሰስ በሚበሉበት ጊዜ የሕፃን ምግብ መመገብ ይመርጣሉ። አምራቾቹ ምርቶቻቸው “ለሕፃናትም ሆነ ለዐዋቂዎች” እንደሚያገለግሉ በመግለጽና ምርቶቻቸውን የሚያካትቱ የምግብ አሠራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሁኔታውን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የጀርመን ስነ ምግብ ማኅበር አዝማሚያው አላስደሰተውም። የማኅበሩ ቃል አቀባይ የሆኑት አኔቴ ብራውን እንደሚሉት ከሆነ ዐዋቂዎች ካልታመሙ በስተቀር እንዲህ ያሉትን ለየት ባለ መንገድ የተዘጋጁ ምግቦች መመገብ አያስፈልጋቸውም። የራሳቸውን ምግብ አኝከው መመገብ አለባቸው። “ጥርስ የኖረንም እኮ ለዚህ ነው” ይላሉ ብራውን።

የሲጋራ ሱስ ወዲያው ሊይዝ ይችላል

በማሳቹሴትስ የሚሠሩ ተመራማሪዎች አንዳንድ ሰዎች “ሲጋራ ማጨስ በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ” ሱስ እንደያዛቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች እንደታዩባቸው አረጋግጠዋል ይላል አሶስዬትድ ፕሬስ ያወጣው ዘገባ። ከ12 እስከ 13 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 681 ልጆች የማጨስ ልማድ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ክትትል በማድረግ የተካሄደው ይህ ጥናት ሱስ እንደያዛቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች እንደታዩባቸው አመልክቷል። “ቀደም ሲልም ብዙ ሰዎች ወዲያውኑ ሱሰኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመን ነበር” ይላሉ ዶክተር ሪቻርድ ኸርት፤ “ሆኖም ይህ እንደሚሆን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ስናገኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።” የምርምር ቡድኑ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ዲፍራንሳ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “የዚህ ጥናት ትልቁ አንድምታ እንዲሁ በግብታዊነት ስሜት ወይም ለመሞከር ያህል ብቻ በሚል ለጥቂት ሳምንታት አጭሶ መተው እንደማይቻል ልጆችን ማስጠንቀቅ እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው።”

ጎጂ ምክር

“መገናኛ ብዙሃንና የታወቁ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች [ቁጣን] ‘መወጣት’ ጠቃሚ ነው የሚል አስተሳሰብ ያራምዳሉ” ይላል ሳይኮሎጂ ቱዴይ የተሰኘው መጽሔት። “ይሁን እንጂ ይህ ምክር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።” የአዮዋ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት የሥነ ልቦና ባለሙያው ብራድ ቡሽማን እንዳሉት ከሆነ “ቁጣን መወጣት ይበልጥ ለጠብ ይጋብዛል።” ጥናት ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል እንደ አሸዋ ባለ ነገር የተሞላ ከረጢት በመደብደብ “ቁጣቸውን የሚወጡ” ሰዎች በዚህ መንገድ ቁጣቸውን ለመወጣት ካልሞከሩት ሰዎች ሁለት እጥፍ የበለጠ የጠበኝነትና የጭካኔ መንፈስ ተንጸባርቆባቸዋል። ሌላው ቀርቶ “ቁጣን መወጣት ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች የሚናገር ጽሑፍ ያነበቡ ሰዎች ከረጢቱን ከመደብደባቸው አስቀድመው ሰው በቡጢ ለመምታት ያላቸው ፍላጎት ከሌሎቹ ልቆ ይገኛል” ይላል ጽሑፉ። “ቁጣን ለማብረድ ከመሞከር ይልቅ ይላሉ ቡሽማን፣ ቁጣውን ሙሉ በሙሉ አጥፉት። ካስፈለገ እስከ 10 አለዚያም እስከ 100 ቁጠሩ። ያን ጊዜ ቁጣችሁ ያልፋል።”

ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ትልቅ የኦዞን ሽንቁር

በመስከረም 2000 በኦዞን ንብር ላይ ክትትል የምታካሂደው የናሳ ሳተላይት ከአንታርክቲክ በላይ ባለው ቦታ ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ትልቅ የኦዞን ንብር ሽንቁር መዝግባለች። ይህን የዘገበው በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ውስጥ እየታተመ የሚወጣው ክላሪን የተሰኘው ጋዜጣ ነው። ሽንቁሩ የተከሰተው 28.3 ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ካለው ቦታ በላይ ሲሆን ቀደም ሲል ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር ከ1, 000, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ይበልጣል። ይህ መጠነ ሰፊ ሽንቁር ሳይንቲስቶችን አስገርሟቸዋል። የናሳ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማይክል ከሪሎ እነዚህ ግኝቶች “በቀላሉ የመጎዳት ባሕርይ ያለው መሬታዊው የኦዞን ንብር የፈጠረውን አሳሳቢ ሁኔታ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ብለዋል። የአርጀንቲና የጠፈር እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ባልደረባና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ሩቤን ፒያቼንቲኒ ምንም እንኳ ሽንቁሩ የተከሰተው ሰው ከማይኖርበት የአንታርክቲካ መሬት በላይ ቢሆንም “ውሎ አድሮ እስከ ደቡባዊ [የአርጀንቲና] ምድር ሊስፋፋ ይችላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ኦዞን ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ ኃይል ያለውን የፀሐይ ልእለሃምራዊ ጨረር በመቀነስ መከላከያ ጋሻ ሆኖ ያገለግላል ሲል ክላሪን ገልጿል።

የዚንክ እንክብሎች የጉንፋንን ዕድሜ ሊያሳጥሩ ይችላሉ?

