በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅህ ከአደጋ የተጠበቀ ነውን?

ልጅህ ከአደጋ የተጠበቀ ነውን?

ልጅህ ከአደጋ የተጠበቀ ነውን?

የዩ ኤስ ብሔራዊ የመንገዶች ትራፊክ ደህንነት መምሪያ (ኤን ኤች ቲ ኤስ ኤ) ባወጣው ዘገባ መሠረት ከ5 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት ሕይወት በመቅጠፍ ረገድ የመኪና አደጋ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል። ኤን ኤች ቲ ኤስ ኤ እንዳለው ከሆነ “በመኪና አደጋ ከሚሞቱት ሕፃናት መካከል ከ50 በመቶ የሚበልጡት ለአደጋ መከላከያነት በተዘጋጁ መቀመጫዎችና ቀበቶዎች አልተጠቀሙም። ከዚህም በተጨማሪ ከ5ቱ ውስጥ 4ቱ በእነዚህ መቀመጫዎችና ቀበቶዎች ቢጠቀሙም በተገቢው መንገድ ሳይታሠሩ ቀርተዋል።”

ኤን ኤች ቲ ኤስ ኤ ሕፃናት ይዘው ለሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችና ማሳሰቢያዎች አቅርቧል። ሕጉ ከአገር አገር ብሎም ከግዛት ግዛት ቢለያይም ብዙ ወላጆችና ሞግዚቶች እነዚህን መመሪያዎች ጠቃሚ ሆነው ሊያገኟቸው ይችላሉ። እባክህ የአገርህ ሕግ ምን እንደሚል ለማወቅ ሞክርና አብረውህ የሚጓዙትን ሕፃናት ከአደጋ ለመጠበቅ ስትል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ!

አደጋን ለመከላከል የሚረዱ ነጥቦች

ለሁሉም ልጆች አስተማማኝ የሆነው ቦታ የኋለኛው መቀመጫ ነው።

1 ሕፃናት መቀመጥ የሚኖርባቸው ኋላ ወንበር ላይ በሚገባ በታሠረ መቀመጫ ላይ ለሹፌሩ ጀርባቸውን ሰጥተው ነው።

2 ቢያንስ አንድ ዓመት የሞላውና 9 ኪሎ ግራም የሚመዝን ልጅ ፊቱን ወደ ሾፌሩ አዙሮ መቀመጥ ይችላል።

3 አሥራ ስምንት ኪሎ ግራም የሚመዝን ልጅ ጭን አካባቢ የሚታሰር ቀበቶና በትከሻ በኩል የሚያልፍ ቀበቶ በተገጠመለት ልጁን ከፍ አድርጎ ሊያስቀምጥ በሚችል መቀመጫ ላይ ወይም “ቡስተር ሲት” እንዲቀመጥ ማድረግ ይቻላል።

4 ወደ 36 ኪሎ ግራም ገደማ ክብደትና 140 ሴንቲ ሜትር ገደማ ቁመት ያለው ልጅ ለአዋቂዎች ተብሎ የተዘጋጀውን ቀበቶ መጠቀም ሊጀምር ይችላል።

ማሳሰቢያ

ልጆች ቢያንስ 13 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በፊተኛው ወንበር ላይ መቀመጥ አይኖርባቸውም። በግጭት ጊዜ ወዲያው በመነፋት ሰዎችን ከአደጋ የሚከላከለው የአየር ከረጢት በሕፃናትና በትንንሽ ልጆች ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

“ቡስተር ሲት” መጠቀም ሲያስፈልግ መቀመጫው ሕፃኑ ወደፊት ተወርውሮ እንዳይሄድ የሚከላከል ነገር ከሌለው ጭኑ አካባቢ የሚታሰረው ቀበቶ ብቻውን ሕፃኑን ከአደጋ እንደማያስጥለው መገንዘብ ያስፈልጋል።

በትከሻ በኩል አልፎ የሚታሰር ቀበቶ ብቻውን አንድን ሕፃን ከአደጋ ይጠብቀዋል ብለህ አታስብ። አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ቀበቶው አንገቱን ሊቆርጠውና ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዲያውም ሞት ሳይቀር ሊያስከትልበት ይችላል።

የልጆችን መቀመጫዎች በምትገጥምበትና በምትጠቀምበት ወቅት መመሪያውን በጥብቅ ተከተል። ኤን ኤች ቲ ኤስ ኤ እንዳለው ከሆነ “‘በጣም አስተማማኝ’ የተባለው መቀመጫ እንኳ በትክክል ጥቅም ላይ ካልዋለ ልጅህን ከአደጋ ላይጠብቀው ይችላል።”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልጆችን መቀመጫ በትክክል መግጠም ቀበቶውን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማያያዝን ይጨምራል