በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስልክ መስመሮች መገናኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

በስልክ መስመሮች መገናኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

በስልክ መስመሮች መገናኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጃፓን ከሕዝብ ብዛቷ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ስልክ እንዳላት የሚነገርላት ሲሆን በየቀኑ ከ300 ሚልዮን የሚበልጥ የስልክ ጥሪ ታስተናግዳለች። ጃፓን በየቀኑ አንድ ሚልዮን የሚደርስ ዓለም አቀፍ ጥሪ የምትቀበል ሲሆን ወደ ውጭ አገር የሚደወለውም ከዚህ ቁጥር የማይተናነስ ነው።

አንተም መደበኛ ወይም ተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም በየቀኑ ለማለት ይቻላል ስልክ ትደውል ይሆናል። ዓለም በሥልጣኔ እየተራቀቀ በሄደ መጠን ለብዙዎች በሌላ አህጉር ከሚኖር ሰው ጋር በስልክ መገናኘት የዕለት ተዕለት ተግባር እየሆነ መጥቷል። ይሁን እንጂ የአንተ የስልክ መስመር ከምትደውልለት ሰው የስልክ መስመር ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው ብለህ አስበህ ታውቃለህ?

በስልክ አውታረ መረብ መገናኘት

በመጀመሪያ የአንተ መስመር ከስልክ አውታረ መረብ (network) ጋር መገናኘት ይኖርበታል። ቤትህ ከሚገኘው መደበኛ ስልክ ጋር የተያያዘውን ሽቦ ተከትለህ ብትሄድ ወደ ቤትህ ከሚመጣው ሽቦ ጋር የሚያገናኘውን ሶኬት ወይም ትንሽ ሣጥን ታገኛለህ። * አሁንም ከዚያ የሚወጣውን ሽቦ ተከትለህ ብትሄድ የስልክህ ሽቦ በስልክ እንጨት ላይ ከሚገኝ ወይም መሬት ውስጥ ከተቀበረ ኬብል ጋር እንደተያያዘ ታስተውላለህ። ይህ ሽቦ ደግሞ በአካባቢህ ወደሚገኘው የስልክ ማዞሪያ ጣቢያ ያደርስሃል። ይህም የስልክ ማዞሪያ ጣቢያ ቢሆን ከሌላ ዋና ማዞሪያ ጣቢያ ጋር ተገናኝቷል። በዚህ መንገድ የስልክ አውታረ መረብ ይፈጥራል። ስለዚህ ባለህበት ከተማ ከሚኖር ሰው ጋር በስልክ በምትገናኝበት ጊዜ በአውታረ መረቡ አማካኝነት በአንተና በእርሱ ስልክ መካከል የድምፅ ዙር ይፈጠራል።

ስለ ተንቀሳቃሽ ስልኮችስ ምን ለማለት ይቻላል? የሚገናኙት እንዴት ነው? ይህም ቢሆን የሚሠራበት መንገድ ከመደበኛው ስልክ ጋር ተመሳሳይ ነው። የራዲዮ ሞገድ የሚባል አንድ የማይታይ “ሽቦ” የአንተን ተንቀሳቃሽ ስልክ በአቅራቢያህ ከሚገኝ የተንቀሳቃሽ ስልክ ማዞሪያ ጣቢያ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን ይህም ማዞሪያ ጣቢያ ከስልክ አውታረ መረብ ጋር ይገናኛል። ይሁን እንጂ በሌላ አህጉር ከሚኖር ሰው ጋር በምትነጋገርበት ጊዜስ?

ውቅያኖስ የሚያቋርጡ ኬብሎች

በውቅያኖስ የተከፈሉ ሁለት አህጉራትን በኬብል ማገናኘት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ይህም ባሕር ውስጥ የሚገኙ ገደላገደሎችንና ተራሮችን አቋርጦ የሚያልፍ በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ርዝመት ያለው ኬብል መዘርጋትን ይጠይቃል። የሆነ ሆኖ በአህጉራት መካከል የስልክ ግንኙነት ማድረግ የተጀመረው በዚህ መንገድ ነው። የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ የሚያልፈው የመጀመሪያው የስልክ ኬብል ተዘርግቶ የተጠናቀቀው በ1956 ነው። * ይህ መሥመር ስኮትላንድን ከኒውፋውንድላንድ የሚያገናኝ ሲሆን 36 የስልክ መስመሮችን የሚሸከም ነው። በ1964 ፓስፊክ ውቅያኖስን አቋርጦ የሚያልፍ ኬብል ለመጀመሪያ ጊዜ በጃፓን እና በሃዋይ መካከል ተዘረጋ። ይህ ኬብል 128 የስልክ መስመሮችን የሚሸከም ነበር። ከዚያም አህጉራትን እንዲሁም ደሴቶችን የሚያገናኙ በርካታ የባሕር ሥር ኬብሎች ተዘረጉ።

ስልኮችን ለማገናኘት ሲባል በባሕር ወለል ላይ የሚዘረጉት ኬብሎች ምን ዓይነት ናቸው? መጀመሪያ ላይ በውስጡ ኤሌክትሪክ የሚያስተላልፍ መዳብ ያለው ወልዘንግ (coaxial) ኬብል ወይም ከላዩ ኤሌክትሪክ የሚያስተላልፍ ሽፋን ያለው መዳብ ወይም አሉምንም ቅጠል (aluminium foil) በስፋት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። የመጨረሻው ወልዘንግ ኬብል የተዘረጋው በ1976 ሲሆን እስከ 4, 200 የሚደርስ የድምፅ ዙሮችን የመሸከም አቅም ነበረው። ይሁን እንጂ በ1980ዎቹ በቀጫጭን ሽቦዎች የሚሠራ ፋይበር ኦፕቲክ የሚባል ኬብል ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ። ይህ ዓይነቱ ኬብል ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት አህጉራት መካከል የተዘረጋው በ1988 ሲሆን ይህ መስመር በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት በአንድ ጊዜ 40, 000 የስልክ ጥሪዎችን የመሸከም አቅም ነበረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኬብሎቹ አቅም እየጨመረ እንዲሄድ ተደርጓል። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የተዘረጉ አንዳንድ ኬብሎች 200 ሚልዮን የስልክ መስመሮችን መሸከም ይችላሉ።

የስልክ ኬብሎች በባሕር ሥር የሚዘረጉት እንዴት ነው? እነዚህ ኬብሎች የሚዘረጉት በቀጥታ የውቅያኖሱን ወለል ተከትለው ነው። የባሕር ዳርቻው አካባቢ ሲደርስ በርቀት መቆጣጠሪያ በሚሠራ መቆፈሪያ መኪና በተዘጋጀ ጉድጓድ ውስጥ ጠንካራ መከለያ ተደርጎለት ይቀበራል። መከለያው ኬብሉ በመልሕቅ ወይም በዓሣ ማጥመጃ መረቦች ጉዳት እንዳይደርስበት ይከላከላል። ስለዚህ በሌላ አህጉር ለሚኖር ወዳጅህ በምትደውልበት ጊዜ ድምፅህ የሚያልፈው ከእነዚህ ኬብሎች መካከል በአንዱ ውስጥ ነው።

በዓይን የማይታዩ ኬብሎች የተራራቁ ቦታዎችን ያገናኛሉ

ሆኖም አህጉራትን እንዲሁም ደሴቶችን ማገናኘት የሚቻልበት መንገድ በባሕር ውስጥ የሚዘረጋ ኬብል ብቻ አይደሉም። በዓይን የማይታይ “ሽቦ” ማለትም ሬዲዮ ሞገድም በብዛት ይሠራበታል። ይህ ዓይነቱ ሞገድ (ማይክሮ ሞገድ በመባልም ይታወቃል) የተራራቁ ቦታዎችን በማገናኘት ዓለም አቀፍ የስልክ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል። ማይክሮ ሞገድ ልክ እንደ ብርሃን አመልማሎ በአንድ አቅጣጫ ቀጥ ብሎ የሚጓዝ በመሆኑ ሊያገናኝ የሚችለው በአንድ መሥመር ላይ የሚገኙ ትይዩ የሆኑ ቦታዎችን ብቻ ነው። የመሬት ገፅ ስንድቅ (curvature) በመሆኑ በተለያዩ የምድር ክፍል ላይ ያሉ በአንድ መሥመር ላይ የሚገኙ ቦታዎችን በቀጥታ ማገናኘት አይቻልም። በጣም ተራርቀው የሚገኙ እንዲህ ያሉ ቦታዎችን ለማገናኘት የሳተላይት ግንኙነት ያስፈልጋል።

አንዲት ሳተላይት በምድር ወገብ ላይ ከመሬት 35, 800 ኪሎ ሜትር ከፍ ብላ ምድረ ቋሚ ምህዋር (geostationary orbit) በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ ብትቀመጥ ምድርን ለመዞር የሚወስድባት ጊዜ 24 ሰዓት ገደማ ይሆናል። ይህ ደግሞ ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ ለመሽከርከር ከሚወስድባት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህም ምክንያት ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል ያለችበትን ቦታ ሳትለቅ ትቆያለች። ይህች ሳተላይት አንድ አራተኛ የሚሆነውን የምድር ክፍል መሸፈን ስለምትችል በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙ ማይክሮ ሞገድ የሚያሰራጩና የሚቀበሉ የምድር ጣቢያዎች ከሳተላይቷ ጋር መገናኘት ይችላሉ። ታዲያ በጣም ተራርቀው የሚገኙ ሁለት ቦታዎች በሳተላይት አማካኝነት ሊገናኙ የሚችሉት እንዴት ነው?

አንዲት ሳተላይት በምትሸፍነው ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ የምድር ጣቢያ ወደ ሳተላይቷ ማይክሮ ሞገድ ያሰራጫል። ይህም ከምድር ጣቢያ ወደ ሳተላይት የሚደረግ ግንኙነት (uplink) ተብሎ ይጠራል። በሳተላይቷ ላይ የሚገጠመው ራዲዮ መላሽ ወይም ራዳር ድግግሞሹን (frequency) ወደታች ዝቅ በማድረግ የተቀበለውን ሞገድ መልሶ ምድር ላይ ወደሚገኝ ሌላ ጣቢያ ይልከዋል። ይህም ከሳተላይት ወደ ምድር ጣቢያ የሚደረግ ግንኙነት (downlink) ይባላል። እርስ በርሳቸው በቀጥታ መገናኘት የማይችሉ ሁለት የምድር ጣቢያዎች በሳተላይት አማካኝነት በዓይን በማይታይ ሽቦ በዚህ መንገድ ሊገናኙ ይችላሉ።

የመጀመሪያዋ የንግድ የመገናኛ ሳተላይት ማለትም ኢንቴልሳት 1 (ኧርሊ በርድ በመባልም ትታወቃለች) ወደ ጠፈር የመጠቀችው በ1965 ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደ 200 የሚጠጉ የመገናኛ ሳተላይቶች ያሉ ሲሆን (ብዙዎቹ በምድር ወገብ አናት ላይ የሚገኙ ናቸው) ሁሉም በመላው ምድር ላይ የሚገኙ ቦታዎችን በማገናኘት ይሠራሉ። የእነዚህ ሳተላይቶች ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስልክ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለቴሌቪዥን ስርጭት፣ ለአየር ሁኔታ ትንበያና ለሌሎች ዓላማዎችም ያገለግላሉ። እነዚህ ሳተላይቶች በርካታ ራዳሮች ስላሏቸው የተለያዩ ስርጭቶችን ማስተናገድ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኧርሊ በርድ የምትባለው ሳተላይት በአንድ ጊዜ አንድ የቴሌቪዥን ስርጭትና 240 የስልክ መስመሮችን የማስተናገድ አቅም ነበራት። በ1997 ሥራ የጀመረችው ኢንቴልሳት ተራ ቁጥር VIII ሳተላይት በአንድ ጊዜ ሦስት የቴሌቪዥን ሥርጭቶችንና 112, 500 የሚሆኑ የስልክ መስመሮችን ማስተናገድ ትችላለች።

የተገናኘኸው በየትኛው እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ?

እነዚህ ለውጦች ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪ ዋጋ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርገዋል። ምናልባትም አሁን በሌላ አህጉር ከሚገኝ ወዳጅህ ወይም የቤተሰብ አባልህ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ በስልክ የመነጋገር አጋጣሚ አግኝተህ ይሆናል። ይሁን እንጂ የተገናኘኸው በባሕር ውስጥ በተዘረጋ ኬብል ይሁን ወይም በሳተላይት አማካኝነት እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

ከሳተላይት ጋር የሚያገናኘው በዓይን የማይታየው ሽቦ (ከምድር ወደ መንኮራኩርም ሆነ ከመንኮራኩር ወደ ምድር የሚደረገውን ግንኙነት ጨምሮ) 70, 000 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚደርስ ርዝማኔ አለው። ይህም የምድርን ዙሪያ ሁለት እጥፍ አካባቢ ማለት ነው። ምንም እንኳ ማይክሮ ሞገዶች የብርሃን ብልጭታ ከሚጓዝበት ፍጥነት ጋር በሚመጣጠን ፍጥነት የሚጓዙ ቢሆኑም በሳተላይት አማካኝነት ከአንድ የምድር ጣቢያ ወደ ሌላኛው የምድር ጣቢያ ለመድረስ የአንድ ሴኮንድ አንድ አራተኛ ጊዜ ይፈጅባቸዋል። ይህም ድምፅህ የምታነጋግረው ሰው ጋር ለመድረስ አንድ አራተኛ ሴኮንድ ይወስድበታል ማለት ነው። ወደ አንተም ለመድረስ የሚወስደው ጊዜ ተመሳሳይ ነው። በዚህም የተነሳ የግማሽ ሴኮንድ ልዩነት ይፈጠራል ማለት ነው። በየዕለቱ ከሰዎች ጋር በምናወራበት ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ ስለማይፈጠር ከላይ በተገለጸው መንገድ በስልክ ስታወራ ሳይታወቅህ እኩል መናገር ልትጀምር ትችላለህ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ እየተነጋገርክ ያለኸው በሳተላይት መገናኛ አማካኝነት መሆኑን ሊጠቁም ይችላል። ይሁን እንጂ በሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ቁጥር ተጠቅመህ ስትደውል በመካከላችሁ ምንም ዓይነት የጊዜ ልዩነት አያጋጥምህ ይሆናል። ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባት የተገናኛችሁት ባሕር ውስጥ በተዘረጋ ኬብል ሊሆን ስለሚችል ነው። በሌላ የዓለም ክፍል ከሚኖር ሰው ጋር በየትኛው መሥመር መገናኘት እንዳለብህ የሚወስነው ውስብስብ የሆነው መሣሪያ የስልክ አውታረ መረብ ነው።

የባሕር ውስጥ ኬብልን፣ የምድር ጣቢያንና ሳተላይትን ጨምሮ ያለ ምንም ችግር ከሌሎች ጋር በስልክ መገናኘት የሚያስችለንን ውስብስብ የቴሌፎን አውታረ መረብ ለማዘጋጀት ከፍተኛ እውቀትና ጉልበት ይጠይቃል። ስለዚህ ሌላ ጊዜ ለወዳጅህ ስልክ ስትደውል አንተን በዚህ መንገድ ለማገናኘት ሲባል የተደረገውን ሁሉ ለምን ለአንድ አፍታ አታስብም?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በስልክ ሽቦ ውስጥ የተወሰነ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ዥረት ያለ ሲሆን ስልኩ በሚጠራበት ጊዜ ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሚጨምር ከስልኩ ጋር የተገናኘውን ትንሽ ሳጥን ውስጠኛ ክፍል ወይም ከእርሱ ጋር የተገናኙትን ብረት ነክ ክፍሎች መንካት አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

^ አን.9 በ1866 በአየርላንድ እና በኒውፋውንድላንድ መካከል አትላንቲክን አቋርጦ የሚያልፍ አንድ የቴሌግራፍ ኬብል በተሳካ ሁኔታ ተዘርግቷል።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ራዲዮ ሞገድ

ከምድር ጣቢያ ወደ ሳተላይት የሚደረግ ግንኙነት

ከሳተላይት ወደ ምድር ጣቢያ የሚደረግ ግንኙነት

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ባሕር ውስጥ የተዘረጉ ኬብሎች

ተንቀሳቃሽ ስልክ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘመናዊ የሆኑት ቀጫጭን ኬብሎች እስከ 200 የሚደርሱ የስልክ መስመሮችን ማስተናገድ ይችላሉ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢንቴልሳት VI በጠፈር መንኮራኩር ሠራተኞች እንድትሠራ ስትደረግ

[ምንጭ]

NASA photo

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኬብሎችን የሚዘረጉና የሚጠግኑ መርከቦች

[ምንጭ]

Courtesy TyCom Ltd.