በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርጅናን በተመለከተ የተደረገ የአመለካከት ለውጥ

እርጅናን በተመለከተ የተደረገ የአመለካከት ለውጥ

እርጅናን በተመለከተ የተደረገ የአመለካከት ለውጥ

አረጀህ የሚባለው ዕድሜህ ስንት ሲሆን ነው? መልሱ ጥያቄውን በምታቀርብለት ሰው ላይ የተመካ ይመስላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች ከ25 ዓመት በላይ የሆነን ሰው ሁሉ ከዚህ ጎራ ሊመድቡት ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የኦፔራ ዘፋኞች በሙያቸው የተዋጣላቸው የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ነው። እንዲሁም በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ላይ የመድረስ ዓላማ ያላቸውን ሰዎች በተመለከተ በአውስትራሊያ የሚታተመው ዘ ሰን​—⁠ሄራልድ “በዛሬው ጊዜ ሐቁ 40 ዓመት እስኪሞላህ ድረስ ካልተሳካልህ መቼም ቢሆን አይሳካልህም” የሚል ዘገባ አውጥቷል።

የተለመዱ አመለካከቶች

አንዳንዶች በዕድሜ የገፉ ሰዎች ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆኑና የመማር ችሎታቸው ዘገምተኛ እንደሆነ እንዲሁም አካላቸው በፍጥነት እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ይሰማቸው ይሆናል። እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? እንደ እውነቱ ከሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በመላው አውሮፓ “በመኪና አደጋ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ከሦስት አንዱ ከ25 ዓመት በታች ዕድሜ ያለው ነው።” ከዚህ በተጨማሪ በጣም ፈጣን የሆነ አካላዊ ማሽቆልቆል የሚከሰተው በ30 እና በ40 ዓመት ዕድሜ መካከል ሲሆን የአንድ ጤነኛ ሰው የአእምሮ ችሎታ ከዕድሜ ጋር ይቀንሳል መባሉ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም።

በዕድሜ የገፉ ሰዎች ታማሚ ናቸው ስለሚለው አመለካከትስ ምን ማለት ይቻላል? ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ “እርጅናና በሽታ አይነጣጠሉም የሚባል የተለመደ አባባል አለ” ብሏል። ሐቁ ግን ብዙ አረጋውያን መጠነኛ ጤንነት ያላቸው መሆኑና ራሳቸውን ያረጁ አድርገው አለመመልከታቸው ነው። አንዳንዶች አሜሪካዊው የፖለቲካ ሰው በርናርድ ባሩክ እንዲህ ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ይጋራሉ:- “በእኔ አስተሳሰብ እርጅና የምለው ምንጊዜም ከደረስኩበት ዕድሜ ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ ያለውን ነው።”

ታዲያ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መድልዎ የሚደረግባቸውና አንዳንድ ጊዜም ፈጽሞ የተሳሳተ ግምት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው? በአመዛኙ መልሱ እርጅናን በተመለከተ በሰፈነው አመለካከት ዙሪያ ይገኛል።

እርጅናን በተመለከተ ያሉ አመለካከቶች

ማክስ ፍራንክል “አሜሪካውያን የወጣትነት ዕድሜ በጣም ስለሚማርካቸው መገናኛ ብዙሐን አረጋውያንን በተመለከተ ያለው የሰዎች አመለካከት እንዲዛባ አድርገዋል” ማለታቸው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን ላይ ወጥቷል። “አረጋውያን ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል በመገናኛ ብዙሐን ውስጥ ከመሥራት ተገልለዋል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ዘ ዩኔስኮ ኮሪየር “የዛሬውን ኅብረተሰብ ያህል ለአረጋውያን ትልቅ ውለታ የዋለ . . . ኅብረተሰብ የለም። ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥበቃ አግኝተዋል። ይሁንና ኅብረተሰቡ ለእነሱ ያለው አመለካከት እጅግ አሉታዊ ነው” ሲል የገለጸውን እንቆቅልሽ ለማስተዋል ይረዳናል።

ሌላው ቀርቶ የሕክምና ባለሙያዎችም እንኳ ከዚህ አፍራሽ አመለካከት ነፃ አይደሉም። ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ እንዳለው ከሆነ:- “ብዙ ዶክተሮችን ጨምሮ አጠቃላዩ ኅብረተሰብ ከ65 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች በበሽታ እንዳይጠቁ መከላከል የሚቻልበት ጊዜ አልፎባቸዋል ብለው ያምናሉ። . . . ይህ አሉታዊ አመለካከት . . . አረጋውያን ጠቃሚ በሆኑ በርካታ የምርምር ጥናቶች እንዳይታቀፉ አድርጓል።”

ይኸው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለአረጋውያን ‘ያረጁ ያፈጁ’ የሚል ስያሜ በመስጠት የሚንጸባረቀው አሉታዊ አመለካከት እንደነገሩ ለማከም እንደ ሰበብ ተደርጎ ይቀርባል። የማየትና የመስማት ችሎታ መዳከምን የመሳሰሉ በርካታ የተለመዱ ሆኖም ቀላል አካላዊ ችግሮች ሊወገዱ የማይችሉ የእርጅና ገጽታዎች ተደርገው በመታየት በቸልታ ይታለፋሉ አሊያም ተቀባይነት ያገኛሉ። . . . አረጋውያንን በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ፍቱን የበሽታ መከላከያ መርሐ ግብር ለመንደፍ ወሳኝ ነው።”

“የእርጅና ገጽታ ተደርገው ለሚታዩት ነገሮች በተለምዶ የሚሰጡ ፍቺዎች ሌላው ቢቀር ባደጉ አገሮች ውስጥ በአዲስ መልክ የሚገመገሙበት ጊዜ የደረሰ ይመስላል” በማለት የብሪታኒያው ዘ ላንሴት መጽሔት አሳስቧል። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሔቱ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለእርጅና የሚሰጠው ፍቺ መለወጡ ‘ቁጥራቸው እየተበራከተ’ የመጣ አረጋውያን ውድ ከሆነው የጤና መዋዕለ ነዋይ ‘ተገቢ ያልሆነ ድርሻ’ ያገኛሉ የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለማጠናከር በጣም በሰፊው የሚነገሩ አባባሎች የሚያስከትሉትን አፍራሽ አመለካከት፣ ስጋትና ተስፋ አስቆራጭ ትንበያዎች ሊያስወግድ ይችላል።”

የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ ነው

በአሁኑ ጊዜ እንኳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አረጋውያን እንዳሉ አይካድም። ደግሞም ቁጥራቸው በፍጥነት እየጨመረ ነው። ዘ ዩኔስኮ ኮርየር “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1955 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ 65 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ የሚጨምር ሲሆን ከአጠቃላዩ የሕዝብ ብዛት ከመቶ የሚኖራቸው ድርሻ ደግሞ በእጥፍ ያድጋል” ሲል ዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜ እንኳ በሕንድ የሚኖሩ አረጋውያን ቁጥር ከአጠቃላዩ የፈረንሳይ የሕዝብ ብዛት ቁጥር ልቆ ይገኛል። በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በነበሩት 18 ዓመታት ውስጥ የተወለዱት እንደ አሸን የፈሉ ሕፃናት ተብለው የሚጠሩ 76 ሚልዮን ሰዎች በሚቀጥለው ግማሽ መቶ ዘመን ውስጥ ጡረታ እንደሚወጡ ይነገራል። በዓለም ዙሪያ የአረጋውያን ቁጥር መጨመር ለበርካታ ኢኮኖሚስቶችና የጤና ባለሙያዎች አሳሳቢ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ እርጅናን በተመለከተ አስቀድሞ የነበሩንን አንዳንድ አመለካከቶች በድጋሚ እንድናጤን ያስገድደናል።

የተውኔቱን ጽሑፍ እንደገና መጻፍ

አንዳንዶች ሕይወትን ሦስት ገቢር ካለው ተውኔት ጋር ሊያመሳስሉት ይችላሉ። በወጣትነት ዕድሜ የሚኖረው የጨዋታና የትምህርት ዘመን በመጀመሪያው ገቢር ላይ ጉልህ ቦታ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነቶችና በጣም አድካሚ ጫና የሚፈጥረው የሥራ ሕይወት የሁለተኛውን ገቢር እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ። ሦስተኛው ገቢር ላይ ተዋናዮቹ ከሕዝብ ዕይታ ርቀው አርፈው እንዲቀመጡ የሚመከሩ ከመሆኑም በላይ የሞራል ኪሳራ ደርሶባቸው የመጨረሻው መጋረጃ እስኪዘጋ ድረስ ይጠብቃሉ።

ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን በሕክምና አሰጣጥና በንጽህና አጠባበቅ ረገድ የተደረጉትን አስደናቂ እድገቶች ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ “ተዋናዮቹ” “በሦስተኛው ገቢር” ላይ ከመድረክ ተገልለው የሚያሳልፉት የጊዜ ርዝመት በ25 ዓመት ጨምሯል። አብዛኞቹ ሥራ ፈት ሆነው እንዲቀመጡ መደረጋቸው አያስደስታቸውም። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ እነዚህ ንቁ አረጋውያን የተውኔቱ ጽሑፍ በድጋሚ እንዲጻፍ መጠየቅ ጀምረዋል።

እጅግ ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ

አብዛኞቹ አረጋውያን የሌሎች ጥገኛ ናቸው የሚለው የብዙዎች አመለካከት ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “አብዛኞቹ አረጋውያን ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ፣ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከወጣት ባለትዳሮች የበለጠ ሀብት ያላቸው ናቸው። . . . እንዲሁም ሶሺዮሎጂስቶች ተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ያላቸውና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ . . . ጥሩ ኑሮ ያላቸው አረጋውያን መኖራቸውን አስተውለዋል” ሲል ዘግቧል። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የገበያ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ፊሊፕ ኮትለር በዚህ ጉዳይ ላይ የሰነዘሩት ሐሳብ አለ:- “ነጋዴዎች፣ 55 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ የመሸመት አቅም ያላቸው ጥሩ ትርፍ የሚገኝባቸው እንደሆኑ የሚገነዘቡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።”

ንቁ የሆኑ አረጋውያን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነ አይደለም። የሲንዲው ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ በአውስትራሊያ “ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ተቀጥረው የሚሠሩ በመሆናቸው ሴት አያቶች የልጅ ልጆቻቸውን በመንከባከብ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ” ብሏል።

የፈረንሳይ ከተማ የሆነችው ትሮይን በመሳሰሉ ቦታዎች አረጋውያን ያካበቱት ጥበብ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ሀብት ይታያል። አረጋውያን ከትምህርት ሰዓት ውጪ የአናጢነት ሙያ፣ መስተዋት ሥራ፣ ድንጋይ ጠረባ፣ ግንባታ እንዲሁም ቧንቧ ሥራ የመሳሰሉ ሙያዎችን ለልጆች ሲያስተምሩ ያካበቱት እውቀት ጥቅም ላይ ይውላል። ከማስተማር በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አረጋውያን የተለ​ያዩ ሙያዎችን ለመማር ወደ ትምህርት ቤቶች እየጎረፉ ነው።

የጥር 1999 ዘ ዩኔስኮ ኮርየር “በፓሪስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጡረተኞች ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበር” “በዓለም ዙሪያ ለአረጋውያን ትምህርት የሚሰጡ ከ1, 700 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ” ሲል ገልጿል። እነዚህን ዩኒቨርሲቲዎች በተመለከተ መጽሔቱ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ምንም እንኳ መዋቅራቸውና የአስተዳደር አሠራራቸው ከአገር አገር ሰፊ ልዩነት ቢኖራቸውም ለአረጋውያን የተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ ሰዎች በባሕላዊና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የመርዳት ፍላጎት አላቸው።” በጃፓን የሚገኝ እንዲህ ዓይነት ተቋም 2, 500 ተማሪዎች እንዳሉት ተገልጿል!

በዓለም ጤና ድርጅት የእርጅናና የጤና መርሐ ግብር ቡድን መሪ የሆኑት አሌክሳንደር ካላሽ እንዲህ ብለዋል:- “ምንም እንኳ አረጋውያን ለቤተሰባቸውና ለኅብረተሰቡ ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ በአመዛኙ ገንዘብ ስለማይከፈላቸው በአኀዝ መተመን አዳጋች ቢሆንም አጠቃላይ ውጤቱ ግን በጣም ከፍተኛ ነው። መንግሥታት . . . አረጋውያንን እንደ ችግር ከመቁጠር ይልቅ ለችግሮች መፍትሄ የመስጠት ችሎታ እንዳላቸው . . . በአንደኛ ደረጃ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ምንጭ ሊቆጥሯቸው ይገባል።”

በስተርጅና ዕድሜያችን በምናሳልፈው ሕይወት እርካታ ማግኘታችን የተመካው ሌሎች ባላቸው አስተሳሰብና የተዛባ አመለካከት ላይ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ባመዛኙ እኛ ለሕይወት ባለን አመለካከት ላይ እንደሆነ አይካድም። ምንም እንኳ ሰውነትህ እየደከመ ቢሄድም በአእምሮም ሆነ በአካል ንቁ ሆነህ ለመቀጠል በግልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? እባክህ በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ስታነብብ አንዳንድ አረጋውያን ንቁ ሆነው ለመቀጠልና በሕይወት ለመደሰት ቁልፍ ሆኖ ያገኙትን ነገር ሲናገሩ አስተውል።

ንቁ ሆነህ ለመኖር ጣር

እነዚህ ንቁ የሆኑ አረጋውያን ያላቸው አንድ የጋራ ባሕርይ ለዓለማዊ ሥራም ሆነ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ለሚያከናውኑት ተግባር ትርጉም ያለው የሥራ ፕሮግራም መከተላቸው ነው። በተጨማሪም ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ሙሉ ትኩረት ይሰጣሉ በተጨማሪም መሠረታዊ የሆነውን መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ያሟላሉ። ንቁና ደስተኛ ሆኖ ለመኖር የሚያስችሉት እነዚህ ቁልፍ ነጥቦች ወጣቶችንም ሆነ አረጋውያንን እንደሚጠቅሙ ማስተዋልህ አይቀርም።

ይህን ርዕስ እያነበብክ ባለበት በአሁኑ ጊዜ እንኳ አንተም በዕድሜ እየገፋህ መሆኑ እረፍት የሚነሳ ሐቅ ነው። (መክብብ 12:​1) ሆኖም ቡለቲን ኦቭ ዘ ዎርልድ ሄልዝ ኦርጋናይዜሽን ላይ ለቀረበው የማጠቃለያ ሐሳብ ትኩረት መስጠትህ ጥበብ ነው:- “የተለያየ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጤንነት አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ጤናማ ለመሆን ደግሞ ንቁ ሆኖ መኖር ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው።”

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ንቁና ደስተኞች ናቸው

ደቡብ አፍሪካ:- የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነው የ77 ዓመቱ ፒት ቬንትሰል

“ጥሩ አካላዊ አቋም ይዞ ለመኖር ዘወትር የጉልበት ሥራ መሥራት ጠቃሚ እንደሆነ እገነዘባለሁ። ላለፉት በርካታ ዓመታት የራሴን አንዲት ትንሽ የአትክልት ስፍራ ስንከባከብ ቆይቻለሁ። በአትክልት ስፍራው አንዳንድ ነገሮች ካከናወንኩ በኋላ መንፈሴ ይታደሳል። ብዙ ነገሮች ማከናወን እንድችል ‘መወላወል የጊዜ ሌባ ነው፤ ዛሬ ነገ ማለት የቅርብ አጋሩ ነው’ የሚለውን መርህ ለመከተል ጥሬአለሁ።”

[ሥዕል]

“ዘወትር የጉልበት ሥራ መሥራት ጠቃሚ እንደሆነ እገነዘባለሁ።”​—⁠ፒት

ጃፓን:- የማይንቀሳቀስ ንብረት ግዢ እና ሽያጭ አማካሪ ሆኖ የሚሠራው የ73 ዓመቱ ዮሺሃሩ ሺዮዛኪ

“የጡንቻ ቁርጥማት፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና የጆሮ ሕመም አለብኝ። በሳምንት አራት ቀን ከቤት ወደ ሥራ በቢስክሌት የምሄድ ሲሆን ደርሶ መልስ ጉዞው 12 ኪሎ ሜትር ይፈጃል። ይህ ዓይነቱ የአካል እንቅስቃሴ ጀርባዬ ላይ ውጥረት ስለማያስከትልና ለእግሮቼ ጡንቻዎች ብርታት ስለሚጨምርልኝ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጎረቤቶቼን ጨምሮ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር እጥራለሁ። የሌሎችን ጉድለትና ስህተት ከመለቃቀም ለመቆጠብ እጥራለሁ። ሰዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡት ሲነቀፉ ሳይሆን ማበረታቻ ሲሰጣቸው እንደሆነ እገነዘባለሁ።”

[ሥዕል]

“የሌሎችን ጉድለት ከመለቃቀም ለመቆጠብ እጥራለሁ።”​—⁠ዮሺሃሩ

ፈረንሳይ:- የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነችው የ84 ዓመቷ ሌኦን ሻሎኒ

“የፀጉር ሥራ ሙያዬን እወደው ስለነበር በ1982 ጡረታ ስወጣ በጣም ከበደኝ። ምንም ዓይነት ግዴታ ስላልነበረብኝ አቅኚ (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ) ሆንኩ። ፍላጎት ላላቸው በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናቴ አእምሮዬ ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎኛል። መኪና ስለሌለኝ በእግሬ ብዙ እጓዛለሁ። ይህም ጤናማ እንድሆን ረድቶኛል።”

[ሥዕል]

“በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማግኘቴ አእምሮዬ ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎኛል።”​—⁠ሌኦን

ብራዚል:- የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነው የ78 ዓመቱ ፍራንሲስኮ ላፓስቲና

“አንድ ሰው ሲያስቀይመኝ ወይም ችላ ሲለኝ በቀላሉ አልጎዳም። ሰውዬው ጭንቀትና ችግር አጋጥሞት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚቸግረን ቀን አለ። ቂም ላለመያዝ እንዲሁም ሰዎች እኔን እንደሚታገሡኝ ለማስታወስ ጥረት አደርጋለሁ። ይህ በርካታ የልብ ወዳጆች እንዳፈራ አስችሎኛል።”

[ሥዕል]

“ቂም ላለመያዝ ጥረት አደርጋለሁ።”​—⁠ፍራንሲስኮ

አውስትራሊያ:- አሁንም በሳምንት 40 ሰዓት የሚሠራው የ77 ዓመቱ ዶን ማክሌን

“የልብ ቧንቧ ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ ከአራት ዓመታት በኋላም ጥሩ ጤንነት እንዳለኝ ይሰማኛል። ቀዶ ሕክምናው በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የሚዘልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል አዲስ የሕይወት ምዕራፍ አድርጌ አልተመለከትኩትም። ለዓመታት ሳደርገው እንደቆየሁት ሁሉ በየቀኑ በእግር መጓዜን አላቆምኩም። ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ሌሎች ያለ ዕድሜያቸው ውድቅድቅ ሲሉ ስመለከት መቼም ቢሆን የእነሱ ዓይነት አመለካከት ላለመያዝ ወስኜ ነበር። ከሰዎች ጋር መተዋወቅና መጨዋወት በጣም ያስደስተኛል። መንፈሳዊ ጉዳዮችን የሕይወታችን ክፍል ካደረግን መዝሙር 103:​5 ላይ ‘[ይሖዋ] ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፣ ጎልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል’ በማለት የተገለጸው ነገር ሲፈጸም እናያለን።”

[ሥዕል]

“ያለ ዕድሜያችሁ አታርጁ።”​—⁠ዶን

ጃፓን:- የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነችው የ68 ዓመቷ ቺዮኮ ቾናን

“ጥሩ ጤንነት ለማግኘት የሚረዳው ቁልፍ ጭንቀት ከሚፈጥሩና ሰውነትን ከሚያደክሙ ነገሮች መራቅ ነው። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከልክ በላይ ላለመጨነቅ ጥረት ማድረጌን እንዲሁም አልፎ አልፎ በማከናውናቸው የሥራ ዓይነቶች ላይ ለውጥ ማድረጉን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በቅርቡ ጣቶቼንና አእምሮዬን ለማሠራት ስል አንድ ጨዋታ መማር ጀምሬአለሁ። አዳዲስ ነገሮችን መማር ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማኛል።”

[ሥዕል]

“አዳዲስ ነገሮችን መማር ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማኛል።”​—⁠ቺዮኮ

ፈረንሳይ:- የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነው የ73 ዓመቱ ጆሴፍ ከርዱዶ

“ግርማ ሞገስን እንደጠበቁ የእርጅናን ዘመን ለማሳለፍ የሚቻልበት ዋናው መንገድ አቅም በፈቀደ መጠን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ነው። ሥራ መሥራት እርካታ ያስገኛል። እንዲሁም ለአመጋገብ ልማዳችሁ ትኩረት መስጠትና አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይገባችኋል። ሕይወታችሁ ዓላማ ሲኖረው ለየት ያለ መንፈስ እንደሚፈጥርባችሁ ይሰማኛል። መንፈሳዊ ሰው መሆን ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን በመርዳት ረገድ በጣም ወሳኝ እንደሆነ እገነዘባለሁ። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኔ በፊት በጣም ወላዋይና ተጠራጣሪ ነበርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ አንድ ሰው የተለያዩ ሁኔታዎችን መወጣት እንዲችል የአእምሮ ጥንካሬ የሚሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኃይል አለው።”

[ሥዕል]

“መንፈሳዊ ሰው መሆን በጣም ወሳኝ ነው።”​—⁠ጆሴፍ