በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ስም ሕይወቴን ለወጠው!

የአምላክ ስም ሕይወቴን ለወጠው!

የአምላክ ስም ሕይወቴን ለወጠው!

ሳንዲ ያሲ ድዞሲ እንደተናገረችው

ርሞኖች በራችንን ሲያንኳኩ እኔና እህቶቼ የሌለን ለማስመሰል አልጋ ሥር ተደብቀን እርስ በርስ እየተጎነታተልን እንስቅ ነበር። * በመጨረሻ በሩን ከፈትኩና በባሕላችን የምንኖር ናቫሆዎች መሆናችንን፤ ደግሞም ስለ ነጮች ሃይማኖት መስማት እንደማንፈልግ በቁጣ ነገርኳቸው።

ወላጆቻችን ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመሸመት ገበያ ወጥተዋል። የሚመለሱት ጀንበር ስትጠልቅ ነው። ቤት ከደረሱ በኋላ ሞርሞኖችን በቁጣ ተናግሬ እንደመለስኳቸው ሰሙ። ከዚህ በኋላ ማንንም ሰው አክብሮት በጎደለው ሁኔታ ማነጋገር እንደሌለብኝ ጥሩ አድርገው መከሩኝ። ሰዎችን በአክብሮትና በደግነት እንድንይዝ ያስተምሩን ነበር። አንድ ያልታሰበ እንግዳ ቤታችን የመጣበት ቀን ትዝ ይለኛል። ወላጆቼ ውጭ ምግብ አዘጋጅተው ነበር። በመጀመሪያ እንግዳው ከበላና ከተስተናገደ በኋላ እኛ በላን።

ለአሜሪካ ሕንዳውያን በተከለለ አካባቢ መኖር

የምንኖረው በሕዝብ ከተጨናነቁ ከተማዎችና መንደሮች ርቆ ባለው በሆዌል ሜሳ፣ አሪዞና ሲሆን ለሆፒ ሕንዳውያን ከተከለለው አካባቢ በስተ ሰሜን ምዕራብ ዘጠኝ ማይል ላይ ነው። ይህ ቦታ የሚገኘው ለየት ያሉ ቀይ የአሸዋ ድንጋዮች አለፍ አለፍ ብለው ተቆልለው በሚታዩበትና አስደናቂ የበረሃ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ባለው ደቡብ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነው። በአካባቢው በጣም ከፍ ያሉና ዙሪያቸውን ገደላማ የሆኑ ብዙ አምባዎች አሉ። አምባዎቹ ላይ ሆነን ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተሰማሩትን በጎቻችንን ማየት እንችላለን። ማራኪ የሆነውን ይህን የትውልድ አካባቢዬን በጣም እወደዋለሁ!

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የአሜሪካ ሕንዳውያንን ንቅናቄ (AIM) ከሚደግፉት ከአክስቴ ልጆች ጋር በጣም ተቀራርቤ ነበር። * የአሜሪካ ሕንዳዊ በመሆኔ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ የሕንዳውያን ጉዳይ አስፈጻሚ ቢሮ (BIA) እጅ እንዳለበት አድርጌ ከማስበው ለአሥርተ ዓመታት ከዘለቀው ጭቆና ጋር በተያያዘ ነጮችን እቃወም ነበር። የአክስቴ ልጆች እንደሚያደርጉት ጥላቻዬን በይፋ ገልጬ አላውቅም። በልቤ ይዤው ነበር። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ የማየውን ማንኛውንም ሰው እንድጠላ አድርጎኛል።

ነጮች መሬታችንን፣ መብታችንንና የራሳችንን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የማከናወን ነፃነታችንን የመንፈግ ኃይል ያገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር! ሌላው ቀርቶ አዳሪ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት በቤተ ክርስቲያን በሚካሄደው የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ እንድገኝ እንዳያስገድዱኝ ስል የአባቴን ፊርማ አስመስዬ ፈርሜ አቅርቤአለሁ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የእነሱ ባሕል እንዲዋሃደን ለማድረግና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሕንዳውያን ባሕላችንን ለማስረሳት የታቀዱ ነበሩ። ሌላው ቀርቶ በራሳችን ቋንቋ መነጋገር እንኳ አይፈቀድልንም ነበር!

