በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውቧ የእሳት እራት

ውቧ የእሳት እራት

ውቧ የእሳት እራት

በአንድ ደስ የሚል ምሽት አንዲት የእሳት እራት ወደ አንድ ትልቅ ምግብ ቤት ውስጥ ትገባለች። የእሳት እራቷ በሆቴሉ ውስጥ እየተመገበች ባለች አንዲት ሴት ጠረጴዛ አካባቢ ስታንዣብብ ሴትየዋ በሽታ ተሸካሚ ትንኝ እንደመጣባት ክፉኛ ተወራጭታ አባረረቻት! ከዚያ የእሳት እራቷ ወደ ሌላኛው ጠረጴዛ በመብረር በአንድ ሰውዬ ኮሌታ ላይ ቁጭ አለች። ይህ ሰውዬና ባለቤቱ የነበራቸው አመለካከት ግን ፈጽሞ የተለየ ነበር። ምንም ዓይነት ጉዳት የማታደርስና የምታሳሳ ውብ ፍጥረት መሆኗን በመመልከት የእሳት እራቷን ያደንቁ ጀመር።

ከከኔቲኬት ቢራቢሮዎች ማኅበር መሥራቾች አንዱ የሆኑት ጆን ሂመልማን “እንደ እሳት እራት ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል አንዳች ፍጥረት የለም” ሲሉ አስረድተዋል። “የሚናከሱበት አፍ የላቸውም፤ ሉና እንደተባለው የእሳት እራት ያሉ የታወቁ እሳት እራቶች ደግሞ ጭራሽ ምግብ እንኳ አይመገቡም። ራቢስ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት በሽታ አይሸከሙም ወይም አይናከሱም። . . . እንዲያውም ብዙዎቹ ሰዎች ቢራቢሮዎች በቀን የሚበርሩ የእሳት እራት መሆናቸውን አይገነዘቡም።”

ሁሉም ሰው ቢራቢሮዎችን ያደንቃል። የእሳት እራቶችን ውበትና ዓይነት ቆም ብለው የሚያደንቁ ግን ብዙ አይደሉም። ‘ድንቄም ውበት!’ ትል ይሆናል። አንዳንዶች የእሳት እራቶችን የሚያስቧቸው ውብ የሆነችው ቢራቢሮ አስቀያሚ ዘመዶች እንደሆኑ አድርገው ነው። ይሁንና ለሁለቱም የተሰጣቸው ሳይንሳዊ ስያሜ ሌፒዶፕቴራ የሚል ሲሆን ትርጉሙም “ቅርፍ (scale) ያላቸው ክንፎች” የሚል ነው። በእነዚህ ደስ የሚሉ ፍጥረታት መካከል የሚታየው የዓይነት ልዩነት በጣም አስገራሚ ነው። ዚ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ኢንሴክትስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከ150, 000 እስከ 200, 000 የሚደርሱ የሌፒዶፕቴራ ዝርያዎች መኖራቸው እንደሚታወቅ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል ቢራቢሮዎች 10 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ሲሆኑ የተቀሩት የእሳት እራት ናቸው!

እንደ ሌሎቹ ብዙ ሰዎች ሁሉ እኔም የእሳት እራቶች ትዝ የሚሉኝ የክረምት ልብሶቼን አውልቄ ከእሳት እራት መከላከያ ጋር በማስቀምጥበት ጊዜ ብቻ ነው። ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ እንኳ የእሳት እራቶች ጨርቅ እንደማይበሉ አላውቅም ነበር። ጨርቅ የሚበሉት በእጭነታቸው ማለትም አባ ጨጓሬ ሳሉ ነው። *

