አምላክ ጸሎቴን ይሰማልን?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች...
አምላክ ጸሎቴን ይሰማልን?
“ይሖዋ ጓደኛዬ ስለሆነ ሁሉንም ነገር በጸሎት እነግረዋለሁ። ችግር ከገጠመኝ እንደሚረዳኝ አውቃለሁ።”—አንድሬያ
ወጣቷ አንድሬያ አምላክ ጸሎቷን እንደሚሰማ እርግጠኛ ናት። ሆኖም እንዲህ የሚሰማቸው ሁሉም ወጣቶች አይደሉም። አንዳንዶች አምላክ ሩቅ እንደሆነና ፈጽሞ ሊቀርቡት እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲያውም አምላክ ለእነርሱ የሚያስብላቸው ሆኖ ስለማይሰማቸው ለመጸለይ አይገፋፉም።
ለጸሎት ቁልፍ የሆነው ነገር ምንድን ነው? በቀላል አነጋገር ከአምላክ ጋር እውነተኛ ወዳጅነት መመሥረት ነው። መዝሙራዊው “ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 9:10) አንተስ? አምላክን ምን ያህል ታውቀዋለህ? ስለ እርሱ ያለህስ እውቀት ጸሎትህን እንደሚሰማ ለማመን የሚያስችል ነውን? እባክህ ንባብህን ከመቀጠልህ በፊት “አምላክን ምን ያህል ታውቀዋለህ?” በሚለው ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር። ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉን ለመመለስ ትችላለህ?
አምላክን ምን ያህል ታውቀዋለህ? መልሶቹ ገጽ 19 ላይ ይገኛሉ።
1. የአምላክ ስም ማን ነው? ትርጉሙስ ምንድን ነው?
2. መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጻቸው አራቱ የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት ምንድን ናቸው?
3. አምላክ ለሰው ልጆች ያሳየው የላቀ የፍቅር መግለጫ ምንድን ነው?
4. ከአምላክ ጋር መወዳጀት የምንችለው እንዴት ነው?
5. በምንጸልይበት ጊዜ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?
የሚቀጥሉትን አንቀጾች ከማንበብህ በፊት ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ትችል ይሆን? መመለስ ከቻልክ ከብዙ ሰዎች በተሻለ መንገድ አምላክን ታውቀዋለህ ማለት ነው። ሆኖም መልሶችህ ስለ እርሱ ይበልጥ ማወቅና ወደ እርሱ ይበልጥ መቅረብ እንደሚኖርብህ የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዮሐንስ 17:3) ይህንን ግብ በአእምሮህ በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጸሎት ሰሚ’ ስለሆነው አምላክ ምን እንደሚያስተምረን ተመልከት።—መዝሙር 65:2
አምላክ እውን አካል አለው
በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የተወሰነ አካል የሌለው ኃይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ የተባለ ስም ያለው አካል ነው። (መዝሙር 83:18 NW ) በዕብራይስጥ ይህ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ያሳያል። የተወሰነ አካል የሌለው እንዲሁ የታመቀ ኃይል ይህንን ሊያደርግ አይችልም! ስለዚህ በምትጸልይበት ጊዜ ረቂቅ ለሆነ አንድ ኃይል ወይም እንዲሁ ለአየር እየተናገርክ እንዳልሆነ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። እየተናገርክ ያለኸው ጸሎትህን ሊሰማና ምላሽ ሊሰጥህ ከሚችል አካል ጋር ነው።—ኤፌሶን 3:20
ወጣቷ ዲያና “የትም ቦታ ብሆን ይሖዋ እንደሚሰማኝ አውቃለሁ” ብላለች። እንዲህ ያለው የእርግጠኝነት ስሜት እንዲኖርህ ከፈለግህ አምላክ እውን ሊሆንልህ ይገባል! መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ . . . ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” በማለት ይናገራል።—የጥበብና የኃይል ምንጭ
አምላክ ታላቅ ኃይል ያለው በመሆኑ በእርግጥ ሊረዳን ይችላል። ግዙፍና ውስብስብ ከሆነው አጽናፈ ዓለም መረዳት እንደሚቻለው ኃይሉ ገደብ የለውም። ይሖዋ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩትን ከዋክብት በሙሉ በስም እንደሚያውቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል! ከዚህም በላይ በእነዚህ ከዋክብት ውስጥ የታመቀው ኃይል ሁሉ ምንጭ እርሱ ነው። (ኢሳይያስ 40:25, 26) ይህ አስደናቂ አይደለምን? እነዚህ እውነታዎች የቱንም ያህል አስደናቂ ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የኃይሉ ‘ጥቂቱ ብቻ’ እንደሆነ ይናገራል!—ኢዮብ 26:14 የ1980 ትርጉም
የይሖዋን ገደብ የለሽ ጥበብም ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦቹ “እጅግ ጥልቅ” እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 92:5) የሰውን ዘር የፈጠረው እርሱ ስለሆነ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው የበለጠ ያውቀናል። (መዝሙር 100:3) አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖር በመሆኑ ተሞክሮው ገደብ የለውም። (መዝሙር 90:1, 2) ከእርሱ ማስተዋል ውጪ የሆነ አንድም ነገር የለም።—ኢሳይያስ 40:13, 14
ይሖዋ ይህን ሁሉ ኃይሉንና ጥበቡን የሚጠቀመው እንዴት ነው? ሁለተኛ ዜና 16:9 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ።” በቀላል አነጋገር አምላክ ሊፈታውም ሆነ እንድትቋቋመው ሊረዳህ የማይችለው ምንም ዓይነት ችግር የለም። ወጣቷ ካይላ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በቅርቡ እኔና ቤተሰቤ ከባድ ችግር ላይ ወድቀን በነበርንበት ጊዜ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። እርሱም የደረሰብንን ችግር እንድንወጣ የሚያስችል ኃይል እንደሰጠን ሆኖ ይሰማኛል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ችግሩን ፈጽሞ መቋቋም አንችልም ነበር።” አምላክን በጸሎት ስታነጋግር የጥበብ ሁሉ ምንጭ ወደ ሆነው አካል ዞር አልክ ማለት ነው። ከዚህ የተሻለ ምንም ልታደርግ አትችልም!
የፍትሕና የፍቅር አምላክ
ይሁን እንጂ አምላክ ሊረዳህ እንደሚፈልግ እንዴት ታውቃለህ? ይሖዋ ራሱን ማሳወቅ የፈለገው በታላቅ ኃይሉ፣ በጥልቅ ጥበቡ ወይም በማያወላውል ፍትሑ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በዋነኛነት የሚታወቀው በፍቅር ባሕርዩ ነው። አንደኛ ዮሐንስ 4:8 “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት ይናገራል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲህ ያለው ታላቅ ፍቅር ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ይሆነናል። ከሁሉ የላቀው የፍቅሩ መግለጫ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል አንድያ ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱ ነው።—ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10
አምላክ ፍቅር ስለሆነ ችላ ይለኛል ወይም ደግሞ ፍትህ በጎደለው መንገድ ይይዘኛል ብለህ ፈጽሞ መፍራት አይኖርብህም። ዘዳግም 32:4 “መንገዱ ሁሉ የቀና [“ፍትሕ፣” NW ] ነው” በማለት ይናገራል። አምላክ ለአንተ ያለው ፍቅር ጸሎትህን ልብ ብሎ እንደሚያዳምጥ ማረጋገጫ ይሰጥሃል። ይህን ማወቃችን የውስጥ ሐሳባችንንና ስሜታችንን በልበ ሙሉነት ግልጥልጥ አድርገን እንድንነግረው ይገፋፋናል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ከአምላክ ጋር መወዳጀት
በእርግጥም ይሖዋ ከእርሱ ጋር እንድንነጋገር ይጋብዘናል። ለእኛ እንግዳ እንዲሆንብን አይፈልግም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ በሰው ልጅ ታሪክ በሙሉ ሰዎች ወዳጆቹ እንዲሆኑ ሲጋብዝ ቆይቷል። ለልቡ ተስማሚ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዲሁም አዋቂዎች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት የመሠረቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብርሃም፣ ንጉሥ ዳዊትና የኢየሱስ እናት ማርያም ይገኙበታል።—ኢሳይያስ 41:8፤ ሉቃስ 1:26-38፤ ሥራ 13:22
አንተም የይሖዋ ወዳጅ መሆን ትችላለህ። እርግጥ እንዲህ ያለውን ወዳጅነት መመሥረት ማለት አምላክን የምትፈልገው ነገር ሲኖር ወይም ችግር ሲያጋጥምህ ብቻ እንደምትለማመነው መንፈስ አድርገህ መመልከት ይኖርብሃል ማለት አይደለም። ጸሎቶቻችን በምንፈልጋቸው ነገሮች ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥኑ መሆን የለባቸውም። የአምላክን ወዳጅነት የምንፈልግ ከሆነ በራሳችን ፍላጎት ላይ ከማተኮር ይልቅ የእርሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅና በተግባር ለማዋል መጣር አለብን። (ማቴዎስ 7:21) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሲጸልዩ በአምላክ ዘንድ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው። እንዲህ አለ:- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) በተጨማሪም ጸሎታችን ለአምላክ በሚቀርቡ ውዳሴዎችና ምስጋናዎች የተሞላ መሆን ይኖርበታል!—መዝሙር 56:12፤ 150:6
ሆኖም የሚያስፈልጉን ወይም የሚያስጨንቁን ነገሮች አነስተኛ ወይም ጥቃቅን እንደሆኑ አድርገን በማሰብ በጸሎታችን ውስጥ ፈጽሞ ልንጠቅሳቸው አይገባም ማለት አይደለም። ስቲቭ “በጸሎቴ ግልጽ ለመሆን ብሞክርም አንዳንዴ ግን በረባው ባልረባው አምላክን ለምን አስቸግረዋለሁ ብዬ አስባለሁ” በማለት ተናግሯል። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ሲሰማህ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ለማስታወስ ሞክር:- “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። . . . እንግዲያስ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።” (ሉቃስ 12:6, 7) ይህ የሚያጽናና አይደለም?
እንግዲያው ይሖዋን ይበልጥ እያወቅከው በሄድክ መጠን በጸሎት ወደ እርሱ ለመቅረብ ይበልጥ እንደምትገፋፋና ይሖዋ ሊረዳህ እንደሚችል እንዲሁም እንደሚረዳህ ያለህ ትምክህት ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። ታዲያ ወደ አምላክ በጸሎት ስትቀርብ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖርህ ይገባል? አክብሮት፣ ትሕትናና ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ስሜት ሊኖርህ ይገባል። ከፍተኛ ሥልጣን ያለውን አንድ ሰው በኩራት ወይም አክብሮት በጎደለው መንገድ ለማነጋገር ብትሞክር የሚሰማህ ይመስልሃል? ይሖዋም ለጸሎትህ መልስ ከመስጠቱ በፊት ለእርሱና ለአቋም ደረጃዎቹ አክብሮት እንድታሳይ ቢጠብቅብህ ሊያስገርምህ አይገባም።—ምሳሌ 15:29
በሺህ የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች ልባቸውን ለአምላክ ማፍሰስን ተምረዋል። (መዝሙር 62:8) ብሬት “ይሖዋ ለጸሎቴ መልስ ሲሰጠኝ አሁንም ወዳጄ እንደሆነ ስለሚሰማኝ እበረታታለሁ” በማለት ተናግሯል። አንተስ? ከአምላክ ጋር ይህን የመሰለ ወዳጅነት መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው? ሁለት ክርስቲያን ወጣቶች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:-
ራሄል:- “ከይሖዋ ጋር ለመቀራረብ ቃሉን በጥልቅ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ይሰማኛል። እንዲህ ላለው ጥናት ጉጉት ለማዳበር እየጣርኩ ነው።”—1 ጴጥሮስ 2:2
ጄኒ:- “በአገልግሎቱ ይበልጥ በተሳተፍህ መጠን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረብክ ሆኖ ይሰማሃል።”—ያዕቆብ 4:8
መጸለይ ምን ያህል ጥቅም ያስገኛል ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አንዲት ክርስቲያን ወጣት የሚከተለውን ብላለች:- “አምላክ በቀጥታ ቢያነጋግረኝ ወይም መልእክት ቢልክልኝ ኖሮ ወደ እርሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።” በምንጸልይበት ጊዜ ይሖዋ በድምፅ አይመልስልንም። ታዲያ ጸሎት በእርግጥ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው እትም ይብራራል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በገጽ 17 ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች
1. ይሖዋ። ትርጉሙ “እንዲሆን ያደርጋል።”
2. ፍቅር፣ ኃይል፣ ፍትሕ ጥበብ።
3. ለእኛ ሲል እንዲሞት አንድያ ልጁን ኢየሱስን ልኳል።
4. በሚያስፈልጉን ነገሮች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በአምላክ ፈቃድና ፈቃዱን በማድረግ ላይ ማተኮር።
5. ትህትና፣ አክብሮትና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ስሜት ሊኖረን ይገባል።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ከፍጥረት መማር አምላክን ይበልጥ እንድታውቀው ይረዳሃል