ተመራማሪዎች ዚንክ ጉንፋንን ለመከላከል ይረዳል ወይስ አይረዳም በሚለው ጉዳይ ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲወዛገቡ ኖረዋል። በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት “የጉንፋን ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ የሚመጠጡ [የዚንክ] እንክብሎችን በጥቂት ሰዓቶች ልዩነት መውሰድ የጉንፋንን አማካይ ዕድሜ በግማሽ ያህል እንደሚያሳጥር” አመልክቷል ሲል ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ በጥናቱ ላይ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል ለአራት ወይም ለአምስት ቀናት በየሁለትና ሦስት ሰዓት ልዩነት የሚመጠጡ የዚንክ እንክብሎች የወሰዱ ሰዎች ምንም መድኃኒትነት የሌላቸውን እንክብሎች ከወሰዱ ሰዎች ይልቅ “ሳላቸውና ከአፍንጫቸው የሚወርደው ንፍጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።” ይሁን እንጂ ዚንክ የወሰዱ አንዳንድ ሰዎች እንደ ሆድ ድርቀትና እንደ አፍ መድረቅ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ገጥመዋቸዋል በማለት መጽሔቱ ተናግሯል።

ከውጭ አገር ቄሶች ማስመጣት

ባደጉ አገሮች የተከሰተው የቀሳውስት እጥረት ያሳሰባት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ችግሩን ለመቅረፍ ከውጭ አገር ቀሳውስት ማስመጣት ጀምራለች በማለት ሌስፕሬሶ የተባለ የኢጣሊያ መጽሔት ሪፖርት አድርጓል። “በኢጣሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያሉ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አዳዲስ ቀሳውስትን ማስመረቅ የተሳናቸው ሲሆን ሃገረ ስብከቱም ያሏቸውን ቀሳውስት በአዳዲስ ቀሳውስት መተካት ሳይችሉ ቀርተዋል” ይላል መጽሔቱ። በደብሮች የደረሰውን የቀሳውስት እጥረት ለማስወገድ ከብራዚል፣ ከሕንድና ከፊሊፒንስ ቀሳውስት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። ሌስፕሬሶ እንደዘገበው “አዝማሚያው መታየት የጀመረው በቅርቡ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለውጥ እያስከተለ ነው። . . . በኢጣሊያ በጳጳሳት የበላይ አካል ሥር ሆነው የሚያገለግሉ ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች ውጭ የመጡ 1, 131 ቀሳውስት የሚገኙ ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የቀሳውስት ቁጥር 3 በመቶ ያክል ይሆናል።” በመሆኑም ኢጣሊያ ‘የሚስዮናውያን አገር’ እየሆነች ነው በማለት መጽሔቱ ይናገራል።

ዓይን ያለው እንክብል

ከተዋጠ በኋላ በትንሹ አንጀት ላይ የደረሰን ሕመም ለማጥናት የሚያስችል እንደ ቪዲዮ ካሜራ ያለ ረቂቅ መሣሪያ በአንድ የእስራኤል ኩባንያ መፈልሰፉን በሜክሲኮ የሚታተመው ኤክሴልስዮር የተሰኘው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። ረቂቁ ካሜራ ሕመምተኛው ወገቡ ላይ ወደሚታጠቀው ልዩ ቀበቶ መረጃ ያስተላልፋል። ከዚያም ምስሉ ኮምፒዩተር ውስጥ ይገባና በሕክምና ባለሙያዎች ይጠናል። ትንሿ ካሜራ ከዓይነ ምድር ጋር ከሰውነት ውስጥ ትወገዳለች። ዶክተር ብላየር ሉዊስ እንዳሉት ከሆነ ይህ የምርመራ ዘዴ ካሉት ጥቅሞች መካከል አንዱ ምንም ዓይነት ሕመም የማያስከትል መሆኑ ነው። እንክብሉን ከፈለሰፉት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ስዌይን እንዲህ ብለዋል:- “ሕመምተኛውን ማደንዘዝ ሳያስፈልግ አልፎ ተርፎም የወትሮው እንቅስቃሴ ሳይተጓጎል የትንሹን አንጀት ታችኛ ክፍል የሚያሳይ ምስል ማግኘት ይቻላል።” የዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር እንክብሉን ኒው ዮርክ እና ለንደን በሚኖሩ 20 በሽተኞች ላይ ለመሞከር የሚያስችል ፈቃድ ሰጥቷል።

