በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአያቶቼ ጋር ይበልጥ መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

ከአያቶቼ ጋር ይበልጥ መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...

ከአያቶቼ ጋር ይበልጥ መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

“ሁለቱም የወንድ አያቶቼ የቀደሙ ታሪኮችን መተረክ ያስደስታቸዋል። ይህም የራሴን ስሜት እንድረዳ አስችሎኛል።”​—⁠ጃሽዋ

ቀደም ባሉት ዘመናት ቅደመ አያቶችን ጨምሮ ሁሉም ቤተሰብ በአብዛኛው በአንድ ቤት ውስጥ በአንድነት ይኖር ነበር። ከአያቶች ጋር ተቀራርቦ መኖር የተለመደ የሕይወት ክፍል ነበር።

አሁን ግን ተራርቆ መኖር ወጣቶች ከአያቶቻቸው ጋር እንዳይገናኙ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ በርካታ ቤተሰቦች በፍቺ ያከትማሉ። ዘ ቶሮንቶ ስታር ሪፖርት እንዳደረገው “በፍቺ ምክንያት የሚፈጠር ችግር አያቶችንም ሊነካና ከሚወዷቸው የልጅ ልጆቻቸው ሊያቆራርጣቸው ይችላል።” በሌላ በኩል ያለው ችግር ደግሞ በርካታ ወጣቶች ለአረጋውያን ያላቸው አመለካከት አሉታዊ መሆኑና የዘመኑ ኑሮ የማይገባቸው፣ አመለካከታቸው፣ የሥነ ምግባር መመሪያዎቻቸውና ፍላጎታቸው ከእነርሱ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ መሆናቸው ነው። ይህስ ምን ውጤት ያስከትላል? በርካታ ወጣቶች ከአያቶቻቸው ጋር ይበልጥ መቀራረብ ሲችሉ አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ።

ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው። ቀደም ሲል በዚሁ ዓምድ ላይ የወጣው ርዕስ ከአያቶች ጋር፣ በተለይ ደግሞ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው አያቶች ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ገንቢ፣ ጠቃሚና አስደሳች እንደሆነ ገልጿል። * በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ሪቤካ የተባለች አንዲት ወጣት ስለ አያቶቿ ስትናገር “በተገናኘን ቁጥር የሚያስቁ ነገሮችን እያነሳን እንጫወታለን” ብላለች። ፒተር የተባለ ሌላ ወጣትም በተመሳሳይ “የሚሰማኝን ስሜት ወይም ያወጣኋቸውን ግቦች ለእነርሱ ለመንገር ምንም አላመነታም። አንዳንድ ጊዜ ከወላጆቼ ይልቅ ከእነርሱ ጋር ስሆን የበለጠ ነፃነት ይሰማኛል። ከአያቶቼ ጋር ስለ ፈለግሁት ነገር መነጋገር እንደምችል ሆኖ ይሰማኛል” ብሏል።

ስለ አንተስ ምን ለማለት ይቻላል? ልጅ ሳለህ ትውል የነበረው አያቶችህ ጋር ሊሆን ይችላል። እያደግክ ስትሄድ ግን ከአያቶችህ ጋር ያለህን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት አላደረግህ ይሆናል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ በ2 ቆሮንቶስ 6:​11-13 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ በማዋል ለእነርሱ ያለህን ፍቅር ‘ልታሰፋ’ ትችላለህ። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ፍቅርን እንዴት ማስፋት ይቻላል የሚለው ይሆናል።

ቅድሚያ መውሰድ

‘ማስፋት’ የሚለው ቃል ቅድሚያ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ሐሳብ ያዘለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቸገረው ሰው [“ለሚገባቸው ሰዎች፣” NW ] በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 3:​27) ልጅ በነበርክበት ጊዜ ከአያቶችህ ጋር ያለህን ዝምድና በተመለከተ ልታደርግ ‘የምትችለው’ ነገር አልነበረ ይሆናል። አሁን ግን በዕድሜ ከፍ ያልህ ምናልባትም ሙሉ ሰው ወደመሆን የደረስህ ልትሆን ስለምትችል ልትወስዳቸው የምትችላቸው ተገቢ የሆኑ በርካታ እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል አያቶችህ አንተ በምትኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ አዘውትሮ የመጠየቅ ልማድ ልታዳብር ትችላለህ። እንዲህ ማድረጉ አሰልቺ ይሆንብህ ይሆን? ሄደህ ምንም የማታወራ ከሆነ አሰልቺ ሊሆንብህ ይችላል። ስለዚህ ውይይት መክፈት መቻል ይኖርብሃል። ስለ ምን ጉዳይ አንስተህ መናገር ትችላለህ? በፊልጵስዩስ 2:​4 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ። ጥቅሱ ‘የራሳችንን ጥቅም ብቻ ከመመልከት ይልቅ የባልንጀራችንንም ጥቅም መመልከት’ እንዳለብን ይናገራል። በሌላ አባባል ለአያቶችህ የአሳቢነት ስሜት ይኑርህ። ምን እንደሚሰማቸው፣ ምን ሲያደርጉ እንደቆዩ በመጠየቅ ከእነሱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳህ አጫውታቸው። ስላሳለፉት ጊዜ እያነሱ ማውራት ይወዱ ይሆናል። ስለ ልጅነት ጊዜያቸው ጠይቃቸው። ወይም ስለ አባትህ ወይም ስለ እናትህ የልጅነት ጊዜ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። አያቶችህ ክርስቲያኖች ከሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ውስጥ የማረካቸው ምን እንደሆነ ጠይቃቸው።

