በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሱስ መላቀቅ ይቻላል!

ከሱስ መላቀቅ ይቻላል!

ከሱስ መላቀቅ ይቻላል!

“በወይን ጠርሙሶች ውስጥ በድብቅ ለማስገባት የተሞከረ ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን ተገኘ።” አንድ ጋዜጣ በዚህ ርዕስ ሥር ያወጣው ዘገባ በደቡብ አፍሪካ፣ የጆሃንስበርግ ፖሊሶች ከደቡብ አሜሪካ በመርከብ ተጭኖ የመጣ 11, 600 የወይን ጠርሙሶች የያዘ አንድ ኮንቴይነር እንዴት እንደያዙ ገልጿል። በወይኑ ውስጥ ከ150 እስከ 180 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን ተቀላቅሏል። ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን ወደ አገሪቱ በድብቅ ለማስገባት ሲሞከር ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ይታመናል።

ይህ ግኝት አበረታች ቢሆንም እውነታው ግን በዓለም ዙሪያ ከሚዘዋወሩት ሕጋዊ ያልሆኑ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች መካከል ፖሊስ የሚይዘው ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሆነ ይገመታል። ይህ ሁኔታ ቶሎ ቶሎ የሚፈላን አደገኛ አረም ከላይ ከላይ ብቻ እያረመ ሥሩን ከሚተው አትክልተኛ ጋር ሊመሳሰል ይችላል።

ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ትርፍ መንግሥታት ምርቱንና ሽያጩን ለመግታት በሚያደርጉት ጥረት ላይ መሰናክል ፈጥሯል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ በብዙ ቢልዮን ዶላር የሚገመት የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ንግድ ይካሄዳል። እንዲህ ያለውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ስንመለከት ፖሊስና የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሌላው ቀርቶ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ሳይቀሩ ለሙስና መጋለጣቸው አያስደንቀንም።

ዘ ጋርዲያን የተባለው ሳምንታዊ ጋዜጣ ዘጋቢ የሆኑት አሌክስ ቤሎስ ከብራዚል እንደዘገቡት ፓርላሜንቱ ባደረገው ምርመራ መሠረት “በብራዚል በቡድን በተደራጀ የወንጀል ድርጊትና በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ንግድ ተጠላልፈዋል ተብለው ስማቸው ከተያዘው ከ800 የሚበልጡ ሰዎች መካከል . . . ሦስት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት፣ 12 የተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሦስት ከንቲባዎች ይገኙበታል።” ከዚህም በተጨማሪ በስም ዝርዝሩ ላይ “ብራዚል ውስጥ ካሉት 27 ግዛቶች መካከል በአሥራ ሰባቱ የሚኖሩ ፖሊሶች፣ ዳኞች፣ ነጋዴዎችና ገበሬዎች ስም” ሰፍሮ ይገኛል። በብራዚሊያ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ አንድ የፖለቲካ ፕሮፌሰር ይህንን ግኝት በማስመልከት ሲናገሩ “ችግሩ በብራዚል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍሎች እንደነካ የሚያሳይ ነው” ብለዋል። አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በስፋት በተሰራጩባቸው በሌሎች በርካታ ኅብረተሰቦች ውስጥም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ከአቅርቦትና ከፍላጎት ጋር የተያያዘው የገበያ ደንብ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።

በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ላይ የተጣለው እገዳ እምብዛም ውጤት አለማስገኘቱን የተገነዘቡ አንዳንዶች የተወሰኑ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በሕግ እንዲፈቀዱ በመሟገት ላይ ናቸው። አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳቡ ግለሰቦች ለራሳቸው የሚጠቀሙበት የተወሰነ መጠን ማግኘት እንዲችሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚል ነው። ይህም መንግሥት በቀላሉ ቁጥጥር ማድረግ እንዲችልና የአደገኛ መድኃኒትና ዕፅ ቱጃሮች የሚያገኙትን ከፍተኛ ትርፍ በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳል የሚል አመለካከት አላቸው።

አንዳንዶች ተሳክቶላቸዋል

ሰውነት ውስጥ የተከማቸን መርዝ በሕክምና ዘዴ እንዲወጣ ማድረግ ሱሰኛው ከሱሱ እንዲላቀቅ ከመርዳቱም በላይ አካላዊ ጤናውም እንዲሻሻል ያደርጋል። ይሁን እንጂ ሱሰኛው ወደ ወትሮው የዕለት ተዕለት ሕይወቱ በሚመለስበት ጊዜ ሱሱ እንደገና ሊያገረሽበትና አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን እንደገና ለመውሰድ ሊፈተን ይችላል። ሉዊጂ ዞጃ የተባሉ ደራሲ ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ሲገልጹ “በሽተኛው ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ አስተሳሰብ እንዲያዳብር እስካልተደረገ ድረስ እንዲሁ የባሕርይ ለውጥ እንዲያሳይ ማድረግ አይቻልም” ብለዋል።

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ዳረን አኗኗሩን መቀየር የቻለው “አዲስ አስተሳሰብ” በማዳበሩ ነው። እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ቀደም ሲል በአምላክ መኖር አላምንም ነበር። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ምንም እንኳ ሙሉ ቀን የማሳልፈው ዕፅ በመውሰድ ቢሆንም አንድ አምላክ መኖር አለበት ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። ሁለት ወይም ሦስት ለሚያህሉ ወራት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሱስ ለመላቀቅ ጥረት ባደርግም ጓደኞቼ ቀዳዳ ሊሰጡኝ አልቻሉም። ዕፅ መውሰዴን ገና ያላቆምኩ ቢሆንም እንኳ ማታ ከመተኛቴ በፊት አዘውትሬ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ። ከጓደኞቼ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ ቀነስኩ። አንድ ቀን ምሽት ላይ እኔና የመኝታ ቤት ጓደኛዬ በዕፅ ሰክረን እያለ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንስቼበት ነበር። በቀጣዩ ቀን ጠዋት የይሖዋ ምሥክር ለሆነው ወንድሙ ስልክ ደወለለት። ወንድምየው እኛ በምንኖርበት ከተማ የሚኖርን የአንድ ምሥክር አድራሻ ነገረንና ወደዚያ ሄድኩ።

“እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ከተወያየን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ በርካታ ጽሑፎች ሰጠኝ። ከእርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩና አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ መውሰድና ሲጋራ ማጨስ አቆምኩ። ከዘጠኝ ወር አካባቢ በኋላ ተጠመቅኩና የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።”

ከአደገኛ መድኃኒትና ዕፅ ሱስ መላቀቅ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ማይክል አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ለ11 ዓመታት አላግባብ ሲወስድ ከቆየ በኋላ ለማቆም ሙከራ ባደረገ ጊዜ የገጠመውን ችግር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “መብላት አቃተኝ፣ በዚህም የተነሳ ከሳሁ። ሰውነቴን ውርር ያደርገኛል፣ ያልበኛል እንዲሁም በሰዎች ዙሪያ ብርሃን ነገር ይታየኛል። እንደገና ዕፅ የመውሰድ ከፍተኛ አዕምሮት ያድርብኝ ነበር። ይሁን እንጂ በጸሎት ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረቤና የማደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ ቀድሞ ልማዴ እንዳልመለስ ረድቶኛል።” ቀደም ሲል አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ይወስዱ የነበሩት እነዚህ ሰዎች ከቀድሞ ጓደኞቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጣቸው በጣም አስፈላጊ እንደነበረ ይስማማሉ።

ሰዎች የሚያደርጉት ጥረት የማይሳካው ለምንድን ነው?

የተከለከሉ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የመውሰድ ልማድ በዓለማችን ላይ ያለ የአንድ ትልቅ ችግር አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። ክፋትን፣ ዓመፅንና ጭካኔን የሚያስፋፋ አንድ ታላቅ ኃይል መላውን ዓለም ተቆጣጥሮታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) ሐዋርያው ዮሐንስ “ክፉ” የተባለው ማን እንደሆነ ሲገልጽ በራእይ 12:​9 ላይ እንዲህ ብሏል:- “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”

የሰው ልጅ ከራሱ ድክመት በተጨማሪ ከዚህ ኃያል ከሆነ ጠላት ጋር መዋጋት አለበት። ገና ከመጀመሪያው የሰውን ልጅ ለውድቀት የዳረገው ይኸው ሰይጣን ነው። የሰውን ዘር የከፋ አዘቅት ውስጥ ለመጨመርና ከአምላክ እንዲርቅ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ለዚህም የሚጠቀምበት አንደኛው ዘዴ ሰዎች አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የመውሰድ ልማድ እንዲጠናወታቸው ማድረግ ይመስላል። “ጥቂት ዘመን” እንደቀረው ስለሚያውቅ በከፍተኛ ቁጣ ተነስቷል።​—⁠ራእይ 12:12

አምላክ ምን መፍትሔ ያመጣል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ ኃጢአተኛ የሆነውን የሰው ዘር ለመዋጀት ያደረገውን ፍቅራዊ ዝግጅት ይገልጻል። በ1 ቆሮንቶስ 15:​22 ላይ እንዲህ ተብለናል:- “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።” ኢየሱስ በፈቃደኝነት ፍጹም ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት ምድራዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል።

ብዙዎች ሞት እንዴት እንደመጣና የሰው ልጆች ያሉባቸው ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ ማወቃቸው ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ እንዲነሳሱና ቆራጥ አቋም እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች የሚያስከትሉትን ችግር በግለሰብ ደረጃ ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ከመስጠት የበለጠም ነገር ያደርጋል። የሰይጣን ተጽዕኖ ከተወገደ በኋላ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የመውሰድ ልማድን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል።

የራእይ መጽሐፍ ‘ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን ስለሚወጣ እንደ ብርሌ ስለሚያንጸባርቅ የሕይወት ውኃ ወንዝ’ ይናገራል። (ራእይ 22:1) ይህ ምሳሌያዊ ወንዝ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የሰው ልጆችን ገነት በሆነች ምድር ላይ ወደ ፍጹም ሕይወት ለመመለስ ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ራእይ በወንዙ ግራና ቀኝ ስለሚበቅሉት ዛፎች ሲገልጽ “የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ” በማለት ይናገራል። (ራእይ 22:2) እነዚህ ምሳሌያዊ ቅጠሎች ይሖዋ የሰውን ዘር በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ ወደ ፍጽምና ለመመለስ ያደረገውን የፈውስ ዝግጅት ያመለክታሉ።

በመጨረሻም የሰው ልጅ አደገኛ የሆኑ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ከመውሰድ ልማድ ብቻ ሳይሆን በዚህ ወራዳ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ቀስፈው ከያዙት ሕመሞችና ችግሮች ሁሉ እፎይታ ያገኛል!

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ማሪዋና ጉዳት ስላለማድረሱ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

በርካታ አገሮች ማሪዋናን በተለይ በሕክምናው መስክ ጥቅም ላይ ለማዋል ሲሉ ሕጋዊ ለማድረግ እያሰቡ ነው። መድኃኒቱ በኬሚፈውስ አማካኝነት የሚፈጠረውን የማቅለሽለሽ ስሜት የሚያስታግስ ሆኖ ከመገኘቱም በላይ በኤድስ የሚሠቃዩ ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸው እንዲከፈት እንደሚረዳ የተገኙት ማስረጃዎች ጠቁመዋል። የሥቃይ ማስታገሻም ሆኖ ያገለግላል።

በምርምር በተገኙ ውጤቶች ላይ መስማማት ያልተቻለ ቢሆንም እንኳ በኒው ሳይንቲስት መጽሔት ላይ የቀረበ አንድ የምርመራ ውጤት ማሪዋና የሚያስከትላቸውን አንዳንድ ጉዳቶች ገልጿል።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ማሪዋና በየዕለቱ የሚያጨሱ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድንና አልፎ አልፎ የሚያጨሱ ሰዎችን ያቀፈ ሌላ ቡድን በማወዳደር ምርመራ አደረገ። አእምሮ ላይ የተደረገው መደበኛ ምርመራ ብዙም ልዩነት እንዳለ አላሳየም። ይሁን እንጂ አዳዲስ ከሆኑ ሁኔታዎች ጋር መለማመድን በተመለከተ በተደረገው ጥናት ማሪዋና በብዛት የሚያጨሱት ሰዎች ድክመት እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

አንድ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ማሪዋና አዘውትረው የሚያጨሱ ሰዎችን ባቀፈ አንድ ቡድንና ከ15 ዓመት በላይ ሲጋራ ያጨሱ ሰዎችን ባቀፈ ሌላ ቡድን ላይ ምርመራ አድርጎ ነበር። ማሪዋና አጫሾቹ ብዙውን ጊዜ በቀን ሦስት ወይም አራት ጥቅል የሚያጨሱ ሲሆን ሲጋራ አጫሾቹ ደግሞ በቀን 20 ወይም ከዚያ በላይ ሲጋራ ያጨሱ ነበር። በሁለቱም ቡድን ያሉ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሳልና በብሮንካይተስ ይሰቃያሉ። በሳንባቸው ላይ የተደረገው ምርመራ እንዳሳየው በሁለቱም ቡድ​ኖች ውስጥ በታቀፉት ሰዎች ሕዋሳት ላይ የደረሰው ጉዳት ተመሳሳይ ነው።

ማሪዋና አጫሾቹ የሚያጨሱት ማሪዋና ብዛት አነስተኛ ቢሆንም እንኳ አንዲት የማሪዋና ጥቅል ከአንዲት ሲጋራ ሦስት ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ታር ታወጣለች። ከዚህም በተጨማሪ ኒው ሳይንቲስት እንደዘገበው “ማሪዋና አጫሾች ጭሱን በኃይል ወደ ውስጥ ምገው ለረዥም ጊዜ ያቆዩታል።”

በተጨማሪም በማሪዋና አጫሾች ሳንባ ላይ ያሉት በሽታ የሚከላከሉ ሕዋሳት፣ ባክቴሪያ የመከላከል ችሎታቸው ሲጋራ አጫሾች ሳምባ ላይ ካሉት ሕዋሳት 35 በመቶ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል።

[ምንጭ]

U.S. Navy photo

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወላጆች ‘ተጠያቂዎች’ ናቸው

በደቡብ አፍሪካ በሚታተመው ሳተርዴይ ስታር በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶች ዘንድ አስደንጋጭ በሆነ መንገድ እየተበራከተ የመጣውን አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ የመውሰድ ልማድ በማስመልከት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:-

“ልጆቻችን [አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን የሚወስዱ መሆናቸው] ወላጆች የሆንነውንም ሆነ የኅብረተሰቡ አካል የሆንነውን ሁሉ ያስጠይቀናል። ቁሳዊ ሃብት የምናመልክ በመሆናችን ሳምንቱን ሙሉ ገንዘብ ስናሳድድ እንቆያለን። ልጆቻችን አእምሯችንንና ጉልበታችንን ያሟጥጡብናል። ከልጆቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን? ገንዘብ ሰጥቶ ከፊታችን ዞር እንዲሉልን ማድረግ ቀላል ነው። ፍርሃት ያሳደሩባቸውን፣ ተስፋ የሚያደርጓቸውንና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ከመስማት ይልቅ ገንዘብ መስጠት ቀላል ነው። ዛሬ ማታ ምግብ ቤት እየተዝናናን ወይም ዘና ብለን ቴሌቪዥን እየተመለከትን ሳለን ምን እያደረጉ እንዳሉ እንኳ እናውቅ ይሆን?”

ወይም ስለ ምን ነገር እያሰቡ እንዳሉ እናውቃለን?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች አደገኛ የሆኑ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ ከመውሰድ ልማድ ለመላቀቅ ተገፋፍተዋል