ይሖዋ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነውን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ይሖዋ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነውን?
በዛሬው ጊዜ በብዙ የምድር ክፍል ይሖዋ የሚለው ስም ከዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። ሆኖም፣ ይህ ስም ከይሖዋ ምሥክሮች ውጪ ሌሎች ሃይማኖቶች በሚጠቀሙባቸው በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥም ይገኛል። በእርግጥም፣ በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚጻፈው ይሖዋ የሚለው ስም ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲሠራበት ቆይቷል።
ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ “የእስራኤል አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ዜና መዋዕል 17:24) ከዚህ አባባል በመነሳት አንዳንዶች፣ ዕብራውያን ከሌላ ባህል የወረሱት ወይም ራሳቸው የፈጠሩት የአንድ ብሔር አምላክ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። “[ይሖዋ] መጀመሪያ ላይ ብቅ ያለው የእስራኤላውያን አስፈሪ የብሔር አምላክ ሆኖ ነበር” በማለት ኤ ሂስትሪ ኦቭ ጎድ የተባለውን መጽሐፍ የጻፉት ካረን አርምስትሮንግ ተናግረዋል። “ከጊዜ በኋላ ደግሞ የእስራኤል ነቢያት . . . በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አካባቢ ይህን የብሔር አምላክ እጅግ የላቀ ስብዕና ያለውን አካል ለማመልከት ይጠቀሙበት ጀመር።”
በርካታ የሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊዎች ይሖዋ የሚለው ስም ምንጭ ከከነዓናውያን ወይም ከግብፃውያን የተገኘ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ሌሎች ደግሞ ይህ “በጥንት ጊዜ የነበረ የአንድ ብሔር ስም” እንጂ “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ የሚገኘውን አምላክ የሚያመለክት አይደለም ብለው ይከራከራሉ። ይህ እውነት ነውን? መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ስናነብ የምንገነዘበው ነገር ምንድን ነው?
ይሖዋ—የሁሉም አምላክ
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር የነበረውን የቀረበ ግንኙነት ይገልጻል። ይሁን እንጂ ይህ የአንድ ብሔር አምላክ እንደሆነ አድርገን እንድናስብ ምክንያት አይሆነንም። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን?” በማለት ጠይቋል። ከዚያም ጳውሎስ “አዎን፣ . . . የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ሮሜ 3:29) ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው የትኛውን አምላክ ነው? ሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በተላከው በዚህ ደብዳቤ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም 19 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ሐዋርያው በጥንት ጊዜ የነበረውን ዕብራዊ ነቢይ ኢዩኤልን በመጥቀስ አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት ተናግሯል።—ሮሜ 10:13፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ኢዩኤል 2:32
ነው” በማለት የማያሻማ መልስ ሰጥቷል። (ይሖዋ አምላካቸው እንዲሆን የመረጡት እስራኤላውያን አልነበሩም። ከዚያ ይልቅ ዓላማውን ለማስፈጸም ማለትም መሲሑ የሚመጣበትን መንገድ ለማዘጋጀት የመረጣቸው ይሖዋ ራሱ ነበር። ከዚህም በላይ የአንድ ብሔር አምላክ ዕጣ ፈንታ በሕዝቡ ሕልውና ላይ የተመካ ነው። ብሔሩ ከጠፋ ያም አምላክ አብሮ ይከስማል። ይህ ሁኔታ በይሖዋ ላይ አልተከሰተም።
ክርስትና ከመቋቋሙ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን አሕዛብ በሙሉ በረከትን እንደሚያገኙ የሚገልጽ የተስፋ ቃል አለው። ይህም አምላክ ለሰው ዘር በጠቅላላ እንደሚያስብ ያሳያል። (ዘፍጥረት 12:1-3፤ ሥራ 10:34, 35፤ 11:18) እስራኤላዊ ንጉሥ የነበረው ዳዊት ይሖዋ የእስራኤል ምድር ብቻ ባለቤት እንዳልነበረ ሲገልጽ “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፣ ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 24:1
ከጊዜ በኋላ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለይሖዋ አምልኮ እንዲወሰን ባደረገበት ጊዜ ትሑት የሆነ በየትኛውም ብሔር የሚኖር ሰው ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችልበት መንገድ እንዳለ ገልጿል። ሰሎሞን በዚያ ሥነ ሥርዓት ላይ ባቀረበው ጸሎት እንዲህ ብሏል:- “ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ . . . ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፣ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፣ . . . እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።”—1 ነገሥት 8:41-43
እስራኤል የአምላክን ሞገስ አጣች
እስራኤል ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና በማስመልከት ፕሮፌሰር ሲ ጄ ላበስካክኒ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “እስራኤል በታሪክ ዘመኗ ሁሉ ‘ብሔራዊ’ አምላኳ እርሷን ሳይደግፍ የቀረበት ከዚያም ይባስ ብሎ እርሷን በመቃወም እርምጃ የወሰደባቸው ተደጋጋሚ ጊዜያት ነበሩ።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን እስራኤል መሲሑን ለመቀበል አሻፈረኝ ባለች ጊዜ ብሔሩ ጨርሶ የይሖዋን ሞገስ አጥቷል።
ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚለው ስም በክርስቲያኖችም ዘንድ ማገልገሉን ቀጥሏል። የክርስቲያን ጉባኤ እያደገ ሲሄድ አባላቱ ከሁሉም ብሔራት የመጡ ሰዎችንም ያቀፈ ሆኗል። ኢየሩሳሌም በተካሄደው ስብሰባ ላይ ሰብሳቢ ሆኖ የሠራው አይሁዳዊው ደቀ መዝሙር ያዕቆብ ስለ አምላክ ሲናገር ‘ለስሙ የሚሆንን ወገን ይወስድ ዘንድ ትኩረቱን ወደ አሕዛብ [አይሁዳዊ ወዳልሆኑ] ዞር እንዳደረገ’ ተናግሯል።—ሥራ 15:2, 12-18፤ አሞጽ 9:11, 12
ሁሉንም ይንከባከባል ሁሉንም ይባርካል
የይሖዋ አምላክነት ጽንፈ ዓለማዊ እንደሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሲሰጥ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፣ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው።” (ሮሜ 10:12፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ የይሖዋን በረከት ሊያገኙ ይችላሉ።
ይሖዋ ከየትኛውም ብሔር ወይም ዘር ለመጡ ታማኝና ታዛዥ ለሆኑት ሰብዓዊ ልጆቹ ወደፊት ክብራማ የሆነ ጊዜ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። ቃሉ እነዚህን ሰዎች ‘በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ዕቃ’ እንደሆኑ አድርጎ ይገልጻቸዋል። (ሐጌ 2:7) እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ያውቁታል እንዲሁም ይወድዱታል። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እነርሱ ሲናገር “[ይሖዋ] የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ” በማለት ይናገራል።—ራእይ 15:4
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ አሥርቱን ትእዛዛት እንደያዘ