ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በሥራ ቦታ የሚፈጠር የመንፈስ ጭንቀት
“በሥራ ቦታ የሚከሰት ... የመንፈስ መረበሽ፣ የኃይል መሟጠጥና የመንፈስ ጭንቀት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል” ይላል የለንደኑ ዘ ጋርዲያን ያወጣው ዘገባ። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የሥራ ድርጅት እንዳለው ከሆነ በእንግሊዝ ከ10 ሠራተኞች 3 ያህሉ ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚገጥሟቸው ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ ከ10 ሠራተኞች አንዱ የመንፈስ ጭንቀት እንደሚይዘው ተናግሯል። በጀርመን ቀደም ብለው ጡረታ ከሚወጡት ሠራተኞች መካከል 7 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሥራ የሚያቆሙት በመንፈስ ጭንቀት የተነሳ ነው። በፊንላንድ ከሚገኘው የሠራተኛ ኃይል መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከውጥረት ጋር በተያያዙ ችግሮች ይሠቃያል። በፖላንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የሥራ አጥነት ችግር ሳቢያ የሚፈጠረው ጭንቀት በ1999 50 በመቶ የጨመረ ሲሆን የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል። በሥራ ቦታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የአስተዳደር ስልቶችን ተግባራዊ የማድረጉ ሂደት የቀጠለ በመሆኑ የመንፈስ ጭንቀት ወደፊትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ዘገባው ይተነብያል። በተጨማሪም “በ2020 ከመኪና አደጋዎች፣ ከኤድስና ከኃይል ድርጊቶች በበለጠ ለሥራ ሰዓት መባከን ዋነኛ መንስኤ የሚሆኑት ውጥረትና ከአእምሮ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች ናቸው” ሲል ዘገባው አስጠንቅቋል።
በማጭበርበር ድርጊት የተወነጀለ አርኪኦሎጂስት
በግርምት ያስደምማሉ በተባሉ ግኝቶቹ የተነሳ አቻ ያልተገኘለት መሬት ቆፋሪ ለመባል የበቃ አንድ ስመ ጥር ጃፓናዊ አርኪኦሎጂስት የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽም ተያዘ። አርኪኦሎጂስቱ የመሬት ቁፋሮ የሚያካሂደው ቡድን አርኪኦሎጂያዊ ጥናት ወደሚካሄድበት ቦታ ከመድረሱ በፊት በቦታው የድንጋይ ቅርጻ ቅርጾች ሲቀብር ማይኒቺ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ በአካባቢው በተከለው ቪዲዮ ካሜራ ሊቀረጽ ችሏል። ውንጀላውን ሊያስተባብል ያልቻለው ይኸው አርኪኦሎጂስት የራሱ ስብስብ የሆኑ ቅርጻ ቅርጾችን መቅበሩን አምኖ ለመቀበል ተገድዷል። አሁን፣ ያለፉት 30 ዓመታት የሥራ ውጤቶቹ በሙሉ ዳግም ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው። የመጽሐፍ አሳታሚዎች በእሱ ግኝቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አርኪኦሎጂያዊ የማመሳከሪያ ጽሑፎችና የትምህርት ቤት መማሪያ መጻሕፍት ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደሚወጡ ያምናሉ።
ወረቀት ዛሬም ተመራጭ ነው
ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት ኮምፒውተሮች የተለመዱ የቢሮ ዕቃዎች እየሆኑ ሲመጡና መረጃዎችን ኤሌክትሮኒክስ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስ የወረቀት አስፈላጊነት እየቀረ እንደሚሄድ ተተንብዮ ነበር። ሆኖም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ የወረቀት ፍጆታ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በ1999 ካናዳውያን ፎቶ ኮፒ ለማንሳትና የፋክስ መልእክት ለመቀበል የተጠቀሙበት ወረቀት ብዛት በ1992 ጥቅም ላይ ውሎ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 25 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል። ይህም “በዓመት ውስጥ ልጆችን ጨምሮ እያንዳንዱ ካናዳዊ 66 ፓውንድ (30 ኪሎ ግራም) ወረቀት ይጠቀማል” እንደ ማለት ነው። በቢሮ ሠራተኞች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሠራተኞቹ መጀመሪያ ላይ መረጃዎችን ለማየት ኮምፒውተሮችን የሚጠቀሙ ቢሆንም መረጃውን በወረቀት ታትሞ ማግኘት ይፈልጋሉ። ቤታቸው ውስጥ ኮምፒውተር ያላቸው ሰዎች ፍላጎትም እንዲሁ ነው ይላል ሰን። ልጆች በኮምፒውተር ስክሪን ላይ ያዩትን ወይም የሠሩትን ነገር ሁሉ በወረቀት ማተም ስለሚፈልጉ “ዋነኛ የወረቀት ተጠቃሚዎች” ሆነዋል።
ዶፋማ ደን
በሕንድ አገር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዶፋማ ደኖች የሚገኙት በደቡባዊዋ የኬራላ ግዛት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት ሳምየዲፕ ዱታ በቅርቡ በሰሜን ምሥራቅ የሚገኙትን የአሳምና የአሩናቸል ፕራዴሽ ግዛቶችን የሚያዋስን 500 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ዶፋማ ደን ማግኘታቸውን ዳውን ቱ ኧርዝ የተሰኘው የኒው ዴልሂ መጽሔት ዘግቧል። ይህ ደን “እንደ ዝሆን፣ ነብር፣ የቻይና ፓንጎሊን፣ ድብ፣ አጋዘን፣ ሁሎክ ጊበን የተሰኘች ጦጣ፣ ካሊጅ ፌዛንት በመባል የምትታወቅ ቆቅ መሰል ወፍ፣ ሆርንቢል በመባል የምትታወቀው ወፍና ዳክዬን የመሳሰሉ እምብዛም የማይገኙ ዝርያዎችን ጨምሮ 32 አጥቢ እንስሳትንና 260 የሚሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎችን” በውስጡ አቅፎ የያዘ ነው። ይሁንና የደን ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው በመሆኑ የብዙዎቹ ዶፋማ ደኖች ሕልውና አደጋ ላይ ነው ሲል ዳውን ቱ ኧርዝ ገልጿል። አንዳንድ የሥነ ሕይወት ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነቶቹ የደን ውጤቶች ከሚገባው በላይ ጥቅም ላይ በመዋላቸው ምክንያት እየተመናመኑ ከመጡ፣ ዶፋማ ደኖች ጥበቃ ማግኘታቸው ቀርቶ ለግብርና አገልግሎት ሊውሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
የነብር ግሣት
የነብር ግሣት ሌሎች እንስሳትን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ሰዎችንም በድንጋጤ ክው የሚያደርገው ለምንድን ነው? በዩ ኤስ ኤ ሰሜን ካሮላይና ውስጥ በሚገኘው ፎውና ኮሚዩኒኬሽንስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት የተሰኘ ተቋም የሚሠሩ ሳይንቲስቶች “ነብር የሚያሰማው ጉርምርምታ ጎልቶ የማይወጣ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ‘ታህታይ ድምፅ’ በመሆኑ ሰዎች ሊሰሙት እንደማይችሉ ደርሰውበታል” ሲል የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ሰዎች ሊሰሙ የሚችሉት ከ20 ሄርዝ በላይ የሆነን የድምፅ ድግግሞሽ ብቻ
