በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፍ የጥላቻ ወረርሽኝ

ዓለም አቀፍ የጥላቻ ወረርሽኝ

ዓለም አቀፍ የጥላቻ ወረርሽኝ

ጥላቻ የተባለ አንድ ጭራቅ ተለቅቋል። ይህ ጭራቅ መላዋን ምድር እያመሳት ነው።

በባልካን የምትገኝ አንዲት ግዛት በቅርቡ በተካሄደ የዘር ማጽዳት ዘመቻ መዘዝ ፍዳዋን እያየች ነው። ለብዙ መቶ ዓመታት ተዳፍነው የቆዩ ጥላቻዎች በመፈንዳታቸው የጅምላ ጭፍጨፋና የግዳጅ ወሲብ ተፈጽሟል፣ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ቤቶቻቸውና መንደሮቻቸው በእሳት ጋይተዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ሰብላቸውና ከብቶቻቸው ወድመዋል፣ ራሳቸውም ለረሃብና ለችጋር ተጋልጠዋል። ዛሬም ድረስ ብዙ የተቀበሩ ፈንጂዎች ይገኛሉ።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ በምትገኘው ኢስት ቲሞር ግድያውን፣ ድብደባውን፣ እገሌ ከእገሌ ሳይባል በጥይት መቆላቱንና በኃይል ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀልን የፈሩ 700, 000 ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው ለመሸሽ ተገድደዋል። ትተዋት የሄዱት ከተማ በሚሊሻ ኃይሎች ወድማለች። የችግሩ ተጠቂ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዱ “ለአደን የሚፈለግ እንስሳ እንደሆንኩ ያህል ነው የተሰማኝ” ሲል አማርሯል።

በሞስኮ ሽብርተኞች ባደረሱት ከባድ የቦምብ ጥቃት አንድ የመኖሪያ ሕንጻ ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል። በፍንዳታው የ94 ንጹሐን ሰዎች አስከሬን በየቦታው የተረፈረፈ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ሕፃናት ነበሩ። በጥቃቱ ከ150 በላይ ሰዎች ቆስለዋል። ይህ አሠቃቂ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሰዎች የሚጠይቁት ጥያቄ ‘የሚቀጥለው ማን ይሆን?’ የሚል ነበር።

በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ዘረኝነትን የሚያራምድ አንድ ሰው አይሁዳዊ በሆኑ የመዋዕለ ሕፃናት ተማሪዎች ላይ ባወረደው የጥይት እሩምታ አንድ የፊሊፒንስ ተወላጅ የሆነ ፖስታ አመላላሽ ገድሏል።

በእርግጥም ጥላቻ ምድር አቀፍ ወረርሽኝ ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በየዕለቱ ለማለት ይቻላል የሚወጡ የዜና ዘገባዎች በዘር፣ በጎሳ ወይም በሃይማኖት ጥላቻዎች ምክንያት ስለተፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶች ያወሳሉ። ብሔራት፣ ማኅበረሰቦችና ቤተሰቦች ሲበታተኑ እናያለን። አገሮች በጅምላ ጭፍጨፋ ሲበጣበጡ እንመለከታለን። የተወሰኑ ሰዎች “የተለዩ” ሆነው ስለተገኙ ብቻ በቃላት ለመግለጽ የሚቸግር ዘግናኝ ጭካኔ ሲፈጸምባቸው እናያለን።

ጥላቻ የሚባለው ጭራቅ እንዲታሠር ካስፈለገ በጥላቻ የሚፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶች መንስኤያቸው ምን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልገናል። ጥላቻ በሰው ልጆች በራሂ ውስጥ ያለ ነገር ነው? ከጊዜ በኋላ የሚዳብር ባሕርይ ነውን? የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ ይቻል ይሆን?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Kemal Jufri/Sipa Press