በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፍ ችግር

ዓለም አቀፍ ችግር

ዓለም አቀፍ ችግር

“የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት አሳሳቢ የሆነ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ጠንቅ ነው።”—ዴቪድ ሳቸር የተባሉ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለ ሥልጣን በ1999 የተናገሩት

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለ ሥልጣን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ትልቅ የመወያያ ርዕስ አድርጎ ሲያቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ውስጥ በሌሎች እጅ ከሚገደሉት ሰዎች ይልቅ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት ሰዎች ቁጥር ልቆ ተገኝቷል። የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚያሻ መግለጹ ምንም አያስደንቅም።

ይሁንና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ1997 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ሰዎች ቁጥር ከ100, 000 ሰዎች መካከል 11.4 የነበረ ሲሆን ይህም ከዓለም አቀፉ አኃዝ ያነሰ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2000 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ሰዎች ቁጥር ከ100, 000 ሰዎች መካከል 16 ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት 45 ዓመታት ውስጥ 60 በመቶ ጨምሯል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ። ይህ በግምት በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ያጠፋል እንደ ማለት ነው!

ይሁን እንጂ አኃዛዊ መረጃዎች ሁኔታውን በተሟላ መልኩ ቁልጭ አድርገው አያሳዩም። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል የራሱን ሕይወት ማጥፋቱን በግልጽ መናገር አይፈልጉም። ከዚህም በላይ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ባጠፋ ቁጥር ከ10 እስከ 25 የሚደርሱ ራስን የመግደል ሙከራዎች እንደሚካሄዱ ይገመታል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚገኙት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት ጥናቱ ከመካሄዱ በፊት በነበረው ዓመት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ተነሳስተው እንደነበረ የተናገሩ ሲሆን ጥናቱ ከተካሄደባቸው ተማሪዎች መካከል 8 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ራሳቸውን ለመግደል ሙከራ አድርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዐዋቂ ከሆኑት ሰዎች መካከል ከ5 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት በሆነ ወቅት ላይ የራሳቸውን ሕይወት የማጥፋት ሐሳብ በአእምሯቸው ተጸንሶ እንደነበረ ሌሎች ጥናቶች አመልክተዋል።

የባሕል ልዩነቶች

ሰዎች የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለያያል። አንዳንዶች ወንጀል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፣ ሌሎች የፈሪዎች ሽሽት ነው የሚል አመለካከት ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው በግድ የለሽነት በሠራው ትልቅ ስህተት መጸጸቱን ለማሳየት የሚወስደው አድናቆት የሚቸረው እርምጃ እንደሆነ ያስባሉ። እንዲያውም አንዳንዶች የቆሙለትን ዓላማ ለማራመድ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲህ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ባሕል ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ሄልዝ ሌተር የተሰኘው ጽሑፍ ባሕል “የራስን ሕይወት ወደ ማጥፋት ሊመራ” ይችላል ሲል ገልጿል።

በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኘውን ሀንጋሪን እንውሰድ። ዶክተር ዞልታን ሪመር በሃገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋውን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት የሀንጋሪ “አሳዛኝ ‘ባሕል’” ሲሉ ገልጸውታል። የሀንጋሪ ብሔራዊ የጤና ተቋም ዲሬክተር የሆኑት ቤላ ቡዳ ሀንጋሪያውያን በረባ ባልረባው ሁሉ ማለት ይቻላል፣ ያላንዳች ማመንታት የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ቡዳ አባባል “ካንሰር ከያዘው እንዴት እንደሚገላገል ያውቃል።” ይህ የተለመደ እርምጃ ነው።

በአንድ ወቅት በሕንድ አገር ሰቲ የሚባል ሃይማኖታዊ ልማድ ነበር። ባልዋ የሞተባት ሴት የባልዋ አስከሬን የሚቃጠልበት እሳት ውስጥ በመግባት የምትፈጽመው ይህ ልማድ ከታገደ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። አንዲት ሴት በዚህ መንገድ ሕይወቷን እንዳጠፋች በተነገረ ጊዜ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በእጅጉ አወድሰዋታል። ኢንዲያ ቱዴይ እንደዘገበው ከሆነ በዚህ የሕንድ ክልል “በ25 ዓመት ውስጥ 25 ሴቶች የባሎቻቸው አስከሬን የሚቃጠልበት እሳት ውስጥ በመግባት ራሳቸውን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርገዋል።”

