በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን መመገብ የሚችለው ማን ይሆን?

ዓለምን መመገብ የሚችለው ማን ይሆን?

ዓለምን መመገብ የሚችለው ማን ይሆን?

የሰው ልጅ ሕይወታዊ ሀብትን ማጥፋት ትቶ መንከባከብ ይጀምር ይሆን? እንደ ሥነ ሕይወት ተመራማሪው ጆን ተክሰል አባባል ከሆነ ይህ “ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ” ይጠይቃል። ይሁንና ቀጥለው እንደገለጹት “ሰዎች ስለ ዕፅዋት ሕይወታዊ ሀብት ጠቀሜታ ባላቸው ግንዛቤ፣ ነባሮቹን ልማዶች ለመለወጥ ባላቸው ፍላጎት እና አዳዲስ ዘዴዎችን ለመሞከር ባላቸው ፈቃደኛነት ረገድ መሠረታዊ ማስተካከያ እስካላደረጉ ድረስ” እንዲህ ያለው ለውጥ የሚታሰብ አይሆንም።

ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣል ብለው ማመን ይከብዳቸዋል። ብዙዎች ደግሞ በተክሰል መደምደሚያ አይስማሙም። በአካባቢ ሁኔታ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሕይወታዊ ሀብት የሚጫወተው ሚና ገና በቂ ግንዛቤ እንዳላገኘና አንዳንድ የሥራ ጓደኞቻቸው ደግሞ አጋንነው እንደሚመለከቱት ይሰማቸዋል። ሳይንቲስቶቹ በጉዳዩ ላይ ቢከራከሩም በመስኩ የተሰማሩ ኤክስፐርቶች የሚያሰሙትን የማስጠንቀቂያ ጥሪ ልብ ማለቱ ጠቃሚ ይመስላል። የሚያሳስባቸው ሕይወታዊ ሀብት መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ካለው ጥፋት በስተጀርባ ያለው ስግብግብነትና አርቆ አሳቢነት የጎደለው አመለካከት ነው። የተለያዩ ጸሐፊዎች የሰጧቸውን የሚከተሉትን አስተያየቶች ተመልከት።

“ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በመላ ፕላኔቷ የሚኖሩ በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎች በራሳቸው የዘር ክምችት ላይ የሚያዝዙት ራሳቸው ነበሩ። . . . ዛሬ ግን አብዛኛው የዘር ክምችት ዘሩን መጀመሪያ ባገኙት፣ በጀነቲካዊ ምሕንድስና ማስተካከያ ባደረጉትና የባለቤትነት መብቱን በተቀበሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘንድ የሚቀመጥ የምሁራን ንብረት ሆኗል። . . . ይህ ጥበበ ሕይወት የአጭር ጊዜውን የገበያ ሁኔታ ብቻ በመመልከት ወደፊት መድኃኒቶችን የመቋቋም ኃይል ያላቸውን በሽታዎች በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ሊኖረው የሚችለውን የጀነቲክ ቅርስ ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።”​—⁠የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ ጄረሚ ሪፍኪን

“በመገናኛ ብዙኃን መድረክ ተደጋግሞ የሚነገረው የገበያው መስክ፣ ነፃ የንግድ ልውውጥና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ከምንም ነገር በላይ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው። በመገናኛ ብዙኃን የሚነገረው ወሬ ሁሉ በሃብትና በትላልቅ ድርጅቶች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ከሆነ ይህ ኢኮኖሚያዊ እምነት ጥያቄ የማይነሣበት ሃይማኖታዊ ቀኖና ሆኖ ቁጭ ሊል ይችላል።”​—⁠የጀነቲክ ባለሙያው ዴቪድ ሱዙኪ

