በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ምን ያህል ታጋሽ ነው?

አምላክ ምን ያህል ታጋሽ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ ምን ያህል ታጋሽ ነው?

“ነገር ግን እግዚአብሔር ቊጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ . . . ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት [ችሏቸዋል]።”​—⁠ሮሜ 9:⁠22

አምላክ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ብዙ መጥፎና ዓይን ያወጡ የክፋት ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያየ ታግሷል። ከ3,000 ዓመታት በፊት ኢዮብ እንዲህ ሲል በምሬት ተናግሮ ነበር:- “ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ? ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፣ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው። ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፣ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።” (ኢዮብ 21:7-9) እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ያሉ ሌሎች ፍትህ ወዳድ ሰዎችም አምላክ ክፉዎችን መታገሡ አሳስቦአቸው ነበር።​—⁠ኤርምያስ 12:1, 2

አንተስ ምን ይመስልሃል? አምላክ ክፋት እንዲኖር መፍቀዱ እንቆቅልሽ ሆኖብሃልን? አንዳንድ ጊዜ አምላክ ጊዜ ሳይሰጥ ክፉዎችን ሁሉ በቅጽበት ማጥፋት እንደሚገባው ይሰማሃልን? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ትዕግሥት ስላለው ገደብና ለመታገሥ ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች ምን እንደሚል ተመልከት።

አምላክ ታጋሽ የሆነው ለምንድን ነው?

በቅድሚያ ልናነሳው የሚገባው ጥያቄ በጣም ከፍተኛ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ያሉት አምላክ ክፋትን ለምን ይታገሣል? የሚል ነው። (ዘዳግም 32:4፤ ዕንባቆም 1:13) ይህ ማለት ክፋትን አቅልሎ ይመለከታል ማለት ነው? በፍጹም አይደለም! እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት:- መሠረታዊ የሆኑ የንጽሕና አጠባበቅ መመሪያዎችን የሚጥስና በታካሚዎቹም ላይ ከፍተኛ ስቃይ የሚያደርስ የቀዶ ሕክምና ባለሞያ አለ እንበል። በሆስፒታል ውስጥ የሚሠራ ከሆነ ወዲያውኑ አይባረርም? ሆኖም ከሌላው ጊዜ የተለየ ትዕግሥት ማሳየት የሚያስፈልግባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ እንደ ጦርነት ባለ ፋታ የማይሰጥ ሁኔታ ውስጥ ኋላቀር በሆነ መንገድና ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ አልፎ ተርፎም ተስማሚና የተሟላ የቀዶ ሕክምና መሣሪያ ሳይኖር የሚሠሩ ባለሞያዎችን መታገሡ ግድ አይሆንምን?

በተመሳሳይም ዛሬ አምላክ ፈጽሞ የማይቀበላቸውን ብዙ ነገሮች በትዕግሥት እያሳለፈ ነው። ክፋትን የሚጠላ ቢሆንም እንኳን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ፈቅዷል። ለዚህም በቂ ምክንያቶች አሉት። እንዲህ ማድረጉ በመጀመሪያ ደረጃ ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ በቆሰቆሰው ዓመፅ ምክንያት ለተነሱት አንገብጋቢ ጥያቄዎች የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጊዜ ያስገኛል። ጥያቄዎቹ በአምላክ የአገዛዝ ትክክለኛነትና መብት ዙርያ ያተኮሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ አምላክ የክፋት ድርጊቶችን መቻሉ ክፉ አድራጊዎች እንዲለወጡ ጊዜና አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።

መሐሪና ታጋሽ አምላክ

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር ተባብረው በአምላክ ላይ ዓምፀዋል። አምላክ ወዲያው ሊያጠፋቸው መብት ነበረው። ከዚያ ይልቅ ልጆች እንዲወልዱ በመፍቀድ ፍቅራዊነቱን እንዲሁም መሐሪና ታጋሽ መሆኑን አሳየ። ሆኖም እነዚያ ልጆችም ሆኑ የእነሱ ዝርያ የሆነው መላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ኃጢአትን ወርሶ ነበር።​—⁠ሮሜ 5:12፤ 8:20-22

አምላክ የሰውን ልጅ አሳዛኝ ከሆነው ሁኔታው ለማውጣት ዝግጅት አድርጓል። (ዘፍጥረት 3:15) እስከዚያው ድረስ ግን ከአዳም የወረስነው አለፍፅምና የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ ስለሚገነዘብ ይህ ነው የማይባል ትዕግሥትና ምሕረት ያሳየናል። (መዝሙር 51:5፤ 103:13) ‘ምሕረቱ የበዛ’ እንዲሁም ‘በብዙ ይቅር ለማለት’ ዝግጁና ፈቃደኛ የሆነ አምላክ ነው።​—⁠መዝሙር 86:5, 15፤ ኢሳይያስ 55:6, 7

የአምላክ ትዕግሥት ገደብ አለው

ይሁን እንጂ አምላክ የክፋት ድርጊት ለዘላለም እንዲቀጥል ቢፈቅድ ፍቅራዊም ምክንያታዊም አይሆንም። ማንኛውም አፍቃሪ አባት በሌሎች የቤተሰቡ አባላት ላይ ሆን ብሎ ስቃይ የሚያደርስ ልጁን ክፉ ድርጊት እንደታገሠ አይኖርም። አምላክ ለኃጢአተኞች የሚያሳየው ትዕግሥትም ቢሆን ሁልጊዜ እንደ ፍቅር፣ ጥበብ እና ፍትህ ካሉ ሌሎች ባህርያቱ ጋር የተጣመረ ነው። (ዘጸአት 34:6, 7) ክፋትን የሚታገሥበት ዓላማ ዳር ከደረሰ በኋላ መታገሡ ያበቃል።​—⁠ሮሜ 9:22

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በግልጽ ሲያመለክት “እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው” ብሎ ነበር። (ሥራ 14:16) በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ሕግጋቱንና መመሪያዎቹን ላልታዘዙት ሰዎች ‘እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት እንዳሳለፈላቸው’ [አ.መ.ት ] ተናግሯል። ቀጥሎም ጳውሎስ “አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ [አምላክ] ሰውን ሁሉ ያዛል” ብሏል። ለምን? “ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን . . . በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።”​—⁠ሥራ 17:30, 31

ዛሬውኑ ከአምላክ ትዕግሥት ተጠቀሙ

እንግዲያውስ ማንም የአምላክን ሕግጋት ችላ እያለ ድርጊቶቹ ከሚያስከትሉበት መዘዝ ለማምለጥ ሲል ብቻ ለይስሙላ ያህል አምላክን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚችል አድርጎ ሊያስብ አይገባም። (ኢያሱ 24:19) በጥንትዋ እስራኤል ይኖሩ የነበሩ ብዙዎች እንደዚህ ማድረግ የሚችሉ መስሏቸው ነበር። መለወጥ አልፈለጉም። የአምላክን ቻይነትና ትዕግሥት ዓላማ ሳያስተውሉ ቀርተዋል። አምላክም ክፋታቸውን እንደታገሠ አልኖረም።​—⁠ኢሳይያስ 1:16-20

መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጨረሻ ፍርድ ለማምለጥ የፈለገ ሰው ‘ንስሐ መግባት’ እንደሚኖርበት በሌላ አባባል በአምላክ ፊት ፍጽምና የጎደለው ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ በመቀበል እና በመጸጸት ከክፋት ሙሉ በሙሉ መራቅ እንዳለበት ያሳያል። (ሥራ 3:19-21) ከዚያም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ አምላክ ይቅር ይለዋል። (ሥራ 2:38፤ ኤፌሶን 1:6, 7) አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ አዳማዊው ኃጢያት ያስከተላቸውን አሳዛኝ ውጤቶች በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። ወደፊት በሚመጣው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ይሖዋ “ጥፋትን በራሳቸው ላይ የሚጠሩ ነገሮችን” አይታገሥም። (ራእይ 21:1-5፤ ሮሜ 9:22 ፊሊፕስ) አምላክ ባሳየው ታላቅ ሆኖም ገደብ ያለው ትዕግሥት የተገኘ እንዴት ያለ ድንቅ ውጤት ነው!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ ፈቅዶላቸዋል