እጅግ አስደናቂ የሆነው የደም ዝውውር ሥርዓት
እጅግ አስደናቂ የሆነው የደም ዝውውር ሥርዓት
እጅግ ውስብስብ የሆነ የቧንቧ መሥመር ያለው አንድ ቤት በምናባችን ለመሳል እንሞክር። በቧንቧው ውስጥ የሚያልፈው ፈሳሽ ኦክሲጅን፣ ምግብ፣ ውኃና መወገድ ያለባቸውን ቆሻሻዎች እየተሸከመ ያጓጉዛል። የቧንቧው መስመር ራሱን መጠገን የሚችል ከመሆኑም ሌላ በቤቱ ውስጥ ከሚፈጠሩት ለውጦች ጋር በሚስማማ መንገድ እያደገና እየጨመረ መሄድ ይችላል። ምንኛ የተራቀቀ ምህንድስና ነው!
ይሁን እንጂ የሰውነትህ “የቧንቧ መስመር” ከዚህም የበለጠ ነገር ያከናውናል። የሰውነትህን የሙቀት መጠን የሚቆጣጠር ከመሆኑም በላይ በጣም ውስብስብ የሆኑ ሆርሞኖችን ወይም ኬሚካላዊ መልእክተኞችንና አስተማማኝ የበሽታ መከላከያዎችን የያዘ ነው። ከዚህም በላይ መስመሩ በጠቅላላ ለስላሳና በቀላሉ የሚተጣጠፍ በመሆኑ ንዝረትን ውጦ ማስቀረትና ከሰውነት ክፍሎችህ ጋር አብሮ መተጣጠፍ ይችላል። የትኛውም ሰብዓዊ መሐንዲስ እንዲህ ያለ ሥርዓት መንደፍ አይችልም። ፈጣሪ ግን የሰው አካል ክፍሎች የሆኑትን ደም መላሽና ደም ወሳጅ ቧንቧዎችንና ፀጉሮዎችን (capillaries) በሠራ ጊዜ ይህን ንድፍ አውጥቷል።
የሥርዓቱ ዋና ዋና ክፍሎች
የሰው ልጅ የደም ዝውውር ሥርዓት በጋራ የሚሠሩ ሁለት ሥርዓቶችን አጣምሮ የያዘ ነው። አንዱ ሥርዓተ ልብ ወቧንቧ ሲሆን ልብን፣ ደምንና የደም ሥሮችን በጠቅላላ አካትቶ የያዘ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሥርዓተ ሊንፍ ሲሆን ይህ ሥርዓት ሊንፍ ተብሎ የሚጠራውን ትርፍ ፈሳሽ ከሰውነት ሕብረ ህዋሳት ወደ ደም መልሶ የሚያጓጉዝ የሥሮች መረብ ነው። የአንድ ዐዋቂ ሰው የደም ሥሮች ተቀጣጥለው በአንድ መስመር ቢዘረጉ 100, 000 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ የሚኖራቸው ከመሆኑም በላይ ምድርን ሁለት ከግማሽ ጊዜ ያህል ሊዞሯት ይችላሉ! ይህ መጠነ ሰፊ የሆነ ሥርዓት ከሰውነታችን ክብደት ውስጥ 8 በመቶ ገደማ የሚሆነውንና ሕይወት ሰጪ የሆነውን ደም ተሸክሞ በቢልዮን ወደሚቆጠሩ ሕዋሳት ያደርሳል።
ከሥርዓተ ልብ ወቧንቧ በስተጀርባ የኃይል ምንጭ ሆና የምታገለግለው ልብ ናት። ልብህ የእጅህን ጭብጥ የሚያክል መጠን ያላት ሲሆን በየዕለቱ ቢያንስ ቢያንስ 9, 500 ሊትር ደም ወደ መላ ሰውነትህ ትረጫለች። ይህም በደፈናው ሲሰላ አንድ ቶን ክብደት ያለውን ዕቃ በየ24 ሰዓቱ 10 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ላይ እንደ ማውጣት ይቆጠራል!
