በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

“የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ልጆች እርዳታ ይሻሉ። ሆኖም ልጆች በራሳቸው ጥረት ያን እርዳታ ማግኘት አይችሉም። አንድ አዋቂ ሰው በመጀመሪያ ችግሩን ማወቅና ከዚያም ጉዳዩን በቁም ነገር መመልከት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ነው።”—⁠ዶክተር ማርክ ኤስ ጎልድ

ልጃችሁ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለበት ከጠረጠራችሁ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? በመጀመሪያ ደረጃ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩሉ። ምልክቶቹ ሌላ በሽታን የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ። * ከዚህም በላይ ሁሉም ወጣቶች አልፎ አልፎ ስሜታቸው ሊለዋወጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ችግሩ ካልተወገደና እንዲሁ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የሐዘን ስሜት እንዳልሆነ ከተሰማችሁ ሐኪም ማማከሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተናገራቸውን “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም” የሚሉትን ቃላት ማስታወሱ ጥሩ ነው።​—⁠ማቴዎስ 9:12

የልጃችሁ መንፈስ እንዲዳከም አስተዋጽዖ አድርገዋል ብላችሁ የምታስቧቸውን በቅርቡ በልጁ ሕይወት ላይ የታዩ ለውጦችን ጨምሮ ጠቃሚ ነው ብላችሁ ያሰባችሁትን መረጃ ሁሉ ለሐኪሙ በግልጽ ንገሩት። ሐኪሙ አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረሱ በፊት በቂ ጊዜ ወስዶ ምልክቶቹን በጥሞና ማዳመጡን እርግጠኞች መሆን መቻል አለባችሁ። “በሃያ ደቂቃ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን አሰባስቦ አንድን ልጅ በመመርመር አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ አዳጋች ነው” በማለት ዶክተር ዴቪድ ጂ ፋስለር ያስጠነቅቃሉ።

ያሏችሁን ጥያቄዎች በሙሉ ለሐኪሙ አቅርቡለት። ለምሳሌ ያህል ልጃችሁ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለበት ሐኪሙ ከተሰማው ሌሎች ምርመራዎች ማድረግ ያልፈለገው ለምን እንደሆነ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። በሐኪሙ የምርመራ ውጤት ላይ ጥርጣሬ ካደረባችሁ ሌላ የሕክምና ባለሙያ በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን አስተያየት መስማት እንደምትፈልጉ ንገሩት። ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር የሚያከብርና ቅን አስተሳሰብ ያለው ሐኪም ሐሳብህን ውድቅ እንደማያደርግ የታወቀ ነው።

ሁኔታውን ተቀብሎ መኖር

ልጃችሁ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይዞት ከሆነ ፈጽሞ ሊያሳፍራችሁ አይገባም። የመንፈስ ጭንቀት የትኛውንም ጥሩ የተባለ ልጅ ሊይዝ ይችላል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ የአቅማቸውን ያህል አምላክን ለማገልገል ይጣጣሩ የነበሩ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ መንፈስን በሚረብሹ ስሜቶች እንደተጠቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። አምላክ እንደተወው የተሰማውንና ሞት የተመኘውን ታማኙን ኢዮብ ተመልከቱ። (ኢዮብ 10:1፤ 29:2, 4, 5) ሐና አምላክን የምታገለግል ብትሆንም እንኳ በጣም ‘ከመመረሯ’ የተነሳ መብላት እንኳ ተስኗት ነበር። (1 ሳሙኤል 1:4-10) ለአምላክ ያደረው ያዕቆብም በልጁ ሞት ምክንያት ለብዙ ቀናት በሐዘን ከመደቆሱም በላይ ‘መጽናናትን እንቢ ብሎ’ ነበር። ሌላው ቀርቶ ያዕቆብ እርሱም ሞቶ ወደ ልጁ ወደ መቃብር ሥፍራ ይወርድ ዘንድ ያለውን ምኞት ገልጿል። (ዘፍጥረት 37:33-35) ስለዚህ በስሜት ላይ የሚደርስ ሥቃይ ሁልጊዜ በመንፈሳዊ መዳከምን የሚያመለክት አይደለም።

