በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማዘን ስህተት ነውን?

ማዘን ስህተት ነውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ማዘን ስህተት ነውን?

“ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።”—⁠1 ተሰሎንቄ 4:13

መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ስላላቸው ተስፋ ይናገራል። ኢየሱስ ያከናወናቸው ትንሣኤዎችም ሆኑ የሰጣቸው ትምህርቶች የሞቱ ሰዎች ወደ ሕይወት ስለሚመለሱበት ጊዜ ይጠቁማሉ። (ማቴዎስ 22:23-33፤ ማርቆስ 5:35, 36, 41, 42፤ ሉቃስ 7:12-16) ታዲያ ይህ ተስፋ እኛን ሊነካን የሚገባው እንዴት ነው? ከላይ የተጠቀሱት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳዩት አንድ የምትወደው ሰው ሲሞት ይህ ተስፋ ሊያጽናናህ ይችላል።

የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ የሚያስከትለውን የስሜት ስቃይ እንደቀመስክ ምንም አያጠራጥርም። ቴሬዛ ለ42 ዓመታት አብራው የኖረችው ባሏ የልብ ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሲሞት እንዲህ ብላለች:- “በጣም አስደንጋጭ ነበር! በመጀመሪያ ከፍተኛ ድንጋጤ ተሰማኝ። ይህንን ተከትሎም እየተባባሰ የሚሄድ ኃይለኛ ሕመም ይሰማኝ ጀመር። ብዙ አለቀስኩ።” እንዲህ ዓይነቱ ምላሽ ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት በገባው ቃል ላይ እምነት ማጣትን ያመለክታል? የጳውሎስ ቃላት ማዘን ስህተት ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋሉን?

ማዘናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ምሳሌዎች

ማዘናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ምሳሌዎች ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን። በብዙ ታሪኮች ላይ እንደተገለጸው አንድ ቅርብ የቤተሰብ አባል ሲሞት ቤተሰቡ ለተወሰነ ጊዜ ያዝናል። (ዘፍጥረት 27:41፤ 50:7-10፤ መዝሙር 35:14) ብዙውን ጊዜም ከኃዘኑ ጋር ተያይዘው የሚመጡት ስሜቶች በጣም ጥልቅ ናቸው።

አንዳንድ የእምነት ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ እንዴት እንዳዘኑ ተመልከት። ለምሳሌ ያህል አብርሃም አምላክ ሙታንን እንደሚያስነሳ ጠንካራ እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:19) አብርሃም እንዲህ ዓይነት ጠንካራ እምነት ኖሮትም ሚስቱ ሣራ ስትሞት “ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።” (ዘፍጥረት 23:1, 2) የያዕቆብ ልጆች የሚወደው ልጁ ዮሴፍ እንደሞተ ለያዕቆብ በውሸት በነገሩት ጊዜ “ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ . . . ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ።” (ዘፍጥረት 37:34, 35) እንዲያውም ከብዙ ዓመታት በኋላ እንኳ የሚወደው ልጁ እንደሞተ ማሰቡ ራሱ ከብዶት ነበር! (ዘፍጥረት 42:36-38) ንጉሥ ዳዊትም ቢሆን አምኖንና አቤሴሎም የተባሉት ልጆቹ ሲሞቱ የተሰማውን ከፍተኛ ኃዘንና ምሬት በሌሎች ፊት ገልጿል። ሁለቱም በዳዊትና በቤተሰቡ ላይ መከራ አምጥተው የነበረ ቢሆንም የወለዳቸው ልጆቹ ስለሆኑ ሲሞቱ በጣም አዝኗል።​—⁠2 ሳሙኤል 13:28-39፤ 18:33

በሙሴ ሞት ጊዜ እንዳደረጉት መላው የእስራኤል ሕዝብ ያዘነበት ወቅትም ነበር። ዘዳግም 34:​8 እስራኤላውያን ለሙሴ 30 ቀን እንዳለቀሱለት ይነግረናል።

በመጨረሻም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እናገኛለን። አልዓዛር የተባለው የቅርብ ጓደኛው ሞተ። ኢየሱስ ማርታና ማርያም የተባሉት የአልዓዛር እህቶችና ወዳጆቻቸው ሲያለቅሱ ሲመለከት “በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ።” ኢየሱስ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ወዳጁን ከሞት እንደሚያስነሳው ቢያውቅም “እንባውን አፈሰሰ።” ኢየሱስ ማርታና ማርያም የተባሉ ወዳጆቹን ይወድዳቸው ነበር። ስለዚህ ወንድማቸው በመሞቱ ምን ያህል እንዳዘኑ ሲመለከት ስሜቱ በጥልቅ ተነክቶ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 11:33-36

አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ዳዊትና ኢየሱስ በይሖዋና ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ቢሆንም አዝነዋል። ማዘናቸው የመንፈሳዊ ድክመት ምልክት ነውን? ማዘናቸው በትንሣኤ ላይ እምነት እንደሌላቸው ያሳያልን? በፍጹም! አንድ የምንወደው ሰው ሲሞት ማዘን የሚጠበቅ ነገር ነው።

የምናዝንበት ምክንያት

የሰው ልጆች እንዲሞቱ ፈጽሞ የአምላክ ዓላማ አልነበረም። የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ለአዳምና ሔዋን እንደገለጸላቸው ሁሉ ምድር አፍቃሪና ደስተኛ በሆነ ቤተሰብ የተሞላች ውብ ገነት እንድትሆን ነበር። የሚሞቱት የእርሱን ትእዛዝ ከጣሱ ብቻ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:17) የሚያሳዝነው አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ። ባለመታዘዝ ምክንያት “ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ስለዚህ ሞት በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ውስጥ ያልነበረ ጨካኝ ጠላት ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:26

እንግዲያው የምንወደውን ሰው በሞት ማጣትን የመሰለ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ክስተት በሰዎች ላይ ጥልቅ የስሜት ስቃይ ማስከተሉ ሊያስገርመን አይገባም። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል። ከላይ የተጠቀሰችው ባሏ የሞተባት ቴሬዛ ባሏን አስመልክታ እንዲህ ብላለች:- “በትንሣኤ እንደማየው እርግጠኛ ነኝ። አሁን ግን በጣም ይናፍቀኛል። በጣም የሚከብደው ይህ ነው።” የወላጅ ሞት እኛ ራሳችን ሟቾች መሆናችንን ሊያስታውሰን ይችላል። በተለይ ግን ወጣት ሰው ሲሞት የሕይወቱን በአጭር መቀጨት በማሰብ በጣም እናዝናለን።​—⁠ኢሳይያስ 38:10

አዎን፣ ሞት ተፈጥሮአዊ አይደለም። ስለዚህ ከፍተኛ ኃዘን ማስከተሉ አይቀርም። ይሖዋም ቢሆን ማዘንን በትንሣኤ ላይ እምነት እንደማጣት አድርጎ አይመለከተውም። በአብርሃም፣ በያዕቆብ፣ በዳዊት፣ በእስራኤል ብሔር እና በኢየሱስ ላይ እንደታየው የልባችንን ኃዘን አውጥተን መግለጻችን መንፈሳዊነት እንደጎደለን አያሳይም። *

እንደ ማንኛውም ክርስቲያን የምንወደው ሰው ሲሞት ማዘናችን ባይቀርም “ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች” አናዝንም። (1 ተሰሎንቄ 4:13) ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ያለን አመለካከት ጥርት ያለ በመሆኑ ኃዘናችንን ስንገልጽ ከልክ ወዳለፈ ጽንፍ አንሄድም። ሙታን በስቃይ ወይም በጭንቀት ላይ እንዳልሆኑ ይልቁንም ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል በሰላም እንዳንቀላፉ እናውቃለን። (መክብብ 9:5፤ ማርቆስ 5:39፤ ዮሐንስ 11:11-14) በተጨማሪም “ትንሣኤና ሕይወት” የሆነው ኢየሱስ ‘በመቃብር ያሉትን ሙታን’ ለማስነሳት የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች ነን።​—⁠ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:24, 25

ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ኃዘን ላይ ከሆንክ ይሖዋ ስቃይህን እንደሚረዳልህ በማወቅ ተጽናና። ይህ እውቀትና በትንሣኤ ላይ ያለህ ተስፋ ኃዘንህን እንድትቋቋም እንዲረዳህ እንመኛለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ኃዘንን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ ብሮሹር ከገጽ 14 እስከ 19 ተመልከት።