በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምድርን የእንስሳት ዝርያዎች መታደግ ይቻል ይሆን?

የምድርን የእንስሳት ዝርያዎች መታደግ ይቻል ይሆን?

የምድርን የእንስሳት ዝርያዎች መታደግ ይቻል ይሆን?

“የሰው ልጅ ከጦጣ ጀምሮ አልባትሮስ እስከተባለው የባሕር ላይ ወፍና ድራጎን ፍላይ እስከተባለው የውኃ ላይ ተርብ ድረስ ያሉትንና ሌሎችንም ሕያው ፍጥረታት ከምድረ ገጽ ሊያጠፋቸው የተቃረበ በመሆኑ የገዛ ራሳችንን ሕልውና አደጋ ላይ ጥለናል” በማለት ካናዳ ውስጥ የሚታተመው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል። የጋዜጣው ዘገባ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚገኘው የዓለም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት (IUCN) የ 2000 ሬድ ሊስት ኦቭ ትሬትንድ ስፒሽስ በሚል ያወጣውን ዝርዝር የሚመለከት ነው። ይህ ዝርዝር ከ11, 000 በላይ የሚሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ጨርሶ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል በማለት አስጠንቅቋል። ከሁሉ የበለጠ አደጋ የተደቀነባቸው ደግሞ አጥቢ እንስሳት ናቸው። “በምድር ላይ በሕይወት ከሚገኙት ከአራት የአጥቢ እንስሳ ዝርያዎች መካከል አንዱ ወይም 24 በመቶ የሚሆኑት የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል” በማለት ግሎብ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

ታዲያ ለዚህ ችግር ተጠያቂው ማን ነው? ሳይንቲስቶች በእነዚህ ዝርያዎች ላይ ለሚደርሰው ውድመት መፋጠን ምክንያት እንደሆኑ አድርገው የሚጠቅሷቸው ነገሮች ዓለም አቀፉ የእንስሳት ንግድ፣ አንዳንድ የዓሣ አጠማመድ ዘዴዎችና የተመቻቸ የመኖሪያ ሁኔታ አለመኖር ናቸው። ከዚህም በላይ በደን የተሸፈኑ ድንግል ቦታዎች ተመንጥረው ተጨማሪ መንገዶች በተሠሩ መጠን “ሰዎች ቀድሞ ሊያገኟቸው የማይችሏቸውን የዱር እንስሳት የማግኘት አጋጣሚያቸው እየሰፋ ይሄዳል። ሲያገኟቸው ደግሞ ይገድሏቸውና ለመብልነት ይጠቀሙባቸዋል። እንዲህ ያለው ድርጊት ከቀጠለ ደግሞ ዝርያዎች ጨርሰው ይጠፋሉ።”

ሳይንቲስቶች ይህ አካሄድ ለሰው ልጆችም ጭምር አደገኛ እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። “የእንስሳት ዝርያዎችን ከምድረ ገጽ ባጠፋን ቁጥር ሕይወታችንን ደግፎ በሚያቆየው ሥርዓት ላይ ጉዳት እያደረስን ነው” በማለት በዓለም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት ሥር ዝርያዎችን ከጥፋት ለማዳን ተብሎ የተቋቋመው ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት ዴቪድ ብራኬት ተናግረዋል። “ስፍር ቁጥር በሌለው ሕያው ፍጥረት የተሞላችውን ዓለማችንን በእንስሳት መጠበቂያ ብቻ መታደግ አይቻልም።”

የዓለም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት (IUCN) ያወጣው ሪፖርት “ችግሩን ለማስወገድ አሁን ያለው የሰው ኃይልና ቁሳዊ ሃብት ከ10 እስከ 100 ጊዜ በሚበልጥ መጠን ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት” በመግለጽ ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል። የሚያሳዝነው ግን ስግብግብነት ብዙውን ጊዜ የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ የሚደረገውን ልባዊ ጥረት መና ያስቀረዋል።

ታዲያ የምድርን የእንስሳት ዝርያዎች መታደግ ይቻል ይሆን? የመጀመሪያዎቹ ሰዎችና ልጆቻቸው በምድር ላይ የሚገኙትን የተለያዩ ሕያው ፍጥረታት የመንከባከብ ሥራ ተሰጥቶአቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በዔደን የአትክልት ቦታ አኖረው፤ ይህንንም ያደረገው ሰው የአትክልቱን ቦታ እንዲያለማና እንዲንከባከበው ነው” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:​151980 ትርጉም ) ምንም እንኳ የሰው ልጅ ይህንን ግዴታውን ባይፈጽምም አምላክ ግን ለምድር ያለው ዓላማ አልተለወጠም። ለምድራችን ስለሚያስብ ከግድየለሽነት ወይም ከስግብግብነት የተነሳ እንድትጠፋ አይፈቅድም። (ራእይ 11:​18) ቃሉ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ተስፋ ይሰጣል።​—⁠መዝሙር 37:​29

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./J.D. Pittillo