በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዶሮ ተወዳጅና በብዛት የሚገኝ

ዶሮ ተወዳጅና በብዛት የሚገኝ

ዶሮ ተወዳጅና በብዛት የሚገኝ

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዶሮ በምድር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወፍ ዘር ሳይሆን አይቀርም። በአጠቃላይ ከ13 ቢልዮን የሚበልጡ ዶሮዎች እንዳሉ ይገመታል! እንዲሁም ሥጋው በጣም ተወዳጅ በመሆኑ በየዓመቱ ከ33 ቢልዮን ኪሎ ግራም በላይ ለምግብነት ይውላል። ከዚህም በተጨማሪ ዶሮዎች በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ 600 ቢልዮን ገደማ እንቁላሎችን ይጥላሉ።

ዶሮ በምዕራባውያን አገሮች በብዛት የሚገኝ ሲሆን ዋጋውም ርካሽ ነው። ከአሥርተ ዓመታት በፊት በአሜሪካ እጩ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ በሚፎካከሩበት ጊዜ በምርጫው ካሸነፉ ዶሮ በገፍ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ለመራጮቻቸው ቃል ይገቡ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ዶሮ እንደ ቅንጦት ምግብ መታየቱ ወይም የጥቂቶች ምግብ ብቻ መሆኑ ቀርቷል። በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ የወፍ ዘር እንዲህ በብዛት እንዲገኝ እንዲሁም በጣም ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ድሃ አገሮችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱስ የተትረፈረፈው ምርት ተቋዳሽ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?

የዶሮ ታሪክ

ዶሮ የእስያ ቀይ የዱር ጅግራ ዝርያ ነው። ሰው ዶሮን በቀላሉ ማልመድ እንደሚችል ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። እንዲያውም ከ2, 000 ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ዶሮ ጫጩቶቿን እንዴት ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስባቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:​37፤ 26:​34) ይህን ምሳሌ መጠቀሙ ሰዎች ባጠቃላይ ስለ ዶሮ በደንብ ያውቁ እንደነበር ያሳያል። ሆኖም ዶሮና እንቁላል ለገበያ ለማቅረብ ሲባል በሰፊው የዶሮ እርባታ የተጀመረው ከ19ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነው።

የዶሮ ሥጋ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ምግብ ነው። የከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ለራሳቸውም ሆነ ለገበያ ለማቅረብ ዶሮ ያረባሉ። እንዲያውም የዶሮን ያህል በተለያዩ የአየር ጠባዮች መርባት የሚችል የግብርና እንስሳ የለም ማለት ይቻላል። ብዙ አገሮች ለራሳቸው አገር የአየር ጠባይ የሚስማሙና ጥሩ ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎችን አራብተዋል። ከእነዚህ መካከል የአውስትራሊያው አውስትራሎፕ፣ መጀመሪያ በሜድትራኒያን የተገኘውና አሁን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በብዛት ያለው ሌግሆርን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚረቡት ኒው ሃምፕሻየር፣ ፕላይማውዝ ሮክ፣ ሮሜ አይላንድ ሬድ እንዲሁም ውያንዶቴ፤ የእንግሊዞቹ ኮርኒሽ፣ ኦርፒንግቶን እና ሱሴክስ የሚባሉት ጥቂቶቹ ናቸው።

በእርባታ ረገድ የተገኘው የተሻሻለ ሳይንሳዊ ዘዴ ዶሮ እርባታ ስኬታማ የግብርና ኢንዱስትሪ እንዲሆን አስችሎታል። የዩናይትድ ስቴትስ ገበሬዎች የዶሮ በሽታን በሳይንሳዊ መንገድ ከመቆጣጠራቸው በተጨማሪ አመጋገባቸውንና አሰፋፈራቸውን በተመለከተ ጥንቃቄ በተሞላበት ዘዴ ክትትል ያደርጋሉ። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያለውን በገፍ የማርባት ዘዴ እንደ ጭካኔ ይቆጥሩታል። ይሁን እንጂ ይህ አመለካከት ገበሬዎቹ በየጊዜው ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የዶሮ ማራቢያ ዘዴዎችን ከመፈለግ አላገዳቸውም። ዘመናዊው ዘዴ አንድ ሰው ብቻውን ከ25, 000 እስከ 50, 000 የሚያክሉ ዶሮዎችን እንዲያረባ ያስችላል። አንድን ዶሮ ለገበያ ለማድረስ የሚወስደው ጊዜ ሦስት ወር ብቻ ነው። *