ሥርዓተ ልብ ወቧንቧ ሲቃኝ
ደም በሰውነት ውስጥ የሚዘዋወረው የትኛውን መስመር ተከትሎ ነው? ቅኝታችንን የምንጀምረው በውስጡ ያለውን ኦክሲጅን አሟጥጦ በሁለቱ ትልልቅ ደም መላሽ ሥሮች ማለትም በላእላይ (በላይኛው) እና በታይታይ (በታችኛው) አቢይ ደም መላሽ ቧንቧዎች ወደ ልብ የሚፈሰውን ደም የጉዞ መስመር በመከተል ይሆናል። (ሥዕላዊ መግለጫውን ተመልከት።) እነዚህ ደም መላሽ ሥሮች ይዘውት የመጡትን ደም ወደ መጀመሪያው የልብ ክፍል ማለትም ወደ ቀኝ ተቀባይ ልብ ገንዳ ያስገባሉ። ከዚያም ይህ የቀኝ ተቀባይ ልብ ገንዳ ደሙን ይበልጥ በጡንቻ ወደዳበረው የልብ
ክፍል ማለትም ወደ ቀኝ ሰጭ ልብ ገንዳ ጨምቆ ያስገባዋል። ከዚህ በኋላ ደሙ በሳምባዊ ግንደ አካልና ኦክሲጅን አልባ ደም በሚሸከሙት ብቸኛ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ማለትም በሁለቱ ሳምባዊ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች በኩል ወደ ሳምባ ይገባል። ኦክሲጅን አልባ ደምን የማጓጓዙ ሥራ በአብዛኛው የሚከናወነው ደም መላሽ በሆኑ ቧንቧዎች ነው።ደም ሳምባ ውስጥ ከገባ በኋላ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ያስወጣና ኦክሲጅንን ይወስዳል። ከዚያም ኦክሲጅን የያዘ ደምን በሚያጓጉዙት ብቸኛ ደም መላሽ ቧንቧዎች ማለትም በአራቱ ሳምባዊ ደም መላሽ ቧንቧዎች በኩል አልፎ ወደ ግራ ተቀባይ ልብ ገንዳ ይገባል። የግራ ተቀባይ ልብ ገንዳ ደሙን እጅግ ከፍተኛ ኃይል ወዳለው የልብ ክፍል ማለትም ወደ ግራ ሰጭ ልብ ገንዳ የሚያሻግረው ሲሆን ይህ የልብ ክፍል ደግሞ ኦክሲጅን የያዘውን ደም በዐቢይ ደም ወሳጅ በኩል ወደ ሰውነት ይረጨዋል። መጀመሪያ ሁለቱ ተቀባይ ልብ ገንዳዎች በአንድነት ሲኮማተሩ በመቀጠል ሁለቱ ሰጭ ልብ ገንዳዎች ይኮማተራሉ። ይህ በሁለቱ ክፍሎች ላይ በቅደም ተከተል የሚከናወነው ሂደት የልብ ምት ይፈጥራል። አራት ውስጣዊ ክፍ ክዶች (valves) በልብ በኩል የሚያልፈው ደም ወደኋላ ተመልሶ እንዳይፈስ ይቆጣጠራሉ።
ግራ ሰጭ ልብ ገንዳ ደምን እስከ እጆችና እግሮች ድረስ የሚረጭ በመሆኑ በጡንቻ የዳበረ ሲሆን ከቀኝ ሰጭ ልብ ገንዳ ስድስት ጊዜ እጥፍ ገደማ የሚበልጥ ኃይል አለው። በዚህ ሳቢያ በድንገት የሚፈጠረውን ግፊት ውጦ የሚያስቀር እጅግ የረቀቀ ተፈጥሯዊ ሂደት ባይኖር ኖሮ ግፊቱ የደም ወሳጅ ቧንቧ ግድግዳዎች በቀላሉ እንዲወጠሩ ወይም እንዲለጠጡ ሊያደርግ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርግ በሚችል ሁኔታ በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ ችግር እንዲከሰት መንስኤ ሊሆን ይችል ነበር።
