ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በአረጋውያን ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸም በደል
“የንብረት ጭቅጭቅ በአረጋውያን ላይ በቤት ውስጥ ለሚፈጸመው በደል የተለመደ መንስኤ እየሆነ መጥቷል” ሲል ኦ ኤስታዶ ደ ሳኦ ፓውሎ ዘግቧል። በብራዚል ሳኦ ፓውሎ ከ1991 እስከ 1998 ድረስ ፖሊስ በያዘው የክስ ምርመራ መዝገብ ላይ ከተደረገው ጥናት መረዳት እንደተቻለው 47 በመቶ በሚያክሉት ጉዳዮች ውስጥ ዘመዶች ማለትም ልጆች፣ የልጅ ልጆች፣ የእነርሱ የትዳር ጓደኞችና የሌሎችም እጅ አለበት። “ብዙውን ጊዜ አካላዊና ስነ ልቦናዊ በደል የሚፈጸምባቸው አረጋውያኑ ገና በሕይወት ሳሉ ንብረታቸውን በሌላ ሰው ስም እንዲያዞሩ ወይም ለቤተሰቡ አባላት እንዲያከፋፍሉ ለማስገደድ በሚደረግ ሙከራ ነው” ሲሉ አቃቤ ሕጉ ዛኦ ኤስታቮ ዳ ሲልቫ ተናግረዋል። አረጋውያን በመንግሥት ሆስፒታሎችና መጦሪያዎች ውስጥ ያላንዳች አዘኔታ ተጥለው ዞር ብሎ የሚያያቸው መጥፋቱም አንዳንድ ጊዜ መንስኤው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው። “በድህነት ምክንያት አረጋውያን ሸክም ይሆናሉ፤ ይህ ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት እንዲነግሥ ያደርጋል” ሲሉ ሲልቫ አስረድተዋል።
የተበከሉ የተራራ ላይ ሐይቆች
የተራራ ላይ ሐይቆች የሚታሰበውን ያህል ንጹህ ሆነው አልተገኙም። “ከዞልደን [ኦስትሪያ] በላይ እንደሚገኘው ሽፋርትስዜ ያሉት በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙ ሐይቆች ሳይቀሩ በጣም ተበክለዋል” ሲል ናቹር ኤንድ ኮስሞስ የተባለው የጀርመን መጽሔት ዘግቧል። በከፍታ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ሐይቆች ውስጥ የሚኖሩ ዓሣዎች በዝቅተኛ አካባቢ ካሉት ዓሦች 1,000 እጥፍ የሚበልጥ የዲዲቲ መጠን በውስጣቸው ይገኛል። ለምን? በሐሩር ክልል ባሉት አገሮች መርዘኛ የሆነው ኬሚካል በትነት ከአየር ጋር ይቀላቀልና በንፋስ አማካኝነት ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ይጓዛል። እንደ ተራራ ላይ ሐይቅ ባሉት ቀዝቃዛ ቦታዎች ሲደርስ የዲዲቲው ቅንጣቶች ይጤዙና በዝናብ መልክ ወደ ታች ይወርዳሉ። “እንደ በረዶ የቀዘቀዙት የተራራ ላይ ሐይቆች ቀዝቃዛ ወጥመድ በመሆን ዲዲቲውን ከአየር ላይ ይጠልፋሉ” ሲል መጽሔቱ አስረድቷል። ዲዲቲ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት መርዘኛ የሆነ ፀረ ተባይ ኬሚካል ሲሆን አውሮፓ ውስጥ ሥራ ላይ እንዳይውል ከታገደ 20 ዓመት ቢቆጠርም በታዳጊ አገሮች ውስጥ አሁንም ይሠራበታል።
ልዩ ምልክት ያላቸው መቃብሮች
ሌክስፕሬስ የተባለው የፈረንሳይ የዜና መጽሔት ለንባብ እንዳበቃው “ለየት ያሉ መቃብሮችን መገንባት አዲሱ የቀብር ፋሽን ሆኗል።” መቃብር አዘጋጂዎች ልዩ ምልክት ያላቸውን መቃብሮች በ25 የተለያዩ ዓይነት ቀለሞች፣ በአዳዲስ ንድፎችና በተቀለሙ መስታወቶች ወይም ብረቶች ለመገንባት ምርጫ ያቀርባሉ። እስካሁን ከተሠሩት መቃብሮች መካከል የፓራሹት፣ የውሻና የላም፣ የተሰበረ ባቡር እና በወይን ነጋዴ ትእዛዝ የተሠራ ግዙፍ በርሜል አንዳንዶቹ ናቸው። አንድ ትልቅ ኩባንያ እንደገለጸው ከሆነ መቃብሮችን ለማስጌጥ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በትንሹ 80 የሚያክሉ ሞተር ብስክሌቶችን አስመስሎ ይሠራል። እንደ ጋዜጣው አባባል ከሆነ የአካባቢው ደንብ የሚፈቅደው ሶሌታና ቋሚ ድንጋይ ብቻ ሲሆን የፈረንሳይ ሕግ ግን የግል እምነትን የሚደግፍ መሆኑንና ለመቃብር ቦታው ባለቤት “የግንባታ ነፃነት” እንደሚሰጥ ጠቅሷል።
“‘የሕዝብ መጨናነቅ’ መሠረተቢስ ወሬ ነውን?”
