ዓይነት—ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነው
ዓይነት—ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነው
በ1840ዎቹ የአየርላንድ ሕዝብ ብዛት ከስምንት ሚልዮን ሲያልፍ አገሪቱ ከቀሩት የአውሮፓ አገሮች ሁሉ ይበልጥ በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ሆና ነበር። ድንች ዋነኛ ምግቧ ሲሆን በብዛት የሚበቅለው ለምፐር የሚባለው አንድ የድንች ዓይነት ብቻ ነበር።
በ1845 ገበሬዎቹ እንደተለመደው ይህንኑ የድንች ዓይነት ዘርተው ሲጠባበቁ ድንቹ በጠቅላላ ለማለት ይቻላል በእከክ ተበላ። ፖል ሬበርን ዘ ላስት ሃርቨስት—ዘ ጀነቲክ ጋምብል ዛት ትሬትንስ ቱ ዲስትሮይ አሜሪካን አግሪካልቸር በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “አብዛኛው የአየርላንድ ክፍል ይህን አስቸጋሪ ዓመት እንደምንም አሳልፎታል። የከፋ ነገር የመጣው በሚቀጥለው ዓመት ነበር። ገበሬዎቹ ያንኑ ድንች ደግመው ከመዝራት ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ሌላ ዓይነት የድንች ዝርያም አልነበራቸውም። እከኩ አሁንም ድንቹን በላው። እንዲያውም በዚህ ጊዜ የደረሰው ውድመት እጅግ የከፋ ነበር። የደረሰውን መከራ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል።” ታሪክ ጸሐፊዎች እስከ 1 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ ማለቃቸውን ገምተዋል። ሌሎች 1.5 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ ተሰድደው አብዛኞቹ ዩናይትድ ስቴትስ ገብተዋል። እዚያው የቀሩትም በከፋ የድህነት አለንጋ ተገርፈዋል።
በደቡብ አሜሪካ በአንዲስ ተራራዎች ይኖሩ የነበሩ ገበሬዎች ብዙ የድንች ዓይነቶችን ተክለው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በእከክ የተበሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ። በመሆኑም እከኩ በወረርሽኝ ደረጃ አልተከሰተም። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የተለያዩ ዝርያዎችና በአንዱም
ዝርያ ሥር የተለያዩ ዓይነቶች መኖራቸው ራሱ ጥበቃ ነው። አንድ ዓይነት ዝርያ ብቻ ማብቀል ይህንን የመከላከያ ስልት የሚቃረን ከመሆኑም ሌላ ዕጽዋቱን የአካባቢውን ምርት በሙሉ ሊያወድም ለሚችል በሽታና ተባይ ሊያጋልጠው ይችላል። ፀረ ተባይ፣ ፀረ አረምና ፀረ ፈንገስ ኬሚካሎች ብዙውን ጊዜ ለአካባቢ ደህንነት አደገኛ ቢሆኑም ብዙ ገበሬዎች አዘውትረው እነዚህኑ ኬሚካሎች የሚጠቀሙበት ምክንያት ይኸው ነው።ታዲያ ገበሬዎች በአገራቸው ያሉትን ብዙ ዓይነት ዝርያዎች በአንድ ዓይነት ሰብል ብቻ የሚተኳቸው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ከሚገጥማቸው ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የተነሣ ነው። ተመሳሳይ ዓይነት ሰብል ብቻ ማብቀል የመሰብሰቡን ሥራ ቀላል ያደርገዋል፣ ለምርቱ ማማር አስተዋጽኦ ያደርጋል እንዲሁም የምርት መባከን እንዳይኖርና ምርታማነት እንዲያድግ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ዓይነቱ ዘዴ በሰፊው መጠቀም የተጀመረው በ1960ዎቹ አረንጓዴው አብዮት ወቅት ነው።
አረንጓዴው አብዮት
በመንግሥትና በማኅበራት በተደረገ ሰፊ ዘመቻ ለድርቅ በተጋለጡ አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች ልዩ ልዩ ዓይነት ያላቸውን ሰብሎቻቸውን ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ አንድ ዓይነት እህሎች በተለይም ደግሞ በሩዝና በስንዴ መተካታቸው ጥሩ እንደሆነ እንዲያምኑ ተደርጓል። እነዚህ “ተዓምር” ይሠራሉ የተባሉ እህሎች ለዓለም ረሃብ መፍትሔ እንደሚያመጡ ታምኖባቸው ነበር። ይሁንና ዋጋቸው በቀላሉ የሚቀመስ አልነበረም። ለዘር የሚሆነው እህል ራሱ ከመደበኛው ዋጋ እስከ ሦስት እጥፍ ድረስ የሚበልጥ ነበር። ምርታማነቱ በእጅጉ የተመካው ማዳበሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀማቸው ላይ ነው። ይህ ሁሉ እንግዲህ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁትን እንደ ትራክተር ያሉ መሣሪያዎች ግምት ውስጥ ሳናስገባ ነው። ያም ሆኖ ከመንግሥት በሚገኝ የገንዘብ ድጎማ አረንጓዴው አብዮት ተፋፋመ። ሬበርን እንደሚሉት ይህ አብዮት “ሚልዮኖችን ከረሀብ ቢታደግም ዛሬ የዓለምን አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት ሕልውና እየተፈታተነ ነው።”
በሌላ አባባል አረንጓዴው አብዮት ጊዜያዊ መፍትሔ ቢያመጣም ዘላቂ መሥዋዕትነት አስከፍሏል ለማለት ይቻላል። ማዳበሪያዎችን በብዛት መጠቀም አረም እንዲስፋፋ በር የሚከፍትና ፀረ ተባይ መድኃኒቶችም ጠቃሚ የሆኑ ነፍሳትንና ተባዮችን ጨምረው የሚያጠፉ ቢሆንም አንድ ወጥ ሰብል የመዝራቱ ልማድ ብዙም ሳይቆይ በየአህጉራቱ ተስፋፍቷል። ሩዝ በሚበቅልባቸው ውኃማ ቦታዎች ላይ የሚረጨው መርዛማ ኬሚካል እንደ ዓሣ፣ ሽሪምፕ፣ ሸርጣን፣ እንቁራሪት ያሉትን እንስሳት እንዲሁም ለመብልነት የሚያገለግሉትንና ሌሎችንም ወፍ ዘራሽ እጽዋት አጥፍቷል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ብዙዎቹ ለተጨማሪ ምግብነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ናቸው። ከገበሬዎችም መካከል አንዳንዶቹ በኬሚካሉ የመመረዝ ችግር ገጥሟቸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ክፍል አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ሜ-ዋን ሆ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “‘አረንጓዴው አብዮት’ ያመጣቸው በፈረቃ አልባ ዘዴ የሚመረቱ (monoculture) ሰብሎች በምድር ዙሪያ ሕይወታዊ ሃብትንና የምግብ ዋስትናን በእጅጉ መጉዳታቸው የማይታበል ሐቅ ሆኗል።” በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ገለጻ መሠረት ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በሰብል ምርት ይሠራባቸው ከነበሩት ጀነቲካዊ ዓይነቶች መካከል ዛሬ 75 በመቶ የሚሆኑት የሉም። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ኢንዱስትሪያዊ የግብርና ልማድ ነው።
ወርልድ ዎች የተባለው ተቋም ያሳተመው ጽሑፍ “ጀነቲካዊ ተመሳሳይነት እንዲኖር በማድረግ እየተከተልነው ያለነው ጎዳና ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል። ይህንን አደጋ መቀነስ የሚቻለው እንዴት ነው? የግብርና ሳይንቲስቶችንና የታለመውን ውጤት የሚያመጡ ኬሚካሎች ማግኘት እንዲሁም ገበሬዎችን በገንዘብ መደገፍ ያስፈልጋል። ይሁንና ለዚህም ቢሆን ምንም ዋስትና የለም። ጀነቲካዊ ተመሳሳይነት በዩናይትድ ስቴትስ በበቆሎ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ዋግ እንዲከሰት በኢንዶኔዥያ ደግሞ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተዘራ ሩዝ እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ የግብርና አብዮት ተጀምሯል።
ይህም ሕይወትን ከመሠረቱ ማለትም በጂን ደረጃ የመለወጥ ሂደት ነው።ጀነቲካዊ አብዮት
በጀነቲካዊ መስክ የሚደረገው ጥናት ጥበበ ሕይወት (Biotechnology) በመባል የሚታወቅ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ አዲስ የኢንዱስትሪ መስክ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል። ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ባዮሎጂን (ስነ ሕይወት) እና እንደ ጀነቲካዊ ምሕንድስና ያለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጣምሮ የያዘ አዲስ ዘዴ ነው። ይህን አዲስ ጥበበ ሕይወት ከሚያራምዱት ኩባንያዎች መካከል አንዳንዶቹ በግብርናው መስክ ተሠማርተው የሚገኙ ሲሆን ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ በሽታን፣ ድርቅንና ውርጭን የሚቋቋሙና አደገኛ ኬሚካሎች የመጠቀሙን አስፈላጊነት የሚቀንሱ ዘሮች ለማግኘት እየጣሩ ነው። እዚህ ግብ ላይ መድረስ ከተቻለ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይሁን አንጂ አንዳንዶች በጀነቲካዊ ምሕንድስና ከሚገኙ ሰብሎች ጋር በተያያዘ አንዳንድ አሳሳቢ ሁኔታዎች እንዳሉ ይገልጻሉ።
“ተፈጥሮአዊው የጀነቲክ ልዩነት ገደብ አለው” ሲል ጀነቲክ ኢንጂነሪንግ፣ ፉድ ኤንድ አወር ኢንቫይሮሜንት የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። “አንድ ጽጌረዳ ከሌላ ዓይነት ጽጌረዳ ጋር ሊዳቀል ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ጽጌረዳ ከድንች ጋር ሊዳቀል አይችልም። . . . ጀነቲካዊ ምሕንድስና ግን ብዙውን ጊዜ ተፈላጊ የሆነን ባሕርይ ለማወራረስ ሲባል ከአንዱ ዝርያ የተገኘውን ጂን ወስዶ ሌላ ዝርያ ውስጥ የመጨመር ተግባር ያከናውናል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ቅዝቃዜን የመቋቋም ባሕርይ ለማዳበር የሚረዳ ኬሚካል ለማመንጨት የሚያግዘውን ጂን በአርክቲክ ከሚገኝ ዓሣ (እንደ ፍላውንደር ካሉት አሳዎች) በመውሰድ ውርጭ ለመቋቋም የሚችል ዝርያ ለማግኘት ድንች ወይም እንጆሪ ውስጥ ይጨመራል። በዛሬው ጊዜ በዚህ ጀነቲካዊ ምሕንድስና አማካኝነት ከባክቴሪያ፣ ከቫይረስ፣ ከሦስት አጽቄዎች፣ ከእንስሳት አልፎ ተርፎም ከሰዎች ሳይቀር የተወሰዱ ጂኖችን ለዕጽዋት መስጠት ተችሏል።” * ይህ ጥበበ ሕይወት የሰው ልጅ በተለያዩ ዝርያዎች መካከል ያለውን የጂን ግድግዳ እንዲያፈርስ አድርጓል ሊባል ይችላል።
እንደ አረንጓዴው አብዮት ሁሉ አንዳንዶች ጀነቲካዊው አብዮት ብለው የሚጠሩት እንቅስቃሴም ጀነቲካዊ መመሳሰል ላስከተለው ችግር የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት የጀነቲካዊ ምሕንድስናው ባለሙያዎች ፍጹም አንድ ዓይነት የሆኑ ነገሮችን ማስገኘት የሚያስችሉትን እንደ ሕዋስ ማቸገን (cloning) እና ርባተ ህብረህዋስ (tissue culture) ያሉትን ዘዴዎች ስለሚጠቀሙ ችግሩ ይበልጥ የከፋ ነው። በመሆኑም የሕይወታዊ ሀብት መመናመንን በተመለከተ ያለው ስጋት አልተቃለለም። ይሁን እንጂ ጀነቲካዊ ለውጥ የተደረገባቸው ዕጽዋት በእኛና በአካባቢው ላይ ምን ውጤት ይኖራቸዋል የሚል ሌላ ጥያቄ ያስነሣሉ። “ትልቅ ተስፋ ብቻ አዝለን ግራ ቀኛችንን ሳናይና ምን እንደሚገጥመን ሳናገናዝብ አዲስ ወደሆነ የግብርና ጥበበ ሕይወት ዘመን በጭፍን እየተጓዝን ነው” ሲሉ የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ጄረሚ ሪፍኪን ተናግረዋል። *
በሌላ በኩል ደግሞ በጂን ደረጃ ሕይወትን ለመቆጣጠር መቻል የአዳዲስ ዝርያዎችን የባለቤትነት መብት ለማግኘትና ሌሎች ዓይነት ዘአካላትን ለማስገኘት ለሚሯሯጡ ኩባንያዎች ወርቅ እንደሚዛቅበት የማዕድን ስፍራ ሆኖላቸዋል። በዚህ መሃል ግን ዕጽዋት መጥፋታቸውን ይቀጥላሉ። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በዚህ ረገድ የሚደርሰውን ጥፋት ለመከላከል ሲሉ አንዳንድ መንግሥታትና የግል ተቋማት የዘር ማከማቻ ባንኮችን አቋቁመዋል። ታዲያ እነዚህ ባንኮች ለዘርና ለምርት የሚሆኑ ብዙ ዓይነት ዝርያዎችን ለመጪው ትውልድ ጠብቀው ማቆየት ይችሉ ይሆን?
የዘር ማከማቻ ባንኮች —ዘር እንዳይጠፋ ዋስትና ይሆናሉን?
በእንግሊዝ ኪው የሚገኘው ዘ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ “እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ታላላቅ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ፕሮጄክቶች አንዱ” እንደሆነ በመግለጽ ያወደሰውን ሚሊኒየም የዘር ማከማቻ ባንክ ፕሮጄክት ጀምሯል። የዚህ ፕሮጄክት ዋነኛ ዓላማዎች (1) እስከ 2010 ባለው ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት ዘር የሚሰጡ ዕጽዋት መካከል 10 በመቶ የሚያህሉትን ማለትም ከ24, 000 በላይ የሚሆኑ ዝርያዎችን ማሰባሰብና ጠብቆ ማቆየት እንዲሁም (2) ከዚያ ጊዜ ብዙ ቀደም ብሎ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙትን አገር በቀል ዘር የሚሰጡ ዕጽዋት ዘሮች በሙሉ ማሰባሰብና ጠብቆ ማቆየት ነው። ሌሎች አገሮችም እንዲሁ የዘር ማከማቻ ወይም በሌላ አጠራራቸው የጂን ባንኮችን ከፍተዋል።
የስነ ሕይወት ተመራማሪው ጆን ተክሰል እንደገለጹት በዘር ባንኮች ውስጥ ከተጠራቀሙት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ
ዘሮች መካከል ቢያንስ ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚያገለግሉና ሌሎች ጠቃሚ ዕፅዋት ናቸው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ድንች፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ጥጥ፣ እንዲሁም ቦሎቄና የመሳሰሉት ዓይነት እጅግ ጠቃሚ አዝርዕትና ተክሎች ይገኙበታል። ይሁን እንጂ የእህል ዘሮች በውስጣቸው ያለው ኃይል ተጠብቆ እስከቆየ ድረስ ብቻ የሚያገለግሉ ሕያው ዘአካላት ናቸው። ታዲያ የዘር ማከማቻ ባንኮች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው?በባንኮቹ ያለው ችግር
የዘር ባንኮቹን ለማካሄድ በዓመት 300 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ ተክሰል ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህም ገንዘብ እንኳ በቂ ላይሆን እንደሚችል ሲገልጹ “በጂን ባንክ ውስጥ ከተቀመጡት ዘሮች መካከል ለረጅም ጊዜ መቆየት በሚችሉበት፣ የተሟላ የውስጥ ድርጅት ባላቸው ተቋማት ውስጥ የሚገኙት 13 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ናቸው” ብለዋል። በጥሩ ሁኔታ ያልተቀመጡ የእህል ዘሮች ብዙ ስለማይቆዩ ሌላ ትውልድ ዘር ማግኘት እንዲቻል መዘራት ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ ግን የዘር ባንኮች መሆናቸው ይቀርና የዘር መቀበሪያ ይሆናሉ። እርግጥ እንዲህ ያለው ሥራ ብዙ የሰው ኃይልና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ቀድሞውንም የገንዘብ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን ተቋማት ሁኔታ ይበልጥ ያወሳስበዋል።
ሲድስ ኦቭ ቼንጅ—ዘ ሊቪንግ ትሬዠር የተባለው መጽሐፍ በዩ ኤስ ኤ ኮሎራዶ የሚገኘው ብሔራዊ የዘር ማከማቻ ላብራቶር “የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥን፣ የማቀዝቀዣ መሣሪያዎች መበላሸትንና ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ስላጋጠሙት ቦታ ቦታቸውን ሳይዙ እንደተተራመሱ ተቆልለው የሚገኙ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ዘሮች” እንዳሉት ገልጿል። የዘር ማከማቻ ባንኮችም በፖለቲካው ዓመፅ፣ በኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እና በተፈጥሮ አደጋዎች መነካታቸው አይቀርም።
ዘሮቹን ለረጅም ጊዜ አስቀምጦ ማቆየትም ራሱ ሌሎች ችግሮች አሉት። ዕፅዋት በተፈጥሯዊ አካባቢያቸው ሲቆዩ ከአካባቢያቸው ጋር የመላመድ ባሕርይ አላቸው። ይህ ባሕርያቸው የተገደበ ቢሆንም በጣም ወሳኝ ነው። በሽታዎችንና ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ እንደ ዘር ባንክ ባለው የተጠበቀ አካባቢ ከጥቂት ትውልዶች በኋላ ያንን ችሎታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በሚገባ ተጠብቀው የተቀመጡ ዘሮች በድጋሚ መተከል ሳያስፈልጋቸው ለብዙ መቶ ዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት የአቅም ውስንነቶችና አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም የዘር ማከማቻ ባንኮች መቋቋማቸው ራሱ የሰው ልጅ የምግብ ሰብሎች ወደፊት የሚኖራቸውን ሁኔታ በተመለከተ ያለውን ስጋት የሚያንጸባርቅ ነው።
የሚጠፉትን ዘሮች ለመቀነስ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የአካባቢውን መካነ ሕይወት (habitat) መጠበቅና የአዝርዕት ዓይነት እንዲበራከት ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን ተክሰል እንዳሉት “በሰው ልጅ ፍላጎትና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ አዲስ ጥረት ማድረግ” ይኖርብናል። ይሁንና ሰዎች ኢንዱስትሪያዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደ ሃይማኖት ሥራዬ ብለው በሚከታተሉበት በዛሬው ጊዜ ‘የተፈጥሮን ሚዛን ለማስጠበቅ’ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናልን? ቀደም ሲል እንዳየነው በዛሬው ጊዜ የግብርናው መስክ ሳይቀር ታላላቅ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱበት በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ የጦፈ የገበያ ውድድር ውስጥ ገብቷል። ለችግሩ ሌላ መፍትሔ ሊኖር ይገባል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.13 ጀነቲካዊ ማስተካከያ የተደረገባቸው ምግቦች በእንስሳትና በሰው ልጅ ጤና ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ውጤት የሚናገሩት ንድፈ ሐሳቦች አሁንም እንዳወዛገቡ ነው። ምንም ዓይነት ተዛምዶ የሌላቸውን ሕያዋን ነገሮች ጂኖች የማዋሃዱ ተግባር የሥነ ምግባር ጥያቄ አስነስቷል።—ሚያዝያ 22, 2000 ንቁ ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 25-27 ተመልከት።
^ አን.14 ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው ከሆነ “አንድን ዓይነት አረም ማጥፊያ መቋቋም እንዲችሉ ተብለው ጀነቲካዊ ማስተካከያ የተደረገባቸው” የአውሮፓ ስኳር ድንቾች “እንዳጋጣሚ ሌላ ፀረ አረም ኬሚካልንም የመቋቋም ብቃት ኖሯቸው ተገኝተዋል።” ሌላ ዓይነት ፀረ አረም ኬሚካል እንዲቋቋም ተብሎ ከተዘጋጀ የስኳር ድንች ዓይነት ጋር ድንገት በመዳቀሉ እነዚህ ጂኖች ወደዚህኛው ተክል ገብተዋል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ፀረ አረም ኬሚካሎችን የመቋቋም አቅም ያላቸው የተለያዩ የእህል ዝርያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ፀረ አረም ኬሚካሎችን የሚቋቋሙ አደገኛ አረሞች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ገበሬው ‘አደጋ ተጋርጦበታልን?’
“ከ1950 ወዲህ በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች በሙሉ በግብርናው መስክ የተሰማሩት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ አሽቆልቁሏል። በአንዳንድ አካባቢዎች ከ80 በመቶ በላይ ቀንሷል” ሲል ወርልድ ዎች የተባለው መጽሔት ዘግቧል። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ያሏት ገበሬዎች ቁጥር ከእስረኞቿ ቁጥር ያነሰ ነው። ይህንን የገበሬዎች ፍልሰት ያስከተለው ምንድን ነው?
የገቢ መቀነስ፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ እዳዎች መጨመር እንዲሁም የድህነትና በዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዘ የአስተራረስ ዘዴ መስፋፋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በ1910 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የነበሩ ገበሬዎች እያንዳንዱ ሸማች ለምግብ ከሚያወጣው አንድ ዶላር ውስጥ 40 ሳንቲሙን ያገኙ የነበረ ሲሆን በ1997 የገበሬዎቹ ድርሻ ወደ 7 ሳንቲም ዝቅ ብሏል። ወርልድ ዎች እንዳለው ከሆነ አንድ የስንዴ ገበሬ፣ ሸማቹ “አንድ ዳቦ ለመግዛት ከሚያወጣው ዶላር ላይ የሚያገኘው 6 ሳንቲም ብቻ ነው።” ይህም ማለት ሸማቹ ገበሬው ላመረተው ስንዴ የሚያወጣው ገንዘብ ለመጠቅለያው ከሚከፍለው ገንዘብ ጋር እኩል ነው እንደማለት ነው። በታዳጊ አገሮች ያሉ ገበሬዎች ሁኔታ ደግሞ ከዚህም ይበልጥ የከፋ ነው። በአውስትራሊያ ወይም በአውሮፓ ያለ አንድ ገበሬ በዚህ ዓመት ችግር ቢገጥመው ይህን ዓመት ለማሳለፍ ከባንክ ሊበደር ይችላል። በምዕራብ አፍሪካ የሚገኝ ገበሬ ግን ሁለተኛ ማንሰራራት አይችል ይሆናል። ምናልባት ሕይወቱን እንኳን ማትረፍ ይሳነው ይሆናል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“‘አረንጓዴው አብዮት’ ያመጣቸው በፈረቃ አልባ ዘዴ የሚመረቱ ሰብሎች በምድር ዙሪያ ሕይወታዊ ሀብትንና የምግብ ዋስትናን በእጅጉ [ጎድተዋል]።”—ዶክተር ሜ-ዋን ሆ
[ምንጮች]
መደቡ:- U.S. Department of Agriculture
Centro Internacional de Mejoramiento de Maíz y Trigo (CIMMYT)
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በእንግሊዝ የሚገኘው ሚሊኒየም የዘር ማከማቻ ባንክ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የዕፅዋት ዘሮችን ጠብቆ ለማቆየት እየሞከረ ነው
[ምንጭ]
© Trustees of Royal Botanic Gardens, Kew