በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት ለምንድን ነው?

ሰዎች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት ለምንድን ነው?

ሰዎች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት ለምንድን ነው?

“ዕድሜዬ ገና 13 ዓመት ነበር። የጓደኛዬ እህት አንድ ቀን ምሽት ቤታቸው ጋበዘችንና ሄድን። ሁሉም ማሪዋና ማጨስ ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ እንዳጨስ የቀረበልኝን ግብዣ ሳልቀበል ቀረሁ። በኋላ ግን ውትወታቸው ሲበዛብኝ ተቀብዬ ማጨስ ጀመርኩ።” በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማይክል አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች መውሰድ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

“ተወልጄ ያደግኩት ክላሲካል ሙዚቃ በመጫወት በሚተዳደር፣ ወግ አጥባቂ ቤተሰብ ውስጥ ነው። በአንድ የሙዚቃ ጓድ ውስጥ እጫወት የነበረ ሲሆን ከሙዚቀኞቹ አንዱ በእረፍት ሰዓት አዘውትሮ ማሪዋና ያጨስ ነበር። ለብዙ ወራት እኔም እንዳጨስ ይጎተጉተኝ ነበር። በመጨረሻ ተሸነፍኩና ደንበኛ አጫሽ ሆንኩ።” ካናዳዊው ዳረን አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች መውሰድ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

ውሎ አድሮ እንደ ኤል ኤስ ዲ እና ኦፒየም ያሉ እንዲሁም ሌሎች የሚያነቃቁ አደገኛ መድኃኒቶችን መውሰድ ጀመሩ። ቀደም ሲል አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ይወስዱ የነበሩት እነዚህ ግለሰቦች ወደኋላ መለስ ብለው ያለፈውን ሲያስታውሱ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ መውሰድ እንዲጀምሩ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት የእኩዮች ተጽዕኖ እንደሆነ ይስማማሉ። “ዕፅ እወስዳለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር” ይላል ማይክል፤ “ይሁን እንጂ ያሉኝ ጓደኞች እነዚህ ልጆች ብቻ ነበሩ። ስለዚህ ያለህ ምርጫ እነርሱ የሚያደርጉትን ማድረግ ነው።”

የመዝናኛው መስክ

ብዙዎች አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መውሰድ እንዲጀምሩ ያደረጋቸው የእኩዮች ተጽዕኖ ሲሆን በዚህ ረገድ ደግሞ በቀላሉ የሚጠቁት ወጣቶች ናቸው። በተጨማሪም በመዝናኛው ዓለም እንደ ጣዖት የሚታዩና ወጣት ደጋፊዎቻቸውን የመማረክ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ሰዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።

በተለይ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የመጠቀም አባዜ ተጠናውቶታል። ብዙውን ጊዜ በሙዚቃው መስክ የተሰለፉ የታወቁ የሙዚቃ ተጫዋቾች በሕይወታቸው ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ የከባድ ዕፅ ሱሰኞች ሲሆኑ ይታያል። በርካታ የፊልም ኮከቦችም የዕፅ ሱሰኞች ናቸው።

በመዝናኛው መስክ የተሰለፉ የመድረክ ሰዎች አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በጣም ማራኪና ተወዳጅ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ወጣቶቹ በጣም እንዲጓጉ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ኒውስዊክ በ1996 የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “የሲያትል ጎዳናዎች [የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ] የሆነው ኮቤን የወሰደውን ሄሮይን የተሰኘ ዕፅ ለመውሰድ በመጡ ወጣቶች ተጥለቅልቀዋል።”

መጽሔቶች፣ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ማራኪና ተወዳጅ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ። በተመሳሳይም በፋሽኑ ዓለም የተሰለፉ አንዳንድ የታወቁ የልብስ ንድፍ አውጪዎች በዕፅ ሱስ የተጠመዱ ሰዎችን ቁመና በመኮረጅ ቀጭንና የመነመነ ቁመና ያላቸውን እንስት ሞዴሎች መጠቀም ይመርጣሉ።

አንዳንዶች በዕፅ ሱስ የሚጠመዱት ለምንድን ነው?

አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እንዲበራከት ያደረጉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት፣ ጭንቀትና የሕይወት ትርጉም ማጣት ይገኙበታል። የኢኮኖሚ ችግር፣ ሥራ አጥነትና ወላጆች ጥሩ ምሳሌ አለመሆናቸው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

ከሰዎች ጋር በቀላሉ መደባለቅ የማይችሉ አንዳንዶች ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ዕፅ ይወስዳሉ። ዕፅ መውሰዳቸው ይበልጥ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው እንደሚረዳቸውና ተጫዋችና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆኑ ሆነው እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንዴት በተሳካ ሁኔታ መምራት እንደሚችሉ ለመማር ከመሞከር ይልቅ ዕፅ ወስዶ በቀላሉ መገላገል የተሻለ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ።

ወጣቶች ወደ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ዞር እንዲሉ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ ስልቹ የመሆን ስሜት ነው። ዘ ሮማንስ ኦቭ ሪስክ​—⁠ዋይ ቲንኤጀርስ ዱ ዘ ቲንግስ ዘይ ዱ የተባለው መጽሐፍ ስልቹ መሆንንና የወላጆች ቁጥጥር ማነስን በተመለከተ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቤት ማንንም አያገኙም። የብቸኝነት ስሜት ቢሰማቸውና ብቸኛ መሆኑን ቢጠሉት ምንም አያስደንቅም። ጓደኞቻቸው አብረዋቸው የሚሆኑ ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ የመሰልቸት ስሜት ይሰማቸዋል። ደስታ ለማግኘት ሲሉም ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥንና የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ይመለከታሉ ወይም በኢንተርኔት ይጠመዳሉ። ሲጋራ፣ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች እንዲሁም መጠጥ በቀላሉ የዚህ ገጽታ ክፍል ሊሆኑ ይችላሉ።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማይክል በቤተሰባቸው ውስጥ የነበረውን የወላጆች ቁጥጥር ማነስ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የቤተሰባችን ሕይወት አስደሳች ነው። እርስ በርሳችን በጣም እንቀራረባለን። ሆኖም ሁለቱም ወላጆቼ ሥራ ስለሚውሉ በቀን ውስጥ የት ናቸው የሚለን ሰው እንኳ አልነበረም። በዚህ ላይ ደግሞ ወላጆቻችን ሙሉ ነፃነት ሰጥተውን ነበር። የሚገሥጸንም ሆነ የሚቀጣን ሰው አልነበረም። ወላጆቼ ዕፅ እንደምወስድ ፈጽሞ አያውቁም ነበር።”

ብዙዎች አንዴ በሱስ ከተጠመዱ በኋላ ደስታ ለማግኘት በሚል ሰበብ ብቻ ዕፅ መውሰዳቸውን ይቀጥላሉ። በየቀኑ ዕፅ ይወስድ የነበረው ማይክል ያስከተለበትን ውጤት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “የምኖረው በሕልም ዓለም ውስጥ ነበር። የሚያሳስበኝና የሚያስጨንቀኝ ነገር ሁሉ ይጠፋል። ፍርሃት የሚባል አይሰማኝም። ሁሉም ነገር አስደሳች ሆኖ ይታየኛል።”

ቀደም ሲል አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ይወስድ የነበረው በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ዲክ በ13 ዓመቱ ማሪዋና ማጨስ ሲጀምር ይሰማው የነበረውን ስሜት ሲገልጽ “በትንሹም በትልቁም እስቃለሁ። ሁሉም ነገር ያስፈነድቀኝ ነበር” ብሏል።

አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳት የሚነገሩትን ማስጠንቀቂያዎች ወጣቶች ከመጤፍ የሚቆጥሯቸው አይመስልም። “በእኔ ላይ አይደርስም” የሚል ዝንባሌ አላቸው። ቶኪንግ ዊዝ ዩር ቲንኤጀር የተባለው መጽሐፍ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በጤና ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳት የሚነገሩ ማስጠንቀቂያዎችን ለምን ችላ እንደሚሉ ሲናገር “ጠንካሮችና ብርቱዎች በመሆናቸው ጤናቸው ሊቃወስ እንደሚችል ፈጽሞ አያስቡም። ብዙዎቹ ወጣቶች ‘ምንም አልሆንም’ የሚል አመለካከት አላቸው። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሳንባ ካንሰር፣ የመጠጥ ሱስና ከባድ የዕፅ ሱስ በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የሚደርሱ እንጂ በእነርሱ ላይ የሚደርሱ አይመስላቸውም።” በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ባገኘው ኤክስታሲ በተባለው ዕፅ እንደታየው በርካታ ወጣቶች አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ስለሚያደርሱት ጉዳት ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ኤክስታሲ ምንድን ነው?

ኤክስታሲ እና ዳንስ ቤቶች

ኤክስታሲ በመባል የሚታወቀው አምፌታሚን በብዛት የሚገኝበት ዕፅ (ኤም ዲ ኤም ኤ) ሌሊቱን ሙሉ በሚጨፈርባቸው ዳንስ ቤቶች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ይዘወተራል። ይህንን ዕፅ የሚሸጡ ሰዎች ኤክስታሲ ምንም ጉዳት እንደማያስከትልና የደስታ ስሜት ለማግኘትና ሙሉ ሌሊት ሳይደክሙ ለመደነስ የሚያስችል ኃይል አንደሚሰጥ ይናገራሉ። አንድ ጸሐፊ እንዳሉት ይህ ዕፅ ጨፋሪዎቹ “መጨረሻ ላይ ደንዝዘው እስኪዝለፈለፉ ድረስ” ለብዙ ሰዓት እንዲጨፍሩ ይረዳቸዋል። አንዲት ወጣት ኤክስታሲ ብዙዎችን ምርኮኛ የሚያደርግበትን ምክንያት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “በውስጥህ የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ከእግር ጥፍርህ ይጀምርና ቀስ በቀስ ሙቀትና ፍቅር በሰውነትህ ውስጥ እያሰራጨ ወደ ጭንቅላትህ ይወጣል።”

አዘውትረው ኤክስታሲ በሚወስዱ ሰዎች አንጎል ላይ በተደረገ ምርመራ ኤክስታሲ ሻጮቹ እንደሚሉት ጉዳት የማያስከትል ዕፅ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ተገኝቷል። በተገኘው መረጃ መሠረት ኤክስታሲ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የነርቭ አውታሮችን ይጎዳል እንዲሁም የሴሮቶኒንን መጠን ይቀንሳል። ይህም ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ውሎ አድሮም የመንፈስ ጭንቀትና የመርሳት ችግር ሊያስከትል ይችላል። ኤክስታሲ ከሚወስዱ ሰዎች መካከል የሞቱ እንዳሉም ሪፖርት ተደርጓል። በርካታ የዕፅ ነጋዴዎችም ደንበኞቻቸው በሱስ እንዲጠመዱ ለማድረግ ሲሉ ኤክስታሲን ከሄሮይን ጋር ቀላቅለው ይሸጣሉ።

ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ ምን ያህል ሰፊ ነው?

በአንዳንድ አገሮች የአቅርቦቱ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ዋጋ ቀንሷል። ለዚህም በከፊል ምክንያት የሆነው በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ የተደረገው ለውጥ ነው። በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካ ዓይነተኛ ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገውን የንግድ ልውውጥና ግንኙነት አሳድጎታል። ይህ ሁኔታና በድንበር ላይ ያለው ቁጥጥር ልል መሆን የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተከለከሉ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን በመሸጥ ኑሯቸውን ይገፋሉ። ብዙውን ጊዜ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሲበራከቱ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች መስፋፋታቸው አይቀርም። አንድ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ መሠረት በደቡብ አፍሪካ፣ ጎቴንግ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች (የአንዳንዶቹ ዕድሜ ገና 13 ነው) አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን የሚያዘዋውሩ በመሆናቸው የፖሊስ ክትትል ይደረግባቸዋል። በዚህ አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ዕፅ መውሰድ አለመውሰዳቸውን ለማረጋገጥ ምርመራ ማካሄድ ጀምረዋል።

መሠረታዊው መንስኤ ምንድን ነው?

ሰዎች አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ለመውሰድ የሚገፋፉባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አንድ ጠለቅ ያለ ችግር ማለትም መሠረታዊ መንስኤ እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። ቤን ዊትከር የተባሉ አንድ ደራሲ መሠረታዊውን መንስኤ እንዲህ በማለት ጠቁመዋል:- “በጊዜያችን አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን የመውሰድ ልማድ በእጅጉ መስፋፋቱ ኅብረተሰባችን ከብቸኝነትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት በተጨማሪ ድክመቶችና ጉድለቶች እንዳሉበት የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። አለዚያማ ከፍተኛ ተሰጥዖ ያላቸውና በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ገሃዱን ዓለም ከመጋፈጥ ይልቅ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መውሰድ ለምን ይመርጣሉ?”

ይህ ሊጤን የሚገባው ጥያቄ ሲሆን በፍቅረ ንዋይ የተጠመደውና ለስኬት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የዘመናችን ኅብረተሰብ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን እንደማያሟላልን እንድንገነዘብም ይረዳናል። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች እንኳ ሳይቀሩ ለሰው ልጆች ችግር መሠረታዊ መንስኤ የሆነውን ነገር ባለማስተዋላቸው ምክንያት እነዚህን ፍላጎቶች ሊያሟሉ አልቻሉም።

በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሳቢያ ለተፈጠሩት ችግሮች ዘላቂና ብቸኛ የሆነውን መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ከማድረጋችን በፊት መሠረታዊውን መንስኤ ማወቅና መጋፈጥ ይገባናል። ይህንን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ጊዜ ዝነኛ ሰዎች አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ማራኪ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘመናዊው የሙዚቃ ዓለም አደገኛ በሆኑ መድኃኒቶችና ዕፆች ተጥለቅልቋል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤክስታሲ የተባለው ዕፅ በምሽት ዳንስ ቤቶች እንደልብ ይገኛል

[ምንጮች]

AP Photo/Greg Smith

Gerald Nino/U.S. Customs