ቫይታሊቲ የተባለው መጽሔት “ጠቅላላው የዓለም ሕዝብ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት በሆነችው በቴክሳስ ውስጥ በቂ መኖሪያ አግኝቶ ሊቀመጥ መቻሉ ያስገርምህ ይሆናል” ሲል ዘግቧል። እንደ መጽሔቱ ገለጻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ያወጣው የዓለም ሕዝብ ብዛት ግምታዊ አኃዝ ስድስት ቢልዮን ሲሆን የቴክሳስ የቆዳ ስፋት ደግሞ 680, 000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው። በመሆኑም ለእያንዳንዱ ሰው የሚደርሰው የመኖሪያ ቦታ ከ113 ስኩዌር ሜትር በላይ ስፋት ያለው ይሆናል። “በዚህ መሠረት 5 አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ 565 ስኩዌር ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ይደርሰዋል። ይህ በቴክሳስ ግዛትም እንኳ ትልቅ መኖሪያ ነው” ሲል ቫይታሊቲ ዘግቧል። “የቀረው የዓለም ክፍል ደግሞ በአጠቃላይ ለመላው የሰው ዘር የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት እና የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች ማካሄጃ የተተወ ይሆናል።”
በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚታይ የአየር ብክለት
በሰሜናዊው ሕንድ ውቅያኖስ አብዛኛው ክፍል ከሚገመተው በላይ ከፍተኛ የአየር ብክለት እንደሚታይበት ሞርገንቬልት ኖክሪክተን የተባለው ፓምፍሌት ገልጿል። ከስድስት አገሮች የተውጣጡ ተመራማሪዎች በክረምት ወቅት ስግር ነፋሳት ከደቡብና ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ጥቀርሻ፣ የአመድ ብናኝ፣ ካርቦናዊ ቅንጣቶች፣ የሚንራል ትቢያ፣ ናይትሬት እና ሰልፌት ይዘው ወደ ሕንድ ውቅያኖስ እንደሚነፍሱ ደርሰውበታል። ከጥር እስከ መጋቢት 1999 ድረስ ባለው ጊዜ 3 ኪሎ ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ድንግዥ (haze) 10 ሚልዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን ክልል ሸፍኖ የነበረ ሲሆን ይህም ከካናዳ የቆዳ ስፋት የሚበልጥ ክልል ነው። “እንደ ሳይንቲስቶቹ አገላለጽ በእስያ ያሉ አካባቢን የሚበክሉ ነገሮች በመበራከታቸው የአየሩ ጥራት በእጅጉ ቀንሷል። ይህ ደግሞ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ሲል ፓምፍሌቱ ዘግቧል።
ቸኮላታ—ለጤና ጥሩ ነውን?
