በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት እነማን ናቸው?

ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት እነማን ናቸው?

ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት እነማን ናቸው?

ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“ሱስ የሚያስይዝ ነገር የማይወስድ ሰው የለም።” ምንም የማያውቅ አንድ ገራገር ሰው የተከለከሉ መድኃኒቶችንና ዕፆችን እንዲወስድ ለማግባባት እንዲህ ያለ እውነት የሚመስል ነገር ይነገረው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ “ሱስ የሚያስይዙ ብለን ከምንፈርጃቸው ነገሮች” አንጻር ሲታይ ይህ አባባል በተወሰነ መጠን እውነትነት አለው።

ሱስ የሚያስይዝ ነገር “በመረዳት ችሎታ፣ በስሜት፣ ወይም በሌላ ሥነ ልቦናዊ ሁኔታ ላይ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል በተፈጥሮ የሚገኝ ወይም ሰው ሠራሽ የሆነ ማንኛውም ዓይነት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ አገላለጽ ለአካላዊ ሕመሞች የሚሰጡ በርካታ መድኃኒቶችን የሚያጠቃልል ባይሆንም እንኳ በአእምሮና በባሕርይ ላይ ለውጥ የሚያሳድሩ ንጥረ ነገሮችን ሰፋ ባለ መንገድ የሚገልጽ ጥሩ መግለጫ ነው።

በዚህ መግለጫ መሠረት የአልኮል መጠጥም ሱስ የሚያስይዝ ነገር ነው። የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ መጠጣት አደገኛ ሲሆን ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለውም ይህ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣ ችግር ነው። በአንዲት ምዕራባዊ አገር በሚኖሩ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው “ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን በመውሰድ ረገድ በኮሌጅ ተማሪዎች ዘንድ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው ትልቁ ችግር ጠጪነት ነው።” ጥናቱ እንዳመለከተው 44 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ጠጪዎች ናቸው። *

ትምባሆ ኒኮቲን የሚባል ኃይለኛ መርዝ በውስጡ የያዘ ቢሆንም እንኳ እንደ አልኮል መጠጥ በሕግ የተፈቀደ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ሲጋራ በየዓመቱ ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎችን ይገድላል። ሆኖም የትምባሆ ቱጃሮች እጅግ የበለጸጉና በኅብረተሰቡ ዘንድ አክብሮትን ያተረፉ ሰዎች ናቸው። ሲጋራ ምናልባትም ከብዙዎቹ የተከለከሉ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ይበልጥ በከፍተኛ ደረጃ ሱስ የማስያዝ ኃይል አለው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ አገሮች የትምባሆ ማስታወቂያዎችን ያስቆሙ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ እገዳዎችንም ጥለዋል። የሆነ ሆኖ ሲጋራ ማጨስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ድርጊት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ በርካታ ሰዎች አሁንም አሉ። የፊልሙ ኢንዱስትሪ ሲጋራ ማጨስ ማራኪና አስደሳች እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡን አሁንም ተያይዞታል። ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘው የካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ ከ1991 እስከ 1996 በነበሩት ዓመታት በተሠሩ ከፍተኛ ትርፍ በተዛቀባቸው ፊልሞች ላይ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው ከዋና ዋናዎቹ የወንድ ተዋንያን መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የሚያጨሱ ገጸ ባሕርያትን ወክለው ተጫውተዋል።

ስለ መድኃኒቶችስ ምን ለማለት ይቻላል?

በሕክምና የሚሰጡ መድኃኒቶች ብዙዎችን የሚጠቅሙ ቢሆኑም አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውሉም ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ዶክተሮች መድኃኒቶችን በችኮላ ሊያዙ ወይም በታካሚዎቹ ጉትጎታ ሳያስፈልግ ሊሰጡ ይችላሉ። አንድ ሐኪም የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝረዋል:- “አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ ጊዜ ወስደው በቂ ምርመራ አያደርጉም። ‘ይህን መድኃኒት ውሰድ’ ማለት ይቀናቸዋል። ሆኖም ይህ መሠረታዊውን ችግር አይቀርፈውም።”

እንደ አስፕሪን እና ፓራሴታሞል (ታይሌኖል፣ ፓናዶል) ያሉ ያለ ሐኪም ትእዛዝ ሊገኙ የሚችሉ መድኃኒቶችም እንኳ አላግባብ ከተወሰዱ በጤና ላይ ከባድ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። በዓለም ዙሪያ ፓራሴታሞልን አላግባብ የሚወስዱ ከ2, 000 የሚበልጡ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ።

ጠዋት ቁርስ ላይ የምንጠጣውን ሻይ ወይም ቡና ብዙውን ጊዜ በዚህ መልኩ የማንመለከተው ቢሆንም እንኳ ቀደም ሲል በተሰጠው ትንተና መሠረት በሻይና በቡና ውስጥ የሚገኘው ካፌይንም ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር ነው። እንደ ሻይ ወይም ቡና ያሉትን በኅብረተሰቡ ዘንድ የተለመዱ መጠጦችን እንደ ሄሮይን ካሉ ለጤና ጠንቅ ከሆኑ አደገኛ ዕፆች ጋር ለማወዳደር መሞከር ሞኝነት ነው። እንዲህ ማድረጉ አንዲትን የድመት ግልገል አስፈሪ ከሆነ አንበሳ ጋር የማወዳደር ያህል ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ የጤና ባለ ሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በቀን ከአምስት ስኒ በላይ ቡና ወይም ከዘጠኝ ስኒ በላይ ሻይ የመጠጣት ልማድ ካለህ ልትጎዳ ትችላለህ። ከዚህም በላይ እንዲህ ዓይነቱን በብዛት የመጠጣት ልማድ በአንድ ጊዜ ብታቆም ሻይ በብዛት ትጠጣ የነበረች አንዲት ሴት ያጋጠማት ዓይነት ችግር ማለትም ትውከት፣ ኃይለኛ ራስ ምታትና ብርሃንን ለመቋቋም ያለመቻል ችግር ሊያጋጥምህ ይችላል።

የተከለከሉ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ስለመጠቀምስ ምን ለማለት ይቻላል?

ከሁሉ ይበልጥ አወዛጋቢ የሆነው ጉዳይ በስፖርቱ ዓለም መድኃኒቶችን የመጠቀም ልማድ ነው። በ1998 በተካሄደው ቱር ደ ፍራንስ ተብሎ በሚታወቀው የብስክሌት ውድድር ላይ አንደኛ ሆኖ ይመራ የነበረው የብስክሌት ቡድን ዘጠኝ አባላት ኃይል ሰጪ መድኃኒቶችን ወስደው በመገኘታቸው ምክንያት ከውድድሩ በተሰረዙበት ጊዜ ይህ ሁኔታ በጉልህ ተንጸባርቆ ነበር። አትሌቶች አበረታች መድኃኒቶች መውሰዳቸው በምርመራ እንዳይረጋገጥ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎች ፈልስፈዋል። ታይም መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው አንዳንድ ስፖርተኞች “‘የሌላን ሰው ሽንት እስከ ማዘዋወር’ ማለትም ሥቃይ የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ የሌላን ሰው ‘ንጹሕ’ ሽንት በካቴተር አማካኝነት ወደ ፊኛቸው ውስጥ እስከማስገባት” ደርሰዋል።

“ለመዝናናት” ተብሎ የሚወሰዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተከለከሉ መድኃኒቶችና ዕፆችም አሉ። ከእነዚህ መካከል ማሪዋና፣ ኤክስታሲ (ሜቲሊንዳይኦክሳይ-ሜትአምፌታሚን ወይም ኤም ዲ ኤም ኤ)፣ ኤል ኤስ ዲ (ላይሰርጂክ አሲድ ዳይኢትልአማይድ)፣ የሚያነቃቁ መድኃኒቶችና ዕፆች (እንደ ኮኬይንና አምፌታሚንስ ያሉ)፣ ድባቴ ውስጥ የሚከቱ መድኃኒቶችና ዕፆች (መንፈስን ለማረጋጋት ተብለው እንደሚወሰዱ መድኃኒቶች ያሉ) እና ሄሮይን ይገኙበታል። እንደ ማስቲሽና ቤንዚን ያሉ በብዙ ወጣቶች ዘንድ የተለመዱ በትንፋሽ የሚሳቡ ንጥረ ነገሮችም አሉ። እርግጥ ነው እነዚህ የሚሳቡ ንጥረ ነገሮች የታገዱ ካለመሆናቸውም በላይ እንደ ልብ የሚገኙ ናቸው።

የዕፅ ሱሰኛ ሁሉ ሰውነቱ የመነመነና በየኩሳንኩሱ የሚገኝ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ስህተት ሊሆን ይችላል። የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሱስ ያለባቸው በርካታ ሰዎች ሱሱ ይብዛም ይነስ በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ቢሆንም እንኳን አንጻራዊ በሆነ መንገድ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን መምራት ይችላሉ። ሆኖም የአደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መጥፎ ገጽታ አቅልለን መመልከት አንችልም። አንድ ጸሐፊ ኮኬይን የሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች “ገላቸው በመርፌ እስኪበሳሳ፣ በደም እስኪነከርና እስኪበልዝ ድረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየደጋገሙ ‘በደም ሥራቸው ዕፅ’ እንደሚወስዱ” ተናግረዋል።

በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ የተከለከሉ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ ከሄደ በኋላ በዓለም ዙሪያ እንደገና ማሻቀብ ጀምሯል። ኒውስዊክ መጽሔት እንዲህ ይላል:- “በድብቅ የሚገባው አደገኛ መድኃኒትና ዕፅ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ የየትኛውም ዕፅ ተጠቃሚዎች ማለት ይቻላል፣ ቁጥራቸው መበራከቱና ይህን ሁኔታ ለመዋጋት የሚያስችል ባጀትም ሆነ መረጃ አለመኖሩ ባለ ሥልጣናትን ግራ አጋብቷቸዋል።” በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ የሚታተመው ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው በመንግሥት አኃዛዊ መረጃ መሠረት “በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ የአልኮል መጠጥ ወይም የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሱሰኛ ነው።”

በተመድ የማኅበራዊ እድገት የምርምር ተቋም እንዳመለከተው “ዕፅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች . . . በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደራጁ ሲሆን ከዕፅ ንግድ የሚያገኙትን አብዛኛውን ገንዘብ ምሥጢራቸውን በሚጠብቁላቸውና ጥሩ የኢንቨስትመንት ትርፍ በሚያስገኙላቸው የገንዘብ ተቋማት ያስቀምጣሉ። . . . በአሁኑ ጊዜ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ያለ ማንም ተቆጣጣሪ ገንዘባቸውን በኮምፒውተር በዓለም ዙሪያ በማንቀሳቀስ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚያገኙትን ትርፍ ሕጋዊ አስመስለው መጠቀም ችለዋል።”

በርካታ አሜሪካውያን ሳይታወቃቸው በየቀኑ ከኮኬይን ጋር ንክኪ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ዲስከቨር በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው አብዛኞቹ የአሜሪካ የገንዘብ ኖቶች የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ብናኝ አለባቸው።

በዛሬው ጊዜ በሕግ የተከለከሉትን ጨምሮ መድኃኒቶችንና ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ የኑሮ ክፍል ሆኗል። የተከለከሉ መድኃኒቶችና ዕፆች እንዲሁም ሲጋራና የአልኮል መጠጥ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ በግልጽ እየታወቀ ሰዎች ያላግባብ የሚጠቀሙባቸው ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ በምንመለከትበት ጊዜ እግረ መንገዳችንንም እኛ ራሳችን ለእንዲህ ዓይነቶቹ ንጥረ ነገሮች ያለንን አመለካከት ብንመረምር ጥሩ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ‘በአንድ ጊዜ አምስት ወይም ከዚያ በላይ የሚጠጡ ወንዶችና አራት ወይም ከዚያ በላይ የሚጠጡ ሴቶች’ ጠጪ ሊባሉ ይችላሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጠጪነት በብዙ ኮሌጆች ውስጥ ትልቅ ችግር ሆኗል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች ሲጋራና “ለመዝናናት” ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶችና ዕፆች ጉዳት እንደሌላቸው አድርገው ያስባሉ