በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የናያጋራ ፏፏቴ ልዩ ትንግርት

የናያጋራ ፏፏቴ ልዩ ትንግርት

የናያጋራ ፏፏቴ ልዩ ትንግርት

በቅርቡ የናያጋራን ፏፏቴ በጣም ከቅርበት ማለትም ከዚህ በፊት ካየሁት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ የማየት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ብቻ ምን ልበላችሁ ልዩ ትንግርት ነው። እኔና ጓደኞቼ በካናዳ የሚገኘውን ሆርስሹ ፎልስ እየተባለ የሚጠራውን ፏፏቴ ጎብኝተን ነበር። ይህ ስም የተሰጠው በቅርጹ ምክንያት ነው። ይህን ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጎበኘሁበት ከ1958 ጀምሮ በተደጋጋሚ ጊዜ የጎበኘሁት ቢሆንም በቀጥታ ፏፏቴው ድረስ በጀልባ ሄጄ አላውቅም ነበር። ሆኖም ሜይድ ኦቭ ዘ ሚስት በተባለችው ጀልባ አማካኝነት የሽርሽር ጉዞ ማድረግ ከተጀመረበት ከ1848 አንስቶ ሰዎች ይህን ዓይነት ጉዞ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን አስደሳች ጉዞ አድርገዋል። አሁን እኔም አጋጣሚ አገኘሁ።

ከሁለቱም የወንዙ ዳርቻዎች ማለትም ከአሜሪካም ሆነ ከካናዳ አቅጣጫ በየጊዜው ጀልባዎች ይነሳሉ። በማንኛውም ጊዜ ሰልፍ ይዘው የሚጠባበቁ ሰዎች አይጠፉም። ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ በተለያየ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሰዎች ወጨፎውን ለመከላከል ባለ ሰማያዊ ቀለም ቀላል ፕላስቲክ የዝናብ ልብስ ለብሰው አይተናል። (በሌላው አቅጣጫ በአሜሪካ በኩል የሚገኘውን ፏፏቴ የሚጎበኙ ሰዎች የሚለብሱት የዝናብ ልብስ ቢጫ ነው።) ሜይድ ኦቭ ዘ ሚስት VII የተባለችው ጀልባ እስከ 582 የሚደርሱ መንገደኞች መጫን የምትችል ስትሆን 132 ሜትሪክ ቶን ክብደት፣ 24 ሜትር ርዝመትና 9 ሜትር ስፋት አላት። በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ጀልባዎች አሉ፤ እነዚህም ሜይድ ኦቭ ዘ ሚስት አራተኛ፣ አምስተኛ፣ ስድስተኛና ሰባተኛ ናቸው።

በውኃ መበስበስ አሁን የእኛ ተራ ነው

ከሌሎች ሰዎች ጋር ተሰልፈን ስንጠብቅ ቆየን። ከዚያም ሜይድ ኦቭ ዘ ሚስት VII የተባለችው ጀልባ በውኃ ብስብስ ያሉትን ጎብኚዎች አራግፋ እንደጨረሰች እኛ ተሳፈርን። በጣም አስደሳች ጉዞ እንደሚጠብቀን ገና ከወዲሁ ታየኝ። አንድ ማይል ከማይሞላ ርቀት ላይ ውኃው ከገደሉ አፋፍ ተንደርድሮ 52 ሜትር ቁልቁል ከወረደ በኋላ ከበታቹ ወደሚገኘውና 55 ሜትር ጥልቀት ወዳለው ጥልቅ ዝብጥ (basin) ይገባል። ጀልባችን በወንዙ ላይ እየቀዘፈች በአሜሪካ በኩል ወደሚገኘውና 54 ሜትር ያህል ቁልቁል ወደሚወረወረው ፏፏቴ ያቀናች ሲሆን ከፏፏቴው ሥር የሚገኘውን እየተጥመለመለ የሚሄድ ውኃ በትግል ማቋረጥ ነበረብን። * በጣም አስደሳች የሆነው ክፍል ገና ይጠብቀናል።