ተለጣጭ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች
የሰውነትህ ዐቢይ ደም ወሳጅ ቧንቧና ዋና ዋና ቅርንጫፎቹ “ተለጣጭ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች” ናቸው። ቀዳዳቸው ወይም የውስጥ ክፍላቸው ሰፊ በመሆኑ ደም በቀላሉ መፍሰስ ይችላል። በተጨማሪም አንድ ማዕከል ባላቸው የኢላስቲን (እንደ ላስቲክ ያለ ፕሮቲን) ንብሮች የተሸፈኑና በጡንቻ የዳበሩ ወፍራም ግድግዳዎች አሏቸው። ግራ ሰጭ ልብ ገንዳ ወደ እነዚህ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ደም በሚረጭበት ጊዜ ተለጥጠው ወይም ተወጥረው የሚፈጠረውን ከፍተኛ ግፊት ውጠው *
በማስቀረት ደሙን ወደ ቀጣዮቹ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ያሻግሩታል። እነዚህኛዎቹ አከፋፋይ ሆነው የሚያገለግሉ በጡንቻ የዳበሩ ደም ወሳጅ ቧንቧዎችም በግድግዳዎቻቸው ላይ እንደ ላስቲክ ያለ ተለጣጭ ፕሮቲን አላቸው። ይህ እጅግ አስደናቂ የሆነ ንድፍ ደሙ በቀላሉ ሊጎዱ ወደሚችሉት ፀጉሮዎች በሚደርስበት ጊዜ ግፊቱ አንድ ወጥ እንዲሆን ያደርጋል።አከፋፋይ ሆነው የሚያገለግሉት ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ዲያሜትራቸው ከ1 ሴንቲ ሜትር እስከ 0.3 ሚሊ ሜትር ይሆናል። እነዚህ የደም ሥሮች ለየት ያሉ የነርቭ ቃጫዎች በሚሰጧቸው ትእዛዝ መሠረት እየተለጠጡ ወይም እየተኮማተሩ የደም ዝውውር ሥርዓቱ በእጅጉ የተቀላጠፈ እንዲሆን በማድረግ የደም ፍሰቱን ለመቆጣጠር ይረዳሉ። ለምሳሌ ያህል አደጋ ወይም አስደንጋጭ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ንብር ላይ የሚገኙ ግፊት መፈጠሩን የሚለዩ የአካል ክፍሎች ወደ አንጎል መልእክት ያስተላልፋሉ። አንጎል ደግሞ እንደ ቆዳ ወዳሉ ቅድሚያ ወደማይሰጣቸው የአካል ክፍሎች የሚፈሰውን ደም አቅጣጫ በማስቀየር ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆኑ አባላካላት እንዲፈስ እንዲያደርጉ ወደ ትክክለኛዎቹ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች መልእክት ያስተላልፋል። ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት “ደም ወሳጅ ቧንቧዎችህ የደም ፍሰቱን ሁኔታ ‘ለይተው ማወቅ’ እና አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት ይችላሉ” ይላል። ታዲያ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች “ብልህ ቧንቧዎች” ተብለው መገለጻቸው ሊያስገርመን ይገባል?
