እርዳታ ማግኘት ትችላለህ
እርዳታ ማግኘት ትችላለህ
በስዊዘርላንድ የሚኖር አንድ የ28 ዓመት ሰው ‘አርባ ዘጠኝ የእንቅልፍ ክኒን ብርጭቆ ውስጥ ከጨመረ በኋላ ልዋጠው አልዋጠው?’ ሲል ራሱን ጠየቀ። ሚስቱና ልጆቹ ጥለውት በመሄዳቸው በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተውጧል። መድኃኒቱን ከዋጠ በኋላ ግን ‘የለም፣ መሞት አልፈልግም!’ ሲል ለራሱ ተናገረ። ደግነቱ ከሞት ተርፎ ሁኔታውን ለመተረክ በቅቷል። የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚገፋፉ ስሜቶች ሁልጊዜ ለሞት አያበቁም።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት ባልደረባ የሆኑት አሊክስ ክሮዝቢ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉትን ሙከራ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ለጥቂት ሰዓታት እንኳን ድርጊቱን ማስተው ከቻላችሁ ሙሉ በሙሉ ማስጣል ትችላላችሁ። ድርጊቱን በማስተጓጎል ብዙዎች ሕይወታቸውን ወደማጥፋት ደረጃ እንዳይሸጋገሩ መከላከል ትችላላችሁ። እንዲህ በማድረግ ሕይወታቸውን መታደግ ትችላላችሁ።”
ፕሮፌሰር ሂሳሺ ኩሮሳዋ በጃፓን የሕክምና ኮሌጅ የሕይወት አድንና የአደጋ መከላከያ ማዕከል በሚሠሩበት ወቅት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የተነሳሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመርዳት የመኖር ፍላጎታቸው በውስጣቸው እንዲያንሰራራ አድርገዋል። አዎን፣ በሆነ መንገድ እርዳታ በመስጠት የብዙዎችን ሕይወት መታደግ ይቻላል። ምን ዓይነት እርዳታ ነው የሚያስፈልገው?
ከበስተጀርባ ያሉትን ችግሮች መጋፈጥ
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የሥነ አእምሮ ሕመም ወይም ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን አላግባብ የመውሰድ ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በመሆኑም የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኢቭ ኬ ሞሽቺትስኪ “በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ከማጥፋት እንዲታቀቡ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው አማራጭ የአእምሮ ሕመምንና ሱሰኝነትን መዋጋት ነው” ብለዋል።
የሚያሳዝነው እንዲህ ያሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ብዙዎቹ ሰዎች እርዳታ የመፈለግ ዝንባሌ የላቸውም። ለምን? “በኅብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የተዛባ አመለካከት ያለ በመሆኑ ነው” ይላሉ የቶኪዮ የሥነ አእምሮ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዮሺቶሞ ታካሃሺ። በመሆኑም ደህና እንዳልሆኑ በመጠኑም ቢሆን የሚታወቃቸው ሰዎች እንኳ ወዲያውኑ ሕክምና ለማግኘት አይሞክሩም ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
አንዳንዶች ግን ኀፍረት እንዲያሸንፋቸው አይፈቅዱም። በጃፓን ለ17 ዓመታት በቴሌቪዥን የራሱን ፕሮግራም ሲያቀርብ የነበረ ሂሮሺ ኦጋዋ የተባለ አንድ የታወቀ ሰው የመንፈስ ጭንቀት እንዳለበትና እንዲያውም የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ተቃርቦ እንደነበረ በይፋ አምኗል። “የመንፈስ ጭንቀት የአእምሮ ጉንፋን ነው ሊባል ይችላል” ሲል ኦጋዋ ተናግሯል። ማንኛውም ሰው ሊይዘው ይችላል፤ ቢሆንም ማገገም ይቻላል በማለት ገልጿል።
ችግርህን ለሌላ ሰው አዋየው
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ቤላ ቡዳ የተባሉ የሀንጋሪ የጤና ባለሥልጣን “አንድ ሰው ችግሩን ለብቻው ሲጋፈጥ ብዙውን ጊዜ ከልክ በላይ አግዝፎ የሚመለከተው ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ ሊፈታ እንደማይችል አድርጎ ያስባል” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አስተያየት የሚከተለው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥበብ የተሞላበት መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ ምሳሌ 18:1
መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”—እነዚህን ጥበብ የተሞላባቸው ቃላት ልትሠራባቸው ይገባል። በችግር ባሕር ውስጥ ተዘፍቀህ ብቻህን የምትታገልበት ምንም ምክንያት የለም። እምነት ልትጥልበትና ችግርህን ልታካፍለው የምትችለው ሰው ፈልግ። ምናልባት ‘ችግሬን ላካፍለው የምችለው ሰው የለኝም’ ትል ይሆናል። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ናኦኪ ሳቶ እንደሚሉት ከሆነ ብዙዎች እንዲህ ይሰማቸዋል። ሳቶ እንደገለጹት ሕሙማን ድክመቶቻቸውን መግለጥ ስለማይፈልጉ ችግራቸውን ለሌሎች ከማዋየት ይቆጠባሉ።
አንድ ሰው ችግሩን ሊያዋየው የሚችለው ሰው የት ሊያገኝ ይችላል? በብዙ አገሮች ግለሰቡ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ለመከላከል ከተቋቋመ ማዕከል ወይም በስልክ የምክር አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ደግሞ ከስሜታዊ ችግሮች ጋር የተያያዘ ሕክምና ከሚሰጥ የታወቀ ሐኪም እርዳታ ማግኘት ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ጠበብት ሃይማኖትም ጥሩ የእርዳታ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ሃይማኖት ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘት
በቡልጋሪያ የሚኖር ማሪን የተባለ አካላዊ እክል ያለበት ሰው ራሱን እንዲገድል የሚገፋፋ ስሜት አደረበት። አንድ ቀን በአጋጣሚ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ጽሑፍ አገኘ። የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩት ይፈልግ እንደሆነ መጽሔቱ ላይ ለቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠ። ማሪን የተገኘውን ውጤት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሕይወት የሰማያዊ አባታችን ስጦታ እንደሆነና ሆን ብለን ራሳችንን የመጉዳት ወይም ሕይወታችንን የማጥፋት መብት እንደሌለን እንድገነዘብ አደረጉኝ። በመሆኑም ሕይወቴን ለማጥፋት የነበረኝ ፍላጎት ተወግዶ የመኖር ፍላጎት ዳግም በውስጤ ተጸነሰ!” በተጨማሪም ማሪን ከክርስቲያን ጉባኤ ፍቅራዊ እርዳታ አገኘ። ምንም እንኳ አሁንም አካላዊ እክል ያለበት ቢሆንም “ዛሬ በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ መንፈሴ ተረጋግቷል። ልሠራቸው የምችል በርካታ አስደሳች ነገሮች ስላሉ ጊዜ እንኳን አይበቃኝም! ለዚህ ሁሉ ይሖዋንና ምሥክሮቹን ላመሰግን እወዳለሁ” ብሏል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ስዊዘርላንዳዊ ወጣትም ከይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ አግኝቷል። ወደ ቤታቸው የወሰዱት “አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ያሳዩትን ደግነት” ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማስታወስ ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በኋላ ደግሞ [የይሖዋ ምሥክሮች] ጉባኤ አባላት በየተራ እየወሰዱ ይጋብዙኝ ጀመር። በእጅጉ የረዳኝ ነገር ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ የተደረገልኝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሐሳቤን ላካፍለው የምችለው ሰው ማግኘቴ ጭምር ነው።”
ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው ትምህርት በተለይ ደግሞ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅር ማወቁ ይበልጥ አበረታቶታል። (ዮሐንስ 3:16) በእርግጥም ይሖዋ አምላክ ‘ልብህን በፊቱ በምታፈስስበት’ ጊዜ ይሰማሃል። (መዝሙር 62:8) “ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ።” ይህን የሚያደርገው በሰዎች ላይ ስህተት ለመፈለግ ሳይሆን “ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን” ለማጽናት ነው። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ” ሲል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ኢሳይያስ 41:10
ስዊዘርላንዳዊው ሰው አምላክ ስለ አዲሱ ዓለም የገባውን ቃል አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ተስፋ እንደ ሸክም የተጫነኝን ሐዘንና ብስጭት ለማቅለል በጣም ረድቶኛል” ብሏል። የ“ነፍስ መልሕቅ” ተብሎ የተገለጸው ይህ ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘትን የሚጨምር ነው።—ዕብራውያን 6:19፤ መዝሙር 37:10, 11, 29
ሕይወትህ በሌሎች ዘንድ ውድ ነው
እርግጥ ነው፣ ሙሉ በሙሉ ብቻህን እንደሆንክና የአንተ መሞት አለመሞት በሌሎች ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ እንዲሰማህ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊገጥሙህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በብቸኝነት ስሜት እና ብቸኛ በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን አስታውስ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ነቢዩ ኤልያስ በጣም ተስፋ የቆረጠበት ጊዜ ነበር። “ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ” ሲል ለይሖዋ ተናግሮ ነበር። አዎን፣ ኤልያስ ብቻውን እንደቀረ ተሰምቶት ነበር። ለዚህም ምክንያት ነበረው። እንደሱው ያሉ በርካታ ነቢያት የተገደሉ ሲሆን እርሱም ራሱ የግድያ ዛቻ ስለተሰነዘረበት ሕይወቱን ለማዳን በሽሽት ላይ ነበር። ግን በእርግጥ ብቻውን ነበርን? አልነበረም። ይሖዋ በእነዚያ የጨለማ ዘመናት እንደ እሱ እውነተኛውን አምላክ በታማኝነት ለማገልገል እየጣሩ ያሉ 7, 000 ገደማ የሚሆኑ ታማኝ ሰዎች መኖራቸውን እንዲገነዘብ አደረገው። (1 ነገሥት 19:1-18) ስለ አንተስ ምን ለማለት ይቻላል? አንተም የምታስበውን ያህል ብቸኛ አልሆንክ ይሆናል።
ለአንተ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ወላጆችህን፣ የትዳር ጓደኛህን፣ ልጆችህንና ጓደኞችህን ልታስብ ትችላለህ። ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያስቡልህ፣ በትዕግሥት የሚያዳምጡህና አብረውህም ሆነ በግላቸው ለአንተ የሚጸልዩ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ልታገኝ ትችላለህ። (ያዕቆብ 5:14, 15) በተጨማሪም አለፍጽምና ያለባቸው ሰዎች ሁሉ እንደጠበቅካቸው ሆነው ባይገኙ እንኳ ከቶ የማይተውህ አካል መኖሩን አትዘንጋ። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 27:10፣ አ.መ.ት) አዎን፣ ይሖዋ ‘ያስብልሃል።’ (1 ጴጥሮስ 5:7) በይሖዋ ዓይን ውድ መሆንህን ፈጽሞ አትዘንጋ።
ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ስጦታ ከመሆን ይልቅ ሸክም ሆኖ ሊታይ እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ ለአንድ ሰው ውድ የሆነ ስጦታ ብትሰጠውና ግለሰቡ ስጦታውን ሳይጠቀምበት ቢጥለው ምን ሊሰማህ እንደሚችል መገመት ትችላለህ? እኛ አለፍጽምና ያለብን ሰዎች የሕይወትን ስጦታ ምንም ያህል አልተጠቀምንበትም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዓይን ሲታይ አሁን እየኖርነው ያለነው ሕይወት ‘እውነተኛው ሕይወት’ እንዳልሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) አዎን፣ በቅርቡ ሕይወታችን ይበልጥ የተሟላና ትርጉም ያለው እንዲሁም አስደሳች ይሆናል። እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ይላል። (ራእይ 21:3, 4) እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖርህ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ጊዜ ወስደህ የተሟላና ማራኪ ስዕል በምናብህ ለመሳል ሞክር። ይህ ምናባዊ ስዕል ባዶ ቅዠት አይደለም። ባለፉት ዘመናት ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት ይዟቸው እንደነበር ስታሰላስል በእሱ ላይ ያለህ ትምክህት የሚያድግ ከመሆኑም በላይ ይህ ምናባዊ ስዕል ይበልጥ እውን ሆኖ ይታይሃል።—መዝሙር 136:1-26
የመኖር ፍላጎትህን ሙሉ በሙሉ ለመቀስቀስ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። ‘በመከራችን ሁሉ ወደሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ መጸለይህን ቀጥል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ የሚያስፈልግህን ብርታት ይሰጥሃል። በሕይወት መኖርን የመሰለ ነገር እንደሌለ ያስተምርሃል።—ኢሳይያስ 40:29
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ራሱን የመግደል አዝማሚያ የሚታይበትን ሰው እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ማጥፋት እንደሚፈልግ ቢነግርህ ማድረግ ያለብህ ነገር ምንድን ነው? የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) “ጥሩ አዳማጭ ሁን” ሲል ይመክራል። የሚሰማውን አውጥቶ እንዲናገር ፍቀድለት። ብዙውን ጊዜ ግን የራሱን ሕይወት ለማጥፋት የተነሳሳ ሰው ራሱን የሚያገልል ከመሆኑም በላይ ሐሳቡን ለማካፈል ፈቃደኛ አይደለም። ጥልቅ ሐዘን ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳደረበት ልታውቅለት ይገባል። በጠባዩ ላይ የታዩ አንዳንድ ለውጦችን ጠቅሰህ በለዘበ አንደበት ብታነጋግረው የልቡን አውጥቶ ለመናገር ሊገፋፋ ይችላል።
በምታዳምጥበት ጊዜ እንደ ራስህ ችግር አድርገህ በመመልከት አሳቢነት አሳይ። “የግለሰቡ ሕይወት በአንተም ሆነ በሌሎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ጠበቅ አድርጎ መግለጹ አስፈላጊ ነው” ይላል ሲ ዲ ሲ። የእሱ ሞት በአንተም ሆነ በሌሎች ላይ ምን ያህል ከባድ የመንፈስ ስብራት ሊያደርስ እንደሚችል እንዲገነዘብ አድርግ። ግለሰቡ ፈጣሪው የሚያስብለት መሆኑን እንዲያስተውል እርዳው።—1 ጴጥሮስ 5:7
በተጨማሪም ግለሰቡ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ነገሮች በሙሉ በተለይም እንደ ሽጉጥ ያሉ መሣሪያዎችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ጠበብት ይመክራሉ። ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ ከታየህ ግለሰቡ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ልታበረታታው ትችላለህ። ከዚህ የከፋ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ያለህ አማራጭ አንተ ራስህ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ባለሙያዎችን መጥራት ይሆናል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘እንዲህ ዓይነት ነገር አስቤ አምላክ ይቅር ይለኛል?’
ብዙዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመገናኘታቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ አድርጓቸው የነበረውን ስሜት ማሸነፍ ችለዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ውጥረት ውስጥ ከሚከትቱ ሁኔታዎችና ከመንፈስ ጭንቀት ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ሰው የለም። የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ተነሳስተው የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ለማድረግ ማሰባቸው ብዙውን ጊዜ የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ይህ የበደለኛነት ስሜት ሸክማቸውን ከማክበድ በቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እንግዲያው እንዲህ ዓይነቱን ስሜት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስለ ሕይወት ያደረባቸውን እጅግ አሉታዊ የሆነ ስሜት የገለጹባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው። የዕብራውያን አባት የሆነው የይስሐቅ ሚስት ርብቃ በአንድ ወቅት በቤተሰባቸው ውስጥ በተፈጠረ ችግር ሳቢያ በጣም ከማዘኗ የተነሳ “ሕይወቴን ጠላሁት” ስትል ተናግራለች። (ዘፍጥረት 27:46) ልጆቹን፣ ጤናውን፣ ሀብቱንና በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን ቦታ ያጣው ኢዮብ “ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 10:1) ሙሴ በአንድ ወቅት “እባክህ፣ ፈጽሞ ግደለኝ” ሲል አምላክን ተማጽኗል። (ዘኁልቁ 11:15) የአምላክ ነቢይ የሆነው ኤልያስ በአንድ ወቅት “ይበቃኛል፤ አሁንም፣ አቤቱ፣ . . . ነፍሴን ውሰድ” ብሎ ነበር። (1 ነገሥት 19:4) በተጨማሪም ነቢዩ ዮናስ በተደጋጋሚ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” ሲል ተናግሮ ነበር።—ዮናስ 4:8
ይሖዋ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ ስሜት ስለተሰማቸው ኮንኗቸዋልን? አልኮነናቸውም። እንዲያውም የተናገሩት ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ እንዲቀመጥ አድርጓል። ይሁንና ከእነዚህ ታማኝ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ያደረባቸው ስሜት የራሳቸውን ሕይወት ወደማጥፋት ድርጊት እንዲመራቸው እንዳልፈቀዱ ልብ ማለት ያሻል። ይሖዋ ከፍ አድርጎ ተመልክቷቸዋል፤ በሕይወት እንዲቀጥሉም ፈልጓል። እንዲያውም አምላክ ለክፉዎች ሕይወት ሳይቀር ያስባል። መንገዳቸውን እንዲለውጡና ‘በሕይወት እንዲኖሩ’ ያሳስባቸዋል። (ሕዝቅኤል 33:11) የእርሱን ሞገስ ለማግኘት ለሚጥሩት ሰዎች ሕይወት ደግሞ የበለጠ እንደሚያስብ የተረጋገጠ ነው!
