የፀሐያችን ልዩ ተፈጥሮ
የፀሐያችን ልዩ ተፈጥሮ
ይህን ጽሑፍ እያነበብክ ባለህበት ሰዓት አንድም ፀሐይ ወጥታለች አሊያም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ትወጣለች። ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነውን? አዎን፣ ምክንያቱም የፀሐይ ብርሃን ባይኖር ኖሮ አንተን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉ በትሪልዮን የሚቆጠሩ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ አይኖሩም ነበር። አንድ ሕዋስ ካላቸው ባክቴሪያዎች አንስቶ እስከ ግዙፎቹ ዓሣ ነባሪዎች ድረስ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠር ዝርያ ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ሕልውና ያከትም ነበር።
እርግጥ ነው፣ ፀሐይ ከምታመነጨው ጉልበት ውስጥ ወደ ፕላኔታችን የሚደርሰው የአንድ ቢልዮንኛ ግማሽ ያህል ብቻ ነው። ሆኖም ይህ ከፀሐይ “ማዕድ” የሚንጠባጠበው “ፍርፋሪ” በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ለመመገብና ጠብቆ ለማቆየት በቂ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ እንደ ፍርፋሪ የተቆጠረው አነስተኛ የፀሐይ ጉልበት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ የዘመናዊውን ኅብረተሰብ የኃይል ፍላጎት ከበቂ በላይ ሊያሟላ የሚችል ነው።
አብዛኞቹ የስነ ፈለክ መጻሕፍት ፀሐያችን ተራ ኮከብ ማለትም “ከሌሎቹ ብዙም የማትለይ ሰማያዊ አካል” እንደሆነች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ፀሐይ “ከሌሎቹ ብዙም የማትለይ ሰማያዊ አካል” ነች? ሲያትል ውስጥ በሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የስነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ጊልዬርሞ ጎንዛሌዝ ፀሐያችን በዓይነቷ ልዩ እንደሆነች ገልጸዋል። ይህ በሌሎች ፕላኔቶች ላይ ሕይወት ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? ጎንዛሌዝ “የማሰብ ችሎታ ላላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ተስማሚ የሆኑት ከዋክብት ሰዎች ከሚገምቱት በላይ በጣም ጥቂቶች ናቸው” ሲሉ መልስ ይሰጣሉ። አክለውም “የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ፍለጋቸው እንደ ፀሐይ ባሉ በዓይነታቸው ለየት ያሉ ከዋክብት ላይ እንዲወሰን ካላደረጉ በስተቀር ጊዜያቸውን በከንቱ ሊያባክኑ ይችላሉ” ብለዋል።
ፀሐያችን ለሕይወት ተስማሚ እንድትሆን ካደረጓት ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህን ነገሮች በምንመረምርበት ጊዜ ከጽንፈ ዓለሙ ፊዚክስ ጋር በተያያዘ የተሰጡት ብዙዎቹ አስተያየቶች በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ያሉ መሆናቸውን አትዘንጋ።
እጅግ አስገራሚ የሆኑ ገጽታዎች
● አንድ ነጠላ ኮከብ:- የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት ከሆነ በፀሐይ ዙሪያ ከሚገኙት ከዋክብት መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ከዋክብትን ባካተቱ ቡድኖች የታቀፉ ሲሆኑ አንዳቸው ሌላውን ይዞራሉ። እነዚህ ከዋክብት እርስ በርሳቸው በስበት ኃይሎች የተሳሰሩ ናቸው።
ፀሐይ ግን አንድ ነጠላ ኮከብ ነች። የስነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ኬኔት ጄ ኤች ፊሊፕስ ጋይድ ቱ ዘ ሰን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ፀሐይ ብቻዋን ተነጥላ መቀመጧ እንግዳ ነገር ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