ለተፈጥሮና ለአካባቢያችን ጥልቅ አክብሮት ነበረን። ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ዞረን ጸሎት ካደረስን በኋላ እንደ ቅዱስ ነገር የሚታየውን የበቆሎ አበባ ብናኝ በመበተን ምስጋና እናቀርባለን። * በዚህ ሁኔታ በናቫሆ ባሕል አምልኮ የሚከናወንበትን መንገድ በተመለከተ በወጉ ስልጠና ያገኘሁ ከመሆኑም በላይ የአምልኮ ሥርዓቱንም በሙሉ ልብ በደስታ ተቀብየዋለሁ። ሕዝበ ክርስትና ወደ ሰማይ ስለ መሄድ የምታስተምረው ትምህርት አይዋጥልኝም ነበር፤ ደግሞም ሲኦል እሳታማ የሆነ የመሰቃያ ቦታ ነው የሚል እምነት አልነበረኝም። እዚሁ ምድር ላይ የመኖር ከፍተኛ ምኞት ነበረኝ።

ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ወቅት የጠበቀ አንድነት ካለው ቤተሰቤ ጋር መሆን ያስደስተኝ ነበር። የናቫሆዎች መኖሪያ የሆነውን ባሕላዊ ጎጆአችንን ማጽዳት፣ ሽመናና በጎችን ማገድ የዕለት ተዕለት ተግባሬ ነበር። እኛ ናቫሆዎች ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ በግ አርቢዎች ነን። ጎጆአችንን ባጸዳሁ ቁጥር (ከታች ያለውን ፎቶ ተመልከት) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን መዝሙራትና ከ“አዲስ ኪዳን” በርካታ መጻሕፍትን የያዘ አንድ ትንሽ ቀይ መጽሐፍ አይ ነበር። በውስጡ ምን እንደያዘና ምን መልእክት እንዳለው ምንም ትኩረት ሳልሰጠው አንዴ እዚህ አንዴ እዚያ እያነሳሁ እጥለው ነበር። ከነጭራሹ ግን አላጠፋሁትም።

የትዳር ሕልሜና የገጠመኝ ሁኔታ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ በኒው ሜክሲኮ አልበከርኪ የሙያ ትምህርት ለመከታተል አቀድኩ። ሆኖም ወደዚያ ከመሄዴ በፊት ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ ከሆነው ሰው ጋር ተዋወቅሁ። ከእሱ ጋር ለመጋባት ስል ሬዝ ብለን ወደምንጠራው የናቫሆዎች ክልል ተመለስኩ። ወላጆቼ በትዳር ዓለም በርካታ ዓመታት አሳልፈዋል። የእነሱን ፈለግ የመከተል ፍላጎት ስለነበረኝ እኔም አገባሁ። የቤት እመቤት መሆኔን የወደድኩት ከመሆኑም በላይ በተለይ ደግሞ ወንዱ ልጃችን ላየኔል ከተወለደ በኋላ የቤተሰብ ሕይወታችን አስደሳች ሆነልኝ። በጣም አሳዛኝ ወሬ እስከሰማሁበት ዕለት ድረስ እኔና ባለቤቴ እጅግ ደስተኞች ነበርን!