ታዲያ ለእሳት እራቶች የነበረኝን አመለካከት የለወጠው ነገር ምንድን ነው? ከተወሰነ ጊዜ በፊት እኔና ባለቤቴ ቦብ እና ሮንዳ የተባሉ ጓደኞቻችንን ለመጠየቅ ሄደን ነበር። ቦብ ስለ እሳት እራቶች እውቀት ነበረው። አንድ ሣጥን አሳየኝ። መጀመሪያ ላይ በሣጥን ውስጥ ያለው የሚያምር ቢራቢሮ መስሎኝ ነበር። ሲክሮፒያ ወይም ሮቢን የእሳት እራት እንደሚባልና በሰሜን አሜሪካ ካሉት የእሳት እራቶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ ነገረኝ። ክንፎቹ ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ ያላቸው ርዝማኔ እስከ 15 ሴንቲ ሜትር ያህል ሊደርስ የሚችል ሲሆን የሕይወት ዑደቱ አንድ ዓመት ያህል ይፈጃል። እድገቱን ከጨረሰ በኋላ የሚቆየው ከ7 እስከ 14 ቀን ብቻ እንደሆነ ሳውቅ በጣም ነው የተገረምሁት! የሚያምረውን ሲክሮፒያ ሁኔታ በቅርበት መመርመሬ ስለ እሳት እራት ያለኝን አመለካከት ፍጹም እንድቀይር ረድቶኛል።

ቦብ ሳጥኑ ወለል ላይ ያሉትን እንደ ጉድፍ ያሉ ነጠብጣቦች አሳየኝና “እነዚህ እንቁላሎች ናቸው። የመጨረሻ እድገት ደረጃቸው ላይ እስኪደርሱ ድረስ ለማሳደግ የማደርገው ጥረት ይሳካልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” አለኝ። የእሳት እራት እርባታ? በሐሳቡ ተማረክሁ። ይሁን እንጂ ይህንን ዕቅድ ዳር ማድረስ ያን ያህል ቀላል አልነበረም። ቦብ ለሁለት ሳምንታት ያህል እንቁላሎቹን ለማስፈልፈል ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። ከዚያ በውኃ ሊያርሳቸው ወሰነ። በውኃ ባራሳቸው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ26 እስከ 29 የሚደርሱ እንቁላሎች በአንድ ቀን ውስጥ ተፈለፈሉ። ከዚያም ቦብ እያንዳንዳቸው ትንኝ የሚያክሉትን ጥንቃቄ የሚጠይቁ እጮች በሆዳቸው እየተሳቡ እንዳይሄዱበት ለስላሳ በሆነ ጎድጓዳ ሰሃን ውስጥ ጨመራቸው።

እነዚህ እጮች የተመገቡት የመጀመሪያው ነገር የገዛ እንቁላላቸውን ቅርፊት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ቦብ እነርሱን መመገብ ነበረበት። ይህ ደግሞ ቀላል ሥራ አልሆነም። አንዳንድ ምርምር ካደረገ በኋላ የሜፕል ዛፍ ቅጠል ሊመግባቸው ሞከረ። እጮቹ ግን በቅጠሎቹ ላይ ፈነጩባቸው እንጂ አልተመገቧቸውም። ይሁን እንጂ ቦብ የቼሪና የበርች ቅጠሎችን ሲያቀርብላቸው ሙልጭ አድርገው በሏቸው።

በጣም ትናንሽ የነበሩት እጮች አድገው ወደ አባ ጨጓሬነት ከተለወጡ በኋላ ቦብ ከላይ የሽቦ ወንፊት ባለው የመስተዋት ሣጥን ውስጥ አደረጋቸው። ይህ የመስተዋት ሣጥን ለአባ ጨጓሬዎቹም ሆነ ለእጮቹ የተመጣጠነ እርጥበት ያለበት ቦታ ነበር። አባ ጨጓሬዎቹ መንቀሳቀስ እንደቻሉ ብዙም ሳይቆይ ወዲያ ወዲህ መተረማመስ ስለጀመሩ ሣጥኑ እነርሱንም ለመጠበቅ አገልግሏል።

ለተራቡ 26 አባ ጨጓሬዎች ምግብ ማቅረብ ከታሰበው በላይ ከባድ ሥራ ነበር። ቦብ ሣጥኑን በቅጠሎች ሞልቶ ሲሄድ አባ ጨጓሬዎቹ በሁለት ቀናት ውስጥ ሁሉንም እምሽክ አድርገው ይጠብቁታል። በዚህ ጊዜ እነርሱን በመጠበቁና በመመገቡ ሥራ የእህቱንና የሁለት ወንድና ሴት ጓደኞቹን እርዳታ ጠየቀ።

