በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዲህ መጨነቄን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

እንዲህ መጨነቄን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ...

እንዲህ መጨነቄን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

“አንድን ወጣት በጣም ከሚያሳስቡት ነገሮች መካከል አንዱ የወደፊቱ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ስለ ራስህ ትጨነቃለህ። ራሴን ችዬ ከቤት ልውጣ? ትምህርቴን ልቀጥል? የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ልጀምር? ላግባ ይሆን? ብዙ ምርጫዎች ስላሉህ በጣም ይጨንቅሃል።”​—⁠የ20 ዓመቱ ሼን

አንተስ በጣም ትጨነቃለህ? ብዙ ወጣቶች የሚጨነቁ ሲሆን የጭ​ንቀታቸው መንስኤም የተለያየ ነው። ለወላጆች መመሪያ ለመስጠት ተብሎ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 በሚደርስ በ41 አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶች ላይ የተደረገው አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው የዛሬዎቹን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በዋነኛነት የሚያሳስበው ጥሩ ሥራ ማግኘት ነው።” ከዚህ በመቀጠል ወጣቶችን በጣም የሚያሳስባቸው ነገር ሆኖ የተገኘው የወላጆቻቸው ጤንነት ሲሆን የሚወዱትን ሰው በሞት የማጣት ፍርሃትም በእጅጉ እንደሚያስጨንቃቸው ለመገንዘብ ተችሏል።

የዩ ኤስ ትምህርት ቢሮ ያደረገው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው “ከፍተኛ ውጤት የማምጣት ፍላጎት” በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን ብዙ ወጣቶች በጣም የሚያሳስብ ነገር ነው። ይኸው ጥናት እንዳመለከተው ብዙ ወጣቶች የሼንን (በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው) ስሜት ይጋራሉ። አሽሊ የተባለች ሌላ ወጣት ደግሞ “የወደፊት ሕይወቴ ያስጨንቀኛል” በማለት ተናግራለች።

ሌሎች ደግሞ ስለ ደህንነታቸው ይጨነቃሉ። በ1996 በተደረገው አንድ ጥናት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩት ወጣቶች መካከል ወደ 50 በመቶ የሚጠጉት በትምህርት ቤታቸው የሚካሄደው ዓመፅ እየጨመረ እንደመጣ ተሰምቷቸዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ከስምንት ሚልዮን በላይ (37 በመቶ) የሚሆኑት ራሳቸው የሚያውቁት በጥይት ተመትቶ የቆሰለ ወይም የሞተ ሰው እንዳለ ተናግረዋል!

ይሁን እንጂ ጭንቀት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ሁሉ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ነገሮች ናቸው ማለት አይደለም። ብዙ ወጣቶችን በዋነኛነት የሚያሳስቧቸው ከማሕበራዊ ኑሮ ጋር የተያያዙ ነገሮች ናቸው። ለወላጆች የተዘጋጀ አንድ መጽሔት እንዳመለከተው “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች የወንድ ወይም የሴት ጓደኛ ስለማግኘት ይጨነቃሉ። በአብዛኛው የሚያስጨንቃቸው ግን ጭራሹኑ ጓደኛ አለማግኘታቸው ነው።” ሜገን የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ወጣት ምሬቷን እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “አንድ ሰው ጓደኞች ሳይኖሩት እንዴት ዘመናዊ መስሎ መታየት ይችላል? ጓደኞች ያስፈልጉኛል።” በተመሳሳይም ናትናኤል የተባለ የ15 ዓመት ክርስቲያን ወጣት ያስተዋለውን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- “ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉት ልጆች ስለ አለባበሳቸው፣ ስለ አካሄዳቸው፣ ስለ አነጋገራቸውና ሌሎች እነርሱን ስለሚያዩበት መንገድ ይጨነቃሉ። በሌሎች ፊት ሞኝ መስለው መታየት አይፈልጉም።”

ችግሮች የሕይወት ክፍል ናቸው

ከጭንቀት ነጻ የሆነ ሕይወት መምራት ብንችል ጥሩ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) ስለዚህ ችግሮችና እነርሱን ተከትለው የሚመጡት ጭንቀቶች የሕይወት ክፍል ናቸው። ይሁን እንጂ ጭንቀትና ሐሳብ አስተሳሰብህን እንዲያዛቡብህ የምትፈቅድ ከሆነ በራስህ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ልታመጣ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል” በማለት ያስጠነቅቃል።​—⁠ምሳሌ 12:25

አላስፈላጊ ጭንቀትን ለማስወገድ የሚረዳው አንዱ ቁልፍ የራስህን ባሕርይ መቆጣጠር መቻል ነው። የአሥራ ስድስት ዓመቷ አና እንዲህ ብላለች:- “ብዙዎቹ የክፍል ጓደኞቼ ብናረግዝስ? በጾታ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ቢይዘንስ? እያሉ ይጨነቃሉ።” ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መስፈርቶች አጥብቀህ ከተከተልክ እንዲህ ያለውን ጭንቀት ማስወገድ ትችላለህ። (ገላትያ 6:​7) ያም ሆኖ ያሉብህ ችግሮች በሙሉ በቀላሉ መፍትሄ ያገኛሉ ማለት አይደለም። ታዲያ እንዲህ መጨነቅህን ማቆም የምትችለው እንዴት ነው?

“የሚያስጨንቁ ነገሮችን በጥበብ መወጣት”

ብዙ ሰዎች ጭንቀት የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያዛባባቸው ይፈቅዳሉ። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ተብሎ በተዘጋጀ አንድ መጽሔት ላይ የወጣ ርዕስ እንደጠቆመው አንድ ሰው ጭንቀትን ገንቢ ወደሆነ እርምጃ በመለወጥ “የሚያስጨንቁ ነገሮችን በጥበብ መወጣት” ይችላል! መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ለማድረግ የሚረዱ ብዙ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። ምሳሌ 21:​5ን ተመልከት። “የትጉህ አሳብ [“እቅድ፣” NW  ] ወደ ጥጋብ ያደርሳል።” ለምሳሌ ያህል በጉባኤህ ውስጥ የሚገኙ ጓደኞችህን መጋበዝ ፈለግህ እንበል። ጥሩ እቅድ በማውጣት አብዛኛውን ጭንቀት መቀነስ ትችላለህ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘መጋበዝ የምፈልገው እነማንን ነው? እንዲደርሱ የምፈልገው በስንት ሰዓት ነው? እንዲቆዩ የምፈልገውስ እስከ ስንት ሰዓት ነው? ቀለል ያሉ ምግቦችንና መጠጦችን ለማዘጋጀት ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልገኛል? ሁሉንም ሰው ሊያሳትፉና ሊያስደስቱ የሚችሉ ምን ዓይነት ጨዋታዎች ላዘጋጅ እችላለሁ?’ በግብዣው ላይ ስለሚደረጉት ነገሮች በጥንቃቄ ባሰብክ መጠን እቅድህም የዚያኑ ያህል ይሳካል።

ይሁን እንጂ ነገሮች በጣም እንዲወሳሰቡ በማድረግ በራስህ ላይ ጭንቀት ልትፈጥር ትችላለህ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንግዳዋን ለማስተናገድ ብላ አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ለገባች አንዲት ሴት የሚከተለውን ምክር ሰጥቶ ነበር:- “የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው።” (ሉቃስ 10:42) ስለዚህ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ለዚህ ዝግጅት ስኬታማነት በእርግጥ የሚያስፈልገው ምንድን ነው?’ ነገሮችን ቀላል ማድረግህ ጭንቀትህን ለማቃለል ይረዳሃል።

ሌላው የጭንቀት መንስኤ ደግሞ በትምህርት ቤት አደጋ ይደርስብኝ ይሆናል የሚል ስጋት ነው። በትምህርት ቤት ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ማድረግ የምትችለው ነገር አይኖር ይሆናል። ሆኖም ራስህን ከአደጋ ለመጠበቅ አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ። ምሳሌ 22:​3 “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል” በማለት ይናገራል። ከአደገኛ ቦታዎች መራቁ ብቻ እንኳ ችግር ውስጥ የመግባት አጋጣሚህን ሊቀንሰው ይችላል። ይህም ገለል ካሉ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ሥርዓት አልበኛ ልጆች መሰብሰብ ከሚያዘወትሩበት፣ ብዙም ክትትልና ቁጥጥር ከማይደረግበት ቦታም መራቅን ይጠይቃል።

መምህሮችህ እንድትሠራው የሚሰጡህ የቤት ሥራም ቢሆን ሌላው የጭንቀት መንስኤ ሊሆን ይችላል። ምናልባት አስፈላጊ የሆኑ ብዙ የቤት ሥራዎች ይኖሩህና ሁሉንም በጊዜው ሠርተህ መጨረስ እንደማትችል ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ደግሞ ጭንቀት ላይ ሊጥልህ ይችላል። በዚህ ረገድ በፊልጵስዩስ 1:​10 NW ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚ ነው። “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ።” አዎን፣ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን ተማር! ይበልጥ አጣዳፊ የሆነው የቱ እንደሆነ ወስንና በመጀመሪያ እርሱን ሥራ። ስትጨርስ ደግሞ ወደሚቀጥለው ተሸጋገር። ቀስ በቀስ ሁኔታውን እየተቆጣጠርከው እንዳለ ሆኖ ይሰማሃል።

ምክር ጠይቅ

አሮን ወጣት በነበረበት ወቅት የትምህርት ቤቱን መልቀቂያ ፈተና ማለፍ አለማለፉ አስጨንቆት ነበር። በጣም ከመጨነቁ የተነሣ የደረት ህመም ተሰማው። እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ሁኔታውን ለወላጆቼ ሳማክራቸው ሐኪም ዘንድ ወሰዱኝ። ሐኪሙም ምንም ዓይነት የልብ ችግር እንደሌለብኝ ወዲያው ከተገነዘበ በኋላ ጭንቀት ምን ያህል በአካል ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገለጸልኝ። በኋላም ወላጆቼ ፈተናውን ለመሥራት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጌን እንድገነዘብ ካደረጉ በኋላ አሁን ዘና ማለት ብቻ እንዳለብኝ ነገሩኝ። መጨነቄን ሳቆም ደረቴ ላይ ይሰማኝ የነበረው ሕመምም ተወኝ። ፈተናውንም በደንብ ሠራሁ።”

በጭንቀት እንደተዋጥክ ሆኖ ከተሰማህ ችግሩን ለራስህ ብቻ አምቀህ በመያዝ አትሰቃይ። ቀደም ሲል በከፊል የተጠቀሰው ምሳሌ 12:25 ሙሉ ሐሳቡ እንዲህ ይላል:- “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” ይህንን የሚያበረታታ ‘መልካም ቃል’ ልታገኝ የምትችለው ‘የልብህን ኀዘን’ አውጥተህ ከተናገርክ ብቻ ነው!

በመጀመሪያ ጉዳዩን ለወላጆችህ ማማከር ትፈልግ ይሆናል። ምናልባት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦች ይሰጡህ ይሆናል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙት በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ሌላ የድጋፍ ምንጭ ናቸው። የአሥራ አምስት ዓመቷ ጃኔል እንደሚከተለው ብላለች:- “አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እስካነጋገርኩበት ጊዜ ድረስ አደገኛ ዕፁን፣ የጾታ ብልግናውንና ዓመፁን ሳስበው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መግባት በጣም አስጨንቆኝ ነበር። ሆኖም ሽማግሌው ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ሐሳቦች ሲሰጠኝ ወዲያው ሁኔታዎችን መቆጣጠር እንደምችል በመገንዘቤ እፎይታ ተሰማኝ።”

ዛሬ ነገ አትበል

አንዳንድ ጊዜ ወዲያው መደረግ ያለበት ነገር ይኖር ይሆናል። ሆኖም ያንን ነገር ማድረግ ስለከበደን ብቻ ዛሬ ነገ እያልን እናቆየዋለን። ለምሳሌ ያህል በአሥራ ዘጠኝ ዓመቷ ሼቮንና በአንድ ክርስቲያን ባልንጀራዋ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ከግለሰቡ ጋር ተነጋግራ ጉዳዩን መፍታት እንዳለባት ብታውቅም ዛሬ ነገ እያለች ጉዳዩን አጓተተችው። “ዛሬ ነገ እያልኩ ጉዳዩን ይበልጥ ባጓተትኩ መጠን ጭንቀቴም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ሄደ” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ከዚያም ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን ችግሮች ሳይዘገዩ መፍታት እንዳለባቸው የሚያሳስቡትን በማቴዎስ 5:​23, 24 ላይ የሚገኙ የኢየሱስ ቃላት አስታወሰች። “በመጨረሻ እንደተባለው ሳደርግ” በማለት ሼቮን ታስታውሳለች፣ “እፎይታ አገኘሁ።”

አንተስ ዛሬ ነገ እያልክ ያቆየኸው ነገር ይኖር ይሆን? ይህ ምናልባት አንድ የማትወደው ሥራ ወይም ከሌላ ሰው ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ሊሆን ይችላል። ሳትዘገይ እርምጃ ውሰድ። እንዲህ ካደረግህ አንድ ጭንቀት አቃለልክ ማለት ነው።

አስቸጋሪ ሁኔታዎች

ሁሉም ሁኔታዎች በቀላሉ መፍትሄ ያገኛሉ ማለት አይደለም። አብዱር የተባለውን ወጣት ሁኔታ ተመልከት። እናቱ ካንሰር ያለባት ሲሆን እርስዋንም ሆነ ታናሽ ወንድሙን በገንዘብ መደገፍ አለበት። አብዱር የእናቱ ሁኔታ እንደሚያስጨንቀው የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲህ ይላል:- “‘ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?’ የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ጥሩ ፍንጭ ሰጥተውኛል። በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ ስለ ሁኔታው በጥንቃቄ ካሰብኩ በኋላ ምን ባደርግ እንደሚሻል እወስናለሁ።”​—ማቴዎስ 6:​27

ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የተረጋጋ መንፈስ መያዝ ቀላል አይደለም። አንዳንዶች በጣም ከመጨነቃቸው የተነሳ መመገባቸውን በማቆም ራሳቸውን ችላ እስከማለት ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጅህ ውጥረትን እንዲቋቋም እርዳው በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ እንዳስጠነቀቀው ሰውነትህ መሠረታዊ የሆኑትን ምግቦች እንዳያገኝ ስትከለክለው “ውጥረትን የመቋቋም ኃይልህ ሊዳከምና ለከባድ የጤና ችግሮች ልትጋለጥ ትችላለህ።” ስለዚህ በቂ እረፍት በመውሰድና የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ራስህን ተንከባከብ።

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ታላቅ እፎይታ ማግኘት ትችላለህ:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።” (መዝሙር 55:22) በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሼን ስለ ወደፊት ሕይወቱ ይጨነቅ ነበር። “በአምላክ ቃልና ዓላማ ላይ ይበልጥ ማተኮር ጀመርኩ” በማለት ያስታውሳል። ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱን አምላክን ለማገልገል ከተጠቀመበት ወደፊት ደስተኛ ሕይወት ሊኖረው እንደሚችል ተገነዘበ። (ራእይ 4:11) ሼን “ስለ ራሴ መጨነቄን አቆምኩ” በማለት ተናግሯል። “አሁን ይበልጥ የሚያሳስበኝ ነገር አለ።”

ስለዚህ በጣም የምትጨነቅ ከሆነ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ውሰድ። ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር ጠይቅ። ከሁሉም በላይ ግን ‘እርሱ ስለ አንተ ያስባልና’ የሚያስጨንቅህን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣለው። (1 ጴጥሮስ 5:7) በእርሱ እርዳታ መጨነቅህን ታቆም ይሆናል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚያስጨንቁህን ነገሮች ለወላጆችህ አማክራቸው

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለችግሮች ፈጣን እልባት ባስገኘህ ቁጥር ጭንቀትህም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል