አባቶች የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና
አባቶች የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና
“ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣት ወንዶች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይፈልጋሉ። ከ21 እስከ 39 ባለው የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ወንዶች ውስጥ 82 በመቶ የሚሆኑት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥቂት ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችላቸው የሥራ ዓይነት ይመርጣሉ” ሲል የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ያወጣውን ጥናት በመጥቀስ የካናዳው ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። በጥናቱ መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ዕድሜያቸው ከ21 እስከ 65 እና ከዚያም በላይ ከሚሆኑት 1, 008 ወንዶችና ሴቶች መካከል 71 በመቶ የሚያክሉት ወጣት ወንዶች “ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ሊያገኙት ይችሉ የነበረውን ክፍያ ለመሠዋት ፈቃደኛ እንደሆኑ” ተናግረዋል።
ብዙ አባቶች በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈልጉት ለምንድን ነው? አባቶች ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ የሚያበረታታው ናሽናል ፋዘርሁድ ኢንሽየቲቭ የተባለውን ድርጅት ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ የሆኑት ዴቪድ ብለንከንሆርን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚኖሩ 1, 600 የሚያክሉ ወንዶች ላይ በ1994 በተደረገው ጥናት መሠረት 50 በመቶ የሚሆኑት በልጅነታቸው የአባቶቻቸውን ስሜታዊ እንክብካቤ እንዳላገኙ መናገራቸውን ገልጸዋል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ብዙ አባቶች እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲደገም አይፈልጉም።
በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው አባቶች በእነርሱ ላይ ጥሩ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ዘ ቶሮንቶ ስታር የዩናይትድ ስቴትስ የጤናና ሰብዓዊ አገልግሎቶች ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ምግብ ሲበሉ፣ ሽርሽር ሲሄዱና የቤት ሥራዎቻቸውን እንዲሠሩ ሲያግዟቸው “ልጆች የሚኖራቸው አስቸጋሪ ባሕርይ ይቀንሳል፣ ይበልጥ ተግባቢዎች ይሆናሉ። እንዲሁም ትምህርት ቤት ውስጥ ካሉ ልጆችና ጎልማሶች መካከል የተሻለ ውጤት ያመጣሉ።”
ከላይ ያሉት ሐሳቦች ልጆችን ስለማሳደግ የተሰጠውን አንድ ዝግጅት ጎላ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። ይህ ዝግጅት ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት በጽሑፍ ሲሰፍር ይሠራ የነበረውን ያህል ዛሬም ይሠራል። የቤተሰብ መሥራች የሆነው አካል በተለይ አባቶች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አዝዟል። (ኤፌሶን 3:14, 15፤ 6:4) አባቶች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የአምላክን ፍቅር እንዲተክሉ እንዲሁም መመሪያዎቹንና ትእዛዛቱን ለልጆቻቸው እንዲነግሩ ተመክረው ነበር። ይህንን የሚያደርጉትም ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድም ሲሄዱ፣ ሲተኙ፣ ሲነሱ’ እንደሆነ አምላክ ነግሯቸዋል።—ዘዳግም 6:7
ወላጅነት የአባትም የእናትም ኃላፊነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” በማለት ልጆችን ያሳስባል። (ምሳሌ 1:8፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አባት የሚጫወተው ሚና ወሳኝ ነው። ይህም እናትን መደገፍንና ማክበርን እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ ሥራ መካፈልን ይጨምራል። በተጨማሪም ለልጆች በማንበብና እነርሱን በማነጋገር ጊዜ ማሳለፍን ይጨምራል። ይህ ደግሞ ለልጆች በጣም አስፈላጊ የሆነውን ስሜታዊ ፍላጎት ያሟላል።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ምክርና የተስተካከለ ቤተሰብ ለመመስረት የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች የያዘ ከሁሉ የተሻለ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። የቤተሰቡን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት በትጋት የሚያሟላ አባት አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ነው።