ኒሆን ኬዛይ ሺምቡን የተባለው የጃፓን ጋዜጣ አንዳንዶች ቸኮላታ ለጤና ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ ሲል ገልጿል። ለምን? ምክንያቱም ቸኮላታ ካካኦ ፖሊፊኖል የተባለ ቅመም ስላለውና ይህም አርቲሪዮስክሌሮሲስ የተባለውን በሽታ እንዲሁም ካንሰርን ለመከላከል ስለሚረዳ ነው። ከዚህም
በተጨማሪ ቸኮላታ የሰውነት ሥርዓተ መድህን እንዳይዛባ እንዲሁም ሰውነት ከውጥረት ነፃ እንዲሆን በመርዳት ረገድ ውጤታማ እንደሆነ ይነገርለታል። የኢባራኪ ክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሂሮሺጌ ኢታኩራ እንዲህ ብለዋል:- “ስኳርና ዘይት ሳይበዛበት በርከት ያለ ካካኦ የያዘ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቸኮላታ እጅግ ውጤታማ ነው።” ይሁን እንጂ ፕሮፌሰሩ ሰውነታችን የሚያስፈልጉትን “የተለያዩ የፖሊፊኖል ውሁዶች የያዙ አረንጓዴና ቢጫ አትክልቶች እንዲሁም ፕሮቲን” የመመገብንም አስፈላጊነት ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል።አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን
ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚተነብዩ ሰዎች አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ወደ 100 ከፍ እንደሚል ተስፋ የሚያደርጉ ቢሆንም ከ80 በላይ ማሳደጉ የማይታሰብ ነው። በካናዳ እየታተመ የሚወጣው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል እንዳለው ከሆነ “የሕክምና ተመራማሪዎች የእርጅናን ሂደት የሚለውጥ ዘዴ ካልፈጠሩና ይህም ዘዴ በዝቅተኛ ዋጋ ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ካልቻሉ በቀር አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ጉልህ ለውጥ አያሳይም” በማለት ኤክስፐርቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን የቱንም ያህል የአኗኗር ለውጥ ብናደርግ ምንም ያህል ቫይታሚን ብንውጥ ወይም ምንም ያህል ሆርሞን በመርፌ ብንወጋ ቁጥሩ ከዚህ ብዙም ፈቅ አይልም።” ባለፈው ዓመት የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መመዘኛ መሠረት ከአማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ጋር በተያያዘ ካናዳ ከ191 አገሮች መካከል የ12ኛነትን ደረጃ አግኝታለች። በሽታ ላይ ሳይወድቁ የሚኖሩባቸው የጤንነት ዓመታት ለወንዶች 70 ለሴቶች ደግሞ 74 እንደሆኑ ተሰልቷል። እጅግ ጤናማ ሕዝብ አላት በምትባለው በጃፓን አንድ ዜጋ ቢያንስ 75 ከሕመም ነፃ የሆኑ ዓመታት እኖራለሁ ብሎ ሊጠብቅ እንደሚችል ሪፖርቱ ገልጿል።
በጌጣጌጥ ውስጥ ከሚኖረው ሊድ ተጠንቀቁ
“ልጃችሁ ሊድ ሊኖራቸው የሚችሉ ጌጣጌጦችን ወደ አፉ የሚያስገባ ከሆነ ወዲያውኑ ይህን ነገር ልታስወግዱት ይገባል” በማለት ሄልዝ ካናዳ የተባለው ሪፖርት ምክር ለግሷል። በርካሽ ዋጋ በሚገዙ የልጆች ጌጣጌጦች ላይ በላቦራቶር የተደረጉት ሙከራዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎች ከ50 እስከ 100 እጅ የሚደርስ ሊድ አላቸው። ሪፖርቱ እንደጠቆመው ከሆነ “ዝቅተኛ መጠን ያለው ሊድ እንኳ ወደ ሰውነት ከገባ በሕፃናትና በትናንሽ ልጆች የአእምሮና የባሕርይ ብስለት ላይ የጤና ችግር ያስከትላል።” እርግጥ መለኪያው ከሌለ ምን ያህል የሊድ መጠን እንዳለ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። እንግዲያው የልጆች ጌጣጌጥ ዋጋው ርካሽ ስለሆነ ናሽናል ፖስት የተባለው ጋዜጣ ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ያቀረበው ሐሳብ “ጥርጣሬ ከገባችሁ አውጥታችሁ ጣሉት” የሚል ነው።
ልጆች ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሚቸገሩበት ምክንያት