ሲሆን በአንጻሩ ነብር “18 ሄርዝ እና ከዚያ ያነሰን ታህታይ ድምፅ ልንሰማው ከምንችለው ግሣት ጋር አንድ ላይ ቀላቅሎ ያሰማል። የተቋሙ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኤሊዛቤት ቮን ሙገንታለ እንዳሉት ከሆነ በውጤቱም ሰዎች የነብሩን ግሣት ሊሰሙና ክው የሚያደርግ ጊዜያዊ ድንጋጤ ሊያድርባቸው ይችላል” ሲል ጋዜጣው ይገልጻል። ሌላው ቀርቶ ነብር በማሠልጠን ሙያ ረዘም ያለ ጊዜ ያሳለፉ ሰዎች እንኳ እንዲህ ዓይነት ክስተት አጋጥሟቸዋል።መርከቦች በሽታ ያዛምታሉ
“መርከቦች ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የሚጭኑት ውኃ በዓለም ዙሪያ በሽታ እያዛመተ በመሆኑ የሰዎች፣ የእንስሳትና የዕፅዋት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል” ይላል የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ። መርከቦች በባሕር ላይ ወዲያና ወዲህ እንዳይዋልሉ ሲባል የሚጫነውን ውኃ በባሕር ላይ አለዚያም በቆሙበት ወደብ ያፈስሱታል። በዩናይትድ ስቴትስ ሜሪላንድ ውስጥ የሚገኘው የስሚትሶኒያን የአካባቢ ምርምር ማዕከል ባልደረቦች የሆኑ ተመራማሪዎች በውቅያኖሶች ላይ የሚጓዙ መርከቦች ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የሚጭኑት ውኃ ከፍተኛ መጠን ባላቸው ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች የተሞላ እንደሆነ ደርሰውበታል። በቼስፒክ ባሕረ ሰላጤ 15 መርከቦች በጫኑት ውኃ ውስጥ በሚገኙ ሕያዋን ነገሮች ላይ በተካሄደው ምርመራ ሁሉም የጫኑት ውኃ ኮሌራ አማጭ የሆነው ባክቴሪያ ተገኝቶበታል። በአብዛኛው በእንዲህ ዓይነቱ አንድ ሊትር ውኃ ውስጥ ወደ 830 ሚልዮን የሚጠጉ ባክቴሪያዎችና 7, 400 ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ቫይረሶች ይገኛሉ። ይህም ከሌሎቹ ዘአካላት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከስድስት እስከ ስምንት ጊዜ እጥፍ ይሆናል።
የአሻንጉሊት ብዛት
“አንድ አዲስ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ሕፃናት ስፍር ቁጥር የሌላቸው አሻንጉሊቶችና መጫወቻዎች ስለሚሰጧቸው በአግባቡ መጫወት እየተሳናቸው ነው” ሲል የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ታይምስ ዘግቧል። ጥናቱ እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው አንዱ ነገር በብሪታንያ “ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብረው ጊዜ ከማሳለፍ ይልቅ አሻንጉሊቶች በመስጠት እንዲሁም በኮምፒውተር እንዲጫወቱና ቴሌቪዥን በመመልከት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ በማድረግ የልጅነት ሕይወታቸው ለዘለቄታው እንዲስተጓጎል እያደረጉ መሆኑ” አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ ነው። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ካቲ ሲልቫ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ባላቸው 3, 000 ሕፃናት ላይ ጥናት ካካሄዱ በኋላ “የአሻንጉሊቶች መብዛት ሐሳባቸው እንዲከፋፈል ያደርጋል። ሕፃናት ሐሳባቸው የሚከፋፈል ከሆነ ደግሞ በደንብ መማርም ሆነ መጫወት አይችሉም” ሲሉ ደምድመዋል።
ከተባይ ማጥፊያ ይልቅ አረም መጠቀም ይመረጣል
