በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እማማ እና አሥር ሴቶች ልጆቿ

እማማ እና አሥር ሴቶች ልጆቿ

እማማ እና አሥር ሴቶች ልጆቿ

ኤስተር ሎሳኖ እንደተናገረችው

እናቴም ሆነች አባቴ አርመናውያን ከሆኑት ወላጆቻቸው በቱርክ፣ ቢትሊስ ነበር የተወለዱት። ባለፈው መቶ ዘመን መባቻ ላይ አርመናውያን በገፍ ይጨፈጨፉ በነበረበት ወቅት አባታችን ቱርክን ለቅቆ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጣ። በዚህ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ገደማ ቢሆን ነው። እናታችን ሶፊያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የ12 ዓመት ልጅ እያለች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጣች።

የሁለቱም ወላጆች እናታችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዳ ከአባታችን ከአራም ቫርታንየን ጋር እንዲጋቡ ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ይመስላል። ሶፊያ ካሊፎርኒያ፣ ፍሬስኖ ከደረሰች በኋላ ጎጆ ለመውጣት ገና ልጅ ስለነበረች ለአቅመ ሔዋን እስክትበቃ ድረስ አማቷ ከምትሆነው ሴት ጋር ተቀመጠች።

የወላጆቻችን የመጀመሪያ ልጅ ወንድ ሲሆን አንድራኒግ የሚል ስም አወጡለት። ከጊዜ በኋላ ግን ስሙን ባርኒ ብሎ አስቀየረው። የተወለደው ነሐሴ 6, 1914 ነበር። ከእሱ ቀጥሎ የተወለዱት አሥር ልጆች ባጠቃላይ ሴቶች ነበሩ። አባታችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነው (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሺልድ ቱትጂአን በ1924 ወደ ፍሬስኖ መጥቶ በዚያ ለሚኖሩ አርመናውያን ንግግር በሰጠበት ወቅት ነበር። ከዚህ በኋላ ቤተሰባችን ባጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ጀመር።

በ1931 ወደ ካሊፎርኒያ፣ ኦክላንድ ተዛውረን በዚያ ከሚገኘው ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርን። ባርኒ በ1941 እስከሞተበት ዕለት ድረስ በካሊፎርኒያ፣ ናፐ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። እኔ ከባርኒ ቀጥሎ ከተወለዱት ሴቶች ልጆች ሦስተኛዋ ስሆን በ1935 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። እህታችን ኤግነስ ላለፉት 75 ዓመታት በስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ቆይታ በቅርቡ ተጠመቀች! ሁላችንም በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘን ሲሆን ከአሥር ሴቶች ልጆች መካከል ሳትጠመቅ የቀረችው የመጨረሻዋ በመጠመቋ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል።

የሚያሳዝነው ግን እናታችን በሥነ ሥርዓቱ ላይ አልተገኘችም። የሞተችው ልጅዋ ከመጠመቋ ከአንድ ዓመት በፊት 100 ዓመት ከ2 ቀን ሲሞላት ነበር። በካሊፎርኒያ የሚታተመው ሄይወርድ ኒውስ የሚባለው ጋዜጣ በግንቦት 14, 1996 እትሙ ላይ የእሷን ሞት በተመለከተ ዘግቦ ነበር። ጋዜጣው “ላለፉት 54 ዓመታት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ . . . በማስተማር በይሖዋ ምሥክርነቷ ለኅብረተሰቡ ነፃ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች” ሲል ዘግቧል። በተጨማሪም ጽሑፉ እህታችን ኤሊዛቤት የተናገረችውንም ጠቅሷል:- “እማማ ምንጊዜም እንግዳ ተቀባይ ነበረች፤ በራት ሰዓት ገበታው የሚዘጋጀው ምናልባት አንድ እንግዳ ይመጣ ይሆናል በሚል ታስቦ ነው . . . ‘ወፍራም ቡና ካማራችሁ ጎራ በሉ’ የማለት ልማድ ነበራት። ጣፋጭ ባቅላባ ኬክ በሠራችበት ቀን እግር ከጣላችሁ ደግሞ በእርግጥ ዕድለኞች ናችሁ።”

ታላቅ እህታችን ግላዲስ ዕድሜዋ 85 ዓመት ሲሆን የመጨረሻዋ እህታችን ደግሞ 66 ዓመቷ ነው። ሁላችንም ንቁ ምሥክሮች ነን። ከእኛ መካከል ሦስታችን ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመርቀን በሚስዮናዊነት አገልግለናል። በአሁኑ ጊዜ በካሊፎርኒያ፣ ኒውፖርት ቢች የምትኖረው ኤሊዛቤት በትምህርት ቤቱ 13ኛ ክፍል ተካፍላ በፔሩ፣ ከያው ለአምስት ዓመታት አገልግላለች። ሩት ደግሞ በ35ኛው ክፍል ተካፍላለች። እሷና ባለቤቷ አልቨን ስታውፈር በአውስትራሊያ ለአምስት ዓመታት በሚስዮናዊነት አገልግለዋል። እኔ ደግሞ በአራተኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት የተካፈልኩ ሲሆን በ1947 ሜክሲኮ ተመደብኩ። እዚያም በ1955 ከሩዶልፎ ሎዛኖ ጋር ተጋባን። * ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁለታችንም በሜክሲኮ በማገልገል ላይ ነን።

እህትማማች የሆንነው አሥራችንም ላለን መጠነኛ ጤንነት እጅግ አመስጋኞች ነን። ይሖዋ እስከፈቀደ ድረስ አሁንም ሆነ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በሙሉ አሳባችን፣ ልባችንና ኃይላችን እሱን ለዘላለም ማገልገላችንን እንድንቀጥል ያስችለናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 የሎዛኖ ተሞክሮ በጥር 1, 2001 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤግነስ በ1997 ስትጠመቅ

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤሊዛቤት በ1949 ከጊልያድ በተመረቀችበት ዕለት

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤስተር (በስተ ቀኝ) በ1950 ሜክሲኮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩትና አልቨን ስታውፈር በ1987 ዓለም አቀፍ አገልጋዮች ሆነው ሜክሲኮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ሲያገለግሉ