ከዐለቱ ጋር ወደሚላተመው ውኃ ይበልጥ እየተጠጋን በሄድን መጠን የልብ ምታችንም የዚያኑ ያህል እየጨመረ መጣ። ብዙም ሳይቆይ ከነፋሱና በኃይል ከሚረጨው ውሽንፍር የተነሳ ፎቶ ማንሳት አልቻልንም። መርከበኛው ውኃው በከፍተኛ ኃይል ወደሚላተምበት ቦታ ጀልባዋን በጣም ቀስ እያለ ሲያስጠጋ ዓመታት የሚወስድበት ይመስል ነበር። እዚህ ቦታ ላይ በየደቂቃው 168, 000 ኪውቢክ ሜትር ውኃ ከአፋፉ ላይ ተወርውሮ ልክ ጀልባዋ ፊት ያለው ዐለት ላይ ይነጥራል! ድምፁ በጣም ያስተጋባል። ምንም ያህል ብትጮኽ የራስህን ድምፅ እንኳ መስማት አትችልም። የልቤ ምት ጨመረ። የናያጋራ ውኃ ቀዝቃዛና ንጹህ እንደሆነ ታወቀኝ። ይህ በእርግጥም በሕይወቴ የማልረሳው ነው!

በጣም ረጅም የሚመስለው ጊዜ ካበቃ በኋላ መርከበኛው አደገኛ ከሆነው ቀጣና ጀልባችንን ቀስ በቀስ እያራቀ ወንዙ ወደሚፈስበት አቅጣጫ ሲወስደን ትንፋሼ መለስ አለ። ምንም ችግር ሳይገጥመን በደህና ተመለስን። ደግሞም ምንም የሚያሰጋ ነገር አልነበረም። የጀልባዎቹ ባለንብረት የሆነው ኩባንያ አደጋ አድርሶ አያውቅም። የስቲምቦት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኢሚል ቤንዲ እያንዳንዱ ጀልባ መጫን ለሚችለው ከፍተኛ የተሳፋሪዎች ቁጥር የሚዳረስ በቂ መንሳፈፊያ ጃኬትና ታንኳ እንዳለው አረጋግጠውልናል። የታይታኒክ ተሳፋሪዎችን ለሞት የዳረገው ጥፋት እዚህ አይደገምም!

ፏፏቴዎቹ እያፈገፈጉ ናቸው!

አዎን፣ የአፈር መሸርሸር በፏፏቴዎቹ ላይ ጉዳት አስከትሏል። የናያጋራ ፏፏቴዎች 12, 000 በሚያክሉ ዓመታት ውስጥ ወደ 11 ኪሎ ሜትር ገደማ በማፈግፈግ አሁን የሚገኙበት ቦታ ላይ እንደደረሱ ይገመታል። በአንድ ወቅት የመሸርሸሩ መጠን በዓመት አንድ ሜትር ገደማ ደርሶ ነበር። አሁን ግን ቀንሶ በየአሥር ዓመቱ ወደ 36 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሆኗል። የዚህ መሸርሸር መንስዔ ምንድን ነው?

ወንዙ የሚሄደው ከላይ ባለ ጠንካራ የዶሎሚት ኖራ ድንጋይ ላይ ሲሆን ከሥሩ ልል የአሸዋ ድንጋይና የብሃ ድንጋይ ንብብር አለ። እነዚህ ከሥር ያሉ ንብብሮች ተሸርሽረው ሲያልቁ ኖራ ድንጋዩ ተፈረካክሶ እታች ወዳለው ጥልቅ ዝብጥ ይወርዳል።

ውኃ አይባክንም

አጭር ርዝመት (56 ኪሎ ሜትር) ባለው የናያጋራ ወንዝ የሚፈሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ከአምስቱ ታላላቅ ሐይቆች መካከል ከአራቱ የሚመጣ ነው። ከኢሪ ሐይቅ ተነስቶ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ኦንታሪዮ ሐይቅ ይፈሳል። በዚህ አጭር ጉዞው ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ የሚጠቀሙበት ሃይድሮ ኤሌትሪክ ለማመንጨት ይውላል። ይህ በዓለማችን ላይ ካሉ ከፍተኛ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። የካናዳውና የአሜሪካው የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በድምሩ 4, 200, 000 ኪሎ ዋት የማመንጨት አቅም አላቸው። ተርባይኖቹን የሚያንቀሳቅሰው ውኃ ወንዙ ፏፏቴው ጋር ከመድረሱ በፊት ከናያጋራ ተጠልፎ ይወሰዳል።

የጫጉላ ሽርሽርና የምሽት መብራቶች

የናያጋራ ፏፏቴ ጫጉላ ሽርሽር ላይ የሚገኙ ተጋቢዎች የሚወዱት ቦታ ነው። በተለይ በ1953 ናያጋራ የተባለው ፊልም ከወጣ በኋላ ይህ በገሀድ ታይቷል። ምሽት ላይ ባለ ቀለም ባውዛዎች ፏፏቴዎቹን የሚያስሸበርቁ ሲሆን ፕላኔታችን ላይ የሚገኘው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ይህ ቦታ ባለው ውበትና ግርማ ላይ ድምቀት ይጨምሩለታል። ለጉብኝት ወደ ካናዳና ዩናይትድ ስቴትስ የሄደ ሰው ይህን አስደናቂ ቦታ ካልጎበኘ በእርግጥም ትልቅ ነገር እንደቀረበት ይቆጠራል። ትንሽ ደግሞ ጀብድ መሥራት የምትወድ ከሆነ በጀልባ ሂድ! በሕይወትህ ውስጥ ምን ጊዜም የማትቆጭበት ወይም የማትረሳው ተሞክሮ ይሆንልሃል።​—⁠ተጽፎ የተላከልን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 “በአሜሪካ በኩል የሚገኘው ፏፏቴ ከ21 እስከ 34 ሜትር የሚያህል ርዝመት ቁልቁል ከተወረወረ በኋላ በቀጥታ እታች ካለው ንጣፍ ዐለት ጋር ይላተማል።”​—⁠ኦንታሪዮስ ናያጋራ ፓርክስ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የናያጋራ ስፓኒሽ ኤሮ ካር

ከፏፏቴው 4.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ “ፈረሰኛው ውኃ በሚያቆምበትና ታላቁ የወንዝ ሸለቆ ድንገት በስተ ሰሜን ምሥራቅ በሚታጠፍበት ቦታ ላይ” በጣም ሰፊ የውኃ አዙሪት ይፈጠራል። “እዚህ ቦታ ላይ ደማቅ አረንጓዴ ቀለም ያለው አዙሪት እየታጠፈና እየተዘረጋ በመምጣት በጣም ጠባብ በሆነው የሸለቆው ክፍል ሾልኮ ያልፋል።”​—⁠ኦንታሪዮስ ናያጋራ ፓርክስ

የዚህን የውኃ ክምችት አጠቃላይ ስፋት መረዳት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ በናያጋራ ስፓኒሽ ኤሮ ካር መጓዝ ነው። ይህ በሽቦ ገመድ ላይ የተንጠለጠለ መኪና ሲሆን በውኃው አናት አቋርጦ በማለፍ ከላይ የሚመጣውንም ሆነ ወደታች የሚፈሰውን የወንዙን ማራኪ ገጽታ ለማየት ያስችላል። ታዲያ “ስፓኒሽ” ኤሮ ካር የተባለው ለምንድን ነው? የመኪናውን ንድፍ ያወጣውና ግንባታውን ያካሄደው የፈጠራ ሰው፣ ስፔናዊው መሃንዲስ ሊዮናርዶ ቶሬስ ኬቬቶ (1852-1936) በመሆኑ ነው። መኪናው ከ1916 አንስቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። ይህ በዓለማችን ላይ የሚገኝ በዓይነቱ ብቸኛ መኪና ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ከ1678 አንስቶ የአፈር መሸርሸፏፏቴው በግምት 300 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ወደኋላ እንዲሸሽ አድርጓል

1678

1764

1819

1842

1886

1996

[ምንጭ]

ምንጭ:- Niagara Parks Commission

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ካናዳ

ዩ ኤስ ኤ

ካናዳ

ዩ ኤስ ኤ

ኢሪ ሐይቅ

ናያጋራ ፏፏቴ

ናያጋራ ወንዝ

ኦንታሪዮ ሐይቅ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሜሪካ በኩል ያለው ፏፏቴ

በካናዳ በኩል ያለው ሆርስሹ ፏፏቴ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሽት ላይ በመብራት ያሸበረቀው የፏፏቴው የክረምት ገጽታ