ብዙውን ጊዜ አያቶች የቤተሰቡን የቀድሞ ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆኑ ታሪኮችን መናገር ሊያስደስታቸው ይችላል። አንተም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ብዙ ታሪኮችን እንዲነግሩህ ማድረግ ትችላለህ። ምናልባትም የማስታወሻ ደብተርህን ወይም የድምፅ ወይም የቪዲዮ መቅረጫ መሣሪያ ይዘህ ለአያቶችህ ቃለ መጠይቅ ልታደርግላቸው ትችል ይሆናል። ምን ብለህ እንደምትጠይቃቸው ግራ የሚገባህ ከሆነ ተስማሚ የሆኑ ጥያቄዎች ለማዘጋጀት የወላጆችህን ትብብር ልትጠይቅ ትችላለህ። እንዲህ በማድረግ የምትቀስማቸው በርካታ እውቀቶች ስለ አያቶችህ፣ ስለ ወላጆችህ፣ ሌላው ቀርቶ ስለ ራስህ የተሻለ ግንዛቤ እንድታገኝ ይረዱሃል። “ሁለቱም የወንድ አያቶቼ የቀደሙ ታሪኮችን መተረክ ያስደስታቸዋል” ይላል ጃሽዋ። “የሚነግሩኝ ታሪኮች የራሴን ስሜት እንድረዳ አስችለውኛል።”

አያቶችህ ስለ አንተም ሆነ ስለምታደርጋቸው ነገሮች ማወቅ እንደሚፈልጉም አትዘንጋ። ስለምታከናውነው ተግባር የምትነግራቸው ከሆነ ይበልጥ ስለ አንተ እንዲያስቡ ታደርጋቸዋለህ። ይህ ደግሞ ይበልጥ እንደሚያቀራርባችሁ የታወቀ ነው። ኢጎር የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወጣት “እኔና ሴት አያቴ ወደ አንድ ቡና ቤት ጎራ ብለን ሻያችንን ፉት እያልን በቅርቡ ስላደረግናቸው ነገሮች ማውራት እንወዳለን” በማለት ተናግሯል።

አብረን ምን ልንሠራ እንችላለን?

አንድ ላይ ሆናችሁ የመጫወት ልማድ ካዳበራችሁ በኋላ አንዳንድ ነገሮችን በጋራ መሥራት ልትጀምሩ ትችላላችሁ። ጥቂት አሰብ ብታደርግ አብራችሁ ልታከናውኗቸው የምትችሏቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ልትገነዘብ ትችላለህ። ወጣቷ ዳራ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ሁለቱም ሴት አያቶቼ ምግብ ማብሰል፣ ምግብ በጣሳ ማሸግ፣ መጋገር፣ አትክልት መትከልና መንከባከብ አስተምረውኛል።” ኤሚ ቤተሰቧ አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው በሚጫወቱበትና ለዕረፍት ወጣ ብለው በሚዝናኑበት ጊዜ አያቶቿ እንዲገኙ ታደርጋለች። ከዕድሜያቸው አንጻር አንዳንድ አያቶች ጥሩ ብርታትና አቅም ሊኖራቸው ይችላል። አሮን ከሴት አያቱ ጋር ጎልፍ መጫወት ይወድዳል። ጃሽዋ ከወንድ አያቶቹ ጋር ሆኖ ዓሣ ያጠምዳል እንዲሁም በቤት ውስጥ አንዳንድ የጥገና ሥራዎችን ይሠራል።

አያቶችህ ይሖዋን የሚያመልኩ ከሆነ ሌሎች ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ማነጋገር ባሉ የይሖዋ አምልኮ ዘርፎች አብረሃቸው መካፈልህ ልዩ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል። ኢጎር የይሖዋ ምሥክሮች በፖላንድ ባደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከአያቱ ጋር ተጉዞ ነበር። “አብረን በነበርንባቸው ጊዜያት ፈጽሞ የማይረሳ ትዝታ አሳልፈናል። አሁንም ስለዚያ ጊዜ እያነሳን እንጫወታለን” በማለት ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ሁሉም አያቶች እንደ ልብ መንቀሳቀስ አይችሉም። ያም ሆኖ ግን ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስቆጭ አይደለም።

መንፈሳዊ ቅርስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሎይድ የተባለች አንዲት ሴት የልጅ ልጅዋ የሆነው ጢሞቴዎስ ጥሩ ብቃት ያለው የአምላክ ሰው እንዲሆን በመርዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። (2 ጢሞቴዎስ 1:​5) በዛሬውም ጊዜ ቢሆን በርካታ ክርስቲያን አያቶች ተመሳሳይ ሚና ይጫወታሉ። ጃሽዋ አያቶቹን በማስመልከት እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋን በማገልገል ያሳለፉት ጊዜ ከእኔ ዕድሜ በላይ ነው። በዚህም የተነሳ አያቶቼ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን እስከ አሁን ድረስ ጽኑ አቋም ይዘው በመኖራቸው ለእነርሱ ጥልቅ አክብሮት አለኝ።” ኤሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “አያቶቼ ይሖዋን በታማኝነት ሳገለግል ሲመለከቱ በጣም እንደሚበረታቱና እንደሚደሰቱ ሁልጊዜ ይነግሩኛል። ሆኖም፣ አቅኚ ሆነው [የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆነው] በማገልገል የሚያሳዩትን መልካም ምሳሌና ቅንዓት ስመለከት እኔም በጀመርኩት የአቅኚነት አገልግሎት እንድገፋበት ያበረታታኛል።”

ክሪስ “እንዳጠናና ወደ ጉልምስና እንዳድግ ያነሳሳችኝ” አያቴ ናት ሲል ተናግሯል። ጨምሮም እንዲህ ብሏል:- “‘ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት አለብን’ እያለች የምትናገረውን ፈጽሞ አልረሳውም።” ፔድሮ በመንፈሳዊ እድገት ሊያደርግ የቻለው አያቶቹ ባደረጉለት ከፍተኛ እርዳታ ነው። እንዲህ ይላል:- “ከተሞክሯቸው ብዙ ተምሬአለሁ። አያቶቼ ሁልጊዜ ወደ አገልግሎት ይዘውኝ ይወጣሉ። ለዚህም በጣም አድናቂ ነኝ።” አዎን፣ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው አያቶች ጋር መቀራረብ አምላክን በተሻለ ብቃት እንድታገለግል ሊረዳህ ይችላል።

ርቀው የሚኖሩ አያቶች

አያቶችህ ካለህበት አካባቢ ርቀው የሚኖሩ ከሆነስ? በተቻለ መጠን እየሄድክ ለመጠየቅ ጥረት አድርግ። እስክትሄድ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥም ግንኙነታችሁ እንዳይቋረጥ ማድረግ ትችላለህ። ኦርናን አያቶቹን የሚጠይቀው በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም “በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ስልክ እደውልላቸዋለሁ” በማለት ተናግሯል። ከአያቶቿ በጣም ርቃ የምትኖረው ዳራም እንዲህ ብላለች:- “ለእኔ በጣም የሚያስቡ በመሆናቸው በየሳምንቱ ለማለት ይቻላል በስልክ ወይም በኢ-ሜይል እንገናኛለን።” በኢ⁠-​ሜይልና በስልክ መገናኘቱ ጥሩ ቢሆንም ጥንታዊ የሆነው በእጅ ደብዳቤ ጽፎ የመላክ ልማድም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልለህ አትመልከት። በርካታ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምረው የጻፏቸውን ደብዳቤዎች አያቶቻቸው መልሰው ሲያሳዩአቸው በጣም ተገርመዋል። ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ ሊነበቡ የሚችሉ በመሆናቸው በጣም ተወዳጅ ናቸው። ስለዚህ ከመጻፍ ወደኋላ አትበል!

አያቶች ብዙውን ጊዜ ለልጅ ልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው። (ምሳሌ 17:​6) አያቶችህ የሚኖሩበት አካባቢ ቅርብም ይሁን ሩቅ ከእነርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት መመሥረትና ይህንንም ጠብቀህ ማቆየት የምትችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። በተቻለህ መጠን እነዚህን ዘዴዎች ለመጠቀም ጥረት አድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . አያቶቼን በቅርብ ላውቃቸው የሚገባኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን በግንቦት 2001 እትም ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።