ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ሰባ ዘጠኝ ሚልዮን ሴቶች “ጠፍተዋል”
በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ “በሕንድ፣ በፓኪስታን፣ በባንግላዴሽ፣ በኔፓል፣ በስሪ ላንካ፣ በቡታንና በሞልዲቭ አገሮች” የተካሄደው ጥናት “‘በደቡብ እስያ’ ከወሊድ በፊትም ሆነ በኋላ በሴቶች ላይ በሚፈጸመው መድልዎ ሳቢያ ወደ 79 ሚልዮን የሚጠጉ ሴቶች ‘እንደጠፉ’ አመልክቷል” ይላል ሮይተርስ ያወጣው ዘገባ። እነዚህ ሴቶች “የጠፉት” በውርጃ እንዲሁም “በሕፃናት ላይ በሚፈጸም ግድያና በክልሉ በአመጋገብ ሥርዓት ረገድ ለወንዶች ሕፃናት ልዩ እንክብካቤ የማድረግ ባሕል በመስፈኑ” የተነሳ ነው። ይህ በእንክብካቤ ረገድ ለወንዶቹ ልጆች የሚደረገው አድልዎ ለአካለ መጠን እስኪደርሱ ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ ሴቶቹ ሥር የሰደደ የምግብ እጥረት ችግር እንዲገጥማቸው ያደርጋል። “ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች፣ ልጅ በሚወልዱባቸው ዓመታት የመሞታቸው አጋጣሚ በእጅጉ የሰፋ ነው” ይላል ዘገባው። ወደ 79 ሚልዮን የሚጠጉ ሴቶች የጠፉት በክልሉ በአማካይ ለ100 ወንዶች 94 ሴቶች ብቻ ባሉበት ሁኔታ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ለ100 ወንዶች በአማካይ 106 ሴቶች ይደርሳሉ።
ማሳዳ አደጋ ላይ ወድቋል?
“ማሳዳ ዳግመኛ እጅ መስጠት የለበትም!” ይህ አይሁዶች ዘመናዊውን የእስራኤል ብሔር ሲገነቡ ለሥራ ያነሳሳቸው ቀስቃሽ ጥሪ ነበር። “ይሁን እንጂ ማሳዳ ለተፈጥሮ ኃይሎች እጁን ሊሰጥ ይችላል” ይላል ኤን ቢ ሲ ያሰራጨው የዜና ዘገባ። ይህ ዝነኛ የቱሪስት መስህብ የሚገኘው “እጅግ ተለዋዋጭ ከሆኑት የፕላኔታችን ዝንፈተ መስመሮች አንዱ በሆነው በሙት ባሕር ስምጥ ሸለቆ ነው።” የተራራው ቃጥላዎች (cliffs) በመቶዎች በሚቆጠሩ ክፍሎች የተከፋፈሉ ሲሆን አንዳንዶቹ በምድር ነውጥ ሊናጉ ይችላሉ። እንዲያውም በኮምፒውተር የተካሄደው ጥናት በምሥራቃዊው ስኔክ ፓዝ አቅጣጫ ያሉት የተወሰኑ ክፍሎች እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያመለከተ ሲሆን 18 ሜትር ርዝማኔ ባላቸው የብረት ዘንጎች እንዲጠናከሩ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሄሮድስ በማሳዳ ሰሜናዊ ክፍል የገነባው ቤተ መንግሥት ፍርስራሾችም “መሠረታቸው የተናጋ” በመሆኑ ማጠናከሪያ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በዚህ ሥፍራ ምንም ዓይነት ሥራ አልተጀመረም። ወደ 2, 000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የሮማ ሠራዊት ለሁለት ዓመት ያደረገውን ከበባ 967 የአይሁድ ዓማፅያን ተቋቁመው የቆዩት ከኢየሩሳሌም 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በማሳዳ ነበር። ይሁን እንጂ ሮማውያን ምሽጋቸውን ሰብረው ከመግባታቸው በፊት በነበረው ምሽት አይሁዶቹ እጅ ከመስጠት ይልቅ የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋት እንደመረጡ ይነገራል።
ጠቃሚ ቫይታሚን
ኮምፒውተር ላይ በምንሠራበት ጊዜ ዓይናችን በስክሪኑ ላይ ከሚታዩት ደማቅና ጠቆር ያሉ የብርሃን ገጽታዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ያለማቋረጥ ማስተካከያዎች ያደርጋል ይላል ዝድሮቪዬ የተሰኘው የፖላንድ የጤና መጽሔት። እነዚህ የእይታ ገጽታዎች ከባድ በሚሆኑበት ጊዜ ዓይናችንም ሮዶፕሲን በመባል የሚታወቀውን ለማየት የሚያስችለንንና ለብርሃን ፈጣን ምላሽ የሚሰጠውን ማቅለሚያ ቁስ አካል ይበልጥ ያቃጥላል። ቫይታሚን ኤ ለሮዶፕሲን መበራከት በጣም ወሳኝ ነው። ዝድሮቪዬ እንዳለው ከሆነ ቫይታሚን ኤ በብዛት ከሚገኝባቸው ነገሮች መካከል ጉበትና የዓሣ ዘይት ይጠቀሳሉ። የስብና የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ ከሚያደርጉ ምግቦች መራቅ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ቤታ-ካሮቲን የተሰኘውን ነጥረ ነገር የያዙ ምግቦችን መመገብ ይችላሉ። ሰውነታችን በፀሐይ ብርሃን በመታገዝ ይህን ንጥረ ነገር ወደ ቫይታሚን ኤ ይለውጠዋል። ቤታ-ካሮቲን ቢጫ፣ ብርቱካንማ፣ ቀይና አረንጓዴ ቀለሞች ባሏቸው አትክልቶች እንዲሁም እንደ አፕሪኮት፣ ኮክ፣ ደረቅ ፕሪም፣ ከርቡሽና ማንጎ ባሉ ፍራፍሬዎች ውስጥ ይገኛል።
በፀሐይ ሳቢያ ከሚደርስ ጉዳት ራስህን ጠብቅ
ያለ በቂ መከላከያ ለረጅም ሰዓት ለፀሐይ መጋለጥ የቆዳ ካንሰር ሊያስከትል ይችላል ሲል ኤል ዩኒቨርሳል የተሰኘው የሜክሲኮ ጋዜጣ ገልጿል። የቆዳ ሐኪም የሆኑት አድሪያና አኒዴስ ፎንሴካ እንዳሉት ከሆነ የፀሐይ ጨረር በየጊዜው እየተጠናከረ የሚሄድና በአብዛኛው ከ50 ዓመት በኋላ ካንሰር ሆኖ ብቅ የሚል ችግር ያስከትላል። ፀሐይ ከመሞቅህ 30 ደቂቃ በፊት የፀሐይን ጨረር የሚከላከል የቆዳ ቅባት መጠቀም እንደሚያስፈልግና ውኃ ውስጥ ገብተህ ስትወጣ ወይም ከልክ በላይ ሲያልብህ በየሦስትና አራት ሰዓት ልዩነት ድጋሚ መቀባት እንደሚያሻ በመጠቆም ባለሙያዋ ምክራቸውን ለግሰዋል። ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች የፀሐይን ጨረር የመከላከል ኃይሉ (ኤስ ፒ ኤፍ) ከ30 ወይም ከ40 በላይ የሆነ የቆዳ ቅባት መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። ጠቆር ያለ ቆዳ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የኤስ ፒ ኤፍ መጠኑ ከ15 እስከ 30 የሚደርስ የቆዳ ቅባት መጠቀም አለባቸው። ሆኖም እነዚህም ቅባቶች እንኳ የፀሐይ ጨረር የሚያስከትለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ መከላከል የማይችሉ መሆኑ መታወስ ያለበት ከመሆኑም በላይ ቆዳን የሚያጠቁሩ ቅባቶች ቆዳህ ይበልጥ እንዲቃጠል በማድረግ የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ሕፃናት የቆዳ መከላከያቸው ሙሉ በሙሉ እድገቱን የጨረሰ ባለመሆኑ ቀጥተኛ ለሆነ የፀሐይ ጨረር እንዳይጋለጡ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ጨምሯል
የተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጅ ያደረገውን እድገት አስመልክቶ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደገለጸው ባለፉት 25 ዓመታት በፔሩ የሰው ልጅ አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን በ12.8 ዓመታት ጨምሯል። ከ1970 እስከ 1975 ድረስ በነበሩት ዓመታት አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን 55.5 ዓመት የነበረ ሲሆን ከ1995 እስከ 2000 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ወደ 68.3 አሻቅቧል። ይህ ዕድገት ሊታይ የቻለው
ይላል ኤል ፔሩአኖ የተሰኘው ጋዜጣ፣ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ በመሻሻሉ ነው። በመሆኑም ቀደም ሲል ከ1, 000 ጨቅላ ሕፃናት መካከል 115 ይሞቱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ ወደ 43 አሽቆልቁሏል። በተጨማሪም ቀደም ሲል፣ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ 1, 000 ሕፃናት መካከል 178 በሞት ይቀጩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ ወደ 54 ወርዷል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ “ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 23 በመቶ የሚሆነው እስከ 60 ዓመት እንደሚኖር ይገመታል” ይላል ኤል ፔሩአኖ።ጥሩ ሥራ ማግኘት አሁንም አስቸጋሪ ነው
በሃኖቨር በተዘጋጀው ኤክስፖ 2000 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ “ዓለም አቀፋዊ ውይይት” በሚል ጭብጥ ስለተካሄደው ሲምፖዚየም የዘገበው ሃኖፌርሸ አልገማይነ ሳይቱንግ የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ “ሁሉም ሰው ጥሩ ሥራ እንዲያገኝ ለማድረግ የታለመው ግብ አሁንም አልተጨበጠም” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ወጥቶ ነበር። በ1951 ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ተመጣጣኝ ለሆነ ሥራ እኩል ክፍያ እንዲሰጥ የሚያዝዝ ደንብ ከመውጣቱም በላይ በ1973 በሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን የጉልበት ብዝበዛ የሚያግድ ሕግ ተደንግጓል። ይሁንና በዓለም ዙሪያ 150 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ሥራ የላቸውም። ከዚህም በተጨማሪ 850 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በቂ ሥራ የሌላቸው ሲሆኑ 250 ሚልዮን ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው ሥራ ላይ ለመሠማራት ተገድደዋል። ከዓለም ሕዝብ መካከል ግማሽ ያህሉ የዕለት ገቢው ከሁለት የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ነው። በተጨማሪም ብዙ ጥረት ቢደረግም እንኳ በባለጠጋዎችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ከመሄድ ይልቅ ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል። ሀብታምና ድሃ አገሮችን የሚያሳስቧቸው ጉዳዮችም በጣም የተለያዩ ናቸው። የአውሮፓ ፖለቲከኞች፣ ሠራተኞች አክሲዮን መግዛት የሚችሉበትን መንገድ ስለማመቻቸትና የሠራተኛ ማኅበራት ስለሚጫወቱት ሚና ሲነጋገሩ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያሉት አቻዎቻቸው ሁሉም ሰው መሠረታዊ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ ማድረግንና ለመጪው ትውልድ የሥራ መስክ መፍጠርን በመሳሰሉ በጣም መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ተወጥረው ይታያሉ።
ጡረተኛ ባለ ትዳሮች እየተፋቱ ነው
በፈረንሳይ “ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የተፋቱ ከ55 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር 52 በመቶ ጨምሯል” ሲል ለ ፊጋሮ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ የተፋቱ ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ የሆነ ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ የጨመረ ሲሆን ለፍቺው መንስኤ የሚሆኑት ሴቶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ከጡረታ በኋላ ያለውን ሕይወት መልመድ አለመቻላቸው ነው። በአብዛኛው ቀደም ሲል አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሥራ ይውል በነበረበት ወቅት ይፈቱ የነበሩ ችግሮች አሁን ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች እቤት መዋል ሲጀምሩ መፈታት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን የቻሉ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆነ ሴቶች ቁጥርም ጨምሯል። እነዚህ ሴቶች ቀደም ባሉት ትውልዶች ከነበሩት ሴቶች በበለጠ ሁኔታ፣ ታማኝ ሆነው ያልተገኙ ባሎችን የመፍታት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ጡረታ የወጡ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ከእነሱ በዕድሜ የሚያንሱ የትዳር ጓደኞች የሚያገኙ ሲሆን ባሎቻቸውን በሞት ያላጡ በ60ዎቹና በ70ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ሴቶች ግን ብቻቸውን ይቀራሉ።
የኤድስ ፍንዳታ
የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ የተቀናጀ ፕሮግራም (UNAIDS) እና የዓለም የጤና ድርጅት ያወጡት ዘገባ በ2000 ከአምስት ሚልዮን በላይ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ እንደተያዙ ይገልጻል። ይህ በዓለም ዙሪያ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ36 ሚልዮን በላይ ያደረሰው ሲሆን በ1991 ተሰጥቶ ከነበረው ግምታዊ አኃዝ ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ አለው። ወረርሽኙ በምሥራቅ አውሮፓ በከፍተኛ ደረጃ የተቀጣጠለ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች (አብዛኞቹ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በደም ሥራቸው የሚወስዱ ናቸው) ቁጥር በአንድ ዓመት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በበለጸጉት አገሮች ኤድስ በአብዛኛው የሚዛመተው አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች በደም ሥራቸው በሚወስዱ ሰዎችና በግብረ ሰዶማውያን መካከል በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል የሚደረጉት ጥረቶች ብዙም ለውጥ ሊያሳዩ እንዳልቻሉ ዘገባው ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ 25.3 ሚልዮን ሰዎች በሚገኙባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች በበሽታው የሚያዙ ተጨማሪ ሰዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ዕድገት ሳያሳይ ቀርቷል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ከ21 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ሞተዋል።
እንቅልፍ ቅንጦት አይደለም
“ቢያንስ ቢያንስ አንድ አራተኛ የሚሆኑት የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በእንቅልፍ እጦት ወይም ችግሮች ሳቢያ የመሥራት አቅማቸው በግማሽ ይቀንሳል” ሲል ዘ ናታል ዊትነስ የተሰኘው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ገልጿል። የእንቅልፍ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጄምስ ማስ እንዳሉት ከሆነ እንቅልፍ አንጎላችን ኒውሮትራንስሚተርስ የተባሉትን በጣም ወሳኝ የሆኑ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች መልሶ እንዲተካ የሚያደርግ በመሆኑ ለጥሩ የማስታወስ ችሎታ፣ ለፈጠራ ሥራ፣ ችግሮችን ለመፍታትና ትምህርት በሚገባ ለመቅሰም በቂ እንቅልፍ ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው። የመንፈስ ጭንቀት፣ ግልፍተኛነት፣ የመረበሽ ስሜት፣ እንደ ወትሮው ከሌሎች ጋር ለመጫወትና ለመግባባት አለመቻል፣ ሐሳብን ለማሰባሰብና ለማስታወስ መቸገር፣ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግና ውሳኔ ላይ ለመድረስ አለመቻል፣ ራስን ለአደጋ ማጋለጥ፣ የምርታማነት መቀነስና ደስታ ማጣት በቂ እንቅልፍ ሳያገኙ በቀሩ ሰዎች ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም አምስት ሰዓት ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ የሚተኙ ሰዎች ቫይረሶችን የመቋቋም ኃይላቸው ይቀንሳል። “የተሟላ ብቃት እንዲኖረን” ይላሉ ማስ፣ “የሕይወታችንን አንድ ሦስተኛ ማለትም በቀን በአማካይ ስምንት ሰዓት ያህል ለእንቅልፍ ማዋል አለብን።”