ደም ንዑስ ደም ወሳጅ በመባል የሚታወቁትን ትንንሾቹን ቧንቧዎች ለቅቆ በሚወጣበት ጊዜ 35 የሜርኩሪ ሚሊ ሜትር ገደማ የሚደርስ መጠን ያለው አንድ ወጥ ግፊት ይኖረዋል። ንዑስ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ከሁሉም የደም ሥሮች በጣም አነስተኛ ከሆኑት ፀጉሮዎች ጋር የሚጣመሩ በመሆኑ አንድ ወጥ የሆነ ዝቅተኛ የደም ግፊት መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በአንድ ረድፍ ተሰልፈው የሚያልፉ ቀይ ሕዋሳት
ከስምንት እስከ አሥር ማይክሮሜትር (የአንድ ሜትር አንድ ሚልዮንኛ) የሚደርስ ዲያሜትር ያላቸው ፀጉሮዎች በጣም ጠባብ በመሆናቸው ቀይ የደም ሕዋሳት በውስጣቸው የሚያልፉት በአንድ ረድፍ ተሰልፈው ነው። የፀጉሮ ግድግዳዎች ያላቸው ውፍረት ከሕዋሳት አንድ ነጠላ ንብር የማይበልጥ ቢሆንም እንኳ ንጥረ ምግቦችን (በፕላዝማ ወይም በደም ፈሳሽ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን) እና ኦክሲጅንን (ቀይ ሕዋሳት የተሸከሙትን)
ወደ አዋሳኝ ሕብረ ሕዋሳት ያሸጋግራሉ። በዚሁ ጊዜ ደግሞ ካርቦን ዳይኦክሳይድና ሌሎች ቆሻሻዎች ይወገዱ ዘንድ ከሕብረ ሕዋሳቱ ወደ ፀጉሮዎች ይገባሉ። በተጨማሪም ፀጉሮዎች ስፊንክተር በሚባል እንደ ቋጠሮ ባለ አነስተኛ ጡንቻ አማካኝነት በዙሪያቸው ያለው ሕብረ ሕዋስ የሚያስፈልገውን ያህል ደም እንዲፈስ መቆጣጠር ይችላሉ።ከንዑስ ደም መላሾች ወደ ደም መላሽ ቧንቧዎች ከዚያም ወደ ልብ
ደም ከፀጉሮዎች ከወጣ በኋላ አነስተኛ ወደሆኑት ንዑስ ደም መላሽ ቧንቧዎች ይገባል። ከ8 እስከ 100 ማይክሮሜትር ዲያሜትር ያላቸው ንዑስ ደም መላሾች አንድ ላይ በመጣመር ደምን ወደ ልብ የሚመልሱ ደም መላሽ ቧንቧዎች ይሠራሉ። ደም ወደ ደም መላሽ ቧንቧዎች በሚገባበት ጊዜ ግፊት አልባ የሚሆንበት ደረጃ ላይ የሚደርስ በመሆኑ የደም መላሽ ቧንቧ ግድግዳዎች ከደም ወሳጅ ቧንቧ ግድግዳዎች ይቀጥናሉ። በተጨማሪም በውስጣቸው ያለው የኢላስቲን መጠን አነስተኛ ነው። ይሁን እንጂ ደም መላሽ ቧንቧዎች ቀዳዳቸው ሰፊ መሆኑ በሰውነትህ ውስጥ ካለው የደም መጠን ውስጥ 65 በመቶውን እንዲይዙ አስችሏቸዋል።
ደም መላሽ ቧንቧዎች በውስጣቸው የሚኖረው የደም ግፊት ዝቅተኛ በመሆኑ ደሙን ወደ ልብ የሚያደርሱበት የራሳቸው የረቀቀ ዘዴ አላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የስበት ኃይል ደሙን ከልብ ውስጥ ስቦ እንዳያስወጣ የሚከላከል እንደ ስኒ ያለ ልዩ ክፍ ክድ አላቸው። በሁለተኛ ደረጃ የአፅም ጡንቻዎችህን ይጠቀሙባቸዋል። እንዴት? ለምሳሌ ያህል ስትራመድ እግርህ በሚታጠፍበት ጊዜ ጡንቻዎችህ በአካባቢያቸው ያሉትን ደም መላሽ ቧንቧዎች ይጫኗቸዋል። ይህ ደግሞ ደሙ አንድ መስመር ብቻ ባላቸው ክፍ ክዶች በኩል ወደ ልብ እንዲሄድ ይገፋዋል። በመጨረሻም በሆድና በደረት አካባቢ በአተነፋፈስ ሥርዓት የሚለዋወጠው ግፊት ደም መላሽ ቧንቧዎች በውስጣቸው ያለውን ደም ቀኝ ተቀባይ ልብ ገንዳ ውስጥ እንዲያስገቡ ይረዳቸዋል።
ሥርዓተ ልብ ወቧንቧ አጅግ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሥራውን የሚያከናውን በመሆኑ አንድ ሰው ዕረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ በእያንዳንዱ ደቂቃ 5 ሊትር ደም ወደ ልብ መልሶ ያስገባል! በሚራመድበት ወቅት መጠኑ ወደ 8 ሊትር ገደማ ከፍ የሚል ሲሆን አንድ ጤናማ የማራቶን ሯጭ ደግሞ በእያንዳንዱ ደቂቃ 35 ሊትር ደም ወደ ልቡ ሊጎርፍ ይችላል። ይህ በዕረፍት ወቅት ወደ ልብ ከሚገባው ደም መጠን ጋር ሲነጻጸር ሰባት እጥፍ ይበልጣል!
አንዳንድ ጊዜ ከዘር ውርስ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ወይም ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት፣ በእርግዝና ወይም ለረጅም ሰዓት ከመቆም የተነሳ የደም መላሽ ክፍ ክዶች ደም ሊያፈስሱ ይችላሉ። እነዚህ ክፍ ክዶች መሥራታቸውን በሚያቆሙበት ጊዜ ደም ከበታቻቸው ተከማችቶ ደም መላሽ ቧንቧዎቹ እንዲወጠሩና ግትርትር ደም መላሽ ቧንቧዎች (varicose veins) እንዲሆኑ ያደርጋል። በተመሳሳይም በወሊድ ወቅት የሚኖረው ምጥ ወይም ዓይነ ምድር ለመጸዳዳት ሲባል ማማጥ በሆድ አካባቢ ግፊት የሚጨምር በመሆኑ በፊንጢጣና በትልቁ አንጀት አካባቢ ካሉት ደም መላሽ ቧንቧዎች የሚመለሰውን ደም ያግደዋል። ይህ ሁኔታ የፊንጢጣ ኪንታሮት ተብለው የሚጠሩ ግትርትር ደም መላሽ ቧንቧዎች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።
ሥርዓተ ሊንፍ
ፀጉሮዎች አስፈላጊውን ንጥረ ምግብ ለሕብረ ሕዋሳት ሲያቀርቡና በምትኩ ቆሻሻውን ሲያስወግዱ የሚወስዱት ፈሳሽ ይዘውት ከመጡት ፈሳሽ በትንሹም ቢሆን ያነሰ ነው። በጣም አስፈላጊ የሆኑ የደም ፕሮቲኖች ወደ ሕብረ ሕዋሳቱ ሰርገው ይገባሉ። ሥርዓተ ሊንፍ አስፈላጊ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ሊንፍ ተብሎ የሚጠራውን ትርፍ ፈሳሽ በሙሉ ይሰበስብና ከአንገት ሥር በሚገኝ አንድ ትልቅ ደም መላሽ ቧንቧና በደረት አካባቢ በሚገኝ ሌላ ትልቅ ደም መላሽ ቧንቧ በኩል ከደም ጋር እንዲቀላቀል ያደርጋል።
እንደ ደም ወሳጅና ደም መላሽ ቧንቧዎች ሁሉ የሊንፍ ሥሮችም በተለያዩ ክፍሎች የተከፈሉ ናቸው። በጣም አነስተኛ የሆኑት የሊንፍ ፀጉሮዎች በደም ፀጉሮዎች ንብር ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ጥቃቅን ሥሮች በከፍተኛ ደረጃ ፈሳሽ በውስጣቸው የሚያሳልፉ በመሆኑ ትርፍ የሆነውን ፈሳሽ በመምጠጥ ወደ ትልልቆቹ የሊንፍ ሥሮች ያሻግሩታል። እነዚህ ሥሮች ደግሞ በተራቸው ሊንፉን ወደ ሊንፍ ግንደ አካላት ያሸጋግራሉ። ሥሮቹ አንድ ላይ ተጣምረው የሊንፍ ቱቦዎች በመፍጠር ሊንፉን ወደ ደም መላሽ ቧንቧዎች ያፈስሱታል።
ሊንፍ የሚፈሰው ወደ አንድ አቅጣጫ ማለትም ወደ ልብ ብቻ ነው። በመሆኑም የሊንፍ ሥሮች እንደ ሥርዓተ ልብ ወቧንቧ ዙር አይሠሩም። በሊንፍ ሥሮች ውስጥ የሚካሄደው ብዙም ኃይል የሌለው የጡንቻ እንቅስቃሴ በአቅራቢያ በሚገኙ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ በሚኖረው ትርታና በእጆችና በእግሮች እንቅስቃሴ በመታገዝ የሊንፍ ፈሳሽን ያስወጣል። የሊንፍ ሥሮች ከተዘጉ ሥሮቹ በተዘጉበት ቦታ ላይ ፈሳሽ ስለሚከማች ኤደማ ተብሎ የሚጠራውን እብጠት ያስከትላል።
በተጨማሪም የበሽታ ዘአካላት የሊንፍ ሥሮችን ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። በመሆኑም ፈጣሪያችን ሥርዓተ ሊንፍ አስተማማኝ በሆኑ መከላከያዎች ማለትም በሊንፍ አባላካላት የታጠቀ እንዲሆን አድርጎታል። እነዚህ አባላካላት በትልልቆቹ የሊንፍ ሥሮች ዳር ተበትነው የሚገኙት የሊንፍ እጢዎች፣ ጣፊያ፣ ታይመስ፣ ቶንሲል፣ ትርፍ አንጀትና በትንሹ አንጀት ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ የሊንፍ እጢዎች ናቸው። እነዚህ አባላካላት የሰውነታችን መድህን ዋነኛ ሕዋሳት የሆኑትን ሕዋሳተ ሊንፍ ለማመንጨትና ለማስቀመጥ ያገለግላሉ። ስለዚህ ጤናማ የሆነ ሥርዓተ ሊንፍ ለጤናማ አካል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በደም ዝውውር ላይ ስናደርገው የቆየነው ቅኝት እዚህ ላይ ይደመደማል። ሆኖም ይህ አጠር ያለ ቅኝት እንኳ እጅግ አስደናቂ የሆነ ውስብስብነትና ብቃት ያለውን የምህንድስና ውጤት ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። በዚህ ላይ ደግሞ እክል ካልገጠመው በቀር ማብቂያ የሌለውን ሥራውን ምንም ሳይታወቅህ ድምፁን አጥፍቶ የሚያከናውን መሆኑ የሚያስገርም ነው። እንግዲያው የደም ዝውውር ሥርዓትህን ተንከባከበው፤ እሱም መልሶ ይንከባከብሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 የደም ግፊት በሚሊ ሜትር የሚለካ ሲሆን በመለኪያ መሣሪያው ውስጥ ያለው ሜርኩሪ ወደ ላይ ከፍ እንዲል ያደርጋል። ልብ ስትመታና ዘና ስትል የሚፈጠሩት የላእላይና የታህታይ ግፊቶች ሲስቶሊክ እና ዳያስቶሊክ ግፊቶች በመባል ይታወቃሉ። ይህ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በአእምሯዊና በአካላዊ ውጥረት እንዲሁም በድካም የተነሳ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሴቶች የደም ግፊት ከወንዶቹ ዝቅ ያለ ነው። የልጆች የደም ግፊትም ዝቅ ያለ ሲሆን የአረጋውያን ግን ከፍ ያለ ነው። ምንም እንኳ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉት አመለካከቶች በመጠኑ ሊለያዩ ቢችሉም አንድ ጤናማ ወጣት ከ100 እስከ 140 ሚሊ ሜትር ሜርኩሪ ሲስቶሊክ እና ከ60 እስከ 90 ሚሊ ሜትር ዳያስቶሊክ የደም ግፊት ሊኖረው ይችላል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ደም ወሳጅ ቧንቧዎችህን ተንከባከብ!
