በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተላላፊ በሽታዎች አደገኛ ቢሆኑም መከላከል ይቻላል

ተላላፊ በሽታዎች አደገኛ ቢሆኑም መከላከል ይቻላል

ተላላፊ በሽታዎች አደገኛ ቢሆኑም መከላከል ይቻላል

ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጦችና የጎርፍ አደጋዎች የመጀመሪያውን የጋዜጣ ገጽ የሚሸፍኑ ዜናዎች ቢሆኑም ድምፅ አልባው የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ግን እምብዛም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ አይመስልም። ያም ሆኖ “(እንደ ኤድስ፣ ወባ፣ የመተንፈሻ አካላት ህመምና ተቅማጥ ባሉት) ተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት በተፈጥሮ አደጋ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በ160 እጥፍ እንደሚበልጥ” የቀይ መስቀል/ቀይ ጨረቃ ሕብረት ሰኔ 2000 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ሁኔታው ደግሞ በመባባስ ላይ ነው።”

ለዚህ አስደንጋጭ ቁጥር አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚገመቱ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ሲሆን አንደኛው በየሰዓቱ 300 ሰዎችን በመግደል ላይ ያለው የኤድስ በሽታ የማያቋርጥ ስርጭት ነው። ኤድስ “በሽታ መሆኑ ቀርቶ መቅሰፍት ሆኗል” በማለት የዓለም የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ሕብረት የተፈጥሮ አደጋዎች መከላከያ ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ዎከር ገልጸዋል። “በስፋት የተሰራጨው ይህ በሽታ የሠራተኛውን ኃይል ከማመናመኑም በተጨማሪ ኢኮኖሚውን አዳክሟል።” ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የሕዝባዊ ጤና አጠባበቅ ዘዴዎች እያዘቀጡ መሄድ ነው። ይህ ሁኔታ ቀድሞ በመጠኑም ቢሆን በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ ቂጥኝና ወባ የመሳሰሉ በሽታዎች እንዲያገረሹ ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ አንድ የእስያ አገር በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ 40, 000 የሚያክሉ አዳዲስ የሳንባ ነቀርሳ ህመምተኞች እንደሚያስተናግድ ሪፖርት አድርጓል። በአንዲት የምሥራቅ አውሮፓ አገር ባለፈው አሥርተ ዓመት በቂጥኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ40 እጥፍ አድጓል።

ተላላፊ በሽታዎች የሰው ልጅ ሊከላከላቸው ከሚችላቸው ችግሮች መካከል ሆነው ሳለ መቅሰፍት ሆነው መገኘታቸው የሚያስገርም ነው። እንዲያውም “ለእያንዳንዱ ሰው የጤና እንክብካቤ የሚውል 5 የአሜሪካን ዶላር በመመደብ” በ1999 በተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ ከሞቱት 13 ሚልዮን ሰዎች መካከል አብዛኞቹን ከሞት መታደግ ይቻል እንደነበር” ሪፖርቱ ጠቁሟል። የዓለም መንግሥታት ለእያንዳንዱ ሰው የጤና እንክብካቤ የሚውል 5 ዶላር (በጠቅላላው 30 ቢልዮን ዶላር) ለመመደብ ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ ምን ያህል ሰዎችን ከሞት መታደግ ይቻል እንደነበር አስብ!

ምንም እንኳ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቢሆንም ዓለም ለሌሎች ተግባራት ከሚያውለው ገንዘብ ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ዓለም ለጦርነት የሚያውለው ገንዘብ 864 ቢልዮን ዶላር መድረሱ ይታወቃል። ይህ ቁጥር በአንድ ሰው ሲሰላ 144 ዶላር ማለት ነው። ዓለም የበሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለጦርነት የሚያውለውን ተጨማሪ ገንዘብ እስቲ አስብ! የሰው ልጅ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት መግታት የተሳነው ይበልጥ ውስብስብ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች እንጂ በገንዘብ ማጣት አይመስልም። ሌላው ቀርቶ ሰብዓዊ መንግሥታት ቅድሚያ በሚሰጧቸው ነገሮች ረገድ እንኳ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ አልቻሉም።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ራጂ:- New Jersey Medical School​—National Tuberculosis Center

የሚያስል ሰው ፎቶ:- WHO/Thierry Falise