አባ ኮዳ—የተሳሳተ ግምት የሚሰጠው ወፍ
አባ ኮዳ—የተሳሳተ ግምት የሚሰጠው ወፍ
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“የአባ ኮዳን ያህል መጥፎ ገድ ያለው ወፍ . . . አጋጥሞኝ አያውቅም።” ዘ ዎርልድስ ዋይልድ ፕሌስስ —አፍሪካስ ሪፍት ቫሊ
በአፍሪካ ከሚገኙ በርካታ አእዋፍ መካከል የአባ ኮዳን ያህል የሰላ ነቀፋ የደረሰበት የለም። ብዙውን ጊዜ ወፉ ክፉና አስቀያሚ እንደሆነ እንዲሁም በጎ ዝንባሌ እንደሌለው ተደርጎ ይገለጻል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አባ ኮዳ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ከባድ ሳንካ ገጥሞታል።
የሚያምር መልክና የሚጥም ዜማ ያላቸው አእዋፍ ቀልብህን ይማርካሉ? እንግዲያው አባ ኮዳ ሁለቱም ይጎድለዋል። አንድም ላባ የማይታይበት ሮዝ መልክ ያለው ጭንቅላቱና አንገቱ ወፉን አስቀያሚና የተጎሳቆለ ገጽታ አላብሶታል። ትልልቆቹ ወፎች አንገታቸው ላይ የተንጠለጠለ ወፍራም፣ ሞለል ያለ ክራቫት የሚመስል የሚነፋ ቀይ ኩልኩልት አላቸው። ብዙ ሰዎች ኩልኩልቱ ለወፉ ምንም የሚጨምረው ውበት እንደሌለ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በኬንያ ብሔራዊ ሙዚየሞች የስነ አዕዋፍ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሊኦን ቤኑን እንዲህ ሲሉ አሳስበዋል:- “ኩልኩልቱ ለእኛ አስቀያሚ መስሎ ስለታየን ብቻ ለአባ ኮዳም አላስፈላጊ ነው ማለት አይደለም።” ሆኖም እስካሁን ድረስ የኩልኩልቱን ባዮሎጂያዊ ጠቀሜታ የተገነዘበ ሰው የለም።
የወፉ የአመጋገብ ልማድም በተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነት አላተረፈለትም። በመጀመሪያ ደረጃ ጥንብ በሊታ ነው። ጥንብ ሲያጣ ደግሞ ከፍተኛ የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል ሌሎች ወፎችን አድኖ እንደሚበላ ታውቋል። ብዙ ሰዎች ለወፉ ከባድ ጥላቻ ያደረባቸው መሆኑ ምንም አያስደንቅም።
ሆኖም አባ ኮዳ የማይስብ መልክና ጠባይ ቢኖረውም እንኳ አስደናቂ የሆኑ በርካታ ባሕርያትም አሉት። እስቲ አብረን ይህን በጣም መጥፎ ስም ያተረፈ ወፍ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንሞክር።
የአእዋፍ አውራ
አባ ኮዳ ከእርኩም ቤተሰብ መካከል በጣም ግዙፉ ነው ቢባል ተቀባይነት አለው። እድገቱን የጨረሰ ወንዱ አባ ኮዳ 150 ሴንቲ ሜትር ቁመት ሊኖረውና ከ8 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝን ይችላል። የእንስቶቹ ሰውነት በመጠኑ አነስ ያለ ነው። ግዙፉና ሾጣጣ ቅርጽ ያለው የወፉ ምንቃር ከ30 ሴንቲ ሜትር ርዝመት በላይ ሊያድግ የሚችል ሲሆን ከእንስሳ በድን ላይ ሥጋ ለመቦጨቅ የሚያስችለው ኃይለኛ መሣሪያ ነው።
ይህ የእርኩም ዝርያ ግዙፍ ቢሆንም እንኳ ከፍተኛ የመብረር ችሎታ አለው። የአባ ኮዳ ክንፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከ2.5 ሜትር በላይ ርዝመት ስላለው ጥሩ የመብረር ችሎታ ካላቸው ወፎች መካከል ይመደባል። በሚበርርበት ወቅት ጭንቅላቱ በትከሻዎቹ መሃል ቀበር ብሎና ቅልጥማም እግሮቹ ከሰውነቱ ኋላ ተዘርግተው ሲታይ እጅግ ይማርካል። በሞቃታማ የአየር ሞገድ በመብረር ረገድ የተካነ ስለሆነና በጣም በከፍተኛ ርቀት ላይ መብረር ስለሚችል አንዳንድ ጊዜ ከዓይን ይሰወራል! እንዲያውም አባ ኮዳ በ4, 000 ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚበርር ማወቅ ተችሏል!
ኃላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች
ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደንቀው ግን አባ ኮዳ የወላጅነት ሚናውን በሚገባ የሚወጣ መሆኑ ነው። አድካሚ የሆነውን የወላጅነት ኃላፊነቱን መወጣት የሚጀምረው ጎጆ በመቀለስ ነው። ወንዱ አባ ኮዳ አመቺ ቦታ መርጦ የግንባታውን ሥራ የሚጀምር ሲሆን ትንሽ ቆየት ብሎም ሴቷ ታግዘዋለች። አንዳንድ ጊዜ 40 ሜትር ከፍታ ላይ የሚሠራው ጎጆ ያልተወሳሰበ ነው። ጎጆው አንድ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ከደረቅ እንጨቶች፣ የዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠላ ቅጠሎች የተሠራ ግልጥ መደብ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንቁላል ለመጣል የደረሰች አንዲት ወፍ ቀንበጦችና ሌሎች ቁሳ ቁሶች ጨማምራ አንድን ያረጀ ጎጆ በማደስ መኖሪያዋ ታደርገዋለች። አንዳንድ የአባ ኮዳ ሠፋሪዎች በአንድ የጎጆ መሥሪያ አካባቢ ለ50 ዓመታት ያህል እንደሚቆዩ ማወቅ ተችሏል።
ወንዱ አባ ኮዳ አዲስ ጎጆ በመቀለስ ላይ እያለ ተጓዳኝ መፈለግ ይጀምራል። ሌሎች በርካታ የወፍ ዝርያዎች ካላቸው ልማድ በተለየ ተባዕቱ አባ ኮዳ እንስቷ ቅድሚያውን ወስዳ እስክትቀርበው ይጠብቃል። በወንዱ ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት በርካታ እንስቶች ሙከራ ያደርጋሉ። ተቀባይነት ማጣት ያለ ነገር ነው። ሆኖም ተደጋጋሚ ሙከራ ስኬት ስለሚያስገኝ በመጨረሻ አንዲት እንስት ተቀባይነት ታገኛለች። ቀጥሎ ባለው የተራክቦ ወቅት ሌሎች ወደእነሱ እንዳይጠጉ ለማድረግ ሁለቱም ወፎች አንገታቸው ላይ ያለውን ኩልኩልት እስከመጨረሻ ድረስ ነፍተው ድምፅ ያሰማሉ። ይህም የላም፣ የሲቃና የፉጨት ዓይነት ድምፅ እንደሆነ ተገልጿል። አባ ኮዳ አልፎ አልፎ ግዙፍ ምንቃሩን ከማንገጫገጩ ሌላ የሚያሰማቸው ድምፆች ቢኖሩ እነዚሁ ናቸው። በመካከላቸው የሚፈጠረው ጠንካራ ትስስር አንደኛው ወገን ውጪ ቆይቶ ወደ ጎጆው በተመለሰ ቁጥር “ጎንበስ ቀና” እያሉ በሚያሳዩት የተለመደ ሰላምታ ይጎለብታል። ይህ ሰላምታ ጭንቅላትን ወደኋላ በማድረግና ከዚያም ወደፊት በማጎንበስ ቀጥሎም ለረጅም ጊዜ ምንቃርን በማንገጫገጭ ይገለጻል።
ባልና ሚስቱ ጎጆውን በጋራ ሠርተው ይጨርሳሉ። በተጨማሪም እንቁላል የመታቀፉን ሥራ ሁለቱም ይጋራሉ። እንቁላሎቹን ለአንድ ወር ያህል ከታቀፏቸው በኋላ ነጣ ያሉ ሁለት ወይም ሦስት እንቁላሎች ተፈልፍለው ሮዝ መልክ ያላቸውና ጥቂት ላባ ያበቀሉ ጫጩቶች ይወጣሉ። ሁለቱም ወላጆች ለጫጩቶቹ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። እነዚህ ትንንሽ አባ ኮዳዎች ግሩም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። እንደ ዓሣ የመሳሰሉ በጣም ገንቢ ምግቦችን በደንብ መመገብ ይጀምራሉ። አባ ኮዳዎች በሚያዘወትሯቸው ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ወላጆቹ እንቁራሪት በገፍ ማግኘት ይችላሉ። ይህም ሌላው የተለመደ ምግባቸው ነው። ጫጩቶቹ ወላጆቻቸው ጎጆው ላይ የሚያቀረሹትን ምግብ እየለቃቀሙ ይመገባሉ። የጫጩቶቹ እድገት ዘገምተኛ ከመሆኑም በላይ ከጎጆው ወጥተው መብረርና ራሳቸውን ችለው መኖር እስኪጀምሩ ድረስ አራት ወር ይፈጅባቸዋል።
የጽዳት ሠራተኞች
በአብዛኛው አባ ኮዳ በጥንብ በሊታነቱ የተጠላ ቢሆንም እንኳ በጣም ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ያከናውናል። የአፍሪካ ሜዳማ ቦታዎች አዳኝ እንስሳት በልተው ባስተረፉት ጥንብ ይቆሽሻሉ። ጥንቡ እንዳለ ከተተወ በቀላሉ በሽታ ሊያዛምትና ለሰውም ሆነ ለእንስሳ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አባ ኮዳ ቆሻሻ የማስወገድ ጠቃሚ የሥራ ድርሻ ያበረክታል። በገፍ ከሚበሉትና አዳኝ ወፍ ከሆኑት ከጥንብ አንሣዎች ጋር በመሆን ተገድሎ የተጣለ እንስሳ ፍለጋ አውላላ ሜዳዎችን ይቃኛሉ። የሞተ እንስሳ ሲያገኙ አባ ኮዳዎች ይበልጥ ኃይለኛ የሆኑት ጥንብ አንሳዎች ጠንካራ በሆነው ቆልማማ አፋቸው በድኑን እስኪሰነጥቁ ድረስ ይጠብቃሉ። አባ ኮዳ አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ በፍጥነት ወደ ጥንቡ ቀርቦ ለቀዶ ሕክምና የተዘጋጀ ስለት በሚመስለው ረጅም ምንቃሩ ሥጋ ቦጨቅ አድርጎ ከወሰደ በኋላ ራቅ ብሎ በመቆም ሌላ አጋጣሚ ይጠባበቃል። ጥንብ አንሳዎቹ በልተው ከጠገቡ በኋላ አባ ኮዳዎች የተራረፈ ሥጋ ለመለቃቀም የሚረባረቡበት ተራ ይደርሳቸዋል። አባ ኮዳዎች ከአጥንት በስተቀር መዋጥ የሚችሉትን ማንኛውንም ነገር ከመብላት ወደኋላ አይሉም። እስከ 600 ግራም የሚመዝን ሥጋ ያለ ምንም ችግር ዋጥ ያደርጋሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አባ ኮዳ የጽዳት ሥራውን ሰው ወደሚኖርበት አካባቢም እያስፋፋ ነው። ወፉ ለሰው የነበረው ፍርሃት እየጠፋ ከመሆኑም በላይ አሁን አሁን በከተማና በመንደር ከሚገኙ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች አይጠፋም። ይህ ምን ውጤት አለው? ለአካባቢ ጽዳት አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህም በላይ አባ ኮዳ የተጣለ ሥጋ ለማግኘት ከቄራዎች የሚወጡ ቆሻሻ ፍሳሾችን ያጣራል። ቀጥሎ የቀረበው ምሳሌ ወፉ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል። በምዕራብ ኬንያ በሚገኝ ቄራ አካባቢ አንድ አባ ኮዳ የተጣለ ሥጋ እየፈለገ ሳለ ድንገት የሥጋ መክተፊያ ቢላዋ አግኝቶ ዋጠ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ቢላዋው ምንም ሳይሆን በዚያው አካባቢ የተገኘ ሲሆን ቢላዋውን መልሶ የተፋው አባ ኮዳም አንድም ጉዳት ሳያገኘው የወትሮ እንቅስቃሴውን መቀጠል ችሏል!