አርቲሪኦስክለሮሲስ ወይም “የደም ወሳጅ ቧንቧዎች መጠጠር” በበርካታ አገሮች ለብዙዎች ሞት ዋነኛ መንስኤ እየሆነ ነው። በአብዛኛው የሚከሰተው አተሮስክለሮሲስ የሚባለው ዓይነት ሲሆን በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ በሚከማቹ ወፍራም አጥሚት በመሰሉ የስብ ክምችቶች (አተሮማስ ) ሳቢያ የሚከሰት ነው። እነዚህ ክምችቶች የደም ወሳጅ ቧንቧን ቀዳዳ ወይም የውስጠኛ ክፍል የሚያጠብቡ በመሆኑ ክምችቱ እየጨመረ ሲሄድ ቧንቧው ሙሉ በሙሉ ሊደፈንና ሊተረተር ይችላል። በተጨማሪም በደም መርጋት ወይም በደም ወሳጅ ቧንቧ ግድግዳዎች ላይ በሚፈጠር የጡንቻ መኮማተር የተነሳ ቧንቧው ሊዘጋ ይችላል።
ይበልጥ አደገኛ የሆነ ሁኔታ የሚፈጠረው ለልብ ጡንቻ አስፈላጊውን አገልግሎት በሚሰጡት ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ስብ በሚከማችበት ጊዜ ነው። የልብ ጡንቻ ራሱ በቂ ደም ማግኘት የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርስና አንጃይና የተሰኘ አብዛኛውን ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት የሚከሰት የሚያስጨንቅ ዓይነት የሕመም ስሜት በደረት አካባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል። የልብ ደም ወሳጅ ቧንቧ ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ ልብ ድካም ሊያስከትልና በልብ ጡንቻ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ከባድ የሆነ የልብ ድካም በሽታ በሚከሰትበት ጊዜ ልብ ሙሉ በሙሉ ሥራዋን እንድታቆም ሊያደርግ ይችላል።
ሲጋራ ማጨስ፣ ስሜታዊ ውጥረት፣ የስኳር በሽታ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ስብ የበዛባቸው ምግቦች መመገብና የዘር ውርስ ለአተሮስክለሮሲስ ከሚያጋልጡት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።
[ሥዕሎች]
ጤናማ
መካከለኛ የስብ ክምችት
ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የስብ ክምችት
[ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ልብ ደም ወሳጅ
[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሥርዓተ ልብ ወቧንቧ
ሳምባ
ልብ
ግራ ሰጭ ልብ ገንዳ
ደም መላሽ ቧንቧዎች
ንዑስ ደም መላሽ ቧንቧዎች
ደም ወሳጅ ቧንቧዎች
ፀጉሮዎች
ንዑስ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች
ልብ
ቀኝ ሰጭ ልብ ገንዳ
ኦክሲጅን የያዘ ደም
ኦክሲጅን አልባ የሆነ ደም
ከሰውነት
ላእላይ አቢይ ደም መላሽ
ቀኝ ተቀባይ ልብ ገንዳ
ታይታይ አቢይ ደም መላሽ
ከሰውነት
ቀኝ ሰጭ ልብ ገንዳ
ክፍ ክዶች
ወደ ሳምባ
ሳምባዊ ደም ወሳጅ
ከሳምባ
ግራ ተቀባይ ልብ ገንዳ
ክፍ ክዶች
ግራ ሰጭ ልብ ገንዳ
ዐቢይ ደም ወሳጅ
ወደ ሰውነት
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የልብ አመታት
1. የተኮማተረው ዘና ሲል
2. ተቀባይ ልብ ገንዳ ሲኮማተር
3. ሰጭ ልብ ገንዳ ሲኮማተር
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የደም ሕዋሳት 100,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው የደም ሥሮች ውስጥ ይጓዛሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀይ የደም ሕዋሳት በአንድ ረድፍ ሆነው በፀጉሮዎች ውስጥ ሲያልፉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ
[ምንጭ]
Lennart Nilsson