ጸሐፊው ኬኒ ኦሰቤል ሲድስ ኦቭ ቼንጅ​—⁠ዘ ሊቪንግ ትሬዠር በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ስለሚታየው ግብዝነት ሲገልጹ “መንግሥታቱና ኮርፖሬሽኖች የሰው ልጅ ‘የጋራ ቅርስ’ በሆነው የጂን ሀብት ላይ እየመጣ ባለው ጥፋት ኃዘናቸውን ይገልጻሉ” ብለዋል። ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴንና ፈረቃ አልባ መረታን በማስፋፋት የሕይወታዊ ሀብትን ህልውና ስጋት ላይ የሚጥሉት እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢ ሁኔታን የሚያጠኑት ሰዎች ከፍተኛ ስጋት ተቀባይነት ኖረውም አልኖረው ስለዚህች ፕላኔት የወደፊት ዕጣ አንተም ስጋት ይኖርህ ይሆናል። የሰው ልጅ እንዲህ በስግብግብነት መንፈስ የሚነዳ ከሆነ ፕላኔታችን ምን ያህል ትቆይ ይሆን? ብዙ ሰዎች መልስ ለማግኘት በመጓጓት ሳይንስ ይታደገናል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሕይወታችንን ሊታደግልን ይችላልን?

ዘ ሮያል ሶሳይቲ ኦቭ ኤድንበርግ የተባለው ድርጅት፣ ሳይንሳዊ መሻሻሎች በጣም ፈጣንና ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ሳይንቲስቶች እነዚህን መሻሻሎች ሥራ ላይ ማዋሉ ያለውን አንድምታ ሙሉ በሙሉ ሳይረዱ ጥቅም ላይ ማዋላቸው ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ስጋት እንዳሳደረበት ገልጿል። ዴቪስ ሱዙኪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሳይንስ ስለ ተፈጥሯዊው ዓለም የሚሰጠው እውቀት በጣም አነስተኛ ነው። በምድር ላይ ያለው ሕይወት እርስ በርስ ያለውን ዝምድናና አንዱ በሌላው ላይ ያለውን ጥገኝነት መረዳት ይቅርና ስነ ሕይወታዊ አሠራሩን እንኳን በተመለከተ ያለን ግንዛቤ ኢምንት ነው።”

ሳይንስ መጽሔት እንዳስረዳው “በጀነቲካዊ ምሕንድስና የተገኙት ዘአካላት ጥቅምም ሆነ ጉዳት በእርግጠኝነት አይታወቅም። . . . በጀነቲክ ምሕንድስና የተገኙትን ዘአካላት ጨምሮ መጤ ዝርያዎች በሥነ ምሕዳሩ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ በተመለከተ የመተንበይ ችሎታችን ትክክለኝነት ይጎድለዋል።”

ብዙዎቹ “መሻሻሎች” ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ ናቸው። በጎ ጎን አላቸው ሆኖም የሰው ልጅ ጥበብ የጎደለው መሆኑን የሚያረጋግጡና ብዙውን ጊዜም ስግብግብ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። (ኤርምያስ 10:​23) ለምሳሌ ያህል አረንጓዴው አብዮት ብዙ ምርት ያስገኘና የብዙዎችን ጉሮሮ የደፈነ ቢሆንም ሕይወታዊ ሀብቶች እንዲጠፉም አስተዋጽኦ አድርጓል። አረንጓዴው አብዮት ፀረ ተባይ ኬሚካሎችንና ሌሎች ብዙ ወጪ የሚጠይቁ የግብርና ዘዴዎችን የመጠቀም ልማድ እንዲስፋፋ በማድረግ “ተራውን ሕዝብ ጎድቶ በማኅበራት ተደራጅተው ዕጽዋት የሚያራቡትንና በሦስተኛው ዓለም የሚኖሩ ጥቂቶችን ጠቅሟል” ሲሉ ዶክተር ሜ-ዋን ሆ ገልጸዋል። በጥበበ ሕይወት ላይ የተመሠረተ ግብርና ይበልጥ እያደገና እየተስፋፋ የሚሄድ የንግድ ተቋም በሆነ መጠን ይህ ሁኔታ እንዳለ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ የምግብ ዋስትና ይበልጡኑ በሳይንስ ላይ የተመካ ወደሚሆንበት ዘመን ያሸጋግረናል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ስጋቶች ተስፋችንን ሊያደበዝዙት አይገባም። እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን ትልቅ እውነታ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ይህችን ፕላኔትና አንጡራ ሃብቷን ከሚቆጣጠሩት ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ብዙ ነገር መጠበቅ እንደሌለብን እንድናስተውል ይረዳናል። እስከ ጊዜው ድረስ ስኬት ማጣትና የአስተዳደር ድክመት ከሰው ልጅ ሕይወት ተነጥለው የማይታዩ ሆነው ይቀጥላሉ። በመሆኑም መዝሙር 146:​3 “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” በማለት ይመክረናል። ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ ሙሉ ትምክህታችንን ልንጥል እንችላለን። (ምሳሌ 3:​5, 6) እርሱ እኛን ለመርዳት ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው።​—⁠ኢሳይያስ 40:​25, 26

በቅርቡ ምድር ውበትና ልምላሜ ትላበሳለች

አንድን የወዳደቀ ቤት ከማደስህ በፊት መጀመሪያ ቆሻሻውን ማጽዳት ያስፈልግህ ይሆናል። ይሖዋ አምላክም በተመሳሳይ ፕላኔታችንን፣ ተፈጥሯዊ ሃብቷንና ነዋሪዎቿን ሳይቀር የግለሰብንና የማኅበራትን ሀብት ለማደለብ እንደፈለጉ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ጥሪት አድርገው የሚያስቡትን ሰዎች ጨምሮ ክፉዎችን በሙሉ በቅርቡ ከምድር ላይ ያስወግዳል። (መዝሙር 37:​10, 11፤ ራእይ 11:​18) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚወዱትንና ፈቃዱን ለማድረግ የሚጥሩትን ሰዎች ያድናቸዋል።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​15-17

ከዚያ በኋላ ታዛዥ ሰዎችን ጨምሮ ምድርና በላይዋ የሚኖሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕያዋን ነገሮች በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ይተዳደራሉ። (ዳንኤል 7:​13, 14፤ ማቴዎስ 6:​10) በዚያ ጥበብ የሞላበት አገዛዝ አማካኝነት ምድር የምትሰጠው ምርት ምንኛ የተትረፈረፈ ይሆናል! መዝሙር 72:​16 “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራሮች በእህል ይሸፈኑ” ይላል። አዎን፣ ከዚያ በኋላ የምግብ ጉዳይ የሚያስጨንቅና የሚያወዛግብ አይሆንም። ይልቁንም አስተማማኝና የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል።

በመሆኑም ይህ የነገሮች ሥርዓት ይበልጥ በተስፋ መቁረጥና በግራ መጋባት ጨለማ እየተዋጠ በሄደ መጠን በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች ወደፊት በዚች ምድር ላይ ክብራማ የሆነ ጊዜ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት ሊጠባበቁ ይችላሉ። ይህ የይሖዋ ምሥክሮች የተሻለና ይበልጥ ፍትሐዊ ዓለም ለሚናፍቁ ሰዎች ሁሉ በደስታ በሚያካፍሉት “የመንግሥቱ ወንጌል” ውስጥ የሚገኝ ተስፋ ነው። (ማቴዎስ 24:​14) ለዚህ አስተማማኝ ተስፋና አምላክ ለሕዝቦቹ ለሚያደርግላቸው አባታዊ እንክብካቤ ምስጋና ይግባውና ዛሬም እንኳ ‘በእርጋታ ልንቀመጥና ከመከራ ሥጋት ልናርፍ’ እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 1:​33

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ አስተማማኝና የተትረፈረፈ የምግብ አቅርቦት ይኖራል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

FAO Photo/K. Dunn

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Tourism Authority of Thailand