የአባ ኮዳ የወደፊት ዕጣ
የቅርብ ዝርያው የሆነው ታላቁ የእስያው እርኩም እየተመናመነ ሲሄድ የአፍሪካው አባ ኮዳ ግን በቁጥር እያደገ መጥቷል። በሚኖርበት አካባቢ ይሄ ነው የሚባል ጠላት የለውም። ከዚህ በፊት ከሁሉ የከፋው የአባ ኮዳ ጠላት ሰው ነበር። ይህ ግዙፍ እርኩም ይገደልና የሴቶችን ፀጉር ለማስጌጥ ሲባል ለስላሳ የጅራት ላባው ተነጭቶ ይወሰዳል። “የፊት ማራገቢያ ወይም ሴቶች እንደ ውድ ነገር የሚቆጥሯቸውን አንዳንድ ዕቃዎች ለማስጌጥ የሚያገለግሉት እነዚህ ለስላሳና የሚያማምሩ ላባዎች የሚገኙት ከዚህ ግዙፍ፣ ከሲታና አስቀያሚ ጥንብ በሊታ ነው ብሎ ማሰብ ያዳግታል” ሲል ስቶርክስ፣ አይቢስስ ኤንድ ስፑንቢልስ ኦቭ ዘ ዎርልድ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። ደስ የሚለው ነገር ባለፉት ዓመታት እነዚህ ወፎች በገፍ የመጨፍጨፋቸው ሁኔታ እየቀረ የመጣ ከመሆኑም በላይ ቁጥራቸው እንደገና እያንሰራራ ነው። ስለ አባ ኮዳ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት ያደረግነው መጠነኛ ጥረት ይህ ወፍ በጥላቻ ሊታይ ወይም ሊክፋፋ የማይገባው መሆኑን እንድናስተውል እንዳደረገን አያጠራጥርም። አካባቢን በማጽዳት ረገድ የሚያከናውነው የተቀላጠፈና ትጋት የተሞላበት ሥራ በጣም ይጠቅመናል። አባ ኮዳ በጣም ከሚያማምሩ ወፎች መካከል ባይመደብም እንኳ በመጠኑም ለፈጣሪው ውዳሴ ማምጣቱ አልቀረም።—መዝሙር 148:7, 10
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሾጣጣ ቅርጽ ያለው የወፉ ግዙፍ ምንቃር ከሰላሳ ሴንቲ ሜትር በላይ ሊያድግ ይችላል
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአባ ኮዳ ክንፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከ2.5 ሜትር በላይ ነው
[ምንጭ]
© Joe McDonald
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአባ ኮዳ ጫጩቶች ግሩም እንክብካቤ ያገኛሉ
[ምንጭ]
© M.P. Kahl/VIREO
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአባ ኮዳ ኩልኩልት ምን ዓይነት ባዮሎጂያዊ ጠቀሜታ እንዳለው እስካሁን አልታወቀም
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ጎጆው የሚቀለሰው ከመሬት 40 ሜትር ከፍታ ላይ ነው