በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቢራቢሮዎች፣ በዕፅዋትና በጉንዳኖች መካከል ያለ ወሳኝ ትስስር

በቢራቢሮዎች፣ በዕፅዋትና በጉንዳኖች መካከል ያለ ወሳኝ ትስስር

በቢራቢሮዎች፣ በዕፅዋትና በጉንዳኖች መካከል ያለ ወሳኝ ትስስር

ኔዘርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የሐምሌ ወር ሲገባ በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ ለመንካት የሚያሳሱ ሰማያዊ ቢራቢሮዎች ዘሮቻቸውን ለመተካት ዝግጅት ያደርጋሉ። ሆኖም ቢራቢሮዎቹ ይህን ለማከናወን ተጓዳኝ ብቻ ሳይሆን ሌላም የሚያስፈልጋቸው ነገር አለ። ጄንቺያን የተባሉ ሰማያዊ አበቦች የሚያወጡ ዕፅዋትና የተራቡ ቀይ ጉንዳኖች የሚሰጡትን አገልግሎት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ለምን? ዕፅዋትና ጉንዳኖች በእነዚህ ቢራቢሮዎች የሕይወት ዑደት ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

በኔዘርላንድ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው የድዊንግኤልደርቬልድ ብሔራዊ ፓርክ እንዲህ ያለውን ትኩረት የሚስብ የሦስት ወገን ትስስር ማየት ከሚቻልባቸው ቦታዎች አንዱ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰማያዊ ቢራቢሮዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ። በጸደይና በበጋ ወራት ሰማያዊ አበባ ያላቸውን የጄንቺያን ዕፅዋት፣ ሐምራዊ አበባ ያላቸውን የሂዘር ዕፅዋትና ቢጫ አበባ ያላቸውን የአስፎዴል ዕፅዋት ጨምሮ በተለያዩ አበቦች ያሸበረቁ በርካታ ዕፅዋት የድዊንግኤልደርቬልድን ሜዳዎች እንደ ምንጣፍ ያለብሷቸዋል። ሰማያዊ ቢራቢሮዎችን ይበልጥ የሚስቧቸው የሂዘር እና የጄንቺያን ውብ አበቦች ሲሆኑ ለዚህም ሁለት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። የሂዘር አበቦች ለምግብነት የሚያገለግል ጣፋጭ ያበባ ማር የሚያመነጩ ሲሆን የጄንቺያን አበቦች ደግሞ እንደ ማከማቻ ሆነው ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ ቢራቢሮዎቹ እዚህ የሚያስቀምጡት ምንድን ነው?

ራስን ለማዳን የሚወሰድ እርምጃ

የተዋስቦ (mating) ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ሴቷ ቢራቢሮ በአካባቢው ካሉት ዕፅዋት ሁሉ ረዘም ብሎ የሚታይ የጄንቺያን ተክል ለማግኘት ፍለጋ ታደርጋለች። ቢራቢሮዋ አበባው ላይ ካረፈች በኋላ ጥቂት ነጫጭ እንቁላሎች ትጥላለች። በአራትና በአሥር ቀናት ውስጥ እንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ። ከሁለት እስከ ስድስት የሚደርሱ ትናንሽ አባጨጓሬዎች የአበባውን ቀንበጥ ቦርቡረው ወደ ውስጥ ይገባሉ። ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ለሚደርስ ጊዜ ያለ ማቋረጥ ከተመገቡ በኋላ ወደ መሬት ይወርዳሉ።

የሚያስገርመው ግን አብዛኛውን ጊዜ አባጨጓሬው ወደ መሬት የሚወርደው ምሽት ላይ ነው። በዚያው ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ዓይነት የቀይ ጉንዳን ዝርያዎች ምግብ ፍለጋ ከመኖሪያቸው የሚወጡት ምሽት ላይ በመሆኑ ይህን የሚያደርገው ሆነ ብሎ ነው። አባጨጓሬው እነዚህ ምግብ ፍለጋ የወጡ ጉንዳኖች የሚጓዙበትን መንገድ ዘግቶ ይጠብቃቸዋል። አባጨጓሬው ለመሞት ካልሆነ በስተቀር ወደዚህ ቦታ ምን አስኬደው እንል ይሆናል። ሆኖም ይህ ራሱን ለማዳን ሲል ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ ነው። ታዲያ ቀጥሎ ምን ይሆናል?

ብዙም ሳይቆይ ቀይ ጉንዳኖቹ መንገድ ከዘጋባቸው አባጨጓሬ ጋር ይላተማሉ። ከዚያም ወዲያው አባጨጓሬውን እየጎተቱ ወደ መኖሪያቸው ይወስዱታል። አባጨጓሬው መኖሪያቸው ውስጥ ከገባ በኋላ እንደ ተከበረ እንግዳ ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግለታል። በደንብ እየተመገበ ደልቶትና ተመችቶት የበልጉን፣ የክረምቱንና የጸደዩን ወራት እዚያው ያሳልፋል። ምንም እንኳ አባጨጓሬው የሚያማርጣቸው በርካታ የምግብ ዓይነቶች ባይኖሩትም አንዳንድ የጉንዳን እጮችንና ሠራተኛ ጉንዳኖቹ ዕጮቹን ለመመገብ ሲሉ የሚያቀረሹትን ምግብ ይመገባል። ጉንዳኖቹም ቢሆኑ የሚያገኙት ጥቅም አለ። ከአባጨጓሬው የሚወጣውን ጣፋጭ ፈሳሽ ይመገባሉ። አባጨጓሬው ዕድገቱን ጨርሶ ወደ ሙሽሬነት ከተሸጋገረ በኋላም እንኳ ጉንዳኖቹ የሚወዱትን ይህን ጣፋጭ ፈሳሽም ሆነ ሌላ ምግብ መስጠቱን አያቆምም። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው አብሮ የመኖር ሁኔታ የሚያበቃበት ጊዜ ይቃረባል።

ከእንግድነት ወደ ጠላትነት

በሙሽሬነት ደረጃ ላይ የሚገኘው አባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮነት መለወጥ ይጀምራል። ሙሉ በሙሉ ከተለወጠ በኋላ ሙሽሬው ለሁለት ይከፈልና ቢራቢሮ ይወጣል። ብዙውን ጊዜ ይህ ሂደት የሚከናወነው ማለዳ ላይ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጉንዳኖቹ ማለዳ ላይ ንቁ ስለማይሆኑና በዚህ ወቅት አባጨጓሬው ከአበባው ወደ መሬት ሲወርድ ካደረገው ነገር በተለየ ሁኔታ የጉንዳኖቹን ትኩረት ከመሳብ መቆጠብ ያለበት በመሆኑ ነው።

ጉንዳኖቹ እንደለመዱት ከሙሽሬው የሚወጣውን ፈሳሽ ለመመገብ በሚመጡበት ጊዜ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከዚያ ቀደም አይተውት የማያውቁት ክንፍ ያለው እንግዳ ፍጥረት ሲመለከቱ በጣም ይደነግጣሉ። ከዚያም ወዲያው ጥቃት መሰንዘር ይጀምራሉ። ወደ ቢራቢሮነት የተለወጠው አባጨጓሬ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ክንፉንና ሕይወቱን ለማትረፍ ከጉንዳኖቹ መኖሪያ ቤት ተፈትልኮ ይወጣል። መኖሪያቸውን ከለቀቀ በኋላ አንድ ቀንበጥ ላይ ይወጣል። ጉንዳኖቹም ማሳደዳቸውን አቁመው ይመለሳሉ።

ቢራቢሮው የሚያስተማምን ከፍታ ላይ ከወጣ በኋላ ክንፎቹን ዘርግቶ ማድረቅ ይጀምራል። ከዚያም ሕይወት ካገኘ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ መሆኑ ነው፣ ወሳኝ የሆነ አንድ ነገር ይከናወናል። ቢራቢሮው ለመጀመሪያ ጊዜ ክንፎቹን ያርገበግብና በአበቦቹ አናት ላይ እያንጃበበ ጉዞውን ይቀጥላል! ከጥቂት ቀናት በኋላ ሴቷ ቢራቢሮ እንቁላሏን ለመጣል ሰማያዊ አበባ ያለውን ረዘም ያለ የጄንቺያን ተክል መፈለግ ትጀምራለች። ቀጣዩን ትውልድ ለመተካት ዝግጅት የሚደረግበት ጊዜ ደርሷልና።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋል

የሰማያዊው ቢራቢሮ ኑሮ የተመሠረተው በዕፅዋት በተሸፈነ ሜዳማ አካባቢ ላይ ነው። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በምዕራብ አውሮፓ ሰዎች ጥንታዊ ደኖችን በመጨፍጨፋቸው እንዲህ ያሉ ሜዳማ አካባቢዎች ተፈጥረዋል። ባለፉት ዘመናት የቤልጅየም፣ የጀርመንና የኔዘርላንድ ሰፋፊ ሜዳማ ቦታዎች ወይን ጠጅ አበባ በሚያወጡ ዕፅዋት የተሸፈኑ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህ ሥፍራዎች እየተመናመኑ ሄደዋል። በዚህም የተነሳ የሰማያዊ ቢራቢሮ ሕልውና አደጋ ላይ ወድቋል። ቀደም ሲል ይህ ቢራቢሮ በኔዘርላንድ በ136 ተፈጥሯዊ መኖሪያዎች ይገኝ የነበረ ሲሆን ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ግን ከ57ቱ መኖሪያዎች ጠፍቷል። እንዲያውም ሕልውናው በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ስሙ ሊጠፉ የተቃረቡ የቢራቢሮ ዝርያዎችን ስም ዝርዝር የሚመዘግበው የአውሮፓ ምክር ቤት ባጠናቀረውና ዘራቸው ሊጠፋ የተቃረቡ የቢራቢሮ ዝርያዎች በሰፈሩበት ሰነድ ላይ እንዲካተት ተደርጓል።

የድዊንግኤልደርቬልድ ብሔራዊ ፓርክ ለሰማያዊው ቢራቢሮ ምቹ መኖሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የፓርኩ ጠባቂዎች ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የነበሩ ገበሬዎች ይከተሉት የነበረውን የግብርና ዘዴ በመጠቀም በዕፅዋት የተሸፈነውን ይህን ሥፍራ እየተንከባከቡ ነው። እንደ ቀድሞው ሁሉ እረኞች በጎቻቸውን በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚያሰማሩ ሲሆን ከብቶች ደግሞ ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ሳር በበቀለበት ሜዳ ላይ ይሰማራሉ። በጎቹና ከብቶቹ ሜዳውን በማጥራት መሬቱን ለሂዘር እና ለሌሎች ተክሎች የተመቻቸ ያደርጉታል። (በአሁኑ ጊዜ 580 የሚደርስ ዝርያ ያላቸው ተክሎች በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ።) በዚህም የተነሳ በድዊንግኤልደርቬልድ የሚገኙ ሰማያዊ ቢራቢሮዎች ቁጥራቸው በማደግ ላይ ይገኛል። እንዲያውም ይህ በአውሮፓ በትልቅነቱና በስፋቱ ግንባር ቀደም የሆነው የሂዝ ዕፅዋት ፓርክ በጥቅሉ ለቢራቢሮዎች ምቹ መኖሪያ በመሆኑ የተነሳ በኔዘርላንድ ከሚገኙት የቢራቢሮ ዝርያዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑትን በዚህ ፓርክ ውስጥ ማየት ይቻላል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንዲት ቢራቢሮ ሰማያዊ አበባ ወደሚያወጣው የጄንቺያን ተክል በመብረር እንቁላሎቿን ታስቀምጣለች

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀይ ጉንዳኖች ሙሽሬውን ሲንከባከቡ

[ምንጭ]

ገጽ 20 እና ገጽ 21 ላይ የሚገኙት ጉንዳኖች:- Pictures by David Nash; www.zi.ku.dk/personal/drnash/atta/

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐምራዊ ቦግ ሂዘር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቢጫ ቦግ አስፎዴል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የቢራቢሮው መኖሪያ እንደ ቀድሞው ምቹ እንዲሆን ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት በጎችና ከብቶች የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