በሥራ ቦታ የሚያጋጥም የመንፈስ ጭንቀት እየጨመረ ነው

“በሥራ ቦታ የሚፈጠር ውጥረት፣ ስጋትና የመንፈስ ጭንቀት በዓለም ዙሪያ ከ10 ሠራተኞች መካከል አንዱን እንደሚያጠቃ” የፓሪስ ዕለታዊ ጋዜጣ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን ሪፖርት አድርጓል። የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት ባደረገው ጥናት መሠረት በሥራ ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት አውሮፓንና ዩናይትድ ስቴትስን በዓመት ከ120 ቢልዮን የሚበልጥ የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስወጣቸው አረጋግጧል። ከሥራ ጋር ተዛማጅነት ያለው የመንፈስ ጭንቀት እየጨመረ እንዲመጣ በከፊል ምክንያት የሆነው ነገር በሠራተኞች ላይ ተጨማሪ ውጥረት እያስከተለ ያለው የቴክኖሎጂ አብዮት እንደሆነ ይነገራል። ትሪቡን እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ “ከሥራ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር የአእምሮ ሕመም በየዓመቱ 200 ሚልዮን የሥራ ቀናት የሚባክኑ” ሲሆን በፊንላንድ ደግሞ ከሠራተኛው ኃይል መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከውጥረት ጋር በተያያዙ ችግሮች ይሠቃያል። በተጨማሪም በብሪታንያ 30 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞች ከአእምሮ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉባቸው የሚነገር ሲሆን 5 በመቶ የሚሆኑት በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ናቸው።

በሽታን ማስተላለፍ

“ተላላፊ በሽታዎች የውኃ ቧንቧን እንደ መክፈት ወይም ስልክ እንደማንሳት ባሉ በጣም ቀላል በሆኑ ድርጊቶች ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፉ ይችላሉ” በማለት ዚ ጋርዲያን የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። በአሪዞና፣ ቱሳን፣ ዩ ኤስ ኤ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ሪፖርት እንዳደረጉት ኃይለኛ ጉንፋን የያዘው ሰው ተናፍጦ የቧንቧ ውኃ ቢከፍት “ከ1, 000 የሚበልጡ ቫይረሶችን በመክፈቻው ላይ” ሊተው ይችላል። ሌላ ሰው ቧንቧውን ከተጠቀመ በተለይ ደግሞ ከዚያ በኋላ አፉን፣ አፍንጫውን ወይም ዓይኖቹን የሚነካካ ከሆነ በእነዚህ ቫይረሶች ሊበከል ይችላል። በባክቴሪያዎች ላይ የተካሄዱ ምርመራዎች እንዳሳዩት “የስልክ መነጋገሪያዎች 39% ባክቴሪያዎችንና 66% ቫይረሶችን ሲያስተላልፉ የውኃ ቧንቧ መክፈቻዎች ደግሞ 28% ባክቴሪያዎችንና 34% ቫይረሶችን ያስተላልፋሉ።” በተመረዘ እጅ የታችኛን ከንፈር መንካት ከእነዚህ ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች መካከል አንድ ሦስተኛው እንዲተላለፍ ያደርጋል። በሮታቫይረስ የሚከሰቱ በሽታዎችና በሳልሞኔላ ምክንያት የሚፈጠር ተቅማጥ እጅን ባለመታጠብ የተነሳ በዚህ መንገድ በቀላሉ ሊተላለፉ ይችላሉ።

ክረምት​—⁠ወዳጅ ወይስ ጠላት?

ብርዳማና ዝናባማ የአየር ጠባይ ሁልጊዜ በጤናህ ላይ ጉዳት ያስከትላል ማለት አይቻልም በማለት በጀርመን የሚታተመው የጤና ጋዜጣ አፖቴከን ኡምሻው ሪፖርት አድርጓል። እንዲያውም በተቃራኒው በክረምት ወቅት አዘውትሮ በእግር መጓዝ ልብህ እንዲነቃቃ፣ የደም ዝውውርህ እንዲሻሻልና መላው አካልህ ጥንካሬ እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል በማለት የስነ አየር የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አንዠላ ሹ ተናግረዋል። በሞቀ ክፍል ውስጥ መቆየት ሰውነት በሙቀት መጠን ላይ ለሚከሰት ለውጥ ተገቢውን ምላሽ እንዳይሰጥ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ይህ ደግሞ ሰውነትን ለሕመም እንዲጋለጥ ሊያደርግና ድካምና ራስ ምታት ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ “መጥፎ” የአየር ጠባይ ባለበት ወቅት ዘወትር በሚደረግ የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴ የዳበረ አካል በቀላሉ በብርድ አይጠቃም እንዲሁም የበለጠ ብርታት እያገኘ ይሄዳል።