የምሥራቅ አፍሪካ ገበሬዎች የበቆሎ ሰብል ምርታቸውን ለማሳደግ ከተባይ ማጥፊያ ይልቅ አረም መጠቀም መርጠዋል በማለት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የበቆሎ አምራቾች ሁለት አደገኛ ተባዮች ያስቸግሯቸዋል። አንደኛው ስትሪጋ የተባለ ጥገኛ ተክል ሲሆን በየዓመቱ 10 ቢልዮን ዶላር የሚገመት የበቆሎ ሰብል ያወድማል። ዛይዲን ኻን የተባሉ ኬንያዊ ተመራማሪ ዴስሞዲየም የተባለ አረም በበቆሎ ሰብል መካከል በሚተከልበት ጊዜ ስትሪጋ እንደማይበቅል ደርሰውበታል። ሌላው ተባይ ስቴም ቦረር የተባለው ሦስት አፅቄ እጭ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በዓመት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የበቆሎ ሰብል እምሽክ ያደርጋል። ይሁንና ኻን ስቴም ቦረር የተባለው ተባይ ሙጃ የሚባለውን አረም መብላት እንደሚመርጥ ደርሰውበታል። ገበሬዎቹ በማሳዎቻቸው ላይ ይህን አረም በመትከል ሦስት አፅቄዎቹ ወደ አረሙ እንዲሳቡና ከበቆሎው እንዲርቁ ያደርጓቸዋል። ከአረሙ የሚወጣው የሚያጣብቅ ንጥረ ነገር እጮቹን አጣብቆ በመያዝ ይገድላቸዋል። “ከተባይ ማጥፊያ እጅግ የተሻለ ከመሆኑም በላይ ብዙ ወጪ አይጠይቅም” ይላሉ ኻን። “በተጨማሪም በአካባቢው የእርሻው ምርት ከ60 እስከ 70 በመቶ እንዲያድግ አስተዋጽኦ አድርጓል።”
ነፍሰጡር ታዳጊዎች በዩናይትድ ስቴትስ
“ካደጉት አገሮች መካከል በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሆነው በሚያረግዙ ልጆች ቁጥር ዩናይትድ ስቴትስ የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዛለች” ሲል ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት ዘግቧል። በየዓመቱ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጃገረዶች እንደሚያረግዙና ከእነዚህም መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት የመጀመሪያ ልጃቸውን ከፀነሱ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሌላ ሁለተኛ ልጅ እንደሚደግሙ ተገምቷል። በ1997 የተመዘገበው አኃዝ እንደሚያሳየው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሆነው በሚወልዱ ልጆች ቁጥር ረገድ ከመቶው እጅ ከፍተኛውን (20 በመቶ) በመያዝ ቀዳሚ የሆነችው የሚሲሲፒ ግዛት ስትሆን ዝቅተኛው ቁጥር (7.2 በመቶ) ደግሞ የማሳቹሴትስ ግዛት ነው። በጥቅሉ ሲታይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሆነው የሚያረግዙ ልጆች በብዛት የሚገኙት በተለምዶ ባይብል ቤልት ተብሎ በሚጠራው ደቡባዊ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል ነው።
እየጠፉ ያሉ ቋንቋዎች
አንድ የብራዚላውያንና የጀርመኖች የጋራ ፕሮጄክት ብራዚል ውስጥ ያሉ ለመጥፋት የተቃረቡ ቋንቋዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ የማድረግ እቅድ እንዳለው ፎልያ ዲ ሳኦ ፓውሎ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ ዘግቧል። ተመራማሪዎቹ ጽሑፍና ድምፅ የሚያሰባስቡበት የዲጂታል የመረጃ ባንክ በማዘጋጀት የትሩማይ፣ የአወቲ እና የክዊኩረ ቋንቋዎችን ጠብቀው ለማቆየት አስበዋል። የቋንቋ ምሁር የሆኑት አርዮን ሩድሪጊስ ብራዚል መጀመሪያ ላይ ከነበሯት 1, 200 ቋንቋዎች መካከል ዛሬ ያሉት 180 ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል ቢያንስ 50 የሚሆኑት ቋንቋዎች የሚነገሩት ከ100 በሚያንሱ ሰዎች ነው። በሕይወት ያሉት የማኩ ቋንቋ ተናጋሪ ደግሞ በብራዚል ሰሜናዊ ክፍል የሚኖሩ አንዲት የ70 ዓመት መበለት ብቻ ናቸው። ሩድሪጊስ እንደሚሉት የሕዝቡን ባሕላዊ እሴት ጠብቆ ለማቆየት የአገሬውን ቋንቋዎች መጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው።