በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊ ሕክምና—ምን ያህል ይሳካለት ይሆን?

ዘመናዊ ሕክምና—ምን ያህል ይሳካለት ይሆን?

ዘመናዊ ሕክምና—ምን ያህል ይሳካለት ይሆን?

ብዙ ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው የሚማሩት ነገር ነው:- ቁመታቸው የማይደርስበትን የእንጆሪ ፍሬ ለማውረድ ጓደኞቻቸው ትከሻ ላይ ይወጣሉ። በሕክምናውም መስክ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲከሰት ይታያል። የሕክምና ተመራማሪዎች በጥንቶቹ ዝነኛ የሕክምና ባለሙያዎች ትከሻ ላይ በመቆም የላቀ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ከጥንቶቹ ሐኪሞች መካከል እንደ ሂፖክራቲዝ እና ፓስተር ያሉ እውቅ ሰዎች እንዲሁም እንደ ቨሴሊየስ እና ዊልያም ሞርተን ያሉ ስማቸው ብዙም ያልገነነ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች ለዘመናዊው ሕክምና ያበረከቱት አስተዋጽዖ ምንድን ነው?

በጥንት ዘመን ሕክምና በአብዛኛው ከሳይንስ ጋር ሳይሆን ከአጉል እምነትና ከሃይማኖታዊ ልማዶች ጋር የተያያዘ ሥራ ነበር። በዶክተር ፌሊክስ ማርቲ-ኢባንዬስ የታተመው ዚ ኤፒክ ኦቭ ሜድስን የተሰኘው መጽሐፍ “ሜሶጶጣሚያውያን በሽታ የአማልክት ቅጣት ነው ብለው ያምኑ ስለነበር በሽታን ለመከላከል . . . ይጠቀሙበት የነበረው ሕክምና ሃይማኖታዊ ልማዶችን አጣምሮ የያዘ ነው” ይላል። ከዚያ ዘመን ብዙም ሳይቆይ ብቅ ያለው የግብፃውያን ሕክምናም እንዲሁ ከሃይማኖት ጋር የተሳሰረ ነው። ስለዚህ ገና ከጅምሩ አንስቶ ሐኪሞች ሃይማኖታዊ ከበሬታ ያገኙ ነበር።

ዶክተር ቶማስ ኤ ፕሬስተን ዘ ክሌይ ፔድስታል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የጥንቶቹ ሰዎች ከነበሯቸው እምነቶች መካከል ብዙዎቹ በሕክምናው መስክ እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ የማይፋቅ አሻራ ጥለው አልፈዋል። ከእነዚህ እምነቶች አንዱ በሽታ ከሕመምተኛው ቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር በመሆኑ ማገገም የመቻሉ ሁኔታ የተመካው በሐኪሙ ልዩ ተሰጥኦ ላይ ብቻ ነው የሚለው ነው።”

መሠረቱን መጣል

ይሁንና እያደር የሕክምና ሥራ ሳይንሳዊ እየሆነ መጣ። ቀደም ባሉት ዘመናት በግንባር ቀደምትነት ሳይንሳዊ ሐኪም ሆኖ ብቅ ያለው ሂፖክራቲዝ ነው። በ460 ከዘአበ ኮስ በተባለችው የግሪክ ደሴት የተወለደው ሂፖክራቲዝ በብዙዎች ዘንድ የምዕራባውያን ሕክምና አባት ተደርጎ ይታያል። ሂፖክራቲዝ ሕክምናን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት የሚያስችል መሠረት ጥሏል። በሽታ ተፈጥሯዊ የሆነ ምክንያት ያለው ነገር እንደሆነ በማስረዳት የአማልክት ቅጣት ነው የሚለውን ሐሳብ ውድቅ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል የሚጥል በሽታ ሊፈወስ የሚችለው በአማልክት ብቻ ነው የሚል እምነት ስለነበረ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ቅዱስ በሽታ እንደሆነ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። ሆኖም ሂፖክራቲዝ “ቅዱስ የሚባለው በሽታ ከሌሎቹ በሽታዎች ይበልጥ መለኮታዊም ሆነ ቅዱስ ተደርጎ ሊታይ የሚችልበት ምንም ምክንያት አይታየኝም። ተፈጥሯዊ መንስኤ ያለው በሽታ ነው” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም የተለያዩ በሽታዎችን ምልክቶች እየተከታተለ ለወደፊቱ ማመሳከሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ በመዝገብ ያሰፍር የነበረው የመጀመሪያው መድኃኒተኛ ሂፖክራቲዝ እንደሆነ ይነገርለታል።

ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ በ129 እዘአ የተወለደው ጌለን የተሰኘ ግሪካዊ ሐኪምም እንደዚሁ አዲስ ሳይንሳዊ ምርምር አድርጓል። ጌለን በተበለቱ የሰውና የእንስሳ አካል ክፍሎች ላይ ጥናት በማድረግ ዶክተሮች ለብዙ መቶ ዘመናት የተጠቀሙበትን የአናቶሚ መማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅቷል! በ1514 ብራሰልስ ውስጥ የተወለደው አንድሬያስ ቨሴሊየስ ኦን ዘ ስትራክቸር ኦቭ ዘ ሂውማን ቦዲ የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አበቃ። መጽሐፉ ጌለን ከደረሰባቸው በርካታ ድምዳሜዎች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ተቃውሞ ቢገጥመውም ለዘመናዊ የአናቶሚ ጥናት መሠረት ጥሏል። ዲ ግሮሰን (ታላላቅ ሰዎች) የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ቨሴሊየስ “በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከኖሩት እጅግ ታላላቅ የሕክምና ተመራማሪዎች አንዱ” ለመሆን በቅቷል።

ጌለን ልብንና የደም ዝውውርን በተመለከተ የነበሩት ጽንሰ ሐሳቦችም ከጊዜ በኋላ ተሽረዋል። * እንግሊዛዊው ሐኪም ዊልያም ሃርቬይ እንስሳትንና አዕዋፍን እየበለተ ጥናት በማካሄድ በርካታ ዓመታት አሳልፏል። የልብ ክፍ ክዶችን (valves) ተግባር ከማጥናቱም በላይ በእያንዳንዱ ከርሰ ልብ (ventricle) ውስጥ ያለውን የደም ይዘት በመለካት በሰውነት ውስጥ የሚኖረውን የደም መጠን ለመገመት ሞክሯል። ሃርቬይ የደረሰባቸውን ግኝቶች በ1628 ኦን ዘ ሞሽን ኦቭ ዘ ሃርት ኤንድ ብለድ ኢን አኒማልስ በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ለንባብ አብቅቷል። ትችት፣ ተቃውሞ፣ ጥቃትና ዘለፋ ተሰንዝሮበታል። ይሁን እንጂ የሃርቬይ ምርምር የሰውነትን የደም ዝውውር ሥርዓት በማሳወቅ በሕክምናው መስክ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል!

ከፀጉር ማስተካከል እስከ ቀዶ ሕክምና

በቀዶ ሕክምናውም መስክ ከፍተኛ እመርታዎች በመታየት ላይ ነበሩ። በመካከለኛው ዘመን ቀዶ ሕክምና በአብዛኛው የፀጉር አስተካካዮች ሥራ ነበር። አንዳንዶች የዘመናዊው ቀዶ ሕክምና አባት በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ፈረንሳዊው አንብሮዋዝ ፓሬ ነው ማለታቸው ምንም አያስደንቅም። ፓሬ አራት የፈረንሳይ ነገሥታትን ያገለገለ የቀዶ ሕክምና ፈር ቀዳጅ ከመሆኑም በላይ በርከት ያሉ የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች ፈልስፏል።

ይሁንና በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖር ለነበረ ቀዶ ሐኪም ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ነገር ቀዶ ሕክምና የሚያስከትለውን ሥቃይ ማስቀረት አለመቻሉ ነበር። ሆኖም በ1846 የጥርስ ቀዶ ሐኪም የሆነው ዊልያም ሞርተን በቀዶ ሕክምና ወቅት ሰመመን የመስጠት ልማድ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥርጊያውን አመቻቸ። *

በ1895 ጀርመናዊው ፊዚከኛ ቪልሄልም ሬንትገን ኤሌክትሪክ በመጠቀም ሙከራ በማካሄድ ላይ እንዳለ ጨረሮች በአጥንት ሳይሆን በሥጋ ውስጥ ሲያልፉ ተመለከተ። ጨረሮቹ ከየት እንደመጡ ስላልተገነዘበ ኤክስ ሬይስ ብሎ ሰየማቸው። ይህ ስያሜ አሁንም ድረስ በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም ይሠራበታል። (ጀርመኖች እነዚህን ጨረሮች ሬንትገንስትራለን በማለት ይጠሯቸዋል።) ዲ ግሮሰን ዶይቸን (ታላላቅ ጀርመናውያን) የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚለው ሬንትገን ሚስቱን “ሰዎች ይህን ሲሰሙ ‘ሬንትገን አበደ’ ማለታቸው አይቀርም” ብሏት ነበር። በእርግጥም አንዳንዶች አበደ ብለው ነበር። ሆኖም ሬንትገን የደረሰበት ግኝት በቀዶ ሕክምናው ዘርፍ ታላቅ ለውጥ አስከትሏል። ቀዶ ሐኪሞች የሰውን አካል ሳይቀዱ ውስጣዊ የአካል ክፍሎችን መመልከት ቻሉ።

በሽታን ድል መንሳት

ባለፉት የታሪክ ዘመናት እንደ ፈንጣጣ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በመከሰት ወረርሽኝ፣ ሽብርና ሞት አስከትለዋል። በዘጠነኛው መቶ ዘመን የኖረውና በአንዳንዶች ዘንድ የዘመኑ ታላቅ የእስልምናው ዓለም ሐኪም ተደርጎ ይታይ የነበረው የፋርሱ ተወላጅ አር-ራዚ የፈንጣጣ በሽታን በተመለከተ የመጀመሪያውን ትክክለኛ ትንተና በጽሑፍ አስፍሯል። ሆኖም ኤድዋርድ ጄነር የተባለ ብሪታንያዊ ሐኪም ለበሽታው ፈውስ ያገኘው ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ነበር። ጄነር አንድ ሰው ካውፖክስ በተባለ ምንም ጉዳት የማያስከትል በሽታ አንዴ ከተያዘ ሰውነቱ የፈንጣጣ በሽታ መከላከያ እንደሚያዳብር ተገነዘበ። ጄነር በዚህ ግንዛቤ ላይ በመመርኮዝ በካውፖክስ ሳቢያ ከተፈጠረ ቁስል ላይ የፈንጣጣ መከላከያ ክትባት ሠራ። ይህ የሆነው በ1796 ነበር። ከእሱ ቀደም አዳዲስ ነገሮችን እንዳስተዋወቁት ሰዎች ሁሉ ጄነርም ትችትና ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ይሁን እንጂ ክትባት መፈልሰፉ ውሎ አድሮ በሽታው ከነአካቴው እንዲጠፋ ከማድረጉም በላይ የሕክምናው ዓለም በሽታን የሚዋጋበት ውጤታማ የሆነ አዲስ ብልሃት ሊያገኝ ችሏል።

ፈረንሳዊው ሉዊ ፓስተር የእብድ ውሻ በሽታንና ቁርባን (anthrax) ለመከላከል ክትባት ተጠቅሟል። በተጨማሪም ፓስተር ጀርሞች በሽታ በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አረጋግጧል። በ1882 ሮበርት ኮች “የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ግንባር ቀደም ቀሳፊ በሽታ” ሲሉ አንድ ታሪክ ጸሐፊ የገለጹትን የሳንባ ነቀርሳን የሚያስከትለውን ጀርም ለይቶ አወቀ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ኮች ኮሌራ አማጭ የሆነውን ጀርም ለይቶ አወቀ። ላይፍ የተሰኘው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “የፓስተርና የኮች ሥራዎች የማይክሮባዮሎጂ ሳይንስን ለዓለም ያስተዋወቁ ከመሆናቸውም በላይ በሰውነት መድህን ጥናት፣ በስነ ጤናና በንጽሕና አጠባበቅ ለታዩት መሻሻሎች በር ከፋች ሆነዋል። ይህም የሰውን ልጅ ዕድሜ በማራዘም ረገድ ባለፉት 1, 000 ዓመታት ከታዩት ሳይንሳዊ ዕድገቶች ሁሉ በበለጠ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።”

የሃያኛው መቶ ዘመን ሕክምና

በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሕክምናው ዓለም በእነዚህና በሌሎች የተራቀቁ የሕክምና ባለሙያዎች ትከሻ ላይ ቆሞ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሕክምናው መስክ ፈጣን እድገት ታይቷል። ለስኳር በሽታ ኢንሱሊን፣ ለካንሰር ኬሚፈውስ (chemotherapy)፣ ከእጢ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች በሆርሞን አማካኝነት የሚሰጥ ሕክምና፣ ለሳንባ ነቀርሳ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣ ለተወሰኑ ዓይነት የወባ በሽታዎች ክሎሮክዊንንና ለኩላሊት በሽተኞች ደም የማጣራት ሂደት መፈጠሩ እንዲሁም ልብ ለተወሰነ ጊዜ ሥራውን እንዲያቆም በማድረግ ቀዶ ሕክምና ማካሄድና አባላካልን በቀዶ ሕክምና መተካት መቻሉ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው።

ይሁንና በ21ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት የሕክምና ሳይንስ “የዓለም ሕዝብ ሁሉ ጥሩ ጤና እንዲኖረው” ለማድረግ ወደታለመው ግብ ምን ያህል ተቃርቦ ይሆን?

ሊደረስበት የማይችል ግብ ነውን?

ልጆች ጓደኞቻቸው ትከሻ ላይ ቢወጡም አንዳንድ የማይደርሱባቸው የእንጆሪ ፍሬዎች እንደሚኖሩ ይገነዘባሉ። አንዳንዶቹ በጣም የበሰሉ እንጆሪዎች በዛፉ ጫፍ አካባቢ ሊሆኑና ላይደርሱባቸው ይችላሉ። በተመሳሳይም የሕክምና ሳይንስ ከአንዱ እመርታ ወደ ሌላው እየተሸጋገረ ሲሄድ ቆይቷል። ሆኖም ሁሉም ሰው ጥሩ ጤና እንዲኖረው ለማድረግ የታለመው ከሁሉ የላቀ ግብ ሊደረስበት የሚችል ሆኖ አልተገኘም።

በመሆኑም በ1998 የአውሮፓ ኮሚሽን “አውሮፓውያን የአሁኑን ያህል ረጅምና ጤናማ ሕይወት መምራት የቻሉበት ጊዜ የለም” የሚል ዘገባ ያወጣ ቢሆንም እንኳ ዘገባው “ከአምስት ሰዎች አንዱ 65 ዓመት ሳይሞላው ሕይወቱ ይቀጫል። ከእነዚህም መካከል 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የሚሞቱት በካንሰር ሳቢያ ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከልብና ከደም ቧንቧዎች ጋር በተያያዙ በሽታዎች የሚሞቱ ናቸው . . . ጤናን ለአደጋ የሚያጋልጡ አዳዲስ ሁኔታዎችን ለመዋጋት የተሻለ መከላከያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ሲል አክሎ ገልጿል።

በኅዳር ወር 1998 ጌዙንትሃይት የተሰኘው የጀርመን የጤና መጽሔት እንደ ኮሌራና ሳንባ ነቀርሳ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ስጋት በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ዘግቧል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች “የቀድሞውን ዓይነት ውጤት ማስገኘት እየተሳናቸው መጥቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ ባክቴሪያዎች ቢያንስ ቢያንስ አንድ የተለመደ ዓይነት መድኃኒት መቋቋም ወደሚችሉበት ደረጃ እየተሸጋገሩ ነው። ከአንድ በላይ መድኃኒቶችን መቋቋም የቻሉ ብዙ ባክቴሪያዎችም አሉ።” የቀድሞዎቹ በሽታዎች ማገርሸታቸውም ብቻ ሳይሆን እንደ ኤድስ ያሉ አዳዲስ በሽታዎችም ተከስተዋል። ስታትስቲክስ 1997 የተሰኘው የጀርመን የመድኃኒት አምራቾች ማኅበር ጽሑፍ “እስከ አሁን ባለው ሁኔታ መሠረት ካሉት በሽታዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ ለሚሆኑት ማለትም ወደ 20, 000 ገደማ ለሚጠጉት በሽታዎች መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ማከም የሚቻልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም” ሲል ያሳስበናል።

በጂን አማካኝነት የሚሰጠው ሕክምና መፍትሔ ያስገኝ ይሆን?

እርግጥ ነው፣ አዳዲስ ሕክምናዎች መፈልሰፋቸውን አላቋረጡም። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች ለተሻለ ጤና ቁልፉ ጀነቲካዊ ምህንድስና ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። በ1990ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደ ዶክተር ደብሊው ፍሬንች አንደርሰን በመሳሰሉ ሐኪሞች ምርምር ከተካሄደ በኋላ በጂን አማካኝነት የሚሰጠው ሕክምና “በእጅጉ ቀልብ የሚስብ አዲስ የሕክምና ምርምር መስክ” ተብሎ ተገልጿል። ሃይለን ሚት ጌነን (በጂኖች መፈወስ) የተባለው መጽሐፍ በጂን አማካኝነት የሚሰጠውን ሕክምና በመጠቀም “የሕክምና ሳይንስ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። በተለይ ደግሞ እስካሁን ድረስ ፈውስ ካልተገኘላቸው በሽታዎች ጋር በተያያዘ ይህ ሁኔታ እውን የሚሆንበት ጊዜ ተቃርቧል ማለት ይቻላል” ሲል ገልጿል።

ሳይንቲስቶች ውሎ አድሮ ለታካሚዎች የተስተካከሉ ጂኖችን በመስጠት በዘር የሚተላለፉ ጀነቲካዊ በሽታዎችን መፈወስ እንደሚቻል ተስፋ ያደርጋሉ። ሌላው ቀርቶ እንደ ካንሰር ሕዋሳት ያሉ ጎጂ ሕዋሶች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያጠፉ ማድረግ ይቻል ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው በተፈጥሮው ለአንዳንድ በሽታዎች የተጋለጠ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጀነቲካዊ ምርምር ማካሄድ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። አንዳንዶች ቀጣዩ ሥራ መድኃኒቶችን ከታካሚው ጀነቲካዊ ቅንብር ጋር በሚስማማ መንገድ ማዘጋጀት መቻል ይሆናል ይላሉ። አንድ የታወቁ ተመራማሪ ዶክተሮች አንድ ቀን “የታካሚዎቻቸውን በሽታ ለይተው በማወቅና ተስማሚውን የዲ ኤን ኤ ክፋይ በመስጠት መፈወስ” የሚችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ በጂን አማካኝነት የሚሰጠው ሕክምና ወደፊት “ቅጽበታዊ ፈውስ” ያስገኛል ብለው የሚያምኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። እንዲያውም አንዳንድ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በጀነቲካዊ ቅንብራቸው ላይ ምርምር እንዲካሄድ እንኳ ላይፈልጉ ይችላሉ። በተጨማሪም ብዙዎች በጂን አማካኝነት የሚሰጠው ሕክምና የተፈጥሮ ሥርዓትን ሊያዛባ የሚችል አደገኛ ጣልቃ ገብነት ነው የሚል ስጋት አለባቸው።

ጀነቲካዊ ምህንድስናም ሆነ ሌሎች እጅግ የረቀቁ የሕክምና ዘዴዎች የታለመውንና የተጓጓለትን ውጤት ያስገኙ ይሆን የሚለው ጉዳይ ጊዜ የሚያሳየው ነገር ነው። ይሁንና ከልክ ያለፈ ተስፋ መጣሉ ተገቢ አይሆንም። ዘ ክሌይ ፔድስታል የተባለው መጽሐፍ አንድ በጣም የተለመደ ዓይነት ዑደት ይጠቅሳል:- “አንድ አዲስ የሕክምና ዘዴ ብቅ ይልና ሕክምና ነክ በሆኑ ስብሰባዎችና በትልልቅ መጽሔቶች ላይ ብዙ ይባልለታል። ሕክምናውን የፈለሰፉት ሰዎች በሙያው መስክ ስማቸው ይገንናል፤ መገናኛ ብዙሃንም የታየውን መሻሻል በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ያስተጋባሉ። ለተወሰነ ጊዜ የደስታ ስሜት ይነግሥና ልቆ የተገኘውን የሕክምና ዘዴ በመደገፍ በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ምሥክርነት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ያልታሰቡ ነገሮች ብቅ ማለት ይጀምሩና ለወራት አልፎ ተርፎም ለአሥርተ ዓመታት የሚዘልቅ ግራ መጋባት ይፈጠራል። ከዚያ አዲስ የሕክምና ዘዴ ብቅ ይልና በአንድ ጀንበር ማለት ይቻላል፣ የቀድሞውን ዋጋ አሳጥቶት ቁጭ ይላል።” በእርግጥም፣ አብዛኞቹ ዶክተሮች ፋይዳ ቢስ እንደሆኑ አድርገው በመደምደም እርግፍ አድርገው የተዉአቸው ብዙዎቹ የሕክምና ዘዴዎች ዋነኛ የሕክምና መስጫ ዘዴዎች ተደርገው ይሠራባቸው የነበረበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አይደለም።

ምንም እንኳ በዛሬው ጊዜ ያሉት ዶክተሮች ለጥንቶቹ ሐኪሞች ይሰጥ የነበረው ዓይነት ሃይማኖታዊ ከበሬታ ባይሰጣቸውም የሕክምና ባለሙያዎችን መለኮታዊ ኃይል እንዳላቸው ያህል አድርገው የሚመለከቱና ሳይንስ የሰውን ልጅ ለሚያጠቁት በሽታዎች ሁሉ ፈውስ ማስገኘቱ እንደማይቀር አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አልጠፉም። ይሁን እንጂ እውነታው ይህ ሊሆን እንደማይችል ያሳያል። ዶክተር ሌናርድ ሄይፍሊክ ሃው ኤንድ ዋይ ዊ ኤጅ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “በ1900 ከዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ መካከል 75 በመቶ የሚሆነው የሞተው ስልሳ አምስት ዓመት ሳይሞላው ነው። ዛሬ ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኗል ማለት ይቻላል:- ከሕዝቡ መካከል ወደ 70 በመቶ የሚሆነው የሚሞተው ስልሳ አምስት ዓመት ከሆነው በኋላ ነው” ብለዋል። የሰው ልጅ ዕድሜ በእንዲህ ያለ አስደናቂ ሁኔታ ሊጨምር የቻለው ለምንድን ነው? ለዚህ “ዋነኛው ምክንያት በጨቅላ ዕድሜያቸው የሚቀጩ ሕፃናት ቁጥር መቀነሱ ነው” ሲሉ ሄይፍሊክ ገልጸዋል። ይሁንና የሕክምና ሳይንስ ለአረጋውያን ሞት ዋነኛ ምክንያት የሆኑትን የልብ በሽታን፣ ካንሰርንና በአንጎል ውስጥ የሚከሰትን የደም መፍሰስ ችግር ማስወገድ ቻለ እንበል። ይህ ከሞት ነፃ ሊያደርግ ይችላልን? በፍጹም። ዶክተር ሄይፍሊክ ያን ጊዜም እንኳ ቢሆን “አብዛኞቹ ሰዎች መኖር የሚችሉት መቶ ዓመት ገደማ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም “መቶ ዓመት ገደማ መኖር ቢችሉም እንኳ ከሞት ነፃ አይሆኑም። ለሞት የሚዳርጋቸው ነገር ምንድን ነው? እስኪሞቱ ድረስ እየደከሙና እየመነመኑ ይሄዳሉ” ብለዋል።

ስለዚህ የሕክምና ሳይንስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ሞትን ማስቀረት ሊደረስበት የማይችል ግብ ሆኗል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ጤና ለሁሉም የሚለው ግብ ጨርሶ ሊጨበጥ የማይችል ሕልም ነውን?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደሚለው ከሆነ ጌለን ጉበት በሰውነት ውስጥ የተፈጨውን ምግብ ወደ ደም ከቀየረው በኋላ ደሙ ወደ ተቀረው የሰውነት ክፍል ይሰራጫል ብሎ ያስብ ነበር።

^ አን.12 በጥር 2001 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ከሥቃይ ወደ ሰመመን” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የጥንቶቹ ሰዎች ከነበሯቸው እምነቶች መካከል ብዙዎቹ በሕክምናው መስክ እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ የማይፋቅ አሻራ ጥለው አልፈዋል።”​—⁠ዘ ክሌይ ፔድስታል

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሂፖክራቲዝ፣ ጌለን እና ቨሴሊየስ ለዘመናዊው ሕክምና መሠረት ጥለዋል

[ምንጮች]

ኮስ ደሴት፣ ግሪክ

Courtesy National Library of Medicine

Woodcut by Jan Steven von Kalkar of A. Vesalius, taken from Meyer’s Encyclopedic Lexicon

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አራት የፈረንሳይ ነገሥታትን ያገለገለው አንብሮዋዝ ፓሬ የቀዶ ሕክምና ፈር ቀዳጅ ነው

ፋርሳዊው ሐኪም አር ራዚ (በስተ ግራ) እና ብሪታንያዊው ሐኪም ኤድዋርድ ጄነር (በስተ ቀኝ)

[ምንጮች]

Paré and Ar-Rāzī: Courtesy National Library of Medicine

From the book Great Men and Famous Women

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈረንሳዊው ሉዊ ፓስተር ጀርሞች በሽታ አማጭ መሆናቸውን አረጋግጧል

[ምንጭ]

© Institut Pasteur

[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለሞት ዋና መንስኤ የሆኑት ነገሮች ቢወገዱም እንኳ እርጅና ሞት ማስከተሉ አይቀርም