የሆነ ሆኖ በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው የመንፈስ ጭንቀት ወላጆችን ከባድ ችግር ላይ ሊጥል ይችላል። “ስለምናገረውና ስለማደርገው ነገር በጣም መጠንቀቅ አለብኝ” በማለት የመንፈስ ጭንቀት ያደረባት ልጅ ያለቻት አንዲት እናት ተናግራለች። “እጨነቃለሁ፣ ስጋት ያድርብኛል፣ ቁጣ ቁጣ ይለኛል፣ እበሳጫለሁ እንዲሁም ይደክመኛል።” ሌላ እናት ደግሞ “አንዲት እናት ከሴት ልጅዋ ጋር ገበያ ወጥታ ስመለከት እኔ ከ[ልጄ] ጋር እንደዚያ ማድረግ ባለመቻሌና ወደፊትም እንደዚያ ማድረግ እንደማልችል ሳስብ ልቤ በሐዘን ጦር ይወጋል” በማለት ተናግራለች።

እንደዚህ ያሉት ስሜቶች የተለመዱ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ለምን ለአንድ ለምታምኑት ወዳጃችሁ ስሜታችሁን አታካፍሉትም? ምሳሌ 17:​17 “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” በማለት ይናገራል። መጸለይም አትርሱ። ሸክማችንን በአምላክ ላይ ከጣልን እንደሚደግፈን መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል።​—⁠መዝሙር 55:22

ራስንም ሆነ ሌላውን ተጠያቂ የማድረግ ዝንባሌ

የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ልጅ ያላቸው ብዙ ወላጆች ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ስለሚያድርባቸው በተወሰነ መጠን ተጠያቂ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። “ልጃችሁ የመንፈስ ጭንቀት በሚይዘው ጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማችኋል፤ የትኛውም ሰው ይህ ስሜት እንዳይሰማችሁ ሊያደርግ አይችልም” በማለት አንዲት እናት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “የሠራነው ስህተት ምንድን ነው? ችግሩ የተፈጠረው የት ላይ ነው? እኔ ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ ያበረከትኩት እንዴት ነው?” እያላችሁ ትጠይቃላችሁ። ወላጆች በዚህ ረገድ አስተሳሰባቸው ሚዛኑን እንዳይስት ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

በቤተሰብ ውስጥ የማያፈናፍን ዓይ​ነት ሁኔታ ካለ በልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ “ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” በማለት አባቶችን አጥብቆ ይመክራል። (ቆላስይስ 3:​21) ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚይዙበትን መንገድ መመርመርና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ የመንፈስ ጭንቀት ሁልጊዜ በወላጆች የአያያዝ ድክመት የሚመጣ ነው ማለት አይደለም። ፍቅር በሰፈነበት በብዙ ቤቶች ውስጥም በሽታው ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ ልጆቻቸውን ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ያሉ ወላጆች የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም።

የመንፈስ ጭንቀት የያዘውንም ልጅ ጥፋተኛ እንደሆነ አድርጎ አለመውቀሱም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። በሽታው እሱ ሊቆጣጠረው የሚችለው ነገር እንዳልሆነ መዘንጋት የለበትም። “ኩፍኝ ወይም የሳንባ ምች ቢይዘው ኖሮ ጥፋተኛ እንደሆነ አድርጌ ፈጽሞ አልናገረውም ነበር” በማለት አንዲት እናት ተናግራለች። “የመንፈስ ጭንቀት በያዘው ጊዜ ግን ያደረኩት ይህን ነበር። ጥፋተኛ ያደረግሁት ራሱን ልጄን ነበር። ይህ ደግሞ ሐዘን ውስጥ ከትቶኛል” በማለት አምናለች። ወላጆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የመንፈስ ጭንቀትን እንደ ድክመት ሳይሆን እንደ በሽታ አድርገው መመልከታቸው በሽተኛውን መርዳት በሚችሉበት መንገድ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

የመንፈስ ጭንቀት የያዘውን ልጅ ማሳደግ በወላጆች መካከል ውጥረት እንዲነግሥ ሊያደርግ ይችላል። “በተለይ አልመነው የነበረውን ኑሮና በልጃችን ምክንያት የተፈጠረውን ሁኔታ ስናስብ እርስ በርስ እንወነጃጀላለን” በማለት አንዲት ሚስት ትናገራለች። በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ ልጅ ያለችው ቲም እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ባለቤትህን ጥፋተኛ እንደሆነች አድርጎ መውቀሱ ቀላል ነው። በልጁ ላይ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች መታየት ከመጀመራቸው በፊት በትዳር ውስጥ ችግሮች ተፈጥረው ከነበረ በልጁ ላይ የሚታዩት እንግዳ የሆኑ ባሕርያት ችግሩ ፈንድቶ እንዲወጣ ሊያደርጉት ይችላሉ።” በልጁ ላይ የደረሰው የመንፈስ ጭንቀት ትዳራችሁን እንዲያበጣብጥ አትፍቀዱለት! በራሳችሁ ወይም በልጃችሁ ወይም በትዳር ጓደኛችሁ ላይ ጣታችሁን መቀሰራችሁ የሚያመጣው ምንም ፋይዳ የለም። ከሁሉ የሚሻለው ለሕመምተኛው ድጋፍ መስጠቱ ነው።

ድጋፍ መስጠት

መጽሐፍ ቅዱስ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” በማለት ክርስቲያኖችን አጥብቆ ይመክራል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW ) የመንፈስ ጭንቀት ያደረበት ልጅ የከንቱነት ስሜት የሚሰማው ከሆነ ልትረዱት ትችላላችሁ። እንዴት? “እንዲህ ሊሰማህ አይገባም” ወይም “ይሄማ የተሳሳተ አመለካከት ነው” እንደሚሉት ያሉ የወቀሳ ዓይነት አስተያየቶችን በመስጠት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ከዚያ ይልቅ ‘ችግሩን እንደ ራሳችሁ ችግር አድርጋችሁ በመመልከት’ አዛኝ ለመሆን ጣሩ። (1 ጴጥሮስ 3:8 NW ) ጳውሎስ “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። (ሮሜ 12:15) የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው በጣም እንደሚጎዳ ፈጽሞ አትዘንጉ። ሕመሙ እንዲሁ በሐሳቡ የወለደው ወይም ትኩረት ለመሳብ ብሎ የፈጠረው አይደለም። በሽተኛውን ካዳመጣችሁ በኋላ የልቡን እንዲነግራችሁ ጥረት አድርጉ። እንደዚያ የሚሰማው ለምን እንደሆነ ጠይቁት። ከዚያም ስለ ራሱ ያደረበት የበታችነት ስሜት መሠረት የሌለው እንደሆነ እንዲገነዘብ ቀስ ብላችሁ በትዕግሥት እርዱት። አምላክ አፍቃሪና መሐሪ መሆኑን በመግለጽ ማጽናናቱም በሽተኛው ከጭንቀቱ እረፍት እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:6, 7

ልትወስዷቸው የምትችሏቸው ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎችም ይኖሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የመንፈስ ጭንቀት የያዘው ልጃችሁ በቂ እረፍትና ምግብ እንዲያገኝና በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። (መክብብ 4:6) መድኃኒት ታዝዞለት ከሆነ መድኃኒቱን መውሰድ ያለውን ጥቅም እንዲገነዘብ መርዳቱ ጥበብ ነው። ተስፋ ቆርጣችሁ እርዳታ መስጠታችሁንና ፍቅር ማሳየታችሁን አታቁሙ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ባሉ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው የመንፈስ ጭንቀት በበሽተኛውም ሆነ በተቀሩት የቤተሰቡ አባላት ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀርም። ሆኖም የምታሳዩት ትዕግሥት፣ ጽናትና ፍቅር በመንፈስ ጭንቀት የተያዘውን ልጅ በመርዳት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ሞኖኑክሊዮሲስ፣ የስኳር በሽታ፣ ደም ማነስ፣ ሃይፖታይሮይዲዝም እና በደም ውስጥ ያለው ስኳር መጠን ማነስን ጨምሮ አንዳንድ በሽታዎች ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶች ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይነገራል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው በጣም ይጎዳል። ሕመሙ እንዲሁ በሐሳቡ የፈጠረው አይደለም

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመንፈስ ጭንቀት የያዘህ ልጅ ከሆንክ

እርዳታ ልታገኝ የምትችል ከመሆኑም በላይ ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። የደረሰብህ የመንፈስ ጭንቀት (1) በሰውነትህ ውስጥ በሚከሰት የኬሚካል መዛባት ወይም (2) በሕይወትህ ውስጥ ባጋጠሙህ ከአቅምህ በላይ በሆኑ ሁኔታዎች የተፈጠረ ነው። በዚያም ሆነ በዚህ ለደረሰብህ ህመም ተጠያቂው አንተ አይደለህም። ሆኖም ምን ልታደርግ ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 18:24) እንዲህ ላለ ወዳጅ የውስጥ ስሜትህን ለምን ግልጥልጥ አድርገህ አትነግረውም? ከመንፈስ ጭንቀትህ ጋር በምታደርገው ትግል ወላጆችህ ወይም ሌላ የጎለመሰ አዋቂ ሰው ጥሩ አጋር ሊሆኑልህ ይችላሉ።

ወላጆችህ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንደያዘህ ሆኖ ከተሰማቸው እንዲህ ያለ​ውን ሕመም በማከም ረገድ ተሞክሮ ወዳለው ሐኪም ይወስዱህ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት በሕክምና ሊረዳ ስለሚችል እንዲህ ማድረጉ የጥበብ እርምጃ ነው። ለምሳሌ ያህል በሰውነትህ ውስጥ የኬሚካል መዛባት ደርሶ ከሆነ ጭንቀት የሚያስታግስ መድ​ኃኒት ሊታዘዝልህ ይችላል። መድኃኒት ታዝዞልህ ከሆነ ለመውሰድ አትፈር። መድ​ኃኒቱ በሰውነትህ ውስጥ ያለውን ኬሚካል ወደ ቀድሞ ሁኔታው የሚመልሰው በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ ደስታና መረጋጋት እንድታገኝ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

በመንፈስ ጭንቀት የተጠቁ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ በመቅረብ መጽናኛ አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል። *​—⁠መዝሙር 34:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . በጭንቀት መዋጤን ለሰው መንገር ይኖርብኛልን?” የሚለውን የታኅሣሥ 2000 የንቁ! እትም ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የበሽታው ተጠቂዎች ሊያገኙ የሚችሉት እርዳታና ያላቸው ተስፋ

የመንፈስ ጭንቀት ሰፋ ያለና ጥልቀት ያለው ርዕሰ ጉዳይ እንደመሆኑ በእነዚህ አጠር ያሉ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ ሁሉንም ገጽታዎች መዳሰስ አይቻልም። የሆነ ሆኖ የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች በእነዚህ ርዕሶች ላይ የቀረቡት ነጥቦች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችም ሆኑ ወላጆቻቸው ይህን የሚያዳክም በሽታ እንዲቋቋሙ ሊረዷቸው ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው።

ቀደም ባለው ርዕስ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ መመሪያዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ እንደሆኑ አስተውለህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ መሆኑ እሙን ነው። ሆኖም በውስጡ የሚገኙት ምክሮች በተጻፉበት ዘመን የነበረውን ያህል አሁንም ተግባራዊ ጠቀሜታ ይሰጣሉ። ለምን? ዘመናት ቢለወጡም የሰው ልጅ ተፈጥሮ ግን አልተለወጠም። በጥንት ጊዜ የነበሩ ትውልዶች የገጠሟቸው ዓይነት መሠረታዊ ችግሮች እኛንም ይገጥሙናል። ልዩነቱ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ችግሮች መብዛታቸውና መጠነ ሰፊ መሆናቸው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ጥቅም የሚገኝበት መጽሐፍ እንዲሆን ያደረገው ሌላም ምክንያት አለ። የተጻፈው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት እንዴት መምራት እንደምንችል ያውቃል።

እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ አይደለም። በመሆኑም እንደ መንፈስ ጭንቀት ላሉ ሕመሞች የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት የማድረጉ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሕሙማንን ለማጽናናት የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ከዚህም በላይ ካሉብን ሕመሞች ሁሉ በቅርቡ እንደምንገላገል አምላክ የገባውንም ቃል ይዟል። (መዝሙር 103:3) አዎን፣ ይሖዋ ዓላማው ‘የተቀጠቀጠውን ልብ ሕያው የማድረግ’ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 57:15

ይህን ታላቅ ተስፋ በተመለከተ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ትፈልጋለህ? እባክህ አካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግር ወይም በዚህ መጽሔት በገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ጻፍ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሌላውን ችግር እንደ ራሳችሁ ችግር አድርጋችሁ ለመመልከት ጥረት አድርጉ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጁ ካደረበት ጭንቀት መላቀቅ ካልቻለ ሐኪም ማማከሩ ጥበብ ነው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እንደ ወላጅ መጠን ራሳችሁን፣ የትዳር ጓደኛችሁን ወይም ልጃችሁን ለመውቀስ አትቸኩሉ