በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ ቢተዉኝም አምላክ ግን ወድዶኛል

ወላጆቼ ቢተዉኝም አምላክ ግን ወድዶኛል

ወላጆቼ ቢተዉኝም አምላክ ግን ወድዶኛል

በርናዴት ፊን እንደተናገረችው

ገና አራት ዓመት ሳይሞላኝ ወላጆቼ እኔንና ሦስት ታላላቅ እህቶቼን በአንድ የሴቶች ገዳም ውስጥ ትተውን ሄዱ። የ12 ዓመቷ በርዲ፣ የ8 ዓመቷ ፊሊስና የ7 ዓመቷ አናሜይ ወላጆቼ የት ሄዱ እያልኩ ያለማቋረጥ የጮኽኩባቸውን ሳምንታት ያስታውሳሉ። እዚያ የተተውነው ለምንድን ነው?

በአንድ ሰፊ የካቶሊክ ቤተሰብ ውስጥ ግንቦት 8, 1936 ተወለድኩ። ሁላችንም ከወላጆቻችን ጋር ደንኮርሚክ፣ ዌክስፎርድ፣ አየርላንድ በሚገኝ አንድ ትንሽ ቤት ውስጥ እንኖር ነበር። ለቤተሰባችን ስምንተኛ ልጅ ስሆን ከሌሎች ሰባት ታላላቅ እህቶቼና ወንድሞቼ ጋር አንድ ትልቅ አልጋ ላይ እተኛ ነበር። በኋላ ላይ የተወለዱት አንድ ወንድና ሴት የሚተኙት በልብስ ማስቀመጫ መሳቢያ ውስጥ ነበር።

አባቴ ጠንካራ ገበሬ የነበረ ቢሆንም የሚያገኘው ገቢ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ለቤተሰቡ በቂ ምግብ ማቅረብ አልቻለም። እናቴ፣ ታላላቅ ወንድሞቼና እህቶቼ ትምህርት ቤት ይዘውት የሚሄዱት ትንሽ ምሳ የምታዘጋጅላቸው አልፎ አልፎ ነበር። አገሪቷ ተዘፍቃበት የነበረው ድህነትም ሆነ በጊዜው የነበረው ምህረት የለሹ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አገዛዝ በቤተሰባችን ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

ቤተሰባችን አዘውትሮ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ቢሆንም እናቴ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች ብዙም ፍላጎት አልነበራትም። ሆኖም እናቴ ከእሳት ማንደጃው ፊት ለፊት ተቀምጣ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ታነብብ እንደነበረ እህቶቼ ያስታውሳሉ። ያነበበቻቸውን ነገሮችም ለእኛ ለማካፈል ትሞክር ነበር።

“እናቴ የት ሄደች?”

ወደ ገዳሙ የተወሰድኩበትን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም። ወላጆቼ ኮሪደሩ ላይ ቆመው ከአንዲት መነኩሲት ጋር በቁም ነገር ያወራሉ። ስለ ምን እየተነጋገሩ እንዳለ የማውቀው ነገር ስላልነበረ እዚያ ከሚገኙት ከሌሎች ትንንሽ ልጆች ጋር መጫወት ጀመርኩ። ወዲያው ዞር ብዬ ስመለከት ሁለቱም የሉም። በጣም ደነገጥኩ። “እናቴ የት ሄደች?” በማለት ጩኸቴን ለቀቅኩት። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ለሳምንታት እንዲህ ስል ቆየሁ።

ይሁን እንጂ ቢያንስ ሦስቱ ታላላቅ እህቶቼ ከእኔ ጋር መሆናቸው አጽናናኝ። ሆኖም የምንኖረው በተለያየ ቦታ ስለነበር እንደልባችን መገናኘት አልቻልንም። እኛ ትንንሾቹ ከእነርሱ ሁለት ሰዓት ቀድመን እንተኛ ስለነበር የእነርሱ የመኝታ ሰዓት እስኪደርስ ሳልተኛ እቆያለሁ። ከዚያ ልክ ሰዓቱ ሲደርስ ቀስ ብዬ ከአልጋዬ ተነሥቼ ላይኛው ደረጃ ላይ ከወጣሁ በኋላ በዚያ ሲያልፉ አያቸዋለሁ። እነርሱም ያዩኝና እጃቸውን ያውለበልቡልኛል። በእያንዳንዱ ቀን ይህንን ሰዓት በጉጉት እጠባበቅ ነበር።

ገዳሙ ከወላጆች ጋር መገናኘትን የማያበረታታ በመሆኑ ወላጆቻችንን እምብዛም አላየናቸውም። ከእነርሱ መለየቴ በጥልቅ ተሰምቶኝ ነበር። እርግጥ አንድ ጊዜ ሊያዩን መጥተው እንደነበረ አስታውሳለሁ። በዚህ ጊዜ ግን እኔም ሆንኩ እነርሱ አጠገብ ለአጠገብ አልተደራረስንም። ይሁን እንጂ ታላላቅ እህቶቼ ወላጆቻችን በሌሎች ጥቂት ጊዜያትም ሊያዩን መጥተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ገዳሙን ልክ እንደ ቤቴ አባላቱን ደግሞ እንደ ቤተሰቦቼ አድርጌ መቁጠር ጀመርኩ። እዚያ በነበርኩባቸው 12 ዓመታት ወደ ውጭ የወጣሁት ሁለት ጊዜ ብቻ ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት አቅራቢያችን ወዳሉት ገጠራማ አካባቢዎች ለሽርሽር ተጉዘን ነበር። በጉዞው ወቅት ዛፎችንና እንስሳትን ማየት በመቻላችን በጣም ተደስተን ነበር። ከዚህ በተረፈ ግን መኪናም ሆነ አውቶቡስ ወይም ሱቅ አይተን አናውቅም። እንዲያውም ከቄሱ በስተቀር ወንዶችን እንኳ ያየንባቸው ጊዜያት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

የገዳም ሕይወት

የገዳም ሕይወት አንዳንድ ጥሩ በአብዛኛው ግን መጥፎ የሆኑ ገጽታዎች አሉት። አንዲት ደስ የምትል ወጣት መነኩሲት ጥሩ ነው ብላ ባሰበችው መንገድ ስለ አምላክ አስተማረችን። አምላክ አፍቃሪ አባት እንደሆነ ስትነግረን በጣም ተደሰትኩ። ከዚያን ዕለት ጀምሮ አምላክ ከወላጅ አባቴ ይልቅ አፍቃሪና ደግ በመሆኑ እርሱን ልክ እንደ አባቴ አድርጌ ለመመልከት ወሰንኩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በልጅ አንደበቴ በማቀርባቸው ጸሎቶች አማካኝነት ከአምላክ ጋር ብዙ እነጋገር ነበር። ወጣቷ መነኩሲት ገዳሙን ስትለቅቅ በጣም አዘንኩ።

ጥሩ መሠረታዊ ትምህርት በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ይሁን እንጂ “የቀን ልጆች” የሚል ስያሜ ስለነበራቸው ሴቶች ልጆች አስታውሳለሁ። ለትምህርት ወደ ገዳሙ ሲመጡ ከሌሎቻችን በተለየ አድሎአዊ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ሲሆን የሃብታም ልጆች በመሆናቸው እነርሱ ሲመጡ የመማሪያ ክፍሎቻችንን ለቅቀን መውጣት ይጠበቅብን ነበር። መነኩሴዎቹ እኛ ወላጅ የሌለን እንደመሆናችን መጠን ቦታችንን ማወቅና ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ እንዳለብን ያለማቋረጥ ያሳስቡን ነበር።

በገዳሙ ውስጥ ብዙ ደንቦች ነበሩ። አንዳንዶቹ ደንቦች ምክንያታዊ ስለነበሩ አብዛኞቻችን ደንቦቹ ያስፈለጉበትን ምክንያት እንገነዘባለን። ባሕርይን፣ ሥርዓትንና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት አዝለዋል። እነዚህን ደንቦች ፈጽሞ የማልረሳቸው ሲሆን በሕይወቴ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ሆኖም አንዳንዶቹ ግራ የሚያጋቡና የሚያናድዱ ብሎም የማይጠቅሙና ተገቢ ያልሆኑ ነበሩ። ቅጣት ከሚያስከትሉት ደንቦች ውስጥ አንደኛው ማታ አልጋ ላይ መሽናት ሲሆን ሌላው ደግሞ ማታ ለሽንት መውጣት ነው።

አንድ ቀን ደረጃውን በመውጣት ላይ እያለሁ አጠገቤ ከነበረችው ልጅ ጋር መነጋገር ጀመርኩ። ስለተነጋገርን ብቻ አንዲት መነኩሲት ጠርታ ቀጣችኝ። ቅጣቱ ምን ነበር? በጣም የሚቀዘቅዘውን የአይሪሽ ክረምት በበጋ ልብሴ እንዳሳልፍ ተወሰነብኝ! በጣም ታማሚ የነበርኩ ሲሆን ያለማቋረጥ በአስምና በቶንሲል ሕመም እሰቃይ ነበር። በአንድ ወቅት ግን በገዳሙ ውስጥ እንደነበሩት እንደሌሎቹ ብዙ ሴቶች ልጆች እኔም በጠና ታመምኩና የሳንባ ነቀርሳ ያዘኝ። ከሌሎቹ ተለይተን ወደ ሌላ መኝታ ቤት እንድንዛወር የተደረገ ቢሆንም ምንም ዓይነት የሕክምና እርዳታ አይደረግልንም ነበር። ከዚህ የተነሣ አንዲት በጣም የምቀርባት ጓደኛዬን ጨምሮ አንዳንዶች ሞተዋል።

አንዳንዶቻችን በጥቃቅን ጉዳዮች ሕጉን በመጣሳችን ከፍተኛ ድብደባ ደርሶብናል። በአንድ መደበኛ የሆነ የተማሪዎች ስብሰባ ላይ አንዲት መነኩሲት አንዲትን ልጅ ከሁለት ሰዓታት በላይ ስትደበድባት ተመልክተናል። በዚህ ጊዜ ሁላችንም እናለቅስ ነበር። እርግጥ ሁሉም መነኮሳት ክፉዎች ነበሩ ማለት አይደለም። ሆኖም አንድ ሰው ራሳቸውን መከላከል ለማይችሉ ሕፃናት እንዴት እንዲህ ጨካኝ ይሆናል የሚለው እስካሁን መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው። ይህ መቼም ሊገባኝ አይችልም።

ከጊዜ በኋላ በርዲ እና ፊሊስ እኔንና አናሜይን ትተው ከገዳሙ ወጡ። በዚህ ጊዜ እኔ ከእሷ እሷም ከእኔ ሌላ ማንም ሰው አልነበረንም። አናሜይ እኔን ለማጽናናት ስትል ወላጆቻችን አንድ ቀን እንደሚመጡና መነኮሳቱ ፈጽሞ ወደማያገኙን ቦታ እንደሚወስዱን አድርጋ ትነግረኝ ነበር። አናሜይ ገዳሙን ለቅቃ ስትሄድ ልቤ በሃዘን ተሰበረ። ከዚህ በኋላ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት በገዳሙ ቆይቻለሁ።

ከገዳሙ ውጪ መኖርን መማር

በ16 ዓመት ዕድሜ ገዳሙን መልቀቅ በጣም አስፈሪ ነበር። ከገዳሙ ውጪ ስላለው ሕይወት ምንም የማውቀው ስላልነበረ በጣም ግራ ተጋባሁ። አንድ ቦታ ለመሄድ ብዬ አውቶቡስ ስሳፈር ሒሳብ እንድከፍል ተጠየቅሁ። ሆኖም ሒሳብ ስለመክፈል ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ደግሞም ቤሳ ቤስቲን አልነበረኝም። ስለዚህ ወዲያው ከአውቶቡሱ እንድወርድ ስለተደረግሁ በእግሬ መጓዝ ነበረብኝ። በሌላ ጊዜ ደግሞ አውቶቡስ መሳፈር ፈለግሁ። ሆኖም አንድም አውቶቡስ አልመጣም። አውቶቡስ ለማግኘት አውቶቡስ ማቆሚያ ድረስ መሄድ እንደነበረብኝ አላወቅሁም ነበር።

ይሁን እንጂ ትንሽ ድፍረት፣ ጥንካሬና በራስ የመ​ተማመን መንፈስ እንዳለኝ በማስመሰል ቀስ በቀስ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ መረዳት ቻልኩ። አንድ ቀለል ያለ ሥራ በማግኘቴ ለበርካታ ወራት ሥሠራ ከቆየሁ በኋላ ወደ ቤት ተመልሼ እናቴን ለማየት ወሰንኩ። እዚያም ከታናናሽ እህቶቼና ወንድሞቼ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘን። በዚህ ጊዜ በአጠቃላይ 14 ወንድሞችና እህቶች ነበሩኝ። እነርሱ ጋር ለእኔ የሚሆን ቦታ ስላልነበረ ወላጆቼ ዌልስ ካለችው ከእህቴ ከአናሜይ ጋር እንድኖር ዝግጅት አደረጉ። አባቴ ዌልስ ድረስ አብሮኝ ቢሄድም ወዲያው ተመለሰ።

ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ላይ ወድቄ የነበረ ቢሆንም እንደምንም ብዬ አንሰራራሁ። በ1953 ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ በመዛወር ሊጅየን ኦቭ ሜሪ በተባለ አንድ ተራ የሮማ ካቶሊክ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ሥራው አንዳንድ መንፈሳዊ ገጽታዎች ይኖሩታል ብዬ ብጠብቅም ሁኔታው ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ሳገኘው በጣም ተበሳጨሁ። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ማውራት ቢያስደስተኝም በዚህ ቦታ የምሠራው ሥራ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረውም። እንዲያውም መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜም አልነበረም።

ለንደን ሳለሁ የወንድሞቼ ጓደኛ ከነበረው ከፓትሪክ ጋር ተገናኘን። ከዚያም ተፋቀርንና በ1961 ተጋባን። አንጀላና ስቲቨን የተባሉት ሁለቱ ልጆቻችን የተወለዱት እዚያው ለንደን ውስጥ ነበር። በኋላም በ1967 አንድሪው የተባለው ሦስተኛ ልጃችን ወደተወለደበት ወደ አውስትራሊያ ተሰደድን። ከዚያም ኒው ሳውዝ ዌልስ ውስጥ በሚገኘው ቦምባላ በተባለ የገጠር ከተማ መኖር ጀመርን።

በመጨረሻ መንፈሳዊ ምግብ አገኘን

አውስትራሊያ ከደረስን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቢል ሎይድ የተባለ አንድ ወጣት ቤታችንን አንኳኩቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አነጋገረን። ጥያቄዎቼ በሙሉ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲመለሱልኝ በጣም ደስ አለኝ። ቢል እየተናገረ ያለው ነገር እውነት እንደሆነ ብገነዘብም ቆይቶ ተጨማሪ ማብራሪያዎች እንዲሰጠን ስለፈለግሁ ብዙ ተከራከርኩት። በኋላም አንድ መጽሐፍ ቅዱስና ጥቂት መጽሔቶች አመጣልኝ።

መጽሔቶቹን ማንበብ ቢያስደስተኝም ጽሑፎቹን የሚያትሙት ሰዎች በሥላሴ እንደማያምኑ ስገነዘብ በጣም ደነገጥኩ። ስለዚህ ምናልባት ፓትሪክ መጽሔቶቹን አግኝቶ ካነበበ እምነቱ ይበረዝበታል ብዬ ስላሰብኩ መጽሔቶቹን ደበቅኋቸው። ቢል ተመልሶ ሲመጣ መጽሔቶቹን ለመመለስ ወሰንኩ። ይሁን እንጂ ቢል በሚቀጥለው ጊዜ ሲመጣ ሦስት አካላት ያሉት አንድ እግዚአብሔር አለ የሚለው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ እንደሚጋጭ አብራራልኝ። ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ፣ በአባቱ በይሖዋ አምላክ እንደተፈጠረና መጀመሪያ እንዳለው እንዲሁም አብ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ተረዳሁ።​—⁠ማቴዎስ 16:16፤ ዮሐንስ 14:28፤ ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14

ካቶሊክ ሆኜ የተማርኳቸው ሌሎች ነገሮችም ስህተት መሆናቸውን ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የማትሞት ነፍስ አላቸው ብሎም ሆነ እሳታማ ሲኦል አለ ብሎ አያስተምርም። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ይህንን ማወቄ ትልቅ እፎይታ አስገኘልኝ! እንዲያውም አንድ ቀን ምንም እንኳ ባላውቀውም ስወድደው የኖርኩትን አባት በማግኘቴ በጣም ከመደሰቴ የተነሣ ወጥ ቤት ውስጥ ፈነጠዝኩ። ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረኝ ጥማት መርካት ጀመረ። ፓትሪክም ላገኘነው አዲስ እምነት የእኔው ዓይነት ምላሽ መስጠቱ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አደረገው።

ከዚያም ቢል፣ ተሞራ ተብሎ በሚጠራው ከተማ ውስጥ በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ጋበዘን። ቦታው ራቅ ብሎ የሚገኝ ቢሆንም ግብዣውን በደስታ በመቀበል አርብ አመሻሹ ላይ ተሞራ ደረስን። ቅዳሜ ጠዋት የተወሰኑ ቡድኖች ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ እኔና ፓትሪክ እንዲህ የማድረግ ፍላጎት በውስጣችን ተቀስቅሶ ስለነበር በተገኘው አጋጣሚ ተደሰትን። ሆኖም ቢል ሲጋራ ስለምናጨስ በስብከቱ ሥራ መካፈል እንደማንችል ነገረን። ይሁን እንጂ እርሱ ሲሄድ ከአንድ ሌላ ቡድን ጋር ተቀላቀልን። ወንድሞችም ምሥክር ስለመሰልናቸው አብረው ወሰዱን።

ብዙም ሳይቆይ ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስፈልጉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ምን እንደሆኑ ተገነዘብን። (ማቴዎስ 24:14) በመጨረሻም ማጨሳችንን አቁመን ጥቅምት 1968 ራሳችንን ለይሖዋ አምላክ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት አሳየን።

እምነታችን ተፈተነ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችንና ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና እያደገ ሲሄድ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ተጠናከረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ፓትሪክ በአውስትራሊያ ዋና ከተማ ካንቤራ ውስጥ በሚገኘው አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ልጆችን ማሳደግ የሚያስከትለውን የተለመደ ተፈታታኝ ሁኔታ በመቋቋም ልጆቻችንን በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ ለማሳደግ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል።​—⁠ኤፌሶን 6:4

የሚያሳዝነው ስቲቨን የተባለው ልጃችን ገና በ18 ዓመት ዕድሜው የመኪና አደጋ ደርሶበት ሞተ። ከፍተኛ ኀዘን ቢሰማንም ስቲቨን የይሖዋ አምላኪ መሆኑን ማወቃችን ከፍተኛ ማጽናኛ ሆኖልናል። ይሖዋ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉትን ከሞት ሲያስነሳ እርሱንም ለማየት እንናፍቃለን። (ዮሐንስ 5:28, 29) በተከታዩ ዓመት ማለትም በ1983 ልክ እንደ ልጃችን አንጀላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ይኸው እስከ ዛሬም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እገኛለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታችንን ለሌሎች ማካፈሉ አዎንታዊ አመለካከት እንድይዝና ሐዘኔን እንድቋቋምም ረድቶኛል። በቅርቡ ደግሞ ዌልስ የምትኖረው እህቴ አናሜይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት መጀመሯን መስማቴ ደስታዬን ጨምሮልኛል።

በ1984 ፓትሪክ በወቅቱ ብዙም የማይታወቅ በሽታ ያዘው። በኋላ ላይ ግን ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም የተባለው ኃይለኛ ድካም የሚያስከትል በሽታ እንደሆነ ታወቀ። ከጊዜ በኋላ ሥራውን ለማቆም የተገደደ ሲሆን ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ማገልገሉንም አቆመ። የሚያስደስተው አሁን ሕመሙ ትንሽ ሻል ስላለው የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ያገለግላል።

የልጅነት ሕይወቴ ሥርዓታማነትንና ራስን መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ጨምሮ ቀላል ሕይወት መምራትና በትንሽ ነገር እርካታ ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች አስተምሮኛል። ይሁን እንጂ 11ዱ ልጆች ቤት ሲቆዩ እኛ አራታችን ገዳም የተላክንበት ምክንያት አሁን ድረስ አይገባኝም። ከዓመታት በፊት የሞቱት ወላጆቼ ምናልባትም ሙሉ በሙሉ ልረዳው በማልችለው ሁኔታ ውስጥ እያሉም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዳደረጉ በማሰብ ራሴን አጽናናለሁ። እነዚያ ጊዜያት ከባድ ውሳኔ ማድረግን የሚጠይቁ አስቸጋሪ ወቅቶች ነበሩ። ያም ሆኖ ወላጆቼ ከሁሉ የተሻለ ነው ብለው ባሰቡት መንገድ ስለተንከባከቡኝና የሕይወትን ስጦታ ስላስተላለፉልኝ አመስጋኝ ነኝ። ከሁሉ በላይ ግን ለአባታዊ እንክብካቤው ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዲስ ተጋቢዎች በነበርንበት ጊዜ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችን ትንንሾች በነበሩበት ጊዜ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ከፓትሪክ ጋር