ባለቤቴ ሌላ ፍቅረኛ ነበረችው! ለትዳሩ ታማኝ ባለመሆኑ ምክንያት ጋብቻችን ፈረሰ። ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ደረሰብኝ፤ ለእሱም ከባድ ጥላቻ አደረብኝ። ልበቀለው ፈለግሁ! ሆኖም ልጁን የማሳደግ መብትና የገንዘብ ድጎማ በማግኘት ረገድ ረጅም ጊዜ በፈጀው የፍቺ ሙግት ወቅት ካደረብኝ ከንቱነትና ተስፋ ቢስነት የተነሳ ሐዘን ላይ ወደቅሁ። ሐዘኔን ለመርሳት ስል ብዙ ማይል እሮጥ ነበር። በቀላሉ ሆድ ይብሰኝ የነበረ ሲሆን የምግብ ፍላጎቴም ጠፋ። አይዞሽ ባይ እንደሌለኝ ሆኖ ተሰማኝ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመሳሳይ የጋብቻ ችግር ከነበረበት ሰው ጋር ወዳጅነት ጀመርኩ። ሁለታችንም የስሜት ቁስል አለብን። ይህ ሰው አሳቢነት ያሳየኝ ከመሆኑም በላይ የሚያስፈልገኝን ስሜታዊ ድጋፍ ሰጠኝ። ስለ ሕይወት ያለኝን አመለካከት የውስጤን ግልጥልጥ አድርጌ አጫወትኩት። በጥሞና ስላዳመጠኝ በእርግጥ እንደሚያስብልኝ ተሰማኝ። ለመጋባት አሰብን።

ከዚያም እሱም ቢሆን ታማኝ እንዳልሆነ ደረስኩበት! ምንም እንኳ አስቸጋሪና የሚያሰቃይ ቢሆንም ግንኙነታችንን አቋረጥኩ። የተጣልኩ ሆኖ ተሰማኝ፤ ከባድ የመንፈስ ጭንቀትም አደረብኝ። በጣም ከመናደዴ የተነሳ የበቀል ስሜት ያደረብኝ ሲሆን ሕይወቴን ለማጥፋትም አሰብኩ። ሕይወቴን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ ሙከራ አደረግሁ። በቃ ሞቼ መገላገል ፈለግሁ።

እውነተኛውን አምላክ በተመለከተ ያገኘሁት የመጀመሪያ ፍንጭ

ወደማላውቀው አምላክ ከብዙ እንባ ጋር ጸለይኩ። ይሁን እንጂ ግዙፍ የሆነውን አጽናፈ ዓለም የፈጠረ የሁሉም የበላይ የሆነ አካል መኖሩን አምናለሁ። ፀሐይ ስትጠልቅ ባላት ውበት ስለተማረክሁ በዚህ አስደናቂ ሁኔታ እንድንደሰት ያስቻለን አካል ምን ያህል ድንቅ እንደሆነ ማሰላሰል ጀመርኩ። ለዚያ ለማላውቀው አካል ያለኝ ፍቅር እያደገ መጣ። “አምላክ ሆይ፣ በእርግጥ ካለህ እርዳኝ፣ መመሪያ ስጠኝ፣ ደስታዬ እንዲመለስልኝ አስችለኝ” በማለት እነግረው ጀመር።

በዚህ መሀል ቤተሰቦቼ በተለይ ደግሞ አባቴ ስለ እኔ ይጨነቁ ነበር። ወላጆቼ ፈውስ እንዳገኝ መድኃኒት አዋቂዎችን አመጡልኝ። አባቴ ጥሩ መድኃኒት አዋቂ ፈጽሞ ገንዘብ አይጠይቅም፤ ከዚህ ይልቅ ያመነበትን ነገር ሥራ ላይ ያውላል አለ። ወላጆቼን ለማስደሰት ስል ናቫሆዎች በሚያከናውኗቸው ሃይማኖታዊ የምርቃት ሥነ ሥርዓቶች ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተካፈልኩ።

አልጋዬ አጠገብ ካለው ራዲዮ በስተቀር ማንም አብሮኝ ሳይኖር ለብዙ ቀናት ለብቻዬ ተገልዬ ተቀመጥኩ። ኢየሱስን በልቤ ስላልተቀበልኩ አንድ ቄስ በራዲዮ የሚናገረውን የኩነኔ ፍርድ ሳዳምጥ የጥላቻ ስሜት አደረብኝ። በጣም አንገሽግሾኝ ነበር! እንኳን የነጮቹ ሃይማኖት የራሴም ሃይማኖት ሰልችቶኛል! በራሴ መንገድ አምላክን ለማግኘት ወሰንኩ።

ለብቻዬ ቤት ውስጥ ተዘግቼ በነበረበት ወቅት እንደገና ያቺን ትንሽ ቀይ መጽሐፍ አየኋት። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኗን ተረዳሁ። መዝሙራትን ሳነብብ ንጉሥ ዳዊት ስለደረሰበት መከራና ጭንቀት ተገነዘብኩ፤ መጽናኛም አገኘሁ። (መዝሙር 38:​1-22፤ 51:​1-19) ይሁን እንጂ የነጮች የበላይ እንደሆንኩ አስብ ስለነበር ያነበብኩትን ሁሉ ወዲያው ከአእምሮዬ አወጣሁት። የነጮችን ሃይማኖት አልቀበልም።

የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርብኝም እንኳ ልጄን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ችያለሁ። ልጄ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። የጸሎት አገልግሎት የሚሰጡ ሃይማኖታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መከታተል ጀመርኩ። ስልክ አንስቼ 800 ቁጥር ላይ በመደወል እንዲረዱኝ ተማጸንኳቸው። በመጀመሪያ 50 ወይም 100 የአሜሪካ ዶላር መዋጮ እንደምሰጥ ቃል እንድገባ ሲነግሩኝ ስልኩን ጆሯቸው ላይ ዘጋሁት!

በተለይ ባለቤቴ ለሸንጎው ዳኛ እውነቱን ሲደባብቅ ስመለከት ከፍቺው ጋር በተያያዘ በሚካሄደው የፍርድ ቤት ክርክር በጣም አዘንኩ። ልጃችንን የማሳደግ መብት ለማግኘት እንሟገት ስለነበር ፍቺውን ለመቋጨት ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። ይሁን እንጂ ለእኔ ተፈረደልኝ። አባቴ ችሎቱ በተካሄደባቸው ጊዜያት ምንም ሳያማርር ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ድጋፍ ሰጥቶኛል። በጥልቅ እንደተጎዳሁ ገብቶት ነበር።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘሁ

ለነገ ሳልጨነቅ ለመኖር ወሰንኩ። በአንድ አጋጣሚ አንድ የናቫሆ ቤተሰብ ጎረቤቶቼን ሲያነጋግሩ ተመለከትኩ። ካደረብኝ ጉጉት የተነሳ ተደብቄ አየኋቸው። እነዚህ ሰዎች ከበር ወደ በር እየሄዱ የሆነ ሥራ እያከናወኑ ነበር። ወደ እኔም መጡ። የናቫሆ ዝርያ የሆነችው ሳንድራ የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ነገረችኝ። ይሖዋ የሚለው ስም ይበልጥ ትኩረቴን ሳበው። “ይሖዋ ማን ነው? ይኼ አዲስ ሃይማኖት መሆን አለበት። ቤተ ክርስቲያን የአምላክን ስም ያላስተማረችን ለምንድን ነው?” ስል ጠየቅኋት።

መጽሐፍ ቅዱሷን መዝሙር 83:​18 [NW ] ላይ ገልጣ “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ሁሉ ይወቁ” የሚለውን በደግነት አሳየችኝ። አምላክ የግል ስም እንዳለውና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ አስረዳችኝ። ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ልታስተምረኝ ሐሳብ ካቀረበችልኝ በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት የተባለውን መጽሐፍ ሰጠችኝ። * በደስታ ስሜት “አዎን፣ ስለዚህ አዲስ ሃይማኖት ማወቅ እፈልጋለሁ!” አልኳት።

በአንድ ሌሊት መጽሐፉን አንብቤ ጨረስኩ። የመጽሐፉ ይዘት እንግዳ ሆነብኝ። መጽሐፉ ሕይወት ዓላማ እንዳለው ይገልጻል፤ ይህ ደግሞ ለመኖር ያለኝን ፍላጎት እንደገና ለማቀጣጠል የሚያስፈልገኝ ነገር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩና ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ማግኘቴ አስደሰተኝ። የተማርኩትን ነገር ሁሉ አመንኩበት። ትርጉም ይሰጣል፤ ደግሞም ይህ እውነት መሆን አለበት!

ላየኔል ስድስት ዓመት ሲሆነው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አስተምረው ጀመር። አብረን እንጸልያለን። ይሖዋ አሳቢ እንደሆነና በእሱ መታመን እንዳለብን በሚገልጸው ሐሳብ አንዳችን ሌላውን እናበረታታለን። አንዳንድ ጊዜ ችግሮችን የምቋቋምበት ብርታት አጣለሁ። ሆኖም ላየኔል በትንሽ እጆቹ አቅፎኝ “አታልቅሺ፣ እማዬ፤ ይሖዋ ይደግፈናል” ሲል በትምክህት የሚናገረው የሚያጽናና ቃል ከፍተኛ ለውጥ ያመጣልኛል። ይህ በጣም አጽናንቶኛል፤ ደግሞም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አስችሎኛል! መመሪያ ለማግኘት ደጋግሜ ጸለይኩ።

ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያገኘሁት ጥቅም

ለይሖዋ የነበረን አመስጋኝነት በቱባ ሲቲ በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት 240 ኪሎ ሜትር የደርሶ መልስ ጉዞ እንድናደርግ አነሳሳን። በበጋ ወቅት በሳምንት ሁለት ጊዜ እንሰበሰብ የነበረ ሲሆን ክረምት ላይ ደግሞ የአየር ጠባዩ አስቸጋሪ በመሆኑ እሁድ ሙሉ ቀን እንሰበሰባለን። በአንድ ወቅት ወደ ስብሰባ በመጓዝ ላይ ሳለን መኪናችን በመበላሸቱ መኪና ለምነን ተሳፍረን ለመሄድ ተገደናል። በመኪና የምናደርገው ረጅም ጉዞ አድካሚ ቢሆንም ለሞት እያጣጣርን ካልሆንን በስተቀር ፈጽሞ ከስብሰባ መቅረት የለብንም ሲል ላየኔል የሰጠው ሐሳብ ከይሖዋ የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ትምህርት አክብዶ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን እንድገነዘብ አደረገኝ።

ስብሰባዎች ላይ በሕይወታችን የሚያጋጥሙን መከራዎች ተወግደው ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገሩ የመንግሥቱን መዝሙሮች ስንዘምር እንባዬ ዝም ብሎ ይወርድ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አጽናንተውኛል እንዲሁም አበረታተውኛል። ቤታቸው ጠርተው ምሳና አንዳንድ ጊዜ ሻይ በመጋበዝ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይተውናል። እንዲሁም በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ላይ እንገኛለን። አሳቢነት ያሳዩንና ያዳምጡን ነበር። በተለይ ሽማግሌዎቹ ችግራችንን በመካፈልና ይሖዋ አምላክ እንደሚያስብልን ያለንን ጽኑ እምነት በማጠናከር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። እውነተኛ ወዳጆች በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። መንፈሴ እንዲታደስ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ ተስፋ ቆርጬ ሳለቅስ አብረውኝ ያለቅሱ ነበር።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30

ሁለት ከባድ ውሳኔዎች

በይሖዋ ዝግጅቶች ረክቼ መኖር እንደጀመርኩ የወንድ ጓደኛዬ ይቅርታ ሊጠይቀኝ መጣ። አሁንም እወደው ስለነበር መጥቶ ሲለምነኝ እምቢ ማለት አልቻልኩም። እውነት ይለውጠዋል ብዬ ስላሰብኩ ለመጋባት ተስማማን። ይህ በሕይወቴ የፈጸምኩት ትልቅ ስህተት ነበር! ደስታ አጣሁ፤ ሕሊናዬም እረፍት ነሳኝ። እውነትን አለመፈለጉ ያልጠበኩት ነገር ሆነብኝ።

ከሽማግሌዎቹ ለአንዱ ምሥጢሬን አካፈልኩት። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ በምክንያት አስረዳኝና ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድችል አብሮኝ ጸለየ። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የቱንም ያህል ብንወዳቸው ሊበድሉን ወይም ሊያሳዝኑን እንደሚችሉ ይሖዋ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ፈጽሞ እንደማያደርስብኝ ደመደምኩ። እንዲያውም የደባል ኑሮ የሚባለው ነገር ምንም ዋስትና እንደሌለው ተረዳሁ። ግንኙነታችንን ማቋረጡ በጣም ከባድና ትግል ቢጠይቅም ውሳኔ ላይ ደረስኩ። ምንም እንኳ በገንዘብ ረገድ የምቸገር ቢሆንም በሙሉ ልቤ በይሖዋ መታመን ነበረብኝ።

ይሖዋን ስለምወደው እሱን ለማገልገል ወሰንኩ። ግንቦት 19, 1984 በውኃ በመጠመቅ ሕይወቴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን አሳየሁ። ልጄ ላየኔልም የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ነው። ቤተሰቦቼና የቀድሞ ባለቤቴ ከፍተኛ ስደት ቢያደርሱብንም በይሖዋ ላይ መታመናችንን ቀጥለናል። ይሖዋ አላሳፈረንም። ቤተሰቦቼ 11 ዓመታት ከፈጀ ጊዜ በኋላ ተቃውሟቸውን አቁመው አዲስ የሕይወት መንገዳችንን ተቀበሉልን።

ቤተሰቦቼን በጣም እወዳቸዋለሁ፤ በመሆኑም እነሱም ደስታ ማግኘት እንዲችሉ ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። በመንፈስ ጭንቀትና ራስን በማጥፋት ስሜት እንደተያዝኩ ይሰማው የነበረው አባቴ በድፍረት ይሟገትልኝ ጀመር። እንደገና ደስተኛ ሆኜ በማየቱ ደስ ብሎታል። ወደ ይሖዋ መጸለይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የአምላክን ቃል በሥራ ማዋል በስሜታዊ ሁኔታ ለማገገም አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን ተገንዝቤአለሁ።

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለኝ ተስፋ

የሥቃይ፣ የአለፍጽምና፣ የውሸትና የጥላቻ ርዝራዥ ባጠቃላይ ሙሉ በሙሉ የሚወገድበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። የምንኖርበት የናቫሆ ምድር በፊት በነበሩት የኮክና የፕሪም ዛፎች እንዲሁም ስፍር ቁጥር በሌላቸው እፅዋት ሲያብብ ይታየኛል። የተለያየ ጎሳ ያላቸው ሰዎች በወንዞችና በዝናብ እየታገዙ ምድረ በዳ የሆነውን አገራቸውን ውብ ወደሆነ ገነት በመለወጡ ሥራ በደስታ ሲሳተፉ በዓይነ ህሊናዬ ይታየኛል። የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደሚያሳየው ጎረቤቶቻችን ከሆኑት ከሆፒዎችና ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ባላንጣዎች ከመሆን ይልቅ ርስት ተጋርተን በሰላም ስንኖር ይታየኛል። የአምላክ ቃል ሁሉንም ዘሮች፣ ጎሳዎችና ወገኖች እንዴት እንደሚያስተባብር መገንዘብ ችያለሁ። ወደፊት ደግሞ በትንሣኤ አማካኝነት ቤተሰቦች እንዲሁም ጓደኛሞች በሞት ከተለዩአቸው የሚያፈቅሯቸው ሰዎች ጋር ሲገናኙ አያለሁ። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶልን በታላቅ ደስታ የምንኖርበት ጊዜ ይሆናል። ይህን ግሩም ተስፋ ማወቅ የማይፈልግ ሰው ይኖራል ብዬ መገመት ይከብደኛል።

በናቫሆ ምድር የታየ ቲኦክራሲያዊ እድገት

በቱባ ሲቲ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቶ መመልከቱ እንዲሁም ለሕንዳውያን በተሰጡት በናቫሆና በሆፒ ክልሎች * ላይ ቺንሊ፣ ኬዬንታ፣ ቱባ ሲቲ እና ኪምስ የሚባሉ አራት ጉባኤዎች ሲቋቋሙ ማየቱ በጣም ያስደስታል። በ1983 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ስመዘገብ አንድ ቀን ትምህርት ቤቱ በናቫሆ ቋንቋ ይካሄድ ይሆናል የሚል ምኞት ነበረኝ። ይህ እንዲሁ ምኞት ብቻ ሆኖ አልቀረም። ከ1998 አንስቶ ትምህርት ቤቱ በናቫሆ ቋንቋ ሲካሄድ ቆይቷል።

አምላክ የግል ስም እንዳለው ለሌሎች ማሳወቄ ብዙ በረከቶች አስገኝቶልኛል። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!፣ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? እና በቅርቡ በወጣው የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ! በተባሉት በናቫሆ ቋንቋ በተተረጎሙ ብሮሹሮች ላይ የሚገኙትን እምነት የሚያጠናክሩ መግለጫዎች በራሳችን ቋንቋ ማንበብና ለሌሎች ማካፈል መቻላችን ያስገኘልንን ደስታ በቃላት መግለጽ ያዳግታል። ዲኔ የሚባሉትን የናቫሆ ሕዝቦች ጨምሮ ሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች እንዲጠቀሙ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል ይህን መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመምራቱ በጣም አመስጋኝ ነኝ።​—⁠ማቴዎስ 24:​45-47

ራሴን ችዬ ለመኖር ሙሉ ቀን የምሠራ ብሆንም በየጊዜው በረዳት አቅኚነት አገልግሎት እካፈላለሁ። ነጠላነቴን የማደንቅ ከመሆኑም በላይ ሐሳቤ ምንም ሳይከፋፈል ይሖዋን የማገልገል ምኞት አለኝ። ወገኖቼ ለሆኑትም ሆነ ለሌሎች በተለይ ደግሞ ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች ‘እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነ እና መንፈሳቸው የተሰበረውንም እንደሚያድናቸው’ በማሳወቄ እርካታና ደስታ አግኝቻለሁ።​—⁠መዝሙር 34:​18

አሁን መጽሐፍ ቅዱስን የነጮች ሃይማኖት መጽሐፍ እንደሆነ አድርጌ አልመለከተውም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለመማርና ተግባራዊ ማድረግ ለሚፈልግ ሰው ሁሉ የተጻፈ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችሁ ሲመጡ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምትችሉበትን መንገድ እንዲያሳዩአችሁ ፍቀዱላቸው። ሕይወቴ እንዲለወጥ ስላደረገው፣ ይሖዋ ስለሚባለው የአምላክ ስም ምሥራች ይነግሯችኋል! “አዎን፣ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ስለ ሞርሞን ሃይማኖት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የኅዳር 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።

^ አን.7 ኤ አይ ኤም አንድ የአሜሪካ ሕንዳዊ በ1968 ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ነው። ኤ አይ ኤም አብዛኛውን ጊዜ፣ ከውጭ ሲታይ የአገሪቱን ሕንዶች ደህንነት የሚያስጠብቅ የሚመስለውን በ1824 የተቋቋመውን ቢ አይ ኤ የተባለውን መንግሥታዊ ድርጅት ያወግዛል። አብዛኛውን ጊዜ ቢ አይ ኤ ለሕንዳውያን በተከለሉት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ማዕድን፣ ውኃ እና ሌሎች አንጡራ ሀብቶችን ሕንዳውያን ላልሆኑ ሰዎች በሊዝ ይሰጣል።​—⁠ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ

^ አን.9 የአበባ ብናኝ እንደ ቅዱስ ነገር የሚታይ ሲሆን ሕይወትንና መታደስን በማመልከት ለጸሎትና ለአምልኮ ሥርዓት ያገለግላል። ናቫሆዎች አንድ ሰው የአበባ ብናኝ በተነሰነሰበት የእግር መንገድ ላይ ከተጓዘ ሰውነቱ ቅዱስ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።​—⁠ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ኔቲቭ አሜሪካን ሪሊጅንስ

^ አን.25 አሁን መታተም ያቆመ የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁት መጽሐፍ ነው።

^ አን.39 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአሜሪካ ሕንዳውያን​—⁠የወደፊት ዕጣቸው ምንድን ነው?” በሚል የመስከረም 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጡትን ርዕሶች ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የናቫሆ ጎጆ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጄ ከላየኔል ጋር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1993 ሞስኮ ውስጥ በተካሄደው ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከሩሲያውያን ወንድሞች ጋር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሪዞና ኬዬንታ ጉባኤ ከሚገኙት መንፈሳዊ ቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