የሥጋ ዶሮ

የትኛውም ሆቴል፣ ሬስቶራንት ወይም ምግብ ቤት ብትገቡ ዶሮ የማይጠቀስበት የምግብ ዝርዝር አታገኙም ለማለት ይቻላል። እንዲያውም ቶሎ የሚደርሱ ምግቦችን የሚያዘጋጁ ሬስቶራንቶች የዶሮን ሥጋ በማዘጋጀት ረገድ የተዋጣላቸው ሆነዋል። ልዩ ዝግጅት ሲኖራቸው ዶሮ መሥራት የሚመርጡ ማኅበረሰቦች አሁንም አሉ። እንዲሁም እንደ ሕንድ ያሉ አንዳንድ አገሮች አስደናቂ የሆነ የተለያየ ዓይነት የዶሮ አሠራር ዘዴ አላቸው። ለምሳሌ ያህል በበርበሬ የተሠራ ዶሮ ወይም ላል መርጊ፤ ዶሮ ዝልዝል ወይም ከርጊ መርጊ፤ በዝንጅብል የታሸ ዶሮ ወይም አድራክ መርጊ የመሳሰሉ የዶሮ አሠራሮች እጅ የሚያስቆረጥሙ ናቸው!

ከዶሮ የተዘጋጀ ምግብ ይህን ያህል ተወዳጅ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የዶሮን ያህል በተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ጣፍጦ ሊሠራ የሚችል ምግብ የለም። አንተ የምትወደው በምን መልክ ተሠርቶ ሲቀርብ ነው? ጥብስ፣ አሮስቶ ወይስ ወጥ? ማንኛውንም የምግብ አዘገጃጀት መጽሐፍ ብትመለከት እያንዳንዱን ምግብ እንዲጥም ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ በደርዘን የሚቆጠር የዶሮ አሠራር ዓይነት ልታገኝ ትችላለህ።

ዶሮ በብዙ አገሮች በብዛት ስለሚገኝ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ርካሽ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ዶሮ ለሰውነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ፕሮቲን፣ ቫይታሚንና ማዕድኖችን ስለያዘ በምግብ ጥናት ጠበብት ዘንድ ተመራጭ ነው። ሆኖም በዶሮ ሥጋ ውስጥ ያለው የካሎሪ፣ የጠጣር ቅባት (saturated fats) እና የሌሎች ቅባቶች መጠን አነስተኛ ነው።

በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን መመገብ

እርግጥ ነው፣ ሁሉም አገሮች የተትረፈረፈ የዶሮ ምርት አላቸው ማለት አይደለም። የግብርና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ያሰማራው አንድ ግብረ ኃይል “በ2020 የዓለም ሕዝብ ብዛት 7.7 ቢልዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። . . . ይሁን እንጂ አብዛኛው (95%) የሕዝብ ብዛት ጭማሪ የሚጠበቀው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው” በማለት ያቀረበው ሪፖርት የሁኔታውን አሳሳቢነት የሚያሳይ ነው። አሁንም እንኳ 800 ሚልዮን የሚያክል ሕዝብ በተመጣጠነ ምግብ እጦት እንደሚሰቃይ ስትገነዘብ የችግሩ አሳሳቢነት ይበልጥ ጎልቶ ይታይሃል!

የሆነ ሆኖ ብዙ ጠበብት ለረሃብ የተጋለጠውን ይህን ሕዝብ ለመመገብና ገበሬዎች የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ለማድረግ ዶሮ እርባታ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ይሰማቸዋል። ችግሩ ለድሃ ገበሬዎች ዶሮን በሰፊው የማርባቱ ጉዳይ ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። አንደኛ ነገር በድሃ አገሮች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ዶሮ የሚረባው በጠባብ የገጠር እርሻ ቦታዎች ወይም በጓሮ ውስጥ ነው። ይህ ሁኔታ በሚታይባቸው አገሮች ውስጥ ዶሮዎች ጥሩ መጠለያ የላቸውም። ቀን ቀን የትም ምግባቸውን ሲለቃቅሙ ይውሉና ማታ ወደ ቤት ተመልሰው ዛፍ ላይ ወይም በሽቦ በተሠራ ቤት ውስጥ ይሰፍራሉ።

በዚህ መንገድ ከሚረቡት አብዛኞቹ ዶሮዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በፈንግል በሽታ ማለቃቸውና ሌሎች ደግሞ የአዳኝ አውሬና የሰው ሲሳይ መሆናቸው አያስደንቅም። ብዙዎቹ ገበሬዎች ዶሮዎቻቸውን በበቂ ሁኔታ የመመገብ፣ ተገቢ የሆነ መጠለያ የማዘጋጀት ወይም በበሽታ እንዳይጠቁ የመከላከል አቅሙም ሆነ ችሎታው የላቸውም። በዚህ ምክንያት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ገበሬዎችን ለመርዳት ሲባል የማስተማር ፕሮግራም ተጀምሯል። ለምሳሌ ያህል የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት “በአፍሪካ ገጠር ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ገበሬዎች በዶሮ እርባታ የሚያገኙትን ጥቅም ለማሳደግ” ያወጣውን የአምስት ዓመት ዕቅድ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

በቅን ልቦና በመነሳሳት የተወሰዱት እነዚህ እርምጃዎች የሚያስገኙት ውጤት ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ዶሮን የየዕለት ምግባቸው ያደረጉ በበለጸጉት አገሮች የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ቅንጣቢ የዶሮ ሥጋ ያረረበት መሆኑ ሊያሳስባቸው ይገባል። ለአብዛኛው የዓለም ሕዝብ ‘ዶሮ በሽበሽ’ ይሆናል የሚለው ሐሳብ ከሕልም እንጀራ የሚቆጠር ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ለእንቁላል ምርት ሲባል ዶሮዎችን ማርባት የሚቻል ቢሆንም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 90 በመቶ የሚያክሉት ደሮዎች የሚረቡት ለሥጋቸው ሲባል ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጥሬ የዶሮ ሥጋ በጥንቃቄ የሚያዝበት መንገድ

“ጥሬ የዶሮ ሥጋ ሳልሞኔላ የተባለውን ባክቴሪያና ሌሎች አደገኛ ተህዋስያን ሊኖሩት ስለሚችል በዝግጅት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁልጊዜ የዶሮ ሥጋ ከመንካትህ በፊትና በኋላ እጅህን፣ መክተፊያውን፣ ቢላውንና ሌሎች መሣሪያዎችን በሞቀ ውኃና በሳሙና እጠብ። በከፍተኛ ሙቀት ሊታጠብ የሚችል መክተፊያ መጠቀም . . . ከተቻለም አንዱን መክተፊያ ጥሬ የዶሮ ሥጋ ለመክተፍ ብቻ መጠቀም የተሻለ ነው። በበረዶ ውስጥ የቆየውን የዶሮ ሥጋ ማብሰል ከመጀመራችሁ በፊት በረዶው ሙሉ በሙሉ መቅለጥ አለበት።”​—⁠ዘ ኩክስ ኪችን ባይብል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋይት ሌግሆርን፣ ግሬይ ጃንግል ፎል፣ ኦርፒንግቶን፣ ፖሊሽ እና ስፔክልድ ሱሴክስ ከዶሮ ዝርያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው

[ምንጭ]

ከዋይት ሌግሆርን በስተቀር የሁሉም ዝርያዎች ፎቶ የተወሰደው:- © Barry Koffler/www.feathersite.com

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያሉ ገበሬዎች የዶሮ ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ለመርዳት ጥረት በመደረግ ላይ ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 90 በመቶ የሚያክሉት ዶሮዎች የሚረቡት ለሥጋቸው ሲባል ነው