በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥላቻ መንስኤ

የጥላቻ መንስኤ

የጥላቻ መንስኤ

ጥላቻ ብቅ ያለው ገና በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ ነው። በዘፍጥረት 4:​8 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም።” የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ዮሐንስ “ስለ ምንስ ገደለው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “የገዛ ሥራው ክፉ፣ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው” ብሏል። (1 ዮሐንስ 3:12) አቤል ከጥላቻ የተለመዱ መንስኤዎች አንዱ የሆነው የቅንዓት ሰለባ ሆኗል። ምሳሌ 6:​34 “ቅንዓት ለሰው የቁጣ ትኩሳት ነው” ይላል። ዛሬም ሌሎች ባላቸው ሥልጣን፣ ሀብት፣ ንብረት እና ሌሎች ጥቅሞች መቅናት ሰዎች እርስ በርስ እንዲጠላሉ እያደረገ ነው።

ጭፍን አስተሳሰብና ፍርሃት

ይሁንና ቅንዓት ከብዙዎቹ የጥላቻ መንስኤዎች አንዱ ብቻ ነው። ብዙውን ጊዜ ጭፍን አስተሳሰብና ፍርሃትም ጥላቻን ይቀሰቅሳሉ። ዓመፅ የሚያካሂድ የዘረኞች ቡድን አባል የሆነ አንድ ወጣት “መጥላትን ከመማሬ በፊት የተማርኩት ፍርሃትን” ነው ሲል ተናግሯል። እንዲህ ያለው ፍርሃት ብዙውን ጊዜ በጭፍን አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዳለው ከሆነ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ያደረባቸው ሰዎች አመለካከት “እውነታውን ያላገናዘበ ነው። . . . መሠረተ ቢስ ጥላቻ ያደረባቸው ሰዎች አንዴ አእምሯቸው ውስጥ ከቀረጿቸው ሐሳቦች ተቃራኒ የሆነውን እውነት ማጣመም፣ አዛብቶ ማቅረብ፣ ወይም ገሸሽ ማድረግ ይቀናቸዋል።”

እነዚህ ሐሳቦች የሚመነጩት ከየት ነው? አንድ የኢንተርኔት የመረጃ አገልግሎት እንዳለው:- “ታሪክ ራሳቸውን ለሚደግሙት ለብዙዎቹ ስህተቶች ተጠያቂ ቢሆንም ለብዙዎቹ አድሏዊ አስተሳሰቦቻችን ግን ተጠያቂው የራሳችን የግል ታሪክ ነው።”

ለምሳሌ ያህል የባሪያ ንግድ በዮናይትድ ስቴትስ እስከ ዛሬም ድረስ በብዙ ነጮችና አፍሪካዊ ዝርያ ባላቸው ሰዎች መካከል ውጥረት እንዲነግሥ በማድረግ አሻራውን ትቶ አልፏል። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ስለ ሌላው ዘር ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ለልጆች ያስተላልፋሉ። የዘረኝነት አስተሳሰብ እንዳለው ያመነ አንድ ነጭ አሉታዊ አመለካከት ያዳበረው “ከጥቁሮች ጋር የሚገናኝበት አንዳች አጋጣሚ ሳይኖረው” እንደሆነ ተናግሯል።

ከእነርሱ ለየት ያሉ ሰዎች ምንም ዋጋ እንደሌላቸው አድርገው የሚያስቡም አሉ። ምናልባት እንዲህ ያለው አመለካከት ሌላ ዓይነት ዘር ወይም ባሕል ካለው ሰው ጋር በተያያዘ ከገጠማቸው አንድ ደስ የማይል ሁኔታ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በመነሣት ከዚያ ዘር ወይም ባሕል የመጡ ሰዎች ሁሉ ችግር አለባቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ።

ግትር አስተሳሰብ በግለሰቦች ላይ ሲንጸባረቅ አስከፊ የመሆኑን ያህል ይህ ባሕርይ አንድን ብሔር ወይም ዘር ከተጠናወተ ደግሞ የበለጠ አስከፊ ይሆናል። የአንድ ሰው ዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ ባሕል ወይም ቋንቋ ከሌሎች ሰዎች ያስበልጠዋል የሚለው እምነት ግትር አመለካከትን እንዲሁም ባዕድ ምንጭ ያለውን ነገር ሁሉ የመጥላትን ዝንባሌ የሚያበረታታ ይሆናል። በ20ኛው መቶ ዘመን እንዲህ ያለው ግትርነት ብዙውን ጊዜ በኃይል ድርጊቶች ሲገለጽ ቆይቷል።

የሚያስገርመው ጥላቻና ግትርነት ሁልጊዜ ከቆዳ ቀለም ወይም ከዘር ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት አይደለም። የፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ክላርክ መኮሊ እንደጻፉት “ሳንቲም ወደ ላይ በመወርወር በሁለት የመቦደኑ ፍርደ ገምድል ውሳኔ እንኳ ለተመደቡበት ቡድን እንዲወግኑ ለማነሳሳት በቂ ነው።” አንዲት የሦስተኛ ክፍል መምህር የክፍሏን ተማሪዎች ሰማያዊና ቡናማ የዓይን ቀለም ያላቸው በማለት በሁለት ከፍላ ያደረገችው ምርምር ይህንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ብዙም ሳይቆይ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጥላቻ ተቆስቁሷል። አንድን የስፖርት ቡድን መደገፍን የመሳሰሉ ብዙም ክብደት የማይሰጣቸው ነገሮች እንኳ ወደ ከባድ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ።

ይህን ያህል ዓመፅ የበዛው ለምንድን ነው?

እንዲህ ያሉት ጥላቻዎች ብዙውን ጊዜ በኃይል ድርጊት የሚገለጹት ለምንድን ነው? ተመራማሪዎች እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት ሲያጤኑ ቢቆዩም ከቲዮሪ ያለፈ ነገር ማቅረብ አልቻሉም። ክላርክ መኮሊ የሰውን ልጅ ዓመፅና ጠበኝነት በሚመለከት ስለተደረጉት ምርምሮች ሰፊ ሐተታ አዘጋጅተዋል። አንድ ጥናት በመጥቀስ “የኃይል ድርጊት የታከለባቸው ዓመፆች ከጦርነትና ከድል አድራጊነት ጋር በቅርብ የተሳሰሩ” መሆናቸውን ጠቁመዋል። ተመራማሪው እንዳስተዋሉት “በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተካፈሉትና በተለይ ደግሞ በጦርነቶቹ አሸናፊ በነበሩት ብሔራት ውስጥ ከጦርነቱ ማግሥት የሚፈጸመው የነፍስ ግድያ ቁጥር ጨምሯል።” መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ዛሬ የምንኖረው በጦርነት ዘመን ነው። (ማቴዎስ 24:​6) ምናልባት እነዚህ ጦርነቶች ሌላ ዓይነት ዓመፅ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገው ይሆን?

ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ የሰው ልጅ ጠበኛ የሆነበትን ምክንያት ከስነ ሕይወት አንጻር ለማስረዳት ይሞክራሉ። አንድ ጥናት ለተወሰኑ የጠበኝነት ድርጊቶች ምክንያቱ “በአንጎል ውስጥ የሴሮቶኒን መጠን ማነስ” ነው ሲል ለማስረዳት ሞክሯል። ሌላው በተደጋጋሚ የሚሰማው መላ ምት ደግሞ በበራሂያችን ውስጥ የጠበኝነት ባሕርይ አለ የሚለው ነው። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር “[ጥላቻ] በአብዛኛው በዘር የሚወረስ ሊሆንም ይችላል” ሲሉ ለማስረዳት ሞክረዋል።

መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ከመጥፎ ባሕርይና ጉድለት ጋር እንደተወለዱ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:​5፤ ዘዳግም 32:​5) እነዚህ ቃላት ለሁሉም ሰው እንደሚሠሩ የተረጋገጠ ቢሆንም ለሌሎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚያድርባቸው ሁሉም ሰዎች ናቸው ማለት አይደለም። ጥላቻ ከአካባቢያችን የምንማረው ነገር ነው። በመሆኑም ታዋቂው የስነ ልቦና ሐኪም ጎርደን ደብልዩ ኦልፖርት አስተያየታቸውን ሲሰጡ ልጆች “ጉዳት የሚያደርስ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ . . . እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ . . . የለም ለማለት ይቻላል። ሕፃናት አዎንታዊ ከመሆናቸውም ሌላ ማንኛውንም ማባበያም ሆነ ሰው አይርቁም” ብለዋል። እንዲህ ያለው አስተያየት ጠበኝነት፣ ወገናዊነትና ጥላቻ በዋነኝነት ከጊዜ በኋላ የሚዳብሩ ባሕርያት ናቸው የሚለውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። ይህን ጥላቻ የማሳደር ተፈጥሮአዊ ችሎታ የጥላቻ አስተማሪዎች አለገደብ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

አእምሮን መመረዝ

በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው የሚገኙት እንደ አፍቃሪ ናዚዎች፣ የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች እና ኩ ክሉክስ ክላን ያሉትን የጥላቻ ቡድኖች የሚመሩት ሰዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ቡድኖች ዒላማ አድርገው የሚመለምሉት ለእነርሱ አስተሳሰብ በቀላሉ ቀልባቸው የሚማረከውን ቤተሰባቸው የተናጋባቸውን ወጣቶች ነው። በራስ የመተማመን መንፈስ የሌላቸውና የዝቅተኝነት ስሜት የሚሰማቸው ወጣቶች ከእነዚህ የጥላቻ ቡድኖች ጋር የጠበቀ ትስስር መመሥረት እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል።

ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት መረብ አንዳንዶች ጥላቻን ለመቆስቆስ የተጠቀሙበት ኃይለኛ መሣሪያ ሆኗል። በቅርቡ በተደረገ አንድ ቆጠራ መሠረት በኢንተርኔት መረብ እስከ 1, 000 የሚደርሱ ጥላቻን የሚቆሰቁሱ የዌብ ገጾች አሉ። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት “ይህ የመረጃ መረብ አመለካከታችንን በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ለማድረስ አስችሎናል” በማለት አንድ የዌብ ገጽ ባለቤት መኩራራታቸውን ገልጿል። ይህ ሰው የዌብ ገጽ “የልጆች አምድ” ጭምር አለው።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች ኢንተርኔት ውስጥ ገብተው ሙዚቃ ሲያስሱ ጥላቻን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን ያገኛሉ። እንዲህ ያሉት ሙዚቃዎች ብዙውን ጊዜ ጩኸት የበዛባቸውና ዓመፅን የሚያበረታቱ ሲሆኑ ግጥሞቻቸውም የዘረኝነትን መልእክት ያዘሉ ናቸው። እነዚህ የዌብ ገጾች ደግሞ ጥላቻን ከሚያነሳሱ የዜና አምዶች፣ የኢንተርኔት የውይይት መድረኮች (chat rooms) ወይም ሌሎች የዌብ ገጾች ጋር ያገናኟቸዋል።

ጥላቻን የሚያበረታቱት አንዳንዶቹ የዌብ ገጾች ለወጣቶች የተዘጋጁ ጨዋታዎችንና ሌሎች ነገሮችን ያካተቱ ክፍሎች አሏቸው። አንድ የአፍቃሪ ናዚዎች ዌብ ገጽ ዘረኝነትንና ፀረ-ሴማዊነትን ትክክል አስመስሎ ለማቅረብ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ሞክሯል። ይኸው የዌብ ገጽ የዘረኝነት አስተያየቶች ላይ የተመሠረተ የእንቆቅልሽ ጥያቄ ጨዋታዎችንም አዘጋጅቷል። ዓላማው ምንድን ነው? “ነጭ ወጣት አባሎቻችን ትግላችንን እንዲገነዘቡ መርዳት ነው።”

ይሁንና ጥላቻን የሚያበረታቱት ጽንፈኞች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። አንድ የማኅበራዊ ሕይወት ተመራማሪ በቅርቡ በባልካን አገሮች ስለነበረው ግጭት ሲጽፉ አንዳንድ የታወቁ ጸሐፊዎችንና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተደማጭነት ያላቸውን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል:- “የወገኖቻቸውን እኩይ ምግባር የሚያበረታታ፣ በውስጣቸው ያለውን ሥር የሰደደ ጥላቻ የሚቆሰቁስ፣ ስህተት የሚባል ነገር የለም የሚል ጭፍን አመለካከት እንዲይዙ የሚያደርግ . . . እንዲሁም እውነታውን የሚያጣምም የአጻጻፍ ዘይቤ መከተላቸው እጅግ አስገርሞኛል።”

በዚህ ረገድ ቀሳውስት የሚጫወቱት ሚናም ሳይጠቀስ አይታለፍም። ጸሐፊው ጆን ኤ ሆት ሆሊ ሄትሬድ:- ሪሊጂየስ ኮንፍሊክትስ ኦቭ ዘ ናይንቲስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህንን አስደንጋጭ አስተያየት ሰጥተዋል:- “ደግነት ሊያሳይና ስለ ሰዎች ሊያስብ ይገባል የሚባለው ሃይማኖት በ1990ዎቹ ዓመታት የጥላቻ፣ የጦርነትና የሽብር ዋነኛ ቆስቋሽ ሆኖ መገኘቱ በጣም የሚያስገርም ነው።”

በመሆኑም የጥላቻ መንስኤዎች ብዙና ውስብስብ ናቸው። ታዲያ የሰው ልጅ በጥላቻ የተሞላውን አሳፋሪ ታሪኩን ከመድገም እንዲቆጠብ ማድረግ የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም ማለት ነው? በግለሰብ ደረጃም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥላቻ እንዲጸነስ ምክንያት የሚሆኑትን አለመግባባትን፣ ጭፍን አስተሳሰብንና ፍርሃትን ለመዋጋት ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖራል?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወገናዊነትና ጥላቻ ከጊዜ በኋላ የሚዳብሩ ባሕርያት ናቸው!

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥላቻንና ግትር አስተሳሰብን . . .

. . . ይዘን አልተወለድንም

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥላቻ ቡድኖች ወጣቶችን ለመመልመል ኢንተርኔትን እንደ መሣሪያ ይጠቀማሉ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ ለግጭቶች መቆስቆስ ምክንያት ሆኖ ይታያል

[ምንጭ]

AP Photo