የደረሰብንን እጅግ አሳዛኝ መከራ መቋቋም
የደረሰብንን እጅግ አሳዛኝ መከራ መቋቋም
ጄምስ ጄራኖ እንደተናገረው
የልጅ ልጅ ማየት በሕይወት ውስጥ በጣም ከሚያስደስቱ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። እኔና ባለቤቴ ቪኪ የመጀመሪያ የልጅ ልጃችን የሚወለድበትን ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቅን ነበር። ሴት ልጃችን ቴሬዛ እና ባለቤቷ ጆናታን ጥቅምት 2000 መጀመሪያ አካባቢ ልጅ ይወልዳሉ። ማንኛችንም ብንሆን እጅግ አሳዛኝ መከራ ይደርስብናል የሚል ግምት አልነበረንም።
እኔና ባለቤቴ ከወንድ ልጃችንና ከባለቤቱ ጋር ቅዳሜ መስከረም 23 ለእረፍት ሄደን ነበር። ከሌሎች ዘመዶቻችን ጋር ሰሜን ካሮላይና በሚገኘው ኦውተር ባንክስ የመዝናኛ ስፍራ ተገናኝተን እዚያ አንድ ሳምንት እንቆያለን። ቴሬዛ ዘጠነኛ ወሯ ገብቶ ስለነበርና ቦታው ከመኖሪያ ቤታችን ከኦሃዮ በመኪና ወደ 11 ሰዓት ገደማ የሚያስኬድ ስለሆነ እሷና ጆናታን ለእረፍት አብረውን ለመሄድ አልፈለጉም።
የእረፍት ጉዟችንን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ፈልገን ነበር፤ ሆኖም ቴሬዛ መቅረት እንደሌለብንና ስለ እሷ ምንም የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ ነገረችን። ከዚህም በተጨማሪ ሐኪሟ በቀንዋ እንደምትወልድና ሁለት ሳምንት እንደሚቀራት ነግሯታል።
ረቡዕ መስከረም 27, 2000 ቤተሰባችን ላለፉት በርካታ ዓመታት የዕረፍት ጊዜውን በዚህ አካባቢ ለማሳለፍ የመረጠበትን ምክንያት እንዳስታውስ ያደረገኝ በጣም አስደሳች ቀን ነበር። በዚያኑ ዕለት ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነገር እንደሚገጥመን የተገነዘበ አልነበረም።
“ቴሬዛ ጠፋች!”
የዚያን ዕለት ምሽት ወንድሜ ከኦሃዮ ስልክ ደወለልኝ። ምን ብሎ እንደሚነግረኝ ግራ ከመጋባቱም በላይ በጣም ተረብሾ ነበር። በመጨረሻ እንደምንም ብሎ “ቴሬዛ ጠፋች!” በማለት ተናገረ። በመጥፋቷ ዙሪያ የተከሰቱት ሁኔታዎች ከፍተኛ ጥርጣሬን የሚፈጥሩ ስለነበሩ ፖሊሶች ጉዳዩን መከታተል ጀመሩ። ጆናታን የዚያን ዕለት ከሰዓት ወደ ቤት ሲመለስ የፊት ለፊቱን በር ክፍት ሆኖ አገኘው። የቴሬዛ ቁርስ ጠረጴዛው ላይ እንደተቀመጠ ሲሆን ቦርሳዋም አጠገቡ አለ። እንግዳ የሆነው ሌላው ነገር ደግሞ ዘጠነኛ ወሯ ከገባ በኋላ ይሆናት የነበረው ብቸኛ ጫማ በሩ አጠገብ መገኘቱ ነው።
ጆናታን ጠዋት 3:30 ላይ ቤት ሲደውል ቴሬዛ አንዲት ሴትዮ ደውላ እንደነበረና ለመሸጥ ያሰቡትን መኪና ለማየት እመጣለሁ እንዳለቻት ነግራው ነበር። ከዚያ በኋላ ቴሬዛ ለቤተሰቡ አንዳንድ ነገሮችን ለመገዛዛት ወጣ ማለት ነበረባት። ጆናታን በምሳ ሰዓት ወደ ቤት ቢደውል ሊያገኛት አልቻለም። ከሰዓት በኋላም በተደጋጋሚ ሲደውል ስልኩን የሚያነሳ አልነበረም። አሥር ሰዓት ከሩብ ላይ ቤት ሲመጣ መኪናዋ እንደሌለች ተመለከተ። ምናልባት ቴሬዛ ምጥ ይዟት ወደ ሆስፒታል ሄዳ ይሆናል ብሎ
በማሰብ ሆስፒታል ደወለ። እዚያም አልነበረችም። አንዳንድ ዘመዶቻችን ጋ ደውሎ ቢጠይቅም አንዳቸውም አላዩአትም። ሁኔታው ስላስጨነቀው ወደ ፖሊስ ደወለ። ፖሊስ 12:00 ሰዓት ገደማ ላይ መኪናዋን ከቤታቸው ብዙም በማይርቅ ቦታ ላይ አገኛት። ቴሬዛ ግን አልተገኘችም።በሰሜን ካሮላይና እንዳለን መጥፋቷን ስንሰማ በጣም ደነገጥን። እኔና ባለቤቴ ከልጃችንና ከባለቤቱ ጋር ጓዛችንን ጠቅልለን ወደ ቤት ጉዞ ጀመርን። ያን ረጅም ጉዞ ያደረግነው በጣም ተረብሸን ነበር። ሌሊቱን በሙሉ ስንጓዝ አድረን በማግሥቱ ጠዋት ኦሃዮ ደረስን።
ፍንጭ ተገኘ
ጆናታን፣ አንዳንድ ዘመዶቻችን፣ የቅርብ ወዳጆቻችንና ሌሎች ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ ከፖሊሶች ጋር ቴሬዛን ሲፈልጉ ነበር ያደሩት። ፍለጋው ለአምስት አስጨናቂ ቀናት ቀጠለ። በመጨረሻ ሰኞ ጥቅምት 2 አንድ ፍንጭ ተገኘ። በዚህ ጊዜ ፖሊስ ረቡዕ ጠዋት ለቴሬዛ የተደወለው ከየት እንደሆነ ደረሰበት። ሞባይል ስልክ በመጠቀም የደወለችው እዚያው ሠፈር የምትኖር አንዲት ሴት ነች።
ፖሊሶች ሴትየዋን ካነጋገሯት በኋላ ጥርጣሬ አደረባቸው። የዚያን ዕለት ምሽት ፖሊስ ወደ ሴትየዋ ቤት ተመልሶ ሄደ። ሆኖም በር አካባቢ ሲደርሱ የተኩስ ድምፅ ሰሙ። ሰብረው ሲገቡ ሴትየዋን ሞታ አገኟት። ሴትየዋ በጥይት ራሷን ገድላለች። በጣም የሚገርመው በሁለተኛው ፎቅ በአንድ ክፍል ውስጥ አራስ ልጅ አገኙ። አገር ሲሸበር እሱ ለጥ ብሎ ተኝቷል!