አምላክ የልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት፣ የክርስቲያን ጉባኤን፣ መጽሐፍ ቅዱስንና የጸሎት መብት ሰጥቶናል። ከአምላክ ጋር የምንነጋገርበት የጸሎት መስመር ተይዞብን አያውቅም። አምላክ ትሁትና ቅን በሆነ ልቦና የሚቀርቡትን ሁሉ ሊሰማ ይችላል፣ ደግሞም ይሰማል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”—ዕብራውያን 4:16
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የራሱን ሕይወት ያጠፋ የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጅ አለህን?
አንድ ሰው የራሱን ሕይወት በሚያጠፋበት ጊዜ የቤተሰቡ አባላትና የቅርብ ጓደኞቹ ከባድ የአእምሮ መረበሽ ይደርስባቸዋል። ብዙዎች ለደረሰው ሁኔታ ራሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ‘ምነው ያን ቀን ትንሽ አብሬው በቆየሁ ኖሮ፣’ ‘ምነው ምላሴን በቆረጠው ኖሮ’ ‘ይበልጥ በረዳሁት ኖሮ’ ይላሉ። በሌላ አባባል ‘እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ባልሞተ ነበር’ ማለታቸው ነው። ይሁን እንጂ ሌላው ሰው በሕይወቱ ላይ ለወሰደው እርምጃ ራስን ተጠያቂ ማድረጉ አግባብ ነውን?
ሁኔታው ከተፈጸመ በኋላ ግለሰቡ ራሱን ለመግደል አስቦ እንደነበረ የሚጠቁሙ ምልክቶችን መለየት እንደማይከብድ አትዘንጋ። ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት እነዚህን ምልክቶች ማስተዋል መቻል እንዲህ ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም” ይላል። (ምሳሌ 14:10፣ አ.መ.ት ) አንዳንድ ጊዜ ሌላው ሰው የሚያስበውን ወይም የሚሰማውን ስሜት መረዳት አይቻልም። የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ያሰቡ ብዙዎቹ ሰዎች ለሌሎች፣ ለቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ሳይቀር ውስጣዊ ስሜታቸውን ሙሉ በሙሉ መግለጥ ይሳናቸዋል።
ጊቪንግ ሶሮው ወርድስ የተሰኘው መጽሐፍ አንድ ሰው ራሱን ለመግደል ማሰቡን ሊጠቁሙ ስለሚችሉ ምልክቶች ሲናገር “ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉትን ምልክቶች መረዳት ቀላል አይደለም” ብሏል። አንዳንድ ፍንጮች አግኝተህ የነበረ ቢሆን እንኳ ይህ በራሱ ድርጊቱን ማስቀረት ያስችልህ የነበረ ነገር ተደርጎ ሊታይ አይችልም ሲል ይኸው መጽሐፍ አክሎ ገልጿል። ራስህን በበደለኝነት ስሜት ከማሰቃየት ይልቅ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በሚሉት የጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ቃላት ልትጽናና ትችላለህ። (መክብብ 9:5) በሞት ያጣኸው የምትወደው ሰው እሳታማ ሲኦል ውስጥ ገብቶ እየተሠቃየ አይደለም። በተጨማሪም የራሱን ሕይወት ወደማጥፋት ደረጃ ያደረሰው የአእምሮም ሆነ የስሜት ሥቃይ አብቅቶለታል። ሥቃይ ላይ ሳይሆን ዕረፍት ላይ ነው ያለው።
አሁን ራስህን ጨምሮ በሕይወት ስላሉት ሰዎች ደህንነት ማሰቡ የተሻለ ይሆናል። ሰሎሞን በመቀጠል በሕይወት ሳለህ “እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” ብሏል። (መክብብ 9:10) የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች የወደፊት ተስፋ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ እጅ ያለ ጉዳይ መሆኑን አትጠራጠር።—2 ቆሮንቶስ 1:3 *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.40 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች የወደፊት ተስፋቸው ምን እንደሚመስል ሚዛናዊ አመለካከት ይኖርህ ዘንድ በመስከረም 8, 1990 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች ትንሣኤ ይኖራቸዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ችግርህን ለሌላ ሰው አዋየው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕይወትህ በሌሎች ዘንድ ውድ ነው