የሚያስገርመው፣ በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት ሰዎች ቁጥር በመኪና አደጋ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ሦስት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል! ጃፓን​—⁠አን ኢለስትሬትድ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደገለጸው “የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን በማያወግዘው የጃፓን ባሕል የራስን የአካል ክፍል ቆርጦ የማውጣት (ሴፑኩ ወይም ሃሪ-ኪሪ) ሥርዓትና ወግ በእጅጉ የተለመደ ነው።”

ከጊዜ በኋላ የቃል ኪዳኑ ማኅበር ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ኢናዞ ኒቶቤ ቡሺዶ ዘ ሶል ኦቭ ጃፓን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ብዙዎችን የሚማርከውንና ለሞት የሚዳርገውን ይህን ባሕል አስመልክተው የሰጡት ሐሳብ አለ። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በመካከለኛው መቶ ዘመን የተፈለሰፈው [ሴፑኩ] ተዋጊዎች የሠሩትን ወንጀል ለማስተሠረይ፣ ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ለመጠየቅ፣ ከውርደት ለማምለጥ፣ በጓደኞቻቸው ላይ ያደረሱትን ችግር ለማካካስ ወይም ቅንነታቸውን ለማሳየት የሚፈጽሙት ልማድ ነው።” ይህ በልማዳዊ ሥርዓት መልክ የሚፈጸመው የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት በጥቅሉ ጊዜ ያለፈበት ቢሆንም አሁንም አንዳንዶች ማኅበራዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ሲሉ ሲፈጽሙት ይታያል።

በአንጻሩ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት ከረጅም ጊዜ አንስቶ እንደ ወንጀል ሲቆጠር የኖረ ነው። በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመናት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎችን ከአባልነት በመሰረዝ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳይካሄድላቸው አግዳለች። በአንዳንድ ቦታዎች ይታይ የነበረው ሃይማኖታዊ ቀናኢነት የራስን ሕይወት ከማጥፋት ድርጊት ጋር በተያያዘ የሰውየውን አስከሬን በእንጨት ላይ መስቀልን አልፎ ተርፎም ልቡን በእንጨት መብሳትን የመሳሰሉ እንግዳ የሆኑ ልማዶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

የሚገርመው ነገር የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎች የሞት ቅጣት ሊደርስባቸው ይችል ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ እንግሊዛዊ አንገቱን በመገዝገዝ ራሱን ለመግደል በመሞከሩ በስቅላት ተቀጥቷል። በመሆኑም ባለ ሥልጣናቱ ሰውየው በራሱ ማድረግ የተሳነውን ነገር ፈጽመዋል። ራሳቸውን ለመግደል በሞከሩ ሰዎች ላይ የሚበየነው ቅጣት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የተለወጠ ቢሆንም የብሪታንያ ፓርላማ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትም ሆነ ራስን ለመግደል የሚደረግ ሙከራ እንደ ወንጀል ተደርጎ የመታየቱ ጉዳይ ያከተመ መሆኑን ያስታወቀው በ1961 ነው። በአየርላንድ ደግሞ እስከ 1993 ድረስ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር።

በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ደራሲዎች የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት እንደ አንድ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ይናገራሉ። በማይድን በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎችን ዕድሜ ለማሳጠር የሚወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በ1991 የወጣ አንድ መጽሐፍ የሕመምተኛው ሕይወት እንዲያልፍ ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶችን ጠቁሟል። ውሎ አድሮ ግን በእንዲህ ዓይነት አስከፊ በሽታ ያልተያዙ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ በርካታ ሰዎች በመጽሐፉ ላይ ከተጠቆሙት መንገዶች አንዱን ተጠቅመዋል።

ከችግር ለመላቀቅ መፍትሔው የራስን ሕይወት ማጥፋት ነው? ወይስ በሕይወት ለመቀጠል የሚገፋፉ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ከማግኘታችን በፊት የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱት ነገሮች ምን እንደሆኑ እንመርምር።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ። ይህም በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ያጠፋል እንደ ማለት ነው!