በርሊነር ሞርገንፖስት የተባለው ጋዜጣ እንዳሰፈረው በበርሊን የሚገኘው የሕፃናት ሐኪሞች ማኅበር ቃል አቀባይ ልጆች የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ እንዲቸገሩ ምክንያት የሚሆነው ከልክ ያለፈ ቴሌቪዥን የማየትና ኮምፒውተር የመጠቀም ልማዳቸው መሆኑን ተናግሯል። ልጆች በተለይ ደግሞ ገና ትምህርት ቤት ያልገቡ ሕፃናት ቴሌቪዥን በማየት ወይም ኮምፒውተር በመጠቀም የሚያሳልፉት ጊዜ አነስተኛ ሊሆንና በእውን ከሰዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ በማድረግና ከእነርሱ ጋር በመግባባት የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ በብሪታንያ እየታተመ የሚወጣው ዘ ሰንዴይ ታይምስ እንዳለው አንድ አዲስ ምርምር “በሃያዎቹና በሠላሳዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ሕይወታቸው በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ላይ በእጅጉ የተመካ ከመሆኑ የተነሣ ከባድ የማስታወስ ችግር” እንዲሁም “አስፈላጊና አላስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች የመለየት” ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ይጠቁማል።
ምሥክሮቹ በሩስያ ፍርድ ቤት ድል ተቀዳጁ
የካቲት 24, 2001 የወጣው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ዛሬ [የካቲት 23] የይሖዋ ምሥክሮች በሞስኮው ፍርድ ቤት፣ ጥላቻንና ጽንፈኛነትን የሚያራምዱ ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎችን በሚያግደው የ1997 ሕግ ሽፋን ቡድኑን ለማሳገድ ተነስተው በነበሩት ከሳሾች ላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ድል ተቀዳጅተዋል።” ክሱ በመጋቢት 12, 1999 ለሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ አምስት ኤክስፐርቶች የምሥክሮቹን እምነት እንዲያጠኑ ተመረጡ። ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ክሱ በእንጥልጥል ቆይቷል። የካቲት 6, 2001 ችሎቱ እንደገና ጉዳዩን መስማት ሲጀምር የዐቃቤ ሕጉ ክስ መሠረተ ቢስ እንደሆነ ለማስተዋል የወሰደበት ጊዜ ከሦስት ሳምንት ያነሰ ነበር። ይሁን እንጂ የሞስኮ ከተማ አቃቤ ሕግ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ። ግንቦት 30 ቀን ጥያቄው ምላሽ አገኘና ችሎቱ ጉዳዩን እንደገና ለማየት ተሰየመ። ዘ ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንዳለው “በምዝገባው ሂደት ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን ፍዳ ያስቆጠረው የ1997 ሃይማኖታዊ ሕግ ሲወጣ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴን አጥብቃ የምትቃወመው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ አቀንቃኝ ነበረች።”
በእርዳታ ልብሶች ማትረፍ
ዙድቬስት ፕሬሴ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንደገለጸው በእርዳታ ከሚሰጡት ልብሶች መካከል በእርግጥ ችግሩ ላለባቸው ሰዎች የሚደርሰው “ጥቂቱ ብቻ” ነው። ጀርመን ውስጥ ችግረኞችን ለመርዳት በየዓመቱ ከ500, 000 ቶን በላይ አልባሳት በእርዳታ መልክ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ልብሶቹን የሚያሰባስቡት ድርጅቶች ለንግድ ተቋማት በመሸጥ በእርዳታ ልብሶች በመቶ ሚልዮን የጀርመን ማርክ የሚቆጠር ትርፍ ያጋብሳሉ። ብዙውን ጊዜ ልብሱን የሚያሰባስቡት ድርጅቶች ልብሶቹ የት እንደሚደርሱ እንኳ አያውቁም። በመሆኑም ጋዜጣው እንዲህ ብሏል:- “የምትለግሱት ልብስ በእርግጥ ለነዳያን እንዲደርስ የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁ ለችግረኞቹ ማድረስ ወይም ችግሩ ባለበት አካባቢ ለሚገኙ የታመኑ ሰዎች መላክ ይኖርባችኋል።”