ፀሐይ ብቻዋን ተነጥላ የምትገኝ መሆኗ ምድር ቋሚ የሆነ ምህዋር እንዲኖራት እገዛ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በዚህች ሉል ላይ ለሕይወት ተስማሚ የሆኑ ሁኔታዎች እንዲኖሩ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ ጎንዛሌዝ።● ግዙፍ ኮከብ:- ጎንዛሌዝ እንደሚሉት ፀሐይን ልዩ የሚያደርጋት ሌላው ነገር “በዙሪያዋ ከሚገኙት 10 በመቶ የሚሆኑ እጅግ ግዙፍ ከዋክብት አንዷ መሆኗ ነው” ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። “ከሥርዓተ ፀሐይ መጠነቁስ መካከል 99.87 በመቶ የሚሆነውን የያዘችው ፀሐይ ስትሆን ይህም በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉትን አካላት በሙሉ በስበት ኃይል ለመቆጣጠር አስችሏታል” ሲሉ ፊሊፕስ ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ ምድር ከፀሐይ 150 ሚልዮን ኪሎ ሜትር ርቃ እንድትገኝ ያስቻለ ቢሆንም ከዚያ በላይ ርቃ ግን አትሄድም። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እንዲህ ያለ ረጅም ርቀት መኖሩ በምድር ላይ የሚገኘው ሕይወት በፀሐይ ሐሩር ከመንደድ እንዲጠበቅ ያደርገዋል።
● ከባድ ንጥረ ነገሮች:- ጎንዛሌዝ በፀሐይ ላይ የሚገኙት እንደ ካርቦን፣ ናይትሮጅን፣ ኦክሲጅን፣ ማግኒዚየም፣ ሲሊከንና ብረት ያሉ ከባድ ንጥረ ነገሮች በዕድሜም ሆነ በዓይነት ከፀሐይ ጋር ተመሳሳይነት ባላቸው ሌሎች ከዋክብት ላይ ካሉት ከባድ ንጥረ ነገሮች 50 በመቶ በልጠው እንደተገኙ ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ፀሐያችን ከመሰሎቿ ልቃ ተገኝታለች። “በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በፀሐይ አካል ላይ ያሉት ከባድ ንጥረ ነገሮች ብዛት አነስተኛ ነው” ይላሉ ፊሊፕስ፣ “ሆኖም በአንዳንድ ከዋክብት . . . ላይ ያሉት ከባድ ንጥረ ነገሮች ከዚያም ያነሱ ናቸው።” የፀሐይን ያህል ላቅ ያለ መጠን ያላቸውን ከባድ ንጥረ ነገሮች የያዙ ከዋክብት ፖፕዩሌሽን ዋን በሚል መጠሪያ ይመደባሉ።
ይህ በምድር ላይ ካለው ሕይወት ሕልውና ጋር ግንኙነት የሚኖረው እንዴት ነው? እነዚህ ከባድ ንጥረ ነገሮች ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት በጣም አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም መጠናቸው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ከመላው ጽንፈ ዓለም 1 በመቶ የሚሆነውን እንኳ አይሸፍኑም። ይሁን እንጂ እነዚህን ከባድ ንጥረ ነገሮች በሙሉ የያዘችው ምድራችን ነች ለማለት ይቻላል። ለምን? የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ምድር በዓይነቷ ልዩ የሆነችውን ኮከብ ማለትም የኛን ፀሐይ የምትዞር በመሆኑ ነው።
● ወደ ክብነት ያደላ ቅርፅ ያለው ምህዋር:- ፀሐይ ፖፕዩሌሽን ዋን በመባል ከሚታወቁት ከዋክብት አንዷ መሆኗ የሚያስገኘው ሌላ ጥቅምም አለ። “ፖፕዩሌሽን ዋን በመባል የሚታወቁት ከዋክብት በጥቅሉ በከዋክብት
ረጨቱ መካከል የክብ ዓይነት ቅርፅ ባላቸው ምህዋሮች ይሽከረከራሉ” ይላል ጋይድ ቱ ዘ ሰን የተሰኘው መጽሐፍ። የፀሐይ ምህዋር በዕድሜና በዓይነት መሰሎቿ ከሆኑት ሌሎች ከዋክብት ምህዋር ይበልጥ ወደ ክብነት ያደላ ነው። ይህ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው? የፀሐይ ምህዋር ይበልጥ ክብ መሆኑ ፀሐይ ለሱፐርኖቫዎች (የሚፈነዱ ከዋክብት) ወደተጋለጠው የከዋክብት ረጨት ውስጠኛ አካል እንዳትገባ ይከላከላል።● የብርሃን ድምቀት መለዋወጥ:- እኛ በምንገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያለችውን ይህችን ኮከብ በተመለከተ ሌላም ትኩረት የሚስብ እውነታ አለ። ከሌሎች ተመሳሳይ ኮከቦች ጋር ሲነጻጸር የፀሐይ የብርሃን ድምቀት ብዙም የመለዋወጥ ጠባይ አይታይበትም። በሌላ አነጋገር የፀሐይ ብርሃን ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ አንድ ወጥ የሆነና የማይለዋወጥ ነው።
እንዲህ ያለው በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንድ ወጥ የሆነ ብርሃን በምድር ላይ ላለው ሕይወት እጅግ ወሳኝ ነው። “በፕላኔቷ ላይ በሕይወት መገኘታችን ራሱ” ይላሉ የሳይንስ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ካርል ሁፍባወር፣ “ከፀሐይ የሚመነጨው ብርሃን የመለዋወጥ ባሕርይ ከሌላቸው አካባቢያዊ ሁኔታዎች አንዱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው።”
● ያጋደለ ምህዋር:- የፀሐይ ምህዋር ወደ ፍኖተ ሐሊብ የከዋክብት ረጨት ጠለል (plane) በትንሹ ያጋደለ ነው። በመሆኑም በፀሐይ ምህዋር ጠለልና እኛ ባለንበት የከዋክብት ረጨት ጠለል መካከል ያለው አንግል በጣም አነስተኛ ነው። ይህ በምድር ላይ ላለው ሕይወት ደህንነት አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
እኛ ካለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ውጭ የኦርት ዳመና ተብሎ የሚጠራ ክብ ቅርፅ ያለው ግዙፍ የጅራታም ኮከቦች ክምችት በዙሪያችን ይገኛል። * የፀሐይ ምህዋር ወደ ፍኖተ ሐሊብ የከዋክብት ረጨት በጣም ያጋደለ ቢሆን ኖሮስ? ፀሐይ በድንገት የከዋክብት ረጨቱን ጠለል በመሻገር የኦርት ዳመና በመባል የሚጠራውን የጅራታም ኮከቦች ክምችት ልታናጋው ትችላለች። ይህ ምን ያስከትላል? ምድር አውዳሚ በሆነ የጅራታም ኮከቦች ውርጅብኝ ትመታለች ይላሉ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች።
የፀሐይ ግርዶሽ ምን የሚጠቁመን ነገር ይኖራል?
እኛ በምንገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ 60 ጨረቃዎች አሉ። እነዚህ ጨረቃዎች በዚህ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ከሚገኙት ዘጠኝ ፕላኔቶች መካከል ሰባቱን ይዞራሉ። ይሁን እንጂ በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ካሉት ፕላኔቶች መካከል ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚታየው በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ በፀሐይና በምድር መካከል በምትሆንበት ጊዜ ነው። ጨረቃ ፀሐይን ሙሉ በሙሉ የምትሸፍነው ከፀሐይ መጠን ጋር እኩል መስላ የምትታይበት ቦታ ላይ ስትሆን ነው። የፀሐይ ግርዶሽም የሚፈጠረው በዚህ ጊዜ ነው! ምንም እንኳ የፀሐይ ዲያሜትር ከጨረቃ ዲያሜትር 400 ጊዜ ያህል የሚበልጥ ቢሆንም በፀሐይና በምድር መካከል ያለው ርቀት በጨረቃና በፀሐይ መካከል ካለው ርቀት ጋር ሲነጻጸር 400 ጊዜ እጥፍ ይበልጣል።
ይሁን እንጂ ምድር ከፀሐይ ያላት ርቀትና በዚህም ሳቢያ ለዓይናችን የሚታየው የፀሐይ መጠን ሙሉ ግርዶሽ እንዲፈጠር ከማድረጉም በተጨማሪ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ። በምድር ላይ ላለው ሕይወት ሕልውናም በጣም ወሳኝ ነው። “ወደ ፀሐይ ትንሽ ቀረብ ብንል ወይም ከፀሐይ ትንሽ ራቅ ብንል ኖሮ” አሉ ጎንዛሌዝ፣ “ምድር በጣም ሞቃት አለዚያም በጣም ቀዝቃዛ ስለምትሆን ሕይወት የሚባል ነገር አይኖርም ነበር።”
ይህም ብቻ አይደለም። ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ በጣም ግዙፍ የሆነችው የምድር ጨረቃ ያላት የስበት ኃይል ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ አንድ ወጥ ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ እንዳትሽከረከር የሚከላከል በመሆኑ በዚህች ፕላኔት ላይ ላለው ሕይወት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲህ ዓይነቱ አንድ ወጥ ሥርዓት ያልጠበቀ እንቅስቃሴ አደገኛና አውዳሚ የሆነ የአየር ጠባይ ለውጥ ያስከትላል። ስለዚህ በምድር ላይ ሕይወት ሊኖር የቻለው ቀደም ሲል የፀሐይን ተፈጥሮ በተመለከተ ካነሳናቸው ነጥቦች በተጨማሪ በፀሐይና በምድር መካከል ትክክለኛ ርቀት በመኖሩና በዚህ ላይ ደግሞ ትክክለኛ መጠን ያላት ጨረቃ በመኖሯ ነው። ይህ ሁሉ እንዲሁ በአጋጣሚ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ምን ያህል ነው?
በአጋጣሚ የተከሰተ ነውን?
መኪናህን ለማስጠገን ወደ አንድ የሰለጠነና በሙያው የተካነ መካኒክ ሄድክ እንበል። ሥራውን በትጋት ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ ሁሉ ነገር ተስተካክሎ ታገኘዋለህ። መኪናህ በትክክል መሥራት የጀመረው በድንገተኛ አጋጣሚ ወይም በዕድል እንደሆነ አድርገህ ብትናገር ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የፀሐያችንንም አፈጣጠር በተመለከተ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች የፀሐያችን ቅንብር፣ የምትጓዝበት ምህዋር፣ ከምድር ያላት ርቀትና ሌሎች ገጽታዎችዋ ሁሉ በድንገተኛ አጋጣሚ የተፈጠሩ ናቸው ብለህ እንድታምን ሊያደርጉህ ይፈልጋሉ። ይህ ምክንያታዊ ነውን? በአሳማኝ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው ብለህ ታምናለህ?
በጥሩ ሁኔታ የተጠገነ መኪና ስለ መካኒኩ ሙያና ችሎታ የሚያስተላልፈው መልእክት እንዳለ ሁሉ ከሌሎች ሰማያዊ አካላት በተጨማሪ ፀሐያችንም የምታስተላልፈው መልእክት አለ። ፀሐያችን በምድር ላይ ላለው ሕይወት ወሳኝ የሆኑና በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ገጽታዎች ያሏት መሆኑ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታና ኃይል ያለው ንድፍ አውጪና ፈጣሪ የእጅ ሥራ ውጤት እንደሆነች በግልጽ የሚያሳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል።”—ሮሜ 1:20
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.17 ስለ ኦርት ዳመና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 2000 ንቁ! መጽሔት ገጽ 26ን ተመልከት።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ፀሐይ ከምታመነጨው ጉልበት ውስጥ ወደ ፕላኔታችን የሚደርሰው የአንድ ቢልዮንኛ ግማሽ ያህል ብቻ ነው
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህን የመሰሉ በፀሐይ ላይ የሚካሄዱ ፍንዳታዎች በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ለአደጋ አላጋለጡትም
[ምንጭ]
ገጽ 23 እና 24:- NASA photo
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጋጣሚ የፈጠረው ነገር ነው? ፀሐይና ጨረቃ ተመጣጣኝ መጠን ያላቸው ሆነው በሚታዩበት ጊዜ እጅግ ማራኪ የሆነ ግርዶሽ ይፈጥራል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፀሐይ ምህዋር የተለየ ቢሆን ኖሮ አውዳሚ የሆነ የጅራታም ኮከቦች ውርጅብኝ ምድርን ሊደበድባት ይችል ነበር