በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ...

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

“አንዳንዴ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ከባድ ነው። ይህ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል።”—⁠የ17 ዓመቷ አናሌዛ

“መጽሐፍ ቅዱስ አሰልቺ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”—⁠የ22 ዓመቷ ኪምበርሊ

ብዙ ሰዎች ማንበብ አይወዱም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያክል ትልቅ መጽሐፍ እንዲህ ላሉት ሰዎች ይቅርና ማንበብ ለሚወዱት እንኳ የሚዘለቅ ላይመስል ይችላል። “ለእኔ መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ብዙ አስቸጋሪ ቃላትን የያዘ ትልቅ መጽሐፍ ነው” ስትል የ17 ዓመቷ ታሚ ተናግራለች። “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከፍተኛ ትኩረትና ጽናት ይጠይቃል።”

ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ቤት የሚሰጥህ የቤት ሥራ፣ ቤት ውስጥ የምታከናውናቸው ሌሎች ተግባራትና መዝናኛ ጊዜህንና ጉልበትህን ያሟጥጡብህ ይሆናል። ይህም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን በትኩረት ማንበብንና ከንባቡ ደስታ ማግኘትን ከባድ ሊያደርገው ይችላል። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኦሊሲያም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመዘጋጀትና በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንዲሁም እምነቷን ለሌሎች ለማካፈል ጊዜ ትመድባለች። እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “ሌላው ሥራ ማለቂያ ያለው ስለማይመስል መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።”

ሆኖም ኦሊሲያና ታሚም ሆኑ ሌሎች ብዙ ወጣቶች እነዚህን እንቅፋቶች ተወጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብቡ ሲሆን ንባባቸውም አስደሳች ሆኖላቸዋል። አንተም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን አስደሳች ማድረግ ትችላለህ! የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምትችልባቸውን ሦስት መንገዶች ተመልከት።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጊዜ ዋጅ

“ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አሰልቺ ነው የሚሉት ብዙ ስላላነበቡት ይመስለኛል” በማለት የ18 ዓመቷ ኬሊ ተናግራለች። ብዙ ጊዜ ደጋግማችሁ የምትሠሩት ስፖርት ወይም የምትጫወቱት ጨዋታ እንደሚያስደስታችሁ ሁሉ አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስ የምታነብቡ ከሆነ ንባባችሁ አስደሳች ይሆንላችኋል።

ሆኖም ያላችሁ ነፃ ጊዜ ትንሽ ቢሆንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) ቴሌቪዥን መመልከትን በመሳሰሉት ብዙም አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች የምታጠፋውን ሰዓት በመቀነስ ‘ጊዜ መዋጀት’ ትችላለህ። ጳውሎስ “ጊዜ” በማለት የተጠቀመበት ቃል ለአንድ ለተለየ ዓላማ የተወሰነን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የምትወስነው ጊዜ መቼ ሊሆን ይችላል?

ብዙዎች ጠዋት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ የሚገኘውን የዕለቱን ጥቅስና ሐሳብ ከመረመሩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ያነብባሉ። * ሌሎች ደግሞ ከመተኛታቸው በፊት ማንበብን ይመርጣሉ። ለአንተ ሁኔታ ሊሠራ የሚችል የተወሰነ ሰዓት ከመረጥህ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ። ኦሊሲያ ያስተዋለችውን እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ቋሚ የንባብ ፕሮግራም እንዲኖረኝ በማድረግ ረገድ የረዳኝ ቁልፍ ነገር ፕሮግራሜን እንደ ሁኔታው ማስተካከሌ ይመስለኛል።”

አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በየቀኑ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ይመድባሉ። እንዲህ በማድረግ በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበው መጨረስ ችለዋል! ይህ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ከተሰማህ በእያንዳንዱ ቀን የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለማንበብ ግብ አውጣ። ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የመደብከውን ጊዜ በማክበር ረገድ ጥብቅ ከሆንክ ለአምላክ ቃል ያለህ ፍቅር ያድጋል።​—⁠መዝሙር 119:97፤ 1 ጴጥሮስ 2:2

ጥበብ ለማግኘት ጸልይ

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው የሚያነብቡ ሰዎች እንኳ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነው እንደሚያገኟቸው አይካድም። የመጽሐፉ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ መጽሐፉ የያዘውን መልእክት እንድትረዳ ይፈልጋል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ ያለውን ትንቢት ሙሉ በሙሉ መረዳት ስላልቻለ አንድ ኢትዮጵያዊ ተጓዥ ይናገራል። ሰውዬው እርዳታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ስለነበር የይሖዋ መልአክ ትንቢቱን እንዲያብራራለት ፊልጶስ የተባለውን ሚስዮናዊ ላከለት።​—⁠ሥራ 8:26-39

እንዲያውም ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚጀመረው በንባብ ሳይሆን በጸሎት ነው። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ከመክፈታቸው በፊት የሚያነብቡትን ለመረዳትና ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጣቸው ይሖዋን በጸሎት የመጠየቅ ልማድ አዳብረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:7፤ ያዕቆብ 1:5) የአምላክ መንፈስ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወይም የገጠሙህን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችሉህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሳይቀር እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል።

አንድ ወጣት ክርስቲያን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ጥሎን ሄደ። አንድ ቀን ምሽት አልጋዬ ላይ ሆኜ አባቴ የሚመለስበትን መንገድ እንዲያመቻች ይሖዋን ለመንኩት። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሴን አንስቼ መዝሙር 10:​14ን አነበብኩ። እንዲህ ይላል:- ‘ድሀ ራሱን ለአንተ [ለይሖዋ] ይተዋል፣ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።’ ትንሽ ቆም አልኩ። ይሖዋ እያነጋገረኝ እንዳለና አባቴና ረዳቴ መሆኑን እየነገረኝ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። ከእርሱ የተሻለ አባት የት ላገኝ እችላለሁ?”

ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስህን ከማንበብህ በፊት መጸለይን ልማድ ማድረግ ትችላለህ? አድሪያን እንዲህ የሚል አስተያየት ይሰጣል:- “ከይሖዋ ጋር የሁለት ወገን የሐሳብ ልውውጥ ይሆንላችሁ ዘንድ ንባባችሁን ከመጀመራችሁ በፊት ጸልዩ። እርግጥ ንባባችሁን ከጨረሳችሁ በኋላም መጸለዩ ጥሩ ነው።” ልባዊ ጸሎት ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የመደብከውን ጊዜ በማክበር ረገድ ያደረግኸውን ቁርጥ ውሳኔና ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ያጠነክርልሃል።​—⁠ያዕቆብ 4:8

ንባብህን ሕያው አድርገው

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ኪምበርሊ መጽሐፍ ቅዱስ አሰልቺ ሆኖባታል። እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥን ወይም አውሮፕላን ከመፈልሰፉ ከረጅም ጊዜ በፊት ከመሆኑም ሌላ ባለታሪኮቹ ከሞቱ ብዙ ሺህ ዓመታት በማስቆጠራቸው በጣም ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። የሆነ ሆኖ ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም . . . ነው” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 4:12) ታዲያ እንዲህ ያለ ጥንታዊ መጽሐፍ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?

የሕጉ ፈጣን ጸሐፊ በነበረው በዕዝራ ዘመን በሺህዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና “አስተውለውም የሚሰሙ” ሁሉ የሙሴ ሕግ ሲነበብ ለማዳመጥ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ነበር። በዚያን ወቅት ሕጉ ከ1, 000 ዓመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሮ ነበር! ሆኖም ዕዝራና ሌሎች ረዳቶቹ ‘የእውነተኛውን አምላክ ሕግ መጽሐፍ ጮክ ብለው ማንበባቸውን ቀጠሉ፤ ያነበቡትንም ያብራሩላቸውና መልእክቱን ያስረዷቸው ነበር። ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።’ እነዚህ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲያብራሩና ንባቡን ሕያው አድርገው ሲያቀርቡት ምን ውጤት ተገኘ? “ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ።”​—⁠ነህምያ 8:1-12 NW 

በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ወቅት ‘መልእክቱን ማስተዋል’ የምትችለው እንዴት ነው? ማንበብ ከባድ ሆኖ የሚታያት ካቲ ትኩረቷን ለማሰባሰብ ጮክ ብላ ታነብባለች። ኒኪ ደግሞ ራሷን በታሪኩ ውስጥ ለማስገባት ትሞክራለች። “በዚያ ሁኔታ ውስጥ ብገኝ ምን እንደሚሰማኝ አስባለሁ” በማለት ትናገራለች። “ስለ ሩትና ኑኃሚን የሚናገረውን ታሪክ በጣም እወድደዋለሁ። ደግሜ ደጋግሜ ባነብበው አይሰለቸኝም። ወደ አንድ አዲስ ከተማ በተዛወርኩበት ወቅት ከዚህ ታሪክ ማጽናኛ አግኝቻለሁ። ምክንያቱም ሩት ወደማታውቀው አገር ስትሄድ ምን እንደተሰማት መገመት አያቅተኝም። ምን ያህል በይሖዋ ላይ እንደታመነች ማየት ችያለሁ። ይህም እኔም ተመሳሳይ ነገር እንዳደርግ ገፋፍቶኛል።”​—⁠ሩት ምዕራፍ 1-4

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሚሠራ’ ሆኖ እንዲገኝ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። በምታነብበት በእያንዳንዱ ወቅት ጊዜ ወስደህ በጥቅሶቹ ላይ አሰላስል። እንዲሁም የተማርከውን እንዴት በሥራ ላይ ልታውለው እንደምትችል አስብ። ንባብህን ለማጎልበት እንዲረዳህ በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች መመልከት ትፈልግ ይሆናል። *

ጽና!

በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መጽናት ቀላል አይደለም። በጣም ግሩም ነው የሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም እንኳ ሳይቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ መስተካከል ያስፈልገው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ለማንበብ ባወጣኸው ግብ መጽናት የምትችለው እንዴት ነው?

ወዳጆችህና ቤተሰቦችህ ሊረዱህ ይችላሉ። የአሥራ አምስት ዓመቷ አምበር እንዲህ ትላለች:- “የምተኛው ከእህቴ ጋር ነው። አንዳንድ ጊዜ በጣም ስለሚደክመኝ የሚታየኝ መተኛት ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ግን እህቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን እንዳልረሳ ታስታውሰኛለች። ስለዚህ ፈጽሞ ረስቼው አላውቅም!” አስደሳች ሆኖ ያገኘኸው አንድ ጥቅስ ወይም ምዕራፍ ካለ ሐሳቡን ለሌሎች አካፍል። ይህም ለአምላክ ቃል ያለህን አድናቆት ያሳድግልሃል። እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል። (ሮሜ 1:11, 12) የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ቀናት ካቋረጥክ በዚህ ተስፋ አትቁረጥ! ካቆምክበት በመጀመር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የንባብ ፕሮግራምህን ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ከማንበብ የሚገኙትን ብዙ ጥቅሞች ፈጽሞ አትርሳ። ይሖዋን በቃሉ አማካኝነት በማዳመጥ ከእርሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ትችላለህ። ሐሳቡንና ስሜቱን ልትረዳ ትችላለህ። (ምሳሌ 2:1-5) ከሰማያዊ አባታችን ያገኘናቸው እነዚህ ውድ እውነቶች ጥበቃ ይሆኑልሃል። መዝሙራዊው “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል?” በማለት ጠይቋል። “ቃልህን በመጠበቅ ነው።” (መዝሙር 119:9) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አውጣ። እንዲሁም ባወጣኸው ፕሮግራም ጽና። እንዲህ ካደረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ካሰብከው የበለጠ አስደሳች ሆኖ ታገኘዋለህ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።

^ አን.22 መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ለመቆፈር የሚረዱ አንዳንድ ተግባራዊ ሐሳቦች በጥቅምት 1, 2000 የመጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 16-17 ላይ ቀርበዋል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጸሎትና ምርምር ማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ይበልጥ ትርጉም አዘል ከማድረጉም በላይ የቅዱሳን ጽሑፎችን መልእክት እንድታስተውል ይረዳሃል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስህን በታሪኩ ውስጥ ማስገባትህ ቅዱሳን ጽሑፎች ሕያው እንዲሆኑልህ ያደርጋል