ሆኖም ቴሬዛ ያለችበትን የሚጠቁም ምንም ነገር አልተገኘም። ለሚቀጥሉት ጥቂት ሰዓታት ፖሊስ ቤቱን አንድም ሳይቀር ቢፈትሽም ቴሬዛ እዚያ እንደነበረች የሚጠቁም አንዳች ፍንጭ ማግኘት አልተቻለም። ቴሬዛን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ በጋራዡ ውስጥ ተጠናቀቀ። የቴሬዛ አስከሬን ጋራዡ ውስጥ ጫር ጫር ተደርጎ ተቀብሮ ተገኘ። ሬሳ መርማሪው በሆነ ነገር ተመትታ ራሷን ከሳተች በኋላ ከጀርባ በጥይት መመታቷን አረጋገጠ። ወዲያውኑ የሞተች ሲሆን ከዚያም ማሕፀኗ ተቀድዶ ልጁ ተወስዷል። ሁኔታውን መለስ ብዬ ሳስበው ለብዙ ጊዜ ያልተሰቃየች በመሆኑ ከፍተኛ እፎይታ ተሰምቶኛል።
ሕፃኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ይኸውም አንዲት ጭረት እንኳ እንዳላረፈበት ታወቀ! በተደረገው የዲ ኤን ኤ ምርመራ በእርግጥ የልጃችን ልጅ መሆኑ ተረጋገጠ። ጆናታን አስቀድመው ከቴሬዛ ጋር ሆነው የመረጡለትን ኦስካር ጋቪን የተባለ ስም አወጣለት። ለጥቂት ቀናት ሆስፒታል ከቆየ በኋላ ወደ 4 ኪሎ ገደማ የሚመዝነው የልጃችን ልጅ ሐሙስ ጥቅምት 5 አባቱ እንዲወስደው ተደረገ። የልጅ ልጃችንን በማግኘታችን በጣም የተደሰትን ቢሆንም ቴሬዛ እሱን ለማቀፍ ባለመታደልዋ ምን እንደተሰማን በቃላት መግለጽ ያስቸግራል።
ኅብረተሰቡ ያደረገልን
እኔና ቤተሰቤ በአብዛኛው ፈጽሞ የማናውቃቸው በጣም ብዙ ሰዎች እኛን ለመርዳት ሲረባረቡ ስናይ እንባችንን መቆጣጠር አልቻልንም። ቴሬዛ ጠፍታ በነበረችባቸው ቀናት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በፍለጋው ተባብረዋል። ብዙዎች ገንዘብ ለግሰዋል። በአካባቢው ያሉ ብዙ የቢሮ ዕቃዎች መሸጫ መደብሮች በሺህ የሚቆጠሩ የአፋልጉኝ ጥሪ ወረቀቶችን በነፃ አትመውልን የነበረ ሲሆን ሌሎች ሰዎች ደግሞ ወረቀቶቹን የቴሬዛ ቤት ከሚገኝበት እስከ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ በማሰራጨት ተባብረዋል።
በአካባቢው በሚገኝ የአንድ ጠበቃ ቢሮ ተቀጥራ የምትሠራ አንዲት ክርስቲያን እህታችን የደረሰብንን ለጠበቃው ስታጫውተው ሊረዳን እንደሚፈልግ ነገራት። እኛም እንዲረዳን የተስማማን ሲሆን ጠበቃው በእጅጉ ጠቅሞናል። ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን እንዲሁም ከችግሩ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሕግ ነክ ጉዳዮችን እንድናስጨርስ ረድቶናል። ከዚህም በተጨማሪ ጉዳዩን በመከታተል ከፍተኛ እገዛ ካደረጉልን ሁለት የግል መርማሪዎች ጋር እንድንነጋገር ሐሳብ አቀረበልን። እነርሱ ባሳዩን አሳቢነት በእርግጥ ልባችን ተነክቷል።
የልጅ ልጃችን ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ እርዳታው ተጠናክሮ ቀጠለ። ብዙ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መደብሮች ምግብና የቤት ዕቃዎች ላኩልን። ብዙ ግለሰቦች ለኦስካር የሚሆኑ ልብሶች እንዲሁም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሽንት ጨርቆች፣ የዱቄት ወተትና አሻንጉሊቶች ለግሰውናል። ያገኘነው እርዳታ ኦስካር ሊጠቀምበት ከሚችለው በላይ ስለነበረ ትርፉን በአካባቢው ለሚገኝ የአንድ ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ሰጠን። የመገናኛ ብዙሃን የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ ዘግቦ ስለነበር በአካባቢያችን ከሚገኘው ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ከዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ ካርዶችና ደብዳቤዎች ደርሰውናል።
በተለይ ደግሞ ሰዎች ያደረጉልንን ድጋፍ በገሃድ ያየነው እሁድ ጥቅምት 8 የቴሬዛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ንግግር በተሰጠበት ዕለት ነው። በቀብሩ ላይ ብዙ ሰዎች መገኘት
እንደሚፈልጉ ብናውቅም የተገኙት ሰዎች ቁጥር ግን ከገመትነው በላይ ነው። በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመጠቀም ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ሲሆን አዳራሹ ከ1, 400 በሚበልጡ ሰዎች ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ዘመዶቻችን፣ ወዳጆቻችን፣ የፖሊስ መኮንኖች፣ የከተማው ከንቲባና ሌሎች የአካባቢው ሰዎች ተገኝተው ነበር። የመገናኛ ብዙሃን ሰዎችም ተገኝተው የነበረ ሲሆን የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ንግግሩን በቪዲዮ የቀዳ ከመሆኑም በላይ በኢንተርኔት አማካኝነት በቀጥታ ተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በትምህርት ቤቱ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ሆነው ወይም በቀዝቃዛው ዝናብ ውስጥ ጃንጥላ ይዘው በድምፅ ማጉያ የሚተላለፈውን ንግግር ያዳምጡ ነበር። የቀረበው ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነታችን ሰፊ ምሥክርነት ሰጥቷል።ከዚያ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰልፍ ይዘው በትዕግሥት በመጠባበቅ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸውልናል። እዚያ የተገኙትን ሁሉ አቅፈን ሰላም ስንልና የተሰማንን አድናቆት ስንገልጽላቸው ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ቆየን። ከቀብር መልስ በአካባቢው ያለ አንድ ሆቴል ከ300 ለሚበልጡ ዘመዶቻችን፣ ለቅርብ ወዳጆቻችንና የልጅ ልጃችን ወደ ቤት ሲመለስ ለረዱን ሌሎች ሰዎች ምግብ በማቅረብ ደግነት አሳይቶናል።
ሰዎች በተለይም የማናውቃቸው ሰዎች እኛን ለመርዳት ስላደረጉት ርብርቦሽ ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል። ይህ ተሞክሮ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሊነገራቸው የሚያስፈልጋቸው በጣም ብዙ ሩኅሩኅ ሰዎች መኖራቸውን እንድንገነዘብ ስላስቻለን አቅማችን በፈቀደ መጠን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመሳተፍ ከበፊቱ በበለጠ ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ አነሳስቶናል።—ማቴዎስ 24:14
ጉባኤው ያደረገው ርብርብ
ይህ ከባድ ሐዘን ከደረሰብን ጊዜ አንስቶ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እኛን ለመርዳት ተረባርበዋል። ይህን ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረጉልን የጉባኤያችንና በአካባቢያችን ያሉ ጉባኤዎች አባላት ነበሩ።
ከሰሜን ካሮላይና ተመልሰን ቤት ከመድረሳችን በፊት የጉባኤያችን ሽማግሌዎች ቴሬዛን ለመፈለግ ሌሎችን አስተባብረዋል። ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በፍለጋው ለመተባበር ከመሥሪያ ቤታቸው ፈቃድ ወስደዋል። አንዳንዶቹ ከክፍያ ነጻ የሆነ ፈቃድ እንዲሰጣቸው አሠሪዎቻቸውን የጠየቁ ቢሆንም አንዳንድ አሠሪዎች ክፍያ ያለው ዕረፍት ፈቅደውላቸዋል። ቴሬዛ በጠፋችባቸው ቀናት ጆናታን ብቻውን እንዳይሆን አንዳንድ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን አብረውት ይሆኑ ነበር። ብዙ ወንድሞችና እህቶች መጥተው ቤታችንን አጽድተውልናል እንዲሁም አስተካክለውልናል። ሌሎች ደግሞ በፍለጋው ለተሰማሩ ሠራተኞች ምግብ በማብሰልና ስልክ በማንሳት ረድተዋል።
ቴሬዛ ከሞተች ከስድስት ወር በኋላ ባለቤቴና ጆናታን የቴሬዛን ዕቃዎች የመለየትና የማያስፈልጉትንም የማስወገድ ተፈታታኝ ሥራ ገጥሟቸው ነበር። ጆናታን ከቴሬዛ ጋር በኖረበት ቤት ውስጥ ብቻውን መኖር ስላስጠላው ቤቱን ለመሸጥ ወሰነ። የቴሬዛን ዕቃዎች ሲለዩና የማያስፈልጉትን ሲያስወግዱ በነበረበት ጊዜ እያንዳንዱ ነገር እሷንም ሆነ ከእሷ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ ያስታውሳቸው ስለነበር
ሐዘናቸውን አባብሶባቸዋል። በዚህም ጊዜ ቢሆን የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን እርዳታ አልተለየንም። ዕቃዎቿን በማሸግና ሌላው ቀርቶ ቤቱ ከመሸጡ በፊት እድሳት በማድረጉ ረድተውናል።ከሁሉም በላይ ደግሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለቤተሰባችን መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ አድርገውልናል። እኛን ለማጽናናት ስልክ ይደውሉልን እንዲሁም ቤት ድረስ መጥተው ይጠይቁን ነበር። ብዙዎች የሚያጽናኑ ካርዶችንና ደብዳቤዎችን ልከውልናል። እንደዚህ ያለው ፍቅራዊ እርዳታ ለጥቂት ቀናት እና ሳምንታት ብቻ ሳይሆን ለብዙ ወራት ቀጥሎ ነበር።
ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስሜታችንን የሚያዳምጠን ሰው ካስፈለገን በማንኛውም ጊዜ ቀርበን እንድናነጋግራቸው የነገሩን ሲሆን እኛም በደግነት የቀረበውን ይህን ግብዣ ተቀብለናል። ስሜታችሁን በጣም ለምትወዱትና ለምታምኑት ሰው ማካፈል መቻል ምንኛ የሚያጽናና ነው! በእርግጥም “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሠርተውበታል።—ምሳሌ 17:27፤ 18:24
በቤተሰባችን ላይ ያሳደረው ተጽእኖ
የቴሬዛ መገደል በእኔና በቤተሰቤ ላይ ያስከተለብንን የስሜት ስቃይ መቋቋም ቀላል አልነበረም። በእውነቱ ሕይወታችንን ለውጦታል። ከአጠገቤ ላገኛት ባለመቻሌ የምናደድበት ጊዜ አለ። ታቅፈኝና ትስመኝ የነበረው ሁሉ ይናፍቀኛል።
ባለቤቴና ቴሬዛ በጣም ይቀራረቡ ነበር። ቢያንስ ትንሽ እንኳ አብረው ሳይጨዋወቱ ያሳለፉት አንድም ቀን የለም። ስለ ቴሬዛ እርግዝና ለረጅም ሰዓት ያወሩ ነበር። አንድ ላይ የሕፃን አልጋ ሠርተዋል።
ቪኪ የተሰማትን እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “እሷን በማጣቴ ብዙ ነገር ቀርቶብኛል። በስብከቱ ሥራ አብሬያት እካፈል ነበር። አብረን ገበያ እንወጣ ነበር። ይበልጥ የሚያንገበግበኝ ግን ልጅዋን ለማቀፍ አለመታደልዋ ነው። ከመወለዱ በፊት እንኳ ኦስካርን ምን ያህል ትወድደው እንደነበር አውቃለሁ። ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ታውቅ ነበር። ብርድ ልብስ ሠርቼ ከሰጠኋት በኋላ እንዲህ የሚል ካርድ ሰጠችኝ:-
‘ውድ እናቴ፣
የሚያምር የሕፃን ልጅ ብርድ ልብስ ስለሠራሽልኝ በጣም አመሰግንሻለሁ። በእውነቱ ብዙ ነው የደከምሽው። በሕይወቴ ያጋጠሙኝን አንዳንድ ፈታኝ ጊዜያት እንዳልፍ ላደረግሽልኝ እርዳታና ለሰጠሽኝ ማበረታቻ ሁሉ ደግሜ ላመሰግንሽ እወዳለሁ። ምን ጊዜም ሳስታውስሽና ሳመሰግንሽ እኖራለሁ። አንድ ሰው ሲያድግ ከእናት የቀረበ ወዳጅ እንደሌለው ይገነዘባል ሲባል እሰማ ነበር። እኔ ግን ይህን ቶሎ ስለተገነዘብኩ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ምን ጊዜም እወድሻለሁ።’”
የልጃችን ባል ያሳለፈውን ችግር ማየት ራሱ ሐዘናችንን የሚያባብስ ሆኖብን ነበር። ኦስካር ሆስፒታል እያለ ጆናታን አንድ ከባድ ነገር ማድረግ ግድ ሆኖበት ነበር። ለጊዜው ከእኛ ጋር ለመኖር ስለወሰነ እሱና ቴሬዛ የሠሩትን የሕፃን አልጋ ይዞ መምጣት ነበረበት። የመወዝወዣ ፈረስ፣ የሕፃን አልጋውንና አሻንጉሊቶችን ይዞ መጣ።
እንድንቋቋም የረዳን ምንድን ነው?
የምትወዱትን ሰው እንዲህ ባለ አሳዛኝ መንገድ ስታጡ ግራ የሚያጋቡ የተለያዩ ጥያቄዎችና ስሜቶች ይፈጠሩባችኋል። ክርስቲያን ሽማግሌ እንደመሆኔ መጠን ሌሎች እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችና ስሜቶች ሲያጋጥሟቸው እንዳይሸነፉ ለማበረታታትና ለመርዳት ጥረት ያደረግኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ሐዘኑ በእናንተ ላይ ሲደርስ ስሜታችሁና አመለካከታችሁ ይዛባል።
ለምሳሌ ያህል ለአንድ ሳምንት ርቀን ለመሄድ ስንነሳ ቴሬዛ የነበረችበትን ሁኔታ በማሰብ ይሖዋ እንዲጠብቃት ጸሎት አቅርቤ ነበር። ሕይወትዋ በሰው እጅ ሲያልፍ ጸሎቴ ያልተሰማልኝ ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብኝ ነበር። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን በግለሰብ ደረጃ በተአምራዊ መንገድ ለመጠበቅ ቃል እንዳልገባ አውቃለሁ። ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ ስል ሳልታክት ጸሎት አቀረብኩ። ይሖዋ ሕዝቦቹን ይጠብቃል ሲባል የሚጠብቀው በመንፈሳዊ መሆኑን ይኸውም ከእርሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዳይበላሽ መከላከል እንድንችል የሚያስፈልገንን የሚሰጠን መሆኑን ያገኘሁት እውቀት እንድጽናና ረድቶኛል። ይህ ዓይነቱ ጥበቃ ዘላለማዊ ደህንነታችንን ሊነካብን ስለሚችል በጣም አስፈላጊ ነው። ቴሬዛ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት ታገለግለው ስለነበር ይሖዋ በዚህ በኩል ጥበቃ አድርጎላታል ማለት ነው። ወደፊት ሕይወት የማግኘቷ ጉዳይ በእርሱ ፍቅራዊ እጅ ያለ መሆኑን ማወቄ እፎይታ አስገኝቶልኛል።
በተለይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የመጽናናት ምንጭ ሆነውልኛል። ሐዘኑን እንድቋቋም ከረዱኝ ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-
ሥራ 24:15) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚኖር በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ላይ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ እምነት የነበረኝ ሲሆን ይህ ተስፋ አሁን ይበልጥ እውን ሆኖልኛል። ቴሬዛን እንደገና ላገኛት እንደምችል ማወቄ ሐዘኔን እንድቋቋም ብርታት ሰጥቶኛል።
“ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።” (“ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።” (ሉቃስ 20:37, 38) ወደፊት ትንሣኤ የሚያገኙ ሙታን በሙሉ አሁንም እንኳ ለይሖዋ “ሕያዋን” መሆናቸውን ማወቅ በእጅጉ የሚያጽናና ነው። ስለዚህ በይሖዋ ዓይን ስንመለከተው ቴሬዛ አሁንም ሕያው ነች።
ቪኪ የብርታት ምንጭ የሆኗትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ብትናገር ደስ ይላታል:-
“ ‘አምላክ ከቶ ሊዋሽ አይችልም።’ (ዕብራውያን 6:18፤ ቲቶ 1:2) ይሖዋ ሊዋሽ ስለማይችል ሙታንን በትንሣኤ ለማስነሳት የገባውን ቃል እንደሚፈጽም አውቃለሁ።
“ ‘በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” NW ] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . በዚህ አታድንቁ።’ (ዮሐንስ 5:28, 29) ‘የመታሰቢያ መቃብር’ የሚሉት ቃላት ቴሬዛ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤ እስኪያስነሳት ድረስ በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ እንደምትቆይ ያሳያል። ፍጹም በሆነው በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ ከመቆየት የተሻለ ከስጋት ነጻ የሆነ ቦታ እንደሌለ አውቃለሁ።
“ ‘በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።’ (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በተለይ የይሖዋ መንፈስ ብርታት እንዲሰጠኝ በጸሎት ጠየቅኩት። በምበሳጭበት ጊዜ ወደ ይሖዋ ዞር እልና ‘አሁንስ መንፈስህ ይበልጥ ያስፈልገኛል’ ብዬ እጠይቀዋለሁ። ይሖዋም ያደረብኝን ስሜት ተቋቁሜ እንዳልፍ ይረዳኛል። አንዳንድ ጊዜ የምናገረው ነገር ይጠፋኛል። ሆኖም ሐዘኔን እንድቋቋም ብርታት ይሰጠኛል።”
ይሖዋ ይህን በቃላት መግለጽ የሚከብድ አሳዛኝ መከራ እንድንቋቋም ረድቶናል። ውዷ ልጃችን ቴሬዛን በማጣታችን አሁንም ቢሆን እናዝናለን። ይሖዋ በሚያቋቁመው አዲስ ዓለም ውስጥ ዳግም እስክናገኛት ድረስ ሐዘናችን ጨርሶ ይረሳል የሚል ተስፋ የለንም። እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ከምን ጊዜውም የበለጠ ቆርጠናል። ኦስካር ይሖዋን የሚወድና የሚያገለግል ልጅ እንዲሆን ጆናታን አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ ለማድረግ የቆረጠ ሲሆን እኔና ቪኪም በተቻለን መጠን እንረዳዋለን። አምላክ በሚያቋቁመው አዲስ ዓለም ውስጥ ተገኝተን ቴሬዛ ከሞት ስትነሳ ለመቀበልና ለማቀፍ ካልታደለችው ልጅዋ ጋር ለማስተዋወቅ ከልብ እንመኛለን።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጃችን ቴሬዛ የልጅዋን የልብ ምት ስታዳምጥ
[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሰዎች ያደረጉልንን ድጋፍ በገሃድ ያየነው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ንግግር በተሰጠበት ዕለት ነው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከቪኪ ጋር በቴሬዛ ሠርግ ላይ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የልጅ ልጃችን ኦስካር