በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንሥኤውን ማወቅ

መንሥኤውን ማወቅ

መንሥኤውን ማወቅ

“ብዙውን ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የመንፈስ ጭንቀት የሚያድርባቸው እንዲሁ አንድ ችግር ሲገጥማቸው ሳይሆን ውጥረትን የሚያመጡ በርካታ ነገሮች ሲደማመሩ ነው።”​—⁠ዶክተር ካትሊን መኮይ

በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የመንፈስ ጭንቀት የሚይዛቸው ለምንድን ነው? ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው። አንዱ ምክንያት በጉርምስና ዕድሜ ወቅት በአካላቸውና በስሜታቸው ላይ የሚደርሰው ለውጥ በጥርጣሬና በፍርሃት እንዲዋጡ ያደርጋቸዋል። ይህም አሉታዊ ለሆኑ ስሜቶች ያጋልጣቸዋል። እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እኩዮቻቸው ወይም ያፈቀሩት ሰው እንዳገለላቸውና እንደማይፈልጋቸው ሆኖ ሲሰማቸው ብዙውን ጊዜ በአሉታዊ ስሜቶች ይዋጣሉ። እንዲሁም በመክፈቻው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው በዛሬ ጊዜ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሚያድጉት ጭንቀት በሚፈጥር ዓለም ውስጥ ነው። በእርግጥም የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

ከዚህም በተጨማሪ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተጽዕኖዎች ለእነሱ አዲስ ከመሆናቸውም በላይ እንደ አዋቂዎች እነዚህን ተጽዕኖዎች መቋቋም የሚችሉበት ችሎታም ሆነ ተሞክሮ የሌላቸው መሆኑ ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል። በዚህም የተነሳ ብዙውን ጊዜ ወጣቶች በማያውቀው አካባቢ ከሚሄድና በአካባቢው ባለው ሁኔታ ግራ ቢጋባም እርዳታ ከማይጠይቅ አገር ጎብኚ ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ለመንፈስ ጭንቀት በእጅጉ እንዲጋለጡ ያደርጋል።

ሆኖም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በመንፈስ ጭንቀት እንዲያዙ የሚያደርጉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ። እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

የመንፈስ ጭንቀትና የሚወዱትን ሰው ማጣት

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ወይም በትዳር መፍረስ ምክንያት ከወላጅ መለየት አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያስከትላል። በአንዳንድ አገሮች የሚወዱት የቤት እንስሳ በመሞቱ ምክንያት በተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚዋጡ ወጣቶች አሉ።

በጣም ጎልተው የማይታዩ አንዳንድ የሚያጧቸው ነገሮችም የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ያደጉበትን አካባቢ ትተውና ከአብሮ አደጎቻቸው ተለይተው ወደ ሌላ አካባቢ ሊሄዱ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ ትምህርት ጨርሶ መመረቅ የሚያስደስት ነገር ቢሆንም እንኳ መለያየት ቅር የሚያሰኝ ስሜት ሊፈጥር ይችላል። አዲስ ዓይነት አኗኗር መጀመር ፍርሃትና አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን መቋቋም የሚኖርባቸው ወጣቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ከእኩዮቻቸው የተለዩ ሆኖ መታየቱ ምናልባትም ችላ መባሉ ወጣቱ ወይም ወጣቷ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

እርግጥ ነው ሁኔታው የሚፈጥረውን ስሜት መቋቋም የቻሉ በርካታ ወጣቶች አሉ። ያዘኑ ወይም ያለቀሱ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ራሳቸውን ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ማላመድ ችለዋል። ብዙዎቹ ወጣቶች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተጽዕኖዎችን ተቋቁመው ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት ሲችሉ ሌሎች በመንፈስ ጭንቀት የሚጠቁት ለምንድን ነው? የመንፈስ ጭንቀት የተወሳሰበ ሕመም በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ መስጠት አይቻልም። ይሁን እንጂ አንዳንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ለመንፈስ ጭንቀት ይበልጥ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

በሰውነት ውስጥ ካለው ኬሚካል ጋር ያለው ግንኙነት

በአንጎል ውስጥ የሚፈጠር የኬሚካል መዛባት የመንፈስ ጭንቀትን በማስከተል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በርካታ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ያምናሉ። * ተመራማሪዎች በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃይ ወላጅ ያላቸው ወጣቶች በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ማግኘታቸው የኬሚካል መዛባት ችግር በዘር ሊተላለፍ እንደሚችል የሚጠቁም ነው። “የመንፈስ ጭንቀት ካለባቸው ልጆች መካከል አብዛኞቹ ቢያንስ አንደኛው ወላጃቸው በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃይ ነው” በማለት ሎንሊ፣ ሳድ ኤንድ አንግሪ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል።

ይህም በእርግጥ ልጆች የመንፈስ ጭንቀትን በዘር ይወርሳሉ ወይስ በሽታው ካለበት ወላጅ ጋር አብረው በመኖራቸው ምክንያት የመጨነቅ ልማድ ያዳብራሉ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በመንፈስ ጭንቀት እንዲያዙ እንደሚያደርጉት እንደ ሌሎች ምክንያቶች ሁሉ አንጎልም በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው።

የመንፈስ ጭንቀትና የቤተሰብ ሁኔታ

የመንፈስ ጭንቀት ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ ጉዳይ እንደሆነ ተደርጎ የሚነገርለት ሲሆን ለዚህም በቂ ምክንያት አለ። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ከአንድ ትውልድ ወደቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የመንፈስ ጭንቀት የሚያስከትል በራሂያዊ ንጥረ ነገር ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ የቤተሰብ ሁኔታም የራሱ ድርሻ ሊኖረው ይችላል። “በወላጆቻቸው በደል የደረሰባቸው ልጆች በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው” በማለት ዶክተር ማርክ ኤስ ጎልድ ጽፈዋል። “ከሚገባው በላይ ስህተት የሚለቃቅሙና በልጆቻቸው ጉድለት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ወላጆች ያሏቸው ልጆችም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።” በተጨማሪም ወላጆቻቸው የሚያቀብጧቸውና የሚያሞላቅቋቸው ልጆች በመንፈስ ጭንቀት ሊጠቁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንዲት ተመራማሪ እንዳመለከቱት የወላጅ ትኩረት የተነፈጉ ልጆች ለመንፈስ ጭንቀት ይበልጥ የተጋለጡ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው።

ይሁን እንጂ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ልጆች ሁሉ ወላጆቻቸው ጥሩ አድርገው አላሳደጓቸውም ማለት አይደለም። እንዲህ ያለ ጭፍን መደምደሚያ ላይ መድረስ ለችግሩ ተጨማሪ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱትን ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ችላ ማለት ይሆናል። ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ የቤተሰብ ሁኔታ ለችግሩ መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። “በወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነገሠበት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ለመንፈስ ጭንቀት የመጋለጥ ዕድላቸው ብዙ ችግር በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች ከፍ ያለ ነው” በማለት ዶክተር ዴቪድ ጂ ፋስለር ጽፈዋል። “ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ወላጆቻቸው ጊዜያቸውን በጭቅጭቅ የሚያሳልፉ በመሆናቸው የተነሳ የልጆቻቸውን ፍላጎቶች ችላ ይላሉ። ሌላው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ስለሚጨቃጨቁ ልጆቹ የጥፋተኛነት፣ የቁጣና የብስጭት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል።”

እነዚህ በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የመንፈስ ጭንቀት እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ሌሎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተያያዙ ነገሮች (ለምሳሌ ጥሩ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ፣ መርዝነት ያላቸው ንጥረ ነገሮችና ሱስ የሚያስይዙ ነገሮች) የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ አንዳንድ መድኃኒቶች (አንዳንድ ፀረ ሂስታሚን መድኃኒቶችንና ለሥነ ልቦና ችግሮች የሚታዘዙ መድኃኒቶችን የመሳሰሉ) ለመንፈስ ጭንቀት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። የመማር ችሎታቸው ደካማ የሆነ ልጆች በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ከሌሎቹ የክፍል ተማሪዎች ጋር እኩል መራመድ እንደሚሳናቸው ሲገነዘቡ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅ እያለ ስለሚሄድ ሊሆን ይችላል።

መንሥኤው ምንም ይሁን ምን የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመርመሩ ጠቃሚ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 አንዳንዶች እንደሚገምቱት በበሽታው የሚሠቃዩ በርካታ ሰዎች ሲወለዱም በአንጎላቸው ውስጥ የኬሚካል መዛባት የነበረባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጤነኞች ሆነው ይወለዱና በሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥማቸው አንድ ዓይነት መጥፎ ክስተት በአንጎላቸው ውስጥ የኬሚካል መዛባት በመፍጠር ለመንፈስ ጭንቀት የበለጠ የተጋለጡ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት ካለ ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያስከትላል