ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ከሙዝ ተክል የሚሠራ ወረቀት
የሙዝ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ብዙውን ጊዜ አገዳው ማዳበሪያ እንዲሆን እዚያው መሬት ላይ ይተዋል። ይሁን እንጂ የናጎያ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሂሮሺ ሞሪሺማ ከሙዝ ተክል አገዳዎች ወረቀት መሥራት ችለዋል ሲል አሳሂ ሺምቡን የተሰኘው የጃፓን ጋዜጣ ዘግቧል። የተክሉ ቃጫዎች “ረጃጅምና ጠንካራ ከመሆናቸውም በላይ የጥራት ደረጃቸው ማኒላ ሄምፕ ተብሎ ከሚጠራው ተክል ከሚገኘው ወረቀት ለማምረት የሚያገለግል ጥሬ ዕቃ ጋር የሚስተካከል ነው።” በማሽን አማካኝነት ከሙዝ ተክል አገዳ የሚመረተው ወረቀት የጥራት ደረጃ ለኅትመት ከሚያገለግለው መደበኛ ወረቀት አይተናነስም። በተጨማሪም ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ በድጋሚ ፋብሪካ ገብቶ ከሚመረተው ወረቀት ይበልጥ ጠንካራ ሆኖ ተገኝቷል። “ሙዝ በዓለም ዙሪያ በ123 አገሮች ውስጥ በየዓመቱ ከ58, 000, 000 ቶን በላይ የሚመረት በመሆኑ የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ አስተማማኝ እንደሚሆን ይታመናል” ይላል ጋዜጣው።
ከአውሮፕላን አደጋዎች መትረፍ
ናሽናል ፖስት የተሰኘው የካናዳ ጋዜጣ እንደገለጸው ከሆነ “በመንገደኞች አውሮፕላን ላይ ከሚደርሱት አደጋዎች የሚተርፉት ተሳፋሪዎች ቁጥር ከ95 በመቶ በላይ ይሆናል።” ፖስት እንደሚለው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ያካሄደው ጥናት አብዛኞቹ መንገደኞች በአውሮፕላኑ ላይ ከባድ ጉዳት ከሚያስከትሉ “አስከፊ አደጋዎች” ሳይቀር እንደሚተርፉ አመልክቷል። በካናዳ የትራንስፖርት ባለሥልጣን የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዲሬክተር የሆኑት አርት ላፍላም እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “አብዛኞቹ አደጋዎች የሚከሰቱት አውሮፕላኑ በሚያርፍበትና በሚነሳበት ወቅት ነው። እነዚህ አደጋዎች በመገናኛ ብዙሃን ብዙም ሽፋን የማይሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ከእንዲህ ዓይነቶቹ አደጋዎች መትረፍ የሚቻልበት አጋጣሚ በእጅጉ የሰፋ ነው። በአደጋ ጊዜ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ለሚሰጠው መግለጫ አጽንኦት የምንሰጠው ለዚህ ነው።” አዘውትረው በአውሮፕላን የሚጓዙ ሰዎች ለእነዚህ መመሪያዎች እምብዛም ትኩረት አይሰጡም። ይሁን እንጂ የአንድ አየር መንገድ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት “ሰዎች እነዚህን መመሪያዎች በትኩረት መከታተላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ሕይወታቸው በዚህ ላይ የተመካ ይሆናል።”
“ቴክኖሎጂ የሚያስከትለው ውጥረት”
“ቴክኖሎጂ የሚያስከትለው ውጥረት” ማለትም አዲስ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያለው ጫና የሚያስከትለው ብስጭት እየጨመረ መጥቷል ሲል መክሌንዝ የተባለው የካናዳ መጽሔት ዘግቧል። በጉዳዩ ላይ የተካሄዱት ጥናቶች “አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለማወቅ የሚካሄደውን ማብቂያ የሌለው የትምህርት ሂደትና እንደ ኢ-ሜይል፣ የስልክ መልእክቶችን ወደ ሌላ መስመር የማስተላለፍ ዘዴና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ባሉ አዳዲስ ግኝቶች ሳቢያ በመኖሪያ ቤትና በሥራ ቦታ መካከል የተፈጠረውን መመሳሰል” እንደ መንስኤ አድርገው ጠቅሰዋል። ይህን ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? ገደብ ማበጀት ጠቃሚ እንደሆነ ጠበብት ይመክራሉ። ለመጠቀም ያሰብከው መሣሪያ ኑሮን ያቀላል ወይስ ይበልጥ ያወሳስበዋል የሚለውን ጉዳይ ለይተህ ለማወቅ ሞክር። አንድ አዲስ ቴክኖሎጂ የሚሰጠውን ሙሉ ጥቅም ማግኘት ትችል ዘንድ ከቴክኖሎጂው ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ጊዜ እንደሚወስድብህ አስታውስ። “በየዕለቱ መሣሪያውን ለምን ያህል ጊዜ ልትጠቀምበት እንደሚገባ ወስን።” ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችንም ለማከናወን ጊዜ ይኑርህ። “ሰዎች በፕሮግራም ከመመራት ይልቅ ገና በማለዳ ኢ-ሜይላቸውን በመክፈት ትልቅ ስህተት ይሠራሉ” ሲሉ በቫንኩቨር የምርታማነት ኤክስፐርት የሆኑት ዳን ስታምፕ ገልጸዋል። “ይበልጥ ምርታማ የምንሆንበት የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በማይረባ ነገር ባክኖ ይቀራል።”
የራሳቸውን መጻሕፍት የሚጽፉ ልጆች
በዛምቢያ የንባብ ልማድን ለማበረታታት ሲባል ተማሪዎች የራሳቸውን አጭር ይዘት ያለው መጽሐፍ በሥዕላዊ መግለጫዎች አስደግፈው እንዲያዘጋጁ ይነገራቸዋል ይላል ዛምቢያ ዴይሊ ሜይል ያወጣው ዘገባ። መንግሥት ያወጣው ዘገባ እንደሚገልጸው “በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ቤተ መጻሕፍት የያዟቸው ጽሑፎች ለዛምቢያ ልጆች ፍጹም እንግዳ በሆኑ ጉዳዮችና ሁኔታዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።” “ልጆቹ የሚጽፏቸው መጻሕፍት በራሳቸው የእውቀት ደረጃ ያሉና በሚስቧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስለሚሆኑ የራሳቸውን መጻሕፍት ማዘጋጀታቸው ጠቃሚ ነው።” ከሚጽፏቸው ታሪኮች መካከል አንዳንዶቹ በትምህርት ቤት ወይም በክፍል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይቀመጣሉ፣ በራዲዮ ይቀርባሉ አልፎ ተርፎም ታትመው ይወጣሉ። ዴይሊ ሜይል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ይህ ከወረቀትና ከብዕር ሌላ ምንም ነገር የማይጠይቅ በመሆኑ የመጻሕፍት አቅርቦትን በቀላል ዋጋ ለማሳደግ የሚያስችል ጥሩ ዘዴ ነው። በተጨማሪም እምብዛም የማይገኘውንና ውድ የሆነውን እሴት (መጻሕፍት) እንደ ልብ በሚገኝ እሴት (ተማሪዎች) ለመፍጠር የሚያስችል ዘዴ ነው።”
የወባ መድኃኒት ፋይዳ ቢስ ሆነ
‘በዛምቢያ ወባን ለመከላከል እንደ ቀዳሚ እርምጃ ተደርጎ የተወሰደው በአገሪቱ በአብዛኛው ለወባ በሽታ የሚታዘዘውን ክሎሮክዊን የተባለውን መድኃኒት ከመንግሥት መድኃኒት ማከፋፈያዎች ማስወገድ’ እና ይበልጥ ፍቱን በሆነ መድኃኒት መተካት መሆኑን ታይምስ ኦቭ ዛምቢያ ዘግቧል። መድኃኒቱን ለማስወገድ የታሰበው “በየዓመቱ በዛምቢያ በወባ ከሚሞቱት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 25, 000 ሕፃናት መካከል 12, 000ዎቹ የሚሞቱት በሽታው ክሎሮክዊን የተባለውን መድኃኒት መቋቋም በመቻሉ ምክንያት እንደሆነ” አንድ ጥናት ካመለከተ በኋላ ነው። በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አብዛኞቹ
አገሮችም ይህንኑ የለውጥ ሂደት ጀምረዋል። “ምንም እንኳ ክሎሮክዊን አገሪቱን ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በሚገባ ያገለገለ ቢሆንም አሁንም ድረስ በአገሪቱ የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን የወባ በሽታ በመከላከል ረገድ ፋይዳ ቢስ ሆኗል” ይላል ታይምስ።አልኮል ጠጥተህ ብስክሌት አትንዳ
አልኮል ጠጥቶ ብስክሌት መንዳት፣ ጠጥቶ መኪና የማሽከርከርን ያህል አደገኛ ሊሆን ይችላል ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። በዩ ኤስ ኤ ሜሪላንድ የሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ግዎህዋ ሊ “ብስክሌት መንዳት መኪና ከማሽከርከር በበለጠ ከፍተኛ የአእምሮ ብቃትና አካላዊ ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ አልኮል ብስክሌት በሚነዳ ሰው ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ያሳድራል” በማለት ተናግረዋል። ሊ እና ባልደረቦቻቸው ብስክሌት በሚነዱ 466 ሰዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ከአራት በላይ የጠጡት ሰዎች 20 ጊዜ እጥፍ ለከባድ ጉዳት ወይም ለሞት ተጋልጠው እንደነበር መገንዘብ ችለዋል። አንድ ብቻ ጠጥተው ብስክሌት የሚነዱ ሰዎች እንኳ ስድስት እጥፍ ለአደጋ የተጋለጡ ይሆናሉ። “ብስክሌተኞቹ ብዙ በጠጡ መጠን የራስ ቁር ለማድረግም የዚያኑ ያህል ቸልተኛ ስለሚሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል” ሲል ኒው ሳይንቲስት ገልጿል።
የቆዳ ካንሰር እየተስፋፋ ነው
ኤል ፓኢስ ዲኺታል የተባለው የስፔይን የዜና አገልግሎት እንዳለው ከሆነ ከቆዳ እብጠቶች (tumors) ሁሉ በጣም አስከፊ የሆነው ሜላኖማ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ከ1, 500 ሰዎች መካከል በሜላኖማ ይያዝ የነበረው 1 ሰው ብቻ ነበር። በ2000 ግን ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ያሻቀበ ሲሆን ከ75 ሰዎች መካከል 1 ሰው በበሽታው ይያዛል። ለዚህም በዋነኛነት ምክንያት የሆነው ነገር ቆዳን ለማጥቆር ሲባል ፀሐይ ላይ የመንቃቃት ልማድ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው። በእብጠቶች ላይ የሕክምና ጥናት የሚያካሂደው የአውሮፓ ማኅበር በጠራው ስብሰባ ላይ ፕሮፌሰር ጄ ኪርክዉድ 40 በመቶ የሚሆነው የሜላኖማ እብጠት የሚከሰተው ከዘር ውርስ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሳቢያ ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው ግን ከልክ በላይ ለፀሐይ ብርሃን በመጋለጥ የተነሳ የሚከሰት እንደሆነ ገልጸዋል። በአብዛኛው በዚህ በሽታ የሚጠቁት ከ23 እስከ 50 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው። ኪርክዉድ እንደገለጹት በልጅነት ወይም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ወቅት በፀሐይ ጨረር ሳቢያ ቆዳ በሚያቀልሙ ሕዋሳት ውስጥ ጀነቲካዊ ለውጥ ሊከሰት ይችላል። እርግጥ ይህ ሁኔታ ወደ ካንሰርነት ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ብዙ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ። “የፀሐይ ብርሃኑ ያስከተለው ለውጥ በቆዳ ውስጥ ተደብቆ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል” ሲሉ ኪርክዉድ ገልጸዋል።
ማር ያለው የመፈወስ ኃይል
ማር ካለው ጣፋጭ ጣዕም ሌላ የመፈወስ ኃይል እንዳለው ከታወቀ ዘመናት ተቆጥረዋል። ዘ አውስትራሊያን የተሰኘው ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ ከክዊንስላንድ እና ከሲድኒ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጣ አንድ የምርምር ቡድን ማር ባክቴሪያ የመግደል ከፍተኛ ኃይል ሊኖረው የቻለበትን ምክንያት ግልጽ አድርጓል። ማር ከውኃ ጋር ተቀላቅሎ በቆሰለ ወይም በተቃጠለ የአካል ክፍል ላይ ሲቀባ በማሩ ውስጥ ባለው ኤንዛይምና በስኳሩ መካከል የሚካሄደው አፀግብሮት በቤት ውስጥ ለጽዳት በሚሰጠው ግልጋሎት በሰፊው የሚታወቀው ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ ኬሚካል እንደ ስታፊሎኮከስ ኦሪየስ ያሉ ባክቴሪያዎችን መግደል ብቻ ሳይሆን ህብረ ሕዋስ ራሱን በራሱ እንዲጠግንም ይረዳል።
የግብረ ገብ ትምህርት
የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ላለፉት ስምንት ዓመታት ለተማሪዎቹ በሙሉ የነፃ የግብረ ገብ ትምህርት ዕድል ሰጥቷል። ለምን? ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዲን የነበሩት ትራቪስ ሜረት ተማሪዎች “ቅጥ ያጡ፣ የመጣውን ፋሽን ሁሉ የሚከተሉና ሥርዓት የሌላቸው” ናቸው ሲሉ መናገራቸውን ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ጠቅሶ ዘግቧል። ለአንድ ቀን በሚቆየው በዚህ ኮርስ የሚሰጠው ትምህርት የገበታ ሥርዓትን፣ አለባበስን፣ የሥራ ሥነ ምግባርን፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም ሥርዓትንና ከሌሎች ጋር መተዋወቅ የሚቻልባቸውን መንገዶች ያካተተ ነው። ተማሪዎች እንደ አረማመድና እንደ ማስነጠስ ያሉ ነገሮችን አሳቢነት በታከለበት ሁኔታ ማድረግ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚማሩ ከመሆኑም በላይ “ተራ የሆነ ጭውውት ማድረግ የሐሳብ ልውውጥ እንጂ ምርመራ ማካሄድ ማለት እንዳልሆነ” እንዲያስተውሉ ይደረጋል። ሮዛን ቶማስ የተባሉ አንዲት አስተማሪ አድናቆት የተሞላበት አስተያየት በሚሰጠን ጊዜ “አመሰግናለሁ” ማለት አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። “እነዚህ በሕይወት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ክህሎቶች ናቸው” ሲሉ ቶማስ ተናግረዋል። “ሰዎች እነዚህ የማኅበራዊ ግንኙነት ክህሎቶች ለስኬት እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ሲገነዘቡ የሚገረሙ ይመስለኛል።”
በአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ወንጀል እየጨመረ ነው
የፓርላማ ተወካዮችን ያቀፈው የአውሮፓ ምክር ቤት ያጸደቀው ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ ከ1998 ወዲህ “ኢኮኖሚያዊ ወንጀል በእጅጉ እየተባባሰ መጥቷል።” ኢኮኖሚያዊ ወንጀል ምንድን ነው? የኢኮኖሚ ጉዳዮችና የልማት ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት “ሰዎችን እንደ ሸቀጥ መነገድን፣ ሕገወጥ የሆኑ አደገኛ ዕፆችንና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በድብቅ ማስገባትን፣ አስመስሎ በመሥራት ማጭበርበርን፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን፣ በኮምፒውተሮች የሚፈጸም ወንጀልን፣ ቀረጥ ማጭበርበርን፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን፣ ሙስናንና በሥልጣን መነገድን” ይጠቅሳል። ሪፖርቱ እንዲህ ያለው ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ከፖለቲካ ጋር እየተሳሰረ በመምጣቱ “አውሮፓ ይህን ወንጀል ለመዋጋት ያላት የቁርጠኝነት መንፈስ እየተዳከመ ሊሄድና ትግሉ ሊከሽፍ ይችላል” ሲል ያስጠነቅቃል። የሪፖርቱ ጸሐፊ የሆኑት ኢጣሊያዊቷ ቬራ ስክዋርቻሉፒ “ከሁሉ በፊት አደጋ ላይ የሚወድቀው የሠለጠነው ኅብረተሰብ የደም ሥር የሆነው ሕጉ ነው” ብለዋል።