በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መበቀል ምን ስህተት አለው?

መበቀል ምን ስህተት አለው?

የወጣቶች ጥያቄ ...

መበቀል ምን ስህተት አለው?

“ሰደበኝ።”​—⁠በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የታሰረው የ15 ዓመቱ ኮኒል

በትምህርት ቤቱ የጭፈራ ዝግጅት ላይ አስተማሪውን የገደለው የ14 ዓመቱ እንድርያስ ለአስተማሪዎችና ለወላጆቹ ጥላቻ እንዳለው እና ሴቶች ልጆች ስለሚያገልሉት ደሙን እንደሚያፈሉት ተናግሯል።

ታይም መጽሔት ይህን ድርጊት “አደገኛ አዝማሚያ” ብሎታል። በንዴት የበገነ አንድ ወጣት ትምህርት ቤት ውስጥ መሣሪያ ደብቆ ካስገባ በኋላ ጓደኞቹንና አስተማሪዎቹን በጥይት መፍጀት ይጀምራል። በዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት በጣም እየተለመደ ስለመጣ አንድ የቴሌቪዥን ዜና ማሠራጫ ሁኔታውን “የዓመፅ ወረርሽኝ” ሲል ገልጾታል።

ደግነቱ በትምህርት ቤት የሚፈጸም ግድያ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ከስንት አንዴ የሚከሰት ነገር ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ የቁጣ መንፈስ የተፈጸሙ ወንጀሎች አንዳንድ ወጣቶች ምን ያህል የተመረሩ መሆናቸውን ያሳያሉ። እንዲህ ዓይነቱን ቁጣ የሚቆሰቁሰው ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶቹ ወጣቶች ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ባደረሱባቸው የፍትህ መጓደል ወይም በደል የተነሳ ተበሳጭተው ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ሌሎች ደግሞ እኩዮቻቸው ነጋ ጠባ ስለሚተርቧቸው ተናድደው ሊሆን ይችላል። የክፍል ጓደኛውን በጥይት ከገደለ በኋላ ራሱን የገደለ አንድ የ12 ዓመት ልጅ ይህን ያደረገው ልጁ በውፍረቱ ይተርበው ስለነበር ነው።

እርግጥ አብዛኞቹ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ከባድ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ፈጽሞ አያስቡ ይሆናል። ሆኖም የዘር መድልዎ፣ የጥቃትና የሚያቆስል ተረብ ሰለባ በምትሆንበት ጊዜ የሚደርስብህን የስሜት ጉዳትና ስቃይ መቋቋሙ ቀላል አይሆንም። ቤን በትምህርት ቤት ያሳለፈውን ሕይወት በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “ከእኩዮቼ መካከል አብዛኞቹ በቁመት ይበልጡኝ ነበር። ደግሞም ፀጉሬን እላጭ ስለነበር ልጆቹ ባገኙኝ ቁጥር ይተርቡኛል እንዲሁም መላጣዬን ይጠፈጥፉኛል። ይህ በጣም ያናድደኝ ነበር። ሁኔታውን ይበልጥ ያባባሰው ደግሞ የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች መፍትሄ እንዲሰጡኝ ስጠይቃቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ነው። ይህ ይበልጥ ያበግነኝ ነበር!” ቤን “ሽጉጥ አለማግኘቴ ነው እንጂ አንዳቸውንም ቢሆን አልምራቸውም ነበር” ሲል አክሎ ተናግሯል።

በደል የፈጸሙባቸውን ሰዎች ለመበቀል የሚፈልጉ ወጣቶችን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? ደግሞስ አንተ ራስህ በደል ቢፈጸምብህ ማድረግ ያለብህ ነገር ምንድን ነው? የዚህን መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ተመልከት።

ራስን መግዛት የጥንካሬ ምልክት ነው!

በደልና ግፍ አሁን የመጡ ነገሮች አይደሉም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቁጣንም ተወው፤ ወደ እኩይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።” (መዝሙር 37:​8 አ.መ.ት) አብዛኛውን ጊዜ ቁጣ ራስን አለመግዛት የሚታይበት ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ በሚቆጣበት ጊዜ ሊከተል የሚችለውን መዘዝ ግምት ውስጥ አያስገባም። አንድ ሰው ‘መከፋት’ ደረጃ ላይ መድረሱ በቁጣ ቱግ እንዲል ሊያደርገው ይችላል! ይህ ምን ሊያስከትል ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየንና ስለ አቤል የሚናገረውን ተመልከት። ቃየን በወንድሙ በአቤል “እጅግ ተናደደ።” ከዚህም የተነሳ “በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም።” (ዘፍጥረት 4:​5, 8) ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ ያደረበት ሌላው ሰው ንጉሥ ሳኦል ነው። ሳኦል ወጣቱ ዳዊት የተቀዳጀው ወታደራዊ ድል ያሳደረበት ቅንዓት በዳዊት ላይ ብቻ ሳይሆን በልጁ በዮናታን ላይ ሳይቀር ጦር ለመወርወር ዳርጎታል!​—⁠1 ሳሙኤል 18:​11፤ 19:​10፤ 20:​30-34