አባ ጨጓሬዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ መመገባቸው በእጭነታቸው ለሚያደርጉት ዕድገት ብቻ ሳይሆን እድገታቸውን ከጨረሱም በኋላ ላለው ጊዜ የሚሆናቸውን ምግብ ለማሰባሰብ የግድ አስፈላጊ ነው። እድገቱን የጨረሰው ሲክሮፒያ አፍ የሌለው በመሆኑ ምግብ የሚባል ነገር አይቀምስም! እድገቱን ከጨረሰ በኋላ ባለው አጭር የሕይወት ዘመኑ የሚሰነብተው እጭ እያለ በተመገበው ምግብ ብቻ ይሆናል።

አዲስ ቆዳ መልበስ

አባ ጨጓሬዎቹ እያደጉ ሲሄዱ በተደጋጋሚ ጊዜ ቆዳቸው ይገለፈፋል። አባ ጨጓሬዎች ቆዳቸው በሚገለፈፍበት ጊዜ መካከል ያለው ደረጃ ግልፍ ተብሎ ይጠራል።

የአንድ ሲክሮፒያ አባ ጨጓሬ ቆዳ ስለማያድግ አባ ጨጓሬው በጣም ትልቅ በሚሆንበት ጊዜ ቆዳቸው የቻለውን ያህል ይለጠጥና ከዚያ ይገለፈፋል። ቦብ አባ ጨጓሬዎቹ መመገባቸውን አቁመው ስለነበር እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሱ አውቆ ነበር። አባ ጨጓሬዎቹ እንደ ሐር የመሰለ ድብዳብ ይሠሩና አዲስ ቆዳ እስኪያወጡ ድረስ ለቀናት እዚያ ላይ ተጣብቀው ይቆያሉ። አዲሱ ቆዳ ወጥቶ ሲያልቅ አሮጌውን ቆዳቸውን እዚያው ድብዳቡ ላይ ጥለውት ከአሮጌው ቆዳ ሾልከው ይወጣሉ። አባ ጨጓሬዎቹን በመጨረሻው የግልፍ ወቅት ሳያቸው እድገታቸው በጣም አስገረመኝ። ርዝመታቸው እስከ 12 ሴንቲ ሜትር የደረሰ ሲሆን ሰውነታቸውም ከእኔ የአመልካች ጣት ይወፍር ነበር።

ኩብ መሥራት

ከመጨረሻው ግልፍ በኋላ እያንዳንዱ አባ ጨጓሬ ኩብ ይሠራል። ይህም ግራጫ ቀለም ባለው የተደራረበ ድር ከአንድ እንጨት ጋር ተጣብቆ የሚሠራ ነገር ነው። ሲክሮፒያዎች የሚሠሩት ኩብ ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው ትልቅ፣ ዘርዘር ያለና እንደ ከረጢት ያለ ሲሆን ከታቹ ለቀቅ ብሎ ወደ አንገቱ እየጠበበ የሚሄድ ነው። ሌላው ዓይነት ደግሞ አነስ ያለና ጥቅጥቅ ብሎ የተሠራ ሲሆን ከታችም ሆነ ወደ አንገቱ ጠበብ ያለ ቅርጽ ያለው ሞላላ ኩብ ነው። ሁለቱም ዓይነት ኩቦች ከውስጣቸው ጥቅጥቅ ተደርገው የሚሠሩ ናቸው። የሲክሮፒያ ኩቦች በጥቅሉ ወደ ቀይ የሚወስደው ቡናማ፣ ፈዛዛ አረንጓዴ ወይም ግራጫ ቀለም ያላቸው ናቸው። ሌሎች የሰሜን አሜሪካ ዝርያዎች ከሚሠሯቸው ኩቦች ጋር ሲወዳደር ሲክሮፒያ የእሳት እራቶች የሚሠሩት ኩብ ግዙፍ ሲሆን እስከ 10 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔና ከአምስት እስከ ስድስት ሴንቲ ሜትር ስፋት የሚደርስ መጠን አለው። እነዚህ አስገራሚ የሆኑ ኩቦች ከዜሮ በታች እስከ 34 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ የሙቀት መጠን በውስጣቸው ያሉትን ፍጥረታት ደህንነት ለመጠበቅ የሚችሉ ናቸው።

አባ ጨጓሬዎቹ ኩባቸው ውስጥ ከገቡ በኋላ በትዕግሥት ከመጠበቅ ሌላ የምናደርገው ነገር አልነበረም። ከኩቡ ውስጥ የወጡት በሚቀጥለው የፀደይ ወቅት ማለትም ቦብ ጠቅላላ እድገትዋን የጨረሰች እሳት እራት ካመጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ቦብ ኩቦቹ ያሉባቸውን እንጨቶች ወስዶ በፕላስቲክ ፎም ላይ ቀጥ አድርጎ ሰካቸው። ወዲያውም ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሲክሮፒያዎች ከኩባቸው ውስጥ በመውጣታቸው ትዕግሥቱና ድካሙ ሁሉ ተክሷል።

ስለ እሳት እራት የተሻለ ግንዛቤ አግኝቼአለሁ

የሲክሮፒያዎችን አስገራሚ የሕይወት ዑደት በዓይኔ ማየቴ ብርሃን ባዩበት የሚያንዣብቡትንና በሕንጻዎች ላይ አርፈው የሚታዩትን የእሳት እራቶች ይበልጥ በቅርበት እንድከታተል አነሳስቶኛል። ይህ አጋጣሚ ስለ እነዚህ አስደናቂ ፍጥረታት ይበልጥ ለማወቅ እንድነሳሳም ረድቶኛል። ለምሳሌ ያህል የእሳት እራቶችና ቢራቢሮዎች አስገራሚ የመብረር ችሎታ ያላቸው መሆናቸውንና አንዳንዶቹም ከፍተኛ ርቀት አቋርጠው ወደ ሌላ ቦታ እንደሚበርሩ አውቄአለሁ። ዲያመንድባክ የተባለችው ትንሿ የእሳት እራት ክንፎቿ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያላቸው ርዝማኔ 2.5 ሴንቲ ሜትር ብቻ ቢሆንም በየጊዜው ነውጥ የማያጣውን የሰሜን ባሕር አቋርጠው ከአውሮፓ ብሪታንያ ይበርራሉ። ሰፊኒክስ ወይም ሃውክ የእሳት እራት በመባል የሚታወቁት ደግሞ ከሃሚንግበርድ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በአበቦች ላይ ያንዣብባሉ።

የሲክሮፒያ የሕይወት ዑደት ምን እንደሚመስል ካየሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሲክሮፒያ የመብራት ብርሃን ባለበት ቁጥቋጦ ላይ አርፎ ተመለከትሁ። በእሳት እራት ክንፎች ላይ ያለው ቅርፍ በጣም ጥንቃቄ የሚሻ ስለሆነ ክንፉ ተይዞ መነሳት እንደሌለበት አውቄያለሁ። እጃችሁን ዘርግታችሁ ከፊት ለፊቱ ብታስቀምጡ ግን ቀስ ብሎ እጃችሁ ላይ ሊወጣ ይችላል። እንደዚያ ለማድረግ ስሞክር ተወዳጁ የእሳት እራት አላሳፈረኝም። የመሃል ጣቴ ላይ መጥቶ ቁጭ አለ። በኋላም በርሮ ወደ ዛፎቹ ጫፍ ሄደ። በርሮ ሲሄድ ቢራቢሮ ስለመምሰሉ አሰብሁ። በሚቀጥለው ጊዜ ቢራቢሮ ያያችሁ ሲመስላችሁ በደንብ ተመልከቱት። ምናልባትም የሚያምረውና አንዳች ጉዳት የሌለው እሳት እራት ሊሆን ይችላል።​—⁠ተጽፎ የተላከልን

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 አንዳንድ የእሳት እራት እጮች በአዝርዕትም ላይ ከባድ ውድመት ያደርሳሉ።

[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. ሮቢን የእሳት እራት (ሲክሮፒያ)

2. ፖሊፌመስ የእሳት እራት

3. ሳንሴት የእሳት እራት

4. አትላስ የእሳት እራት

[ምንጮች]

Natural Selection©-Bill Welch

A. Kerstitch

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሲክሮፒያ እሳት እራት የእድገት ደረጃ የሚከተሉትን ያካትታል:-

1. እንቁላል

2. እጭ

3. እድገቱን የጨረሰ እሳት እራት

[ምንጭ]

Natural Selection©-Bill Welch