የተለያየ ቀለም ያላቸው ኬርሞዲዎች
የተለያየ ቀለም ያላቸው ኬርሞዲዎች
ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“በኋላ እግሮቻቸው ይቆማሉ፤ በቂጣቸው ይቀመጣሉ . . .፤ ሌላው ቀርቶ ሲተኙ ያንኮራፋሉ። . . . ብልሆች ናቸው፣ የማወቅ ጉጉት አላቸው፣ አንድን ነገር ለመማር ፈጣኖች ሲሆኑ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በደንብ መላመድ ይችላሉ። ነገረ ሥራቸው ሁሉ እንደ ሰው ይመስላል።”
በካናዳ ሰሜናዊ ምዕራብ የባሕር ዳርቻ የሚገኘውን ብርቅዬ ነጭ ድብ አስመልክተው ከላይ ያለውን የተናገሩት የዱር አራዊት ስነ ሕይወት ባለሙያ የሆኑት ዌይን ማክሮሪ ናቸው። የሳይንሱ ዓለም ከዚህ ድብ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በ1900 የኒው ዮርክ የስነ እንስሳ ማኅበር አባል በነበረው በዊልያም ሆርናዴይ አማካኝነት ነው። በወቅቱ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ከምትገኘው ከቪክቶሪያ የተገኙ የድብ ቆዳዎችን ዝርዝር የያዘ ጽሑፍ እያዘጋጀ ሳለ አንድ ለየት ያለ ቆዳ አገኘ። ወርቅማ ቀለም በስሱ የሚንፀባረቅበት ወደ ቢጫነት ወሰድ የሚያደርገው ነጭ ቆዳ ሲሆን ቅርጹ ከጥቁር ድብ ቆዳ ጋር ይመሳሰላል።
ሆርናዴይ የማወቅ ፍላጎቱ በእጅጉ ስለተነሳሳ የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ግዛት ሙዝየም ዲሬክተር የሆኑት ፍራንሲስ ኬርሞዲ አዲስ የድብ ዝርያ መሆን አለበት ብሎ ስላሰበው አውሬ ተጨማሪ መረጃዎችን በመሰብሰቡ ሥራ እንዲረዱት ጠየቃቸው። ኬርሞዲ ናሙናዎችና መረጃዎች ለማግኘት ያደረጓቸውን ጥረቶች ግምት ውስጥ በማስገባት በ1905 ሆርናዴይ ድቡን ኡርሰስ ኬርሞዴይ ማለትም የኬርሞዲ ድብ በማለት ሰየመው።
ኬርሞዲዎች የጥቁሩ ድብ ዝርያዎች ቢሆኑም እንኳ ቀለማቸው ሁልጊዜ እንደ ስማቸው ሆኖ አይገኝም። ኬርሞዲ የተሰኘው ድብ በሚገኝበት ክልል ውስጥ የሚኖሩትና የቺምሲያን ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት የአገሬው ተወላጅ ሕንዶች ይህን ድብ ሞችከሞ ወይም ነጭ ድብ በማለት ይጠሩታል። በተጨማሪም ብርቱካንማ፣ ወደ ቡናማነት የሚወስደው ቀይ፣ ወርቃማ፣ ፈካ ያለ ቢጫና ወደ ሰማያዊነት የሚወስደው ግራጫ ቀለም ያላቸው አልፎ ተርፎም በጥቁር፣ በቡናማና በነጭ ቀለማት የተዥጎረጎሩ ድቦች የታዩባቸው ጊዜያትም አሉ።
የሥነ ሕይወት ባለሙያዎች ነጭ ኬርሞዲዎች ሊኖሩ የቻሉበትን ምክንያት አሁንም ድረስ በእርግጠኝነት መረዳት አልቻሉም። ለየት ያለ ቀለም እንዲኖራቸው የሚያደርገው አንዱ ምክንያት አንድ ወጥ የሆነ ሥርዓት ያልተከተለ በራሂያዊ ቅይርታ (mutation) ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል። ከአሥር ኬርሞዲዎች መካከል ነጭ ቀለም የሚኖረው አንዱ ብቻ ነው። በካናዳ ሰሜናዊ ምዕራብ የባሕር ዳርቻ የሚገኙት ኬርሞዲዎች በዓይነታቸው ለየት ያሉ በመሆናቸው በአድናቆት ሊታዩ ይገባል።
የኬርሞዲን ክልል መጎብኘት
ኬርሞዲዎች በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ሰሜናዊ ዳርቻ 75, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሆን ክልል ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። ከቫንኩቨር ተነስተህ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 600 ኪሎ ሜትር ያህል ብትጓዝ በኪቲማት አቅራቢያ ወደሚገኙት ወደ ፕሪንሰስ ሮያል አይላንድና ደግለስ ቻናል በመባል ወደሚታወቀው አካባቢ ትደርሳለህ። በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 150 ኪሎ ሜትር ያህል ስትጓዝ በስኪና ወንዝ ዳርቻዎች የሚገኙትና ዛፍ እየቆረጡ ግንዲላ በማቅረብ ሥራ የሚተዳደሩት የቴሬስ ሰዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ ትደርሳለህ። ይህ ክልል የኬርሞዲ ማዕከል ሲሆን በምዕራብ ካናዳ ከሚገኙት ሥፍራዎች ሁሉ በዱርነቱና በተፈጥሮ ሃብቱ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛል።
ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወረውን ይህን ነጭ ድብ በጨረፍታ እንኳ ለማየት የኬርሞዲን ጠባይ የሚያውቅ ልምድ ያለው የጫካ አስጎብኚ ማግኘት ያስፈልግሃል። ይህን ድብ ለማየት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓሦች በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጅረቶች ውስጥ የሚርመሰመሱበት የጥቅምት ወር ነው። በዚህ ወቅት ኬርሞዲዎች የተትረፈረፈውን ዓሣ እንደ ልብ ለመመገብ ከከፍተኛ ቦታዎች ላይ ይወርዳሉ። የእነዚህን ድቦች የአመጋገብ ልማድ የተመለከተ አንድ ሰው ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “መዳፋቸውን የመረጡት ዓሣ ጭንቅላት ላይ ያሳርፉና ቆዳውን ከስንጥቡ አንስቶ በመገሽለጥ የሚመገቡትን ሥጋ ያገኛሉ።”
ኬርሞዲዎች ምን ዓይነት እንስሶች ናቸው?
ኬርሞዲዎች ሰላማውያን፣ የሚቀረቡና ጨዋታ የሚወዱ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ሌሎቹ ድቦች ሁሉ ኬርሞዲዎችም የሚያደርጉትን ነገር ለመተንበይ አዳጋች ከመሆኑም በላይ አደገኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የማየት ኃይላቸው ደካማ እንደሆነ ይነገራል። ሾል ያለው ትንሹ አፍንጫቸውና ወጣ ያሉት ያፍንጫቸው ቀዳዳዎች ከፍተኛ የማሽተት ችሎታ እንዲኖራቸው በሚያስችል መንገድ የተነደፉ ናቸው። ሲሄዱ የሚጎተቱ ቢመስሉም በጣም ፈጣኖች ናቸው። አንዳንዶቹ በአጭር ርቀት በሰዓት ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ እንደሚችሉ ተረጋግጧል!
ትልልቆቹ እንስት ድቦች ከ130 እስከ 190 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያላቸው ሲሆን ከ50 እስከ 180 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ። ተባእቶቹ ከእንስቶቹ ገዘፍ ያሉ ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ከ200 ኪሎ ግራም በላይ ይመዝናሉ። ኬርሞዲዎች በኋላ እግሮቻቸው ሲቆሙ ከ250 እስከ 275 ሴንቲ ሜትር ይደርሳሉ። የተዋጣላቸው ዋናተኞችም ናቸው። እንዲያውም ዓሣ የማጥመድ ሥራን እየተዘዋወረ የሚቆጣጠር አንድ መኮንን አንድ ኬርሞዲ በአቅራቢያ ከሚገኝ ደሴት ተነስቶ ወደ ዋናው መሬት እየዋኘ ሲያቋርጥ ተመልክቷል። ጀልባውን አዙሮ ድቡ ወዳለበት አካባቢ ሲጠጋ ድቡ አየር ለመሳብ ብቻ ብቅ እያለ ከውኃው በታች መዋኘቱን ቀጠለ።
ሰዎችን መተናኮል
ድቦች ቀለባቸውን ከሰዎች ማግኘት እንደሚችሉ አድርገው ማሰብ ሲጀምሩ ብዙውን ጊዜ ከሰዎች መራቃቸው ይቀርና ኃይል ሊጠቀሙ እንዲሁም አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ድቦች ይገደላሉ። ስለዚህ ወደፊት ዱር ውስጥ ድብ አጋጥሞህ ዓይን ዓይንህን እያየ ምግብ ቢለምንህና ብትሰጠው በራስህ ላይ አደጋ እየጠራህ ብቻ ሳይሆን መሞቻውንም እያፋጠንክ ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብሃል።
ይህን ማራኪ ድብ ስናስብ በድብ ዝርያዎች ብዛት ለመደመም እንገደዳለን። የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ምንኛ አስደናቂና አስደሳች ናቸው! የሰው ልጅ እንዲህ ያሉትን ማራኪ ፍጥረታት የመንከባከብ ትልቅ ኃላፊነት ወድቆበታል!
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]
Howie Garber/www.wanderlustimages.com