እርግጥ ለመናደድ የሚያበቃ ምክንያት የሚያጋጥመን ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ተገቢ ቁጣ ቁጥጥር ካልተደረገበት ወደ እኩይ ተግባር ሊያመራ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ስምዖንና ሌዊ፣ ሴኬም እህታቸው ዲናን እንዳስነወራት ሲሰሙ መናደዳቸው ተገቢ ነበር። ሆኖም “በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያድርግባትን?” በማለት በኋላ ከተናገሩት ቃል መረዳት እንደሚቻለው መንፈሳቸውን ከመቆጣጠር ይልቅ ሌሎችም በንዴት ቱግ እንዲሉ አደረጉ። (ዘፍጥረት 34:​31) ከዚያም በጦፈ ንዴት ተነሳስተው “እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፣ [ሴኬም በሚኖርበት መንደር ውስጥ ያለውን] ወንዱንም ሁሉ ገደሉ።” ያደረባቸው ቁጣ ሌሎችንም የሚያነሳሳ ዓይነት ስለነበር “የቀሩትም የያዕቆብ ልጆች” (የ1980 ትርጉም) በግድያ ጥቃቱ ተባበሯቸው። (ዘፍጥረት 34:​25-27) ከብዙ ዓመታት በኋላም እንኳ የስምዖንና የሌዊ አባት ያዕቆብ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣቸውን አውግዟል።​—⁠ዘፍጥረት 49:​5-7

ከዚህ አንድ ዐቢይ ቁም ነገር መማር እንችላለን፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ የጥንካሬ ሳይሆን የድክመት ምልክት ነው። ምሳሌ 16:​32 እንዲህ ይላል:- “ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፣ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)

ዐጸፋ ለመመለስ ማሰብ ሞኝነት ነው

በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎች “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ራሳችሁ አትበቀሉ” የሚል ምክር ይሰጣሉ። (ሮሜ 12:​17, 19) አካላዊ ጉዳት በማድረስም ሆነ ኃይለ ቃል በመናገር ዐጸፋ መመለስ አምላካዊ ባሕርይ አይደለም። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ የበቀል እርምጃ ከንቱና ጥበብ የጎደለው ነው። አንደኛ ነገር የኃይል እርምጃ አብዛኛውን ጊዜ የከፋ አጸፋ ያስከትላል። (ማቴዎስ 26:​52) ኃይለ ቃልም ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ በምላሹ የከፋ ኃይለ ቃል ያስከትላል። በአመዛኙ ቁጣ ምክንያታዊነት እንደሚጎድለውም አስታውሱ። ለምሳሌ ያህል ያስቀየመህ ሰው ባንተ ላይ ጥላቻ እንዳለው በእርግጠኝነት መናገር ትችላለህ? ግለሰቡ እንዲሁ አሳቢነት ስለሚጎድለው ወይም እንዳመጣለት ስለሚናገር ይሆን? ደግሞስ አድራጎቱ ክፋት ያዘለ ቢሆን እንኳ ሁኔታው ዐጸፋ መመለስን በእርግጥ ተገቢ ሊያደርገው ይችላልን?

መክብብ 7:​21, 22 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተመልከት:- “ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፤ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።” አዎን፣ ሰዎች ስለ አንተ መጥፎ ነገር መናገራቸው ቅር ሊያሰኝህ ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የማይቀር የሕይወት ክፍል መሆኑን ይናገራል። ምናልባት አንተም ባታወራው ይሻል የነበረ ስለሌሎች ያወራኸው ነገር መኖሩ እውነት አይደለም? ታዲያ አንድ ሰው ስለ አንተ መጥፎ ነገር ቢያወራ ያን ያህል የምትናደድበት ምን ምክንያት አለ? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሲተርቡህ ማድረግ ያለብህ ከሁሉ የተሻለ ነገር ሰምተህ እንዳልሰማህ መሆን ነው።

በተመሳሳይም በደል እንደተፈጸመብህ ሲሰማህ ከልክ በላይ መናደድህ ጥበብ አይደለም። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ዳዊት ከተወሰኑ ክርስቲያን ጓደኞቹ ጋር የቅርጫት ኳስ በሚጫወትበት ጊዜ የተፈጠረውን ነገር በማስታወስ “በተቃራኒው ቡድን ውስጥ የሚጫወት አንድ ልጅ በኳስ መታኝ” አለ። ዳዊት ሆን ብሎ ለመጉዳት ያደረገው ነው ብሎ በችኮላ ስለደመደመ በዐጸፋው ኳሱን ልጁ ላይ ወረወረበት። ዳዊት “በጣም ነበር የተናደድኩት” ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሆኖም ነገሩ ይበልጥ እየተባባሰ ከመሄዱ በፊት ዳዊት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ‘ምን መሆኔ ነው? ከክርስቲያን ወንድሜ ጋር ለጠብ እጋበዛለሁ እንዴ?’ ብሎ አሰበ። በኋላም እርስ በርሳቸው ይቅርታ ተጠያየቁ።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም።” (1 ጴጥሮስ 2:23) አዎን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ስትሆን ዐጸፋ ከመመለስ ይልቅ ራስህን መግዛት እንድትችል ይረዳህ ዘንድ ወደ አምላክ ጸልይ። አምላክ ‘ለሚለምኑት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል።’ (ሉቃስ 11:​13) አንድ ሰው ሲያናድድህ የዐጸፋ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ማድረግ የሚኖርብህ ሰውየውን ቀርበህ ስለ ጉዳዩ ማነጋገር ነው። (ማቴዎስ 5:​23, 24) ወይም ትምህርት ቤት ውስጥ ያለ አንድ ጉልበተኛ ልጅ ነጋ ጠባ ቢያስቸግርህ ጠብ ውስጥ ለመግባት አትጋበዝ። ከዚህ ይልቅ ራስህን ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብሃል። *

ቁጣዋን የተቆጣጠረች ወጣት

ብዙ ወጣቶች እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረጋቸው ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል ካትሪና ለጉዲፈቻ የተሰጠችው ገና ልጅ እያለች ነበር። እንዲህ ትላለች:- “ወላጅ እናቴ ለጉዲፈቻ የሰጠችኝ ለምን እንደሆነ ስለማላውቅ በትንሹም በትልቁም እቆጣ ነበር። ንዴቴን የምወጣው በአሳዳጊ እናቴ ላይ ሲሆን እሷን በመጉዳት ወላጅ እናቴን መበቀል እንደምችል አድርጌ አስብ ነበር። ከዚህም የተነሳ የማላደርገው ነገር አልነበረም። እሰድባታለሁ፣ መሬቱን በእግሬ በኃይል እየመታሁ ሰላም እነሳታለሁ እንዲሁም በቁጣ አንባርቅባታለሁ። በር ማላተም በጣም ያስደስተኛል። እንዲሁም በጣም ከመናደዴ የተነሳ ‘አልወድሽም!’ እላት ነበር። መለስ ብዬ ሳስበው እነዚህን ነገሮች እንዳደረግሁ ማመን ያቅተኛል።”

ካትሪና ቁጣዋን እንድትቆጣጠር የረዳት ምንድን ነው? “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ረድቶኛል! ይሖዋ ስሜታችንን ስለሚረዳ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው” ስትል ተናግራለች። በተጨማሪም ካትሪና እሷ ያለችበትን ዓይነት የቤተሰብ ሁኔታ አስመልክተው የወጡ የንቁ! ርዕሶችን ከቤተሰቧ ጋር ሆና ማንበብዋ አጽናንቷታል። * “ሁላችንም ተሰብስበን በመወያየታችን አንዳችን የሌላውን ስሜት መረዳት ችለናል” ስትል ታስታውሳለች።

አንተም የቁጣ ስሜትን መቆጣጠርን መማር ትችላለህ። ተረብ፣ ማስፈራሪያ ወይም በደል ሲደርስብህ መዝሙር 4:​4 ላይ የሚገኘውን “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አስታውስ። እነዚህ ቃላት ጎጂ ለሆነ ቁጣ እንዳትሸነፍ ሊረዱህ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.18 መድልዎ ከሚፈጽሙ አስተማሪዎች፣ በትምህርት ቤት ከሚያጋጥሙህ ጉልበተኛ ልጆችና ችግር ፈጣሪዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ለማግኘት በየካቲት 8, 1984፣ በነሐሴ 22, 1985 እና በነሐሴ 8, 1989 የንቁ! (እንግሊዝኛ) እትሞች ላይ የወጡትን “የወጣቶች ጥያቄ . . .” ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.21 በግንቦት 8, 1996 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ “የማደጎ ልጅ ማሳደግ​—⁠የሚያስገኘው ደስታና የሚያስከትለው ተፈታታኝ ሁኔታ” በሚል ርዕስ የወጣውን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኛውን ጊዜ ስትተረብ ሰምተህ እንዳልሰማህ መሆን ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው