በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማን ነው?

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማን ነው?

‘የክርስቶስ ተቃዋሚ እንደሚመጣ ሰምታችኋል።’​—⁠ዮሐንስ 2:​18

በጣም አደገኛ የሆነ አንድ ወንጀለኛ ወደምትኖርበት አካባቢ እየመጣ መሆኑን የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ ቢደርስህ ምን ታደርጋለህ? ሰውዬው ምን እንደሚመስልና የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ ለማግኘት መጣርህ አይቀርም። ከዚያም በተጠንቀቅ መጠበቅ ትጀምራለህ።

በዛሬው ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆናል:- “ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፣ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” (1 ዮሐንስ 4:​3) በአሁኑ ጊዜ ለሰው ልጆች ደኅንነት አስጊ የሆነ የአምላክ ጠላትና ሰዎችን የሚያታልል እንዲህ ዓይነት የክርስቶስ ተቃዋሚ አለን?

ዮሐንስ በሁለት መልእክቶቹ ላይ “የክርስቶስ ተቃዋሚ” የሚለውን ቃል አምስት ጊዜ ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠውን ትምህርት የሚቃወምን አካል ከማመልከቱም በተጨማሪ ክርስቶስን መስለው የሚመጡ ወይም የእሱ መልእክተኞች ነን የሚሉ አስመሳዮችን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ተቃዋሚን በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ይሰጣል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስለ ወንጀለኞች የሚናፈሰው ከእውነታው የራቀ ወሬ የብዙዎችን ጆሮ እንደሚያገኝ ሁሉ ይህን ምሥጢራዊ አካል በተመለከተ የሚቀርበው የተዛባ መረጃም ከእውነታው የበለጠ ሰፊ ትኩረት አግኝቷል።

ማንነቱን በትክክል አለመረዳት

ከሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን አንስቶ ሰዎች ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ተቃዋሚ የሰጠው መግለጫ አንድን የተወሰነ ግለሰብ እንደሚያመለክት ሲናገሩ ቆይተዋል። የክርስቶስ ተቃዋሚ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የገመቷቸውን የተለያዩ ግለሰቦች ሲጠቅሱ ቆይተዋል። ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ የክርስቶስ ተቃዋሚ እንደሆነ ብዙዎች አስበው ነበር። ከጊዜ በኋላ አዶልፍ ሂትለር ጥላቻና ሽብር እንዲነግሥ ማድረጉ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚ እሱ ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ሌላው ቀርቶ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬደሪክ ኒትሽ እንኳ ይህ መጠሪያ ተሰጥቶታል። ሌሎች ደግሞ የክርስቶስ ተቃዋሚ ገና እንዳልመጣና ዓለምን የመግዛት ዓላማ ያለው መሠሪና ጨካኝ የፖለቲካ ሰው ሆኖ እንደሚገለጥ ያምናሉ። በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሰው አውሬ ዮሐንስ የክርስቶስ ተቃዋሚ ያለውን በቀጥታ እንደሚያመለክት ያምናሉ። ይህ ቀንደኛ የክፋት አራማጅ ተለይቶ የሚታወቀው ልዩ ምልክቱ በሆነው በ666 ነው ይላሉ።

እነዚህን ሐሳቦች የሚያራምዱ ሰዎች ዮሐንስ የተናገረው ስለ አንድ የክርስቶስ ተቃዋሚ ብቻ ነው የሚል ግምት አላቸው። ሆኖም ዮሐንስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያሳያሉ? 1 ዮሐንስ 2:​18 ምን እንደሚል ልብ በል:- “የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል።” አዎን፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለተፈጠረው መንፈሳዊ ቀውስ ተጠያቂዎቹ “ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” እንጂ አንድ ግለሰብ ብቻ አልነበረም። ዛሬም የክርስቶስ ተቃዋሚ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ተቃዋሚዎችን ያቀፈ ቡድን ነው። በቡድን ደረጃ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ መንፈሳዊ ውድቀት አስከትለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13) በቡድን ደረጃ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች እነማን ናቸው?

በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሰው አውሬ የክርስቶስ ተቃዋሚ ሊሆን ይችል እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፣ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፣ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ።” (ራእይ 13:2፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህ አገላለጾች ምን ያመለክታሉ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በራእይ ምዕራፍ 13 እና በዳንኤል ምዕራፍ 7 መካከል ዝምድና መኖሩን ተገንዝበዋል። አምላክ ነብር፣ ድብና አንበሳን ጨምሮ ምሳሌያዊ አራዊትን የያዘ ራእይ ለዳንኤል ገልጦለት ነበር። (ዳንኤል 7:​2-6) የአምላክ ነቢይ ለእነዚህ አራዊት የሰጠው ፍቺ ምንድን ነው? እነዚህ አራዊት ምድራዊ ነገሥታትን ወይም መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ ጽፏል። (ዳንኤል 7:​17) ስለዚህ ራእይ ላይ የተጠቀሰው አውሬ ሰብዓዊ መንግሥታትን ይወክላል ብለን ብንደመድም ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል። እነዚህ መንግሥታት የአምላክን መንግሥት ስለሚቃወሙ የክርስቶስ ተቃዋሚ ቡድን ክፍል ናቸው።

ሌሎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች እነማን ናቸው?

የአምላክ ልጅ የሆነው ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ብዙ ጠላቶች ነበሩት። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በሥጋዊ አካል ሊገኝ ባይችልም በዚህ ባለንበት ዘመን ባላጋራዎች አሉት። ከእነዚህ ባላጋራዎች መካከል እነማን እንደሚገኙበት ልብ በል።

ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።” (1 ዮሐንስ 2:​22) ከሃዲዎችና የሐሰት አምልኮ መሪዎች ኢየሱስ ያቀረበውን ግልጽ የሆነ ትምህርት በሃይማኖታዊ ማታለያ ተብትበው አጣምመውታል። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ትተው በአምላክና በክርስቶስ ስም ውሸት ያዛምታሉ። በሚያስተምሩት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አማካኝነት በአብና በወልድ መካከል ያለውን ትክክለኛ ዝምድና ይክዳሉ። ስለዚህ እነሱም የክርስቶስ ተቃዋሚ ክፍል ናቸው።

ኢየሱስ በሉቃስ 21:​12 ላይ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ እንዲህ ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል:- “እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኩራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል።” ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጭካኔ የተሞላበትን ስደት በጽናት ተቋቁመዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12) የዚህ ዓይነቱ ስደት ቆስቋሾች ክርስቶስን ይቃወማሉ። እነሱም ቢሆኑ የክርስቶስ ተቃዋሚ ክፍል ናቸው።

“ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፣ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።” (ሉቃስ 11:23) እዚህ ላይ ኢየሱስ እሱንና እሱ የሚያራምደውን መለኮታዊ ዓላማ የሚቃወሙ ሁሉ በክርስቶስ ተቃዋሚ ጎራ እንደሚመደቡ ገልጿል። ተቃዋሚዎቹ የሚጠብቃቸው የመጨረሻ ዕጣ ምንድን ነው?

የክርስቶስ ተቃዋሚዎችን ምን ይጠብቃቸዋል?

መዝሙር 5:​6 “ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል” ይላል። ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚዎችን የሚመለከት ነውን? አዎን። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።” (2 ዮሐንስ 7) የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ውሸታሞችና አታላዮች በመሆናቸው ሁሉን ቻይ አምላክ ያጠፋቸዋል።

ይህ ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ እውነተኛ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ተቃዋሚ የሚጠቀምበት ማታለያና ግፊት (በተለይ ከሃዲዎች የሚያመነጩት) እምነታቸውን እንዳያዳክም መከላከል አለባቸው። ዮሐንስ “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ሲል አሳሳቢ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።​—⁠2 ዮሐንስ 8

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ኔሮ በገጽ 2 እና 28 ላይ:- Courtesy of the Visitors